top of page

እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር::

[መቅድመ ተኣምረ ማርያም] 


እግዚአብሔር ዓለምን  ከመፍጠሩ በፊት ስለሚፈጥረው ዓለም አያውቅም ነበርን? የዓለምንስ ፍጻሜ አያውቅምን? የእግዚአብሔርን ፍጹም አዋቂነት የሚያምን ሁሉ አያውቅም ሊል አይችልም ራሱ ጌታችንና አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመዋዕለ ሥጋዌው 
"ያንጊዜ ንጉሡ በቀኙ ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል አባቴ የባረካችሁ ዓለም ሳይፈጠር ያዘጋጀላችሁን መንግስት ትወርሱ ዘንድ ኑ" ሲል አስተምሮናል፡፡ (ማቴ፳፭÷፴፭)

በዚህ ትምህርቱ ዓለም ሳይፈጠር እመቤታችን መታሰቧ ብቻ ሳይሆን ከእርሷ ሰው ሆኖ ዓለምን ማዳኑ በዕለተ ምጽዓትም በቀኙ የሚቆሙትና በግራ የሚቆሙት ሁሉ መታወቃቸው ተጽፏል፡፡ዓለም ሳይፈጠር ሥሉስ ቅዱስ በፈቃድ አንድ መሆናቸውንና የአካላዊ ቃል ከእመቤታችን ሰው መሆኑ መታወቁን ብቻ ሳይሆን በሰው ድኅነትም ሥላሴ መደሰታቸውን ለማስረዳት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 
"አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ስለወደድከኝ የሰጠኸኝን እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ" ሲል ገልጾለታል፡፡ (ዮሐ፲፯÷፳፬) 

ይህ ንግግር አካላዊ ቃል በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ሰውን መውደዱን፣አብ ቅድመ ሥጋዌ በሥጋዌ መደሰቱን ለመግለጽ የተነገረ ነው፡፡እመቤታችን በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር የሚለውም ሥጋዊው ዓለም ሳይፈጠር ይታወቃል፤ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑ በመታወቁም እርሷ ዓለም ሳይፈጠር ተመርጣለች ታውቃለች ስለዚህም ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡በሌላ መልኩ ደግሞ ይህን በዚህ መልክ የአምላክ ሰው መሆን መታወቁ ትክክል ነው ነገር ግን እመቤታችን ገና ሳትወለድ እንዴት ልትታወቅ ትችላለች? የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ 
"ያልተሠራ አካሌን ዓይኖችህ ዓዩኝ የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድ ስንኳ ሳይቀር በመጽሐፍ ተጻፉ" በማለት ገና ሳንወለድ እግዚአብሔር እንደሚያውቀን ይነግረናል (መዝ፻፴፲÷፲፭) 

ነቢዩ ወደፊት የሚመጣው ነገር ከመኖሩ በፊትም አንድስ ስንኳ ሳይቀር በመጽሐፉ ቀድሞ መጻፉን ከነገረን ስለእመቤታችን እንዲህ መባሉ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሆኑን እንረዳለን፡፡አንዳንዶች ደግሞ የእግዚአብሔርን ዐዋቂነት ቢያምኑም "እመቤታችን ብቻዋን አትታወቅም"  የሚል መከራከሪያን ያመጣሉ፡፡ይህ ንግግራቸውም ራሳቸው ለእመቤታችን ያላቸው አመለካከት የተዛባ እንደሆነ ወይም ዓይናቸውን ጨፍነው መካድ የሚፈልጉ መሆናቸውን ያሳየናል እንጂ የቅዱሳት መጻሕፍት እውቀታቸውን ሊያሳይ አይችልም፡፡እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል ስለሁሉም ግን አልተናገረም አልተጻፈምም፡፡ትንቢት የተነገረላቸው ወይም በሥራቸው እግዚአብሔርን ምን ያህል ደስ እንደሚያሰኙት እርሱ ያወቃቸው ብቻ ናቸው፡፡ነቢዩ ኤርሚያስን "በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ በማኅፀንም ቀድሼሃለሁ" ብሎታል፡፡ (ኤር፩÷፭) 
ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ሌሎቹን በእናታቸው ማኅፀን አያውቃቸውም ሳ ይወለዱና አድገው የሚሆኑትን ሳይሆኑ አስቀድሞ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ቅዱስ ዳዊት 
"ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ" እንዳለ ሁላችንንም አስቀድሞ ያውቀናል፡፡ (መዝ፳፩÷፲) 


ነቢየ እግዚአብሔር ኤርሚያስ የተናገረው ግን በተለየ ሁኔታ ትንቢት የተነገረላቸው ሰዎች አስቀድሞ የሚሆኑትና ቅድስናቸው የታወቀላቸው መሆኑን መናገር ነው፡፡ "ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃለሁ"  ያለው ገና ሳይወለድ ነው፡፡ነብይነትን ተሹሞ ወይም ተቀብቶ በምድር ላይ ከመጣ በኋላ አይደለም ነገር ግን ከተወለደና ካደገ በኋላ የሚደርስበት በዓርግና ቅድስና ቀድሞ የሚታወቅ መሆኑን መናገሩ ነው፡፡ቅዱስ ጳውሎም ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት "ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ አስቀድሞ ስለአንተ እንደተነገረው ትንቢት በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ"  ያለው "ጢሞቴዎስ" በስም ተጠቅሶ ትንቢት ተነግሮለት አይደለም፡፡፩ኛጢሞ፩÷፲፰

ነገር ግን ስለሐዲስ ኪዳን ካህናትና ሐዋርያት የተነገረው ለእርሱ የተነገረ መሆኑ የታወቀ በመሆኑ ነው፡፡እንደዚሁ ሁሉ ስለ አምላክ ሰው መሆን አስቀድሞ የታወቀ ነው ሲባል እመቤታችን ትታወቃለች ማለት ነው፡፡ሥጋዌውን ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር ያውቀዋል ያስበዋል ማለትም እመቤታችን ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡ 
•ዓለም ሳፈጠር ሥሉስ ቅዱስ በፈቃድ አንድ መሆናቸውንና የአካላዊ ቃል ከእመቤታችን ሰው መሆኑ መታወቁን ብቻ ሳይሆን በሰው ድኅነትም ሥላሴ መደሰታቸውን ለማስረዳት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ 
“አባት ሆይ ዓለም ሳይፈጠር ስለወደድኸኝ የሰጠኸኝን ክብሬን እንዲያዩ እኔ ባለሁበት የሰጠኸኝን እነርሱ ደግሞ ከእኔ ጋር ይሆኑ ዘንድ እወዳለሁ፤”ዮሐ.17፡24  ሲል ገልጾታል፡፡ 
ይህ ንግግር አካላዊ ቃል በተዋሕዶ ሰው በመሆኑ ሰውን መውደዱን አብ ቅድመ ሥጋዌ በሥጋዌ መደሰቱን ለመግለጽ የተነገረ ነው፡፡ 
• እመቤታችን በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር የሚለውም ሥጋዌው ዓለም ሳይፈጠር ይታወቃል፤ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ሰው መሆኑ በመታወቁም እርሷዓለም ሳይፈጠር ተመርጣለች፤ታውቃለች፤ስለዚህ ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡ 


• የአምላክ ሰው መሆን መታወቁ ትክክል ነው፤ነገር ግን እመቤታችን ገና ሳትወለድ እንዴት ልትታወቅ ትችላለች? የሚል ጥያቄም ሊነሳ ይችላል፡፡ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ 
“ያልተሰራ አካሌን ዓይኖችህ አዩኝ፤የተፈጠሩ ቀኖቼ ሁሉ አንድስ እንኳን ሳይኖር በመጽሐፍ ተጻፈ፡፡”መዝ.138፡16 በማለት የማያዳግም ምላሽ ሰጥቶናል፡፡ 
• ቅዱሱ ወደፊት የሚመጣው ነገር ከመኖሩ በፊትም አንድስ እንኳን ሳይቀር በመጽሐፍ ቀድሞ መጻፉን ከነገረን ስለእመቤታችን እንዲህ መባሉ ከቅዱስ መጽሐፍ ልዩነት እንደሌለው ያሳየናል፡፡ 
• አንዳንዶቹ ደግሞ የእግዚአብሔርን ዐዋቂነት ቢያምኑም “እመቤታችን ብቻዋን አትታወቅም” የሚል መከራከሪያን ያመጣሉ፡፡መልሱም፡- 


• እግዚአብሔርም ሁሉንም ያውቃል፤ስለ ሁሉም ግን አልተናገረም፤አልተጻፈምም፡፡ትንቢት የተነገረላቸው ወይም ደግሞ የታወቁ መሆናቸው የተገለጸላቸው የተለዩትና የተመረጡት ወይም በሥራቸው    እግዚአብሔርን ምን ያህል ደስ እንደሚያሰኙት እርሱ ያወቃቸው ብቻ ናቸው፡፡ኤርምያስን 
“በሆድ ሳልሰራህ አውቄሃለሁ፤ከማኅፀንም ሳትወጣ ቀድሼሃለሁ፤ለአሕዛብም ነቢይ አድርጌሃሉ፡፡”ኤር.1፡5 ብሎታል፡፡ 
ይህ ማለት ግን እግዚአብሔር ሌሎቹን በእናታቸው ማኅፀን አያውቃቸውም፤ሳይወለዱና አድገው የሚሆኑትን ሳይሆኑ አስቀድሞ አያውቅም ማለት አይደለም፡፡ቅዱስ ዳዊት 
“ከማኅፀን ጀምሮ በአንተ ላይ ተጣልሁ፤ከእናቴ ሆድ ጀምረህ አንተ አምላኬ ነህ፤”መዝ.21፡10 እንዳለ ሁላችንንም አስቀድሞ ያውቀናል፡፡ 
• ነቢየ እግዚአብሔር ኤርምያስ የተናገረው ግን በተለየ ሁኔታ ትንቢት የተነገረላቸው ሰዎች አስቀድሞ የሚሆኑትና ቅድስናቸው የታወቀላቸው መሆኑን መናገር ነው፡፡ 
“ለአሕዛብም ነብይ አድርጌሃሉ፤” ያለው ገና ሳይወለድ ነው፡፡ 
• ነቢይነትን ተሸሞ ወይም ተቀብቶ በምድር ላይ ከመጣ በኋላ አይደለም፡፡ነገር ግን ከተወለደና ካደገ በኋላ የሚደርስበት መዓርግና ቅድስና አስቀድሞ /ቀድሞ/ የሚታወቅ መሆኑን መናገሩ ነው፡፡ 
• ቅዱስ ጳውሎስ ለጢሞቴዎስ ሲጽፍለት 
“ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ አስቀድሞ ስለ አንተ እንደተነገረው ትንቢት በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፡፡” 1ኛ.ጢሞ. 1፡18 
ያለው “ጢሞቴዎስ” በስም ተጠቅሶ ትንቢት ተነግሮለት አይደለም፡፡ነገር ግን ስለ ሐዲስ ኪዳን ካህናትናሐዋርያት የተነገረው ለእርሱ የተነገረ መሆኑ የታወቀ በመሆኑ ነው፡፡ 
• እንደዚሁ ሁሉ ስለአምላክ ሰው መሆን አስቀድሞ የታወቀ ነው ሲባል እመቤታችን ትታወቃለች ማለት ነው፡፡ 
• ሥጋዌውን ዓለም ሳይፈጠር እግዚአብሔር ያውቀዋል፤ያስበዋል ማለትም እመቤታችን ታስባ ትኖር ነበር ማለት ነው፡፡
“ዓለም ሳይፈጠር በፊቱ ቅዱሳንና ነውር የሌለን በፍቅር እንሆን ዘንድ በክርስቶስ መረጠን፡፡”ኤፌ. 1፡4-14 
እመቤታችን ዓለም ሳፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር፡የሚለው የተኣምረ ማርያም መቅድም ምንም አይነት ሕጸጽ የለውም መጽሃፍ ቅዱስም ይደግፈዋል፡፡

እመቤታችን ዓለም ሳይፈጠር በአምላክ ኅሊና ታስባ ትኖር ነበር::
ተአምሯን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደ ተቀበለ ይሆንለታል

ተአምሯን የሰማ ሥጋውን ደሙን እንደ ተቀበለ ይሆንለታል፡፡

 

ይህን ጽንሰ ሐሳብ ለመረዳት በመጀመሪያ በመቅድሙ የተጻፈውን ቃል እንዳለ መመልከት ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡ 
"አስቀድመን እንደተናገርን የታወቀ ምክንያት ኃጢአት ደዌ ካልከለከለው በዚች ቀን ተአምሯን ሰም ሥጋውን ደሙን ይቀበል፡፡ሥጋውን ደሙን መቀበል ካልተቻለው ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሂድ ሥጋውን ደሙን እንደተቀበለ ይሆንለታል ይደረግልኛል በማለት ቢሰማ፡፡" 
ይላል የዚህን አንቀጽ መልእክት አንድ በአንድ በመተንተን ስንመለከት የሚከተሉትን ሦስት ዐበይት መልእክቶች እናገኛለን፡፡ "

ሀ. ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ፡- 
ይህ አንቀጽ በመጀመሪያ ደረጃ ብቻ ሳይሆን በዋናነት የሚያስተላልፈው መልእክት ሥጋውን ደሙን ተቀበሉ የሚል ነው፡፡ምክንያቱም በፍትሐ ነገሥት 
"ከቀዳም ሥዑር በቀር ቅዳሜ ቅዳሜ እና እሑድ እሑድ በቤተክርስቲያን ተሰብስባችሁ ሥጋውን ደሙን ተቀብላችሁ ደስ ይበላችሁ" ተብሎ ታዝዟል፡፡ 
ይህም ብቻ ሳይሆን በበረሐ ያሉ ባሕታውያን ሳይቀሩ መልአከ እግዚአብሔር ሥጋው ደሙን የሚቀበላቸው በሰንበት ነው፡፡

 (በዓላት- ምን? ለምን? እንዴት? ገጽ ፵፮ እና ፷፮)

ነገር ግን በሥርዓተ ቤተክርስቲያን መሠረት አንድ ሰው ሥጋውንና ደሙን እንዳይቀበል ሊያደርጉ የሚችሉ ምክንያቶች ይኖራሉ፡፡እነዚህም በዚህ አንቀጽ የተገለጹት አንደኛ የታወቀ ምክንያት /እንደወሊድ፣ሐዘን፣ለቅሶ፣../ የመሳሰሉት ሲሆኑ ሁለተኛው ደግሞ ኃጢአት ነው፡፡ይከለክሉታል ተብለው ከተጠቀሱት በመጨረሻ የተገለጸው ደግሞ ደዌ ነው፡፡አንድ ሰው በደዌ ምክንያት ፈሳሽ ነገር ከሰውነቱ እየወጣ፣ደም እየፈሰሰው ይህን የመሰሉ ነገሮች እያሉበት ሥጋውን ደሙን ላይቀበል ይችላል፡፡እነዚህ ሁሉ ግን ሰውየውን በቤተክርስቲያን ቅጽር ተገኝቶ ከመጸለይ፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ከማንበብና ከመስማት ሊከለክሉት አይችሉም፡፡ስለዚህ አንድ ሰው እነዚህ ምክንያቶች ካልከለከሉት በቀር ሥጋውን ደሙን ይቀበል በማለት ወንጌልን ይሰብካል እንጂ ከወንጌል የወጣ ቃል የለውም፡፡

ለ. ቤተክርስቲያን አትቅር
ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ሥጋውን ደሙን መቀበል ባይቻልህ ግን ሥጋውን ደሙን መቀበል አይቻለኝም ብለህ ወደ ቤተክርስቲያን ከመሔድ አትከልከል ነው የሚለው፡፡ 
ተአምረ ማርያም ከቅዳሴ በፊት ያለው የቤተክርስቲያን የጸሎት ክፍል አንድ አካል ነው፡፡መቅድሙም የሚለው  "ሥጋውን ደሙን መቀበል ካልተቻለው ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሒድ" ነው፡፡ 
ይህም ማለት ባትቆርብም ቤተክርስቲያን አትቅር ማለት ነው፡፡በጸሎቱ ትምህርቱና በመሳሰለው መርሐ ግብር ሁሉ ተሳተፍ፡፡ዕለቱ ሰንበትና በዓላት ከሆነ አንድ ክርስቲያን ቤተክርስቲያን ካልሔደ በዚያም ተገኝቶ ካልተማረ ካላመሰገነ ክርስትናውን በምን ይገልጸዋል? በዚህ አገላለጽ "ተአምሯን ሰምቶ ወደ ቤቱ ይሒድ" የሚለውን በአስተውሎትና በቅንነት ከተመለከትነው የሚናገረው ስለ ተአምሯ ብቻ አይደለም፡፡ 
"ተአምሯን አታስታጉሉ" ሲል ወደ ቤተክርስቲያን ሂዳችሁ በዚያ ባለው አገልግሎት ተሳተፉ ማለት ነው፡፡ምክንያቱም ተአምረ ማርያም እንዴትና መቼ እንደሚነበብ እናውቃለን፡፡ከተአምሩም በፊት ከተአምሩም በኋላ ሌሎች ጸሎቶችና ምንባባት አሉ፡፡ይህን አጠቃላይ አገልግሎት ለምእመኑ በታወቀ በተረዳ ነገር በዚህ ስያሜ ማስታወቅ ክፋትም ኃጢአትም አይደለም፡፡ሌላው አገልግሎት በዚህ ኣገላለጽ ለምን ጠሩት ቢባል በትርጓሜ ውዳሴ ማርያም ላይ እንደተጻፈው ሌላውን አገልግሎት በመናቅ በማቃለል ሳይሆን  ለእመቤታችን ባላቸው ፍቅር ነው::

ሐ. አትጠራጠር፡- 
ሦስተኛውና የመጨረሻው የዚህ አንቀጽ መልእክት በታወቀ ምክንያት "በዚህች ዕለት" ሥጋውን ደሙን መቀበል ባይቻልህ ለሌሎቹ የተደረገው አይደረግልኝም የዕለቱ በረከት አይደርሰኝም ብለህ አትጠራጠር የሚል ነው፡፡መጽሐፉ የተአምራት መጽሐፍ እንደመሆኑ መጠን ተአምራትም የሚደረገውና ተአምራትም የሚያሰኛቸው ከዘወትራዊ የሕይወት ተግባራትና ድርጊቶች የተለየለሰው የማይቻል በእግዚአብሔር ብቻ የሚቻል ነገር መደረጉ በመሆኑ አንተም"ይደረግልኛል" በማለት በእምነት ከጸሎቱ ተካፍለህ ከተአምሯ ሰምተህ ብትሔድ በዕለቱ የቆረቡትን ሰዎች በረከት ታገኛለህ ማለት ነው፡፡ይህ ደግሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተፃፈ ነው፡፡ራሱ ጌታችን በወንጌል የሰናፍጭ ቅንጣት ታክል እምነት ቢኖራችሁ ተራራ ማፍለስ ባሕር መክፈል… ትችላላችሁ ሲል አስተምሮአል፡፡ይህም በእምነት ኃይለ እግዚአብሔርን በረከተ እግዚአብሔርን ታገኛላችሁ ከእግዚአብሔር ትገናኛላችሁ ማለት ነው፡፡ሥጋ ወደሙ በየሳምንቱ ወይም ከዚህ ባነሰም ይሁን በበዛም የምንቀበለው ለዚሁ ኃይለ እግዚአብሔርን ገንዘብ አድርገን ኃጢአታችን አስተሥርየን በረከተ ሥጋ በረከተ ነፍስ አግኝተን ለመኖር ነው፡፡በዚያች ዕለት አልቻልህ ብሎ ባትቀበል በእምነትም ይህን ታገኛለህና አትጠራጠር ይሉናል ሊቃውንቱ፡፡
የመቅድሙ መልእክት ይሔ ሆኖ ሳለ "ዐውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም" እንደሚባለው ሰዎችን ሆን ብሎ ለማጠራጠርና ከቅዱሳን በረከት ለመለየት አጋንንት በሰዎች አድረው ሊቃውንቱ ያላሉትንና ሊሉም ያላሰቡትን ያቀርባሉ፡፡ቤተክርስቲያኒቱ "ሥጋውን ደሙን አትቀበሉ" ሥጋ ወደሙ መቀበል እና ሥጋ ወደሙ ሳይቀበሉ ተአምረ ማርያም መስማት እኩል ናቸው" የሚል ትምህርት አስተምራ አታውቅም እንዲህም አታምንም፡፡ተአምሯን የሚሰሙትና የሚያሰሙትም ሥጋውን ደሙን የተቀበሉ ወደፊትም የሚቀበሉ ናቸው እንጂ አረማውያን ወይም በሥጋ ወደሙ የሚጠራጠሩ አይደሉም፡፡ "ይደረግልኛል በማለት ቢሰማ" የሚለው ጊዜ የተገደበ ነው፡፡ታዲያ ይህ በውኑ ለምእመኑ መንፈሳዊ ሕይወት መጨነቅ ወይስ ለኑፋቄ ሽፋን መፈለግ? ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው ሁሉንም እግዚአብሔር ያውቃል፡፡

ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ

 

አንዳንድ ሰዎች በአጉል ዐወቅን ፈሊጥ እንዲህ ዐይነት አገላለጽ የአለማወቅ ይመስላቸዋል፡፡አሁን አሁንማ አንዳንዶቹ "ይህን የጻፉት ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስን ቢያውቁ እንዲህ አይሉም ነበር" እስከ ማለትም ደርሰዋል፡፡ለመሆኑ የትኛው ነው መጽሐፍ ቅዱስን የማያውቀው? ቀደም ብለን በመግቢያው ላይ የእመቤታችን ተአምር ከየት ከየት እንደተተረጎመና ምን ዓይነት ሊቃውንት እንዳስተረጉሙት በመዓልቃ ከነበሩት ሊቃውንት ጥቂቶቹን አስቀድመን ያየነው የማናውቃቸውን ቅዱሳን አበው መዳፈር አይገባም ለማለት ነው፡፡መጽሐፍ "ለቅኖች ምስጋና ይገባል" ይላል፡፡ቅኖችን የማያመሰግኑ ሰዎች ግን ይኖራሉ ይህም በሁለት ምክንያት ነው፡፡አንደኛው ለቅኖች የሚገባውን ምስጋና ካለማወቅ ሲሆን ሁለተኛው ግን ቅኖችንም ካለማወቅ ነው፡፡

አሁን የምናየው ግን "ቅኑን" አለማወቅ ብቻ ሳይሆን ቅንነትን ወይም ቅን የሚያሰኘውንም አለማወቅን ነው፡፡ይህ ደግሞ አለማወቅ ብቻ ሳይሆን በአለማወቅ ፍጹምነት ደረጃ ላይ መድረስም ነው፡፡በዕውቀትና በቅድስና ወደ ፍጹምነት የሚሄዱ የመኖራቸውን ያህል በርኩሰትና በአለማወቅ በድፍረትና በትንዕቢትም ወደ ፍጹምነት የሚሔዱ አሉ ማለት ነው፡፡
ቅንነትን አለማወቅን ያነሳነው በድንገት አይደለም፡፡በቅንነት የሚያስብ ሰው ቢያንስ ይህን መጽሐፍ /ተአምረ ማርያምን/ ለአገልግት የሚጠቀሙበት ኦርቶዶክሳውያን ወይም ቤተክርስቲያኗ ራሷ ስለ ሥነ ፍጥረት የምታስተምረው ትምህርት ምንድን ነው? ለመሆኑ ፍጥረታት ለምን ዓላማ ተፈጠሩ ትላለች? እያለ ይጠይቃል፡፡ለጥያቄው የሚያገኘው መልስ"እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ"  የሚል ከሆነ አጠቃላይ የቤተክርስቲያኒቱ ዶግማ መሆኑን ተረድቶ ያንን ሊተች ይችላል፡፡ሥነ ፍጥረት ላይ ያለው ለየት ያለ ከሆነ ግን የየዚህ የተአምረ ማርያም አገላለጽ ምን ማለት ነው? በሥነ ፍጥረት ላይ ካለው /ፍጥረታት ስሙን ቀድሰው ክብሩን ወርሰው ለመኖር ለምግበ ሥጋ ለምግበ ነፍስ፣ለአንክሮ ለተዘክሮ/ ለእነዚህ ለሶስቱ ዓላማዎች ተፈጠሩ ከሚለው ትምህርት አንጻር ምን ማለት ነው? ሥነ ጽሑፋዊ አገላለጹስ ከቤተክርስቲያኒቱ የሥነ ጽሑፍ ትውፊት አንጻር ምን መልእክት አለው? የሚለውን ይጠይቃል፡፡እነዚህን ነገሮች ለማየት ደግሞ እንኳን ሃይማኖት ያለው ሆኖ ቀርቶ በሥነጽሑፍ ግምገማም ዕውቀትና ግንዛቤ መያዝ ብቻ ሊበቃ ይችላል፡፡እኛም የዚህን ጥያቄ መልስ የምንመልስላችሁ ከዚሁ ነጥብ በመነሣት ይሆናል፡፡

ፍጥረታት የተፈጠሩበት ዓላማ ከላይ የተገለጹት ሦስቱ ናቸው፡፡ከእነዚህ ውስጥ የመጀመሪያው የእግዚአብሔርን ስሙን ቀድሶ ክብሩን ወርሶ ለመኖሩ የተፈጠሩ አሉ የሚለው ነው፡፡እነዚህ ፍጥረታት ሰውና መላእክት ናቸው፡፡ሰውና መላእክት እግዚአብሔርን በማመስገናቸው ለእግዚአብሔር የሚጨምሩለት ክብር የለም፡፡ነገር ግን የተፈጠሩለትን ዓለማ ውጤታማ በማድረግ ራሳቸው የእግዚአብሔርን ክብር ይወርሳሉ፡፡

ከቅዱሳት መጻሕፍት መሰጠት በኋላ የሰው ልጅ የቅዱሳት መጻሕፍትን ቃል አምኖ መጠቀም በቃለ መጻሕፍትም መኖር ይጠበቅበታል፡፡ስለዚህም ስለእመቤታችን የተጻፈውን መፈጸም ይገባል፡፡ራሷ እመቤታችን መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል እና ኤልሳቤጥ እንዳመሰገኑኝ ሁሉ "ከአሁን በኋላ ትውልድ ሁሉ ያመሰግኑኛል" በማለት ገልጻዋለች፡፡ሉቃ፩÷፵፰፡፡ይህን ቃል ስትናገር ቅዱስ ሉቃስ እመቤታችን ጋር አልነበረም ነገር ግን ትመሰገን ዘንድ ጸጋውን የሰጣት እግዚአብሔር በጸጋ ገልጾለት በኋላ ዘመን በመጽሐፉ ገለጸው፡፡ቅዱስ  ጳውሎስ እንደተናገረው "እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጠራቱ አይጸጸትምና፡፡" ሮሜ፲፩÷፳፱ስለዚህ በክርስቶስ አምናለሁ ለሚል የወንጌል ቃል መቃወም አይችልም፡፡

"ትውልድ ሁሉ ብጽእት ይሉኛል"  በሚለው ቃል እንስማማለን ነገር ግን የመቅድሙ ቃል የሚለው "ፍጥረት ሁሉ እመቤታችን ለማመስገን ተፈጠረ" ነው ስለዚህ ይህ እንዴት ሊስማማ ይችላል እንል ይሆናል፡፡ለዚህም ቢሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ያሉ አንዳንድ አገላለጾችን ካስተዋልናቸው ልንቸገር አንችልም፡፡ቅዱስ ሉቃስ በወንጌሉ "በዚያም ወራት ዓለሙ ሁሉ እንዲጻፍ ከአውግስጦስ ቄሳር ትእዛዝ ወጣች" ሲልገልቷል፡፡ሉቃ፪÷፩ታዲያ ቄሳር አውግስጦስ ያወጣው ትእዛዝ በውኑ ለዓለም ሁሉ ነውን? አይደለም፡፡ቅዱስ ሉቃስ "ዓለም" ያለው በአውግስጦስ ቄሳር ግዛት ሥር ያሉትን አገሮች እና በዚያም የሚኖሩትን ሰዎች ሁሉ በማጠቃለል እንጂ ዓለም የሚለውን ቃል ባለማወቅ ወይንም የዓለሙን ገዥ የእግዚአብሔርን ሥልጣን ለአውግስጦስ ቄሳር በመስጠት አይደለም፡፡የመቅድመ ተአምረ ማርያም ጸሐፊዎችም መቅድሙን የጻፉት በሐዲስ ኪዳን ዘመን ነው፡፡ስለዚህ "ፍጥረት ሁሉ" ሲሉ አማኞችን ብቻ እንደሚመለከት ግልጽ ነው፡፡በዚያውም ላይ እመቤታችን "ትውልድ ሁሉ" ካለችው ጋር ልዩነት የለውም፡፡ "ለማመስገን ተፈጠረ" ማለትም ከዚህ በኋላ /እመቤታችን ከተናገረች በኋላ/ ያለው ትውልድ በወንጌል የማያምንና በቃለ መጻሕፍትም የማያምን ካልሆነ በቀር እመቤታችን ማመስገን ግዴታው ነው፡፡ኤልሳቤጥን በወንጌል ሊቃውንትንም በኤፌሶን ጉባኤ ተመልክቶ "የጌታዬ እናት" "ወላዲተ አምላክ /Theotokos/ እያለ ያመሰግናል፡፡

ስለዚህ እንዲህ እያለ ለማመስገን ተፈጠረ ቢባል ስህተቱ ምኑ ላይ ነው? ዓረፍተ ነገሩ ይህን ጽንሰ ሐሳብ ብቻ አይገልጽም ከዚህ ያለፈና ሆን ተብሎ የእግዚአብሔርን ክብር ለእርሷ ለመስጠት የተጻፈ ነው የሚል ካለ ማስረጃውን አቅርቦ ለዚያውም በቅንነት ቋንቋው እንዲታረም ቢጠይቅ ያስመሰግነው ነበር፡፡ነገር ግን ይህ አልሆነም፡፡ምክንያቱም ጌታን ሳያውቁ እመቤታችን ሊያውቁ እርሱን ጌታዬ ሳይሉ እርሷን የጌታዬ እናት እርሱን አምላክ ሳይሉ እርሷን ወላዲተ አምላክ ብለው ሊያመሰግኑ የሚችሉ ሰዎች የሉም፡፡አማኙ /ምእመኑ/ ጌታችንን ሳያመሰግን የጌቶች ጌታ ሳይል በእርሱ ማመኑን ትቶ ለእመቤታችን የአምምልኮት ምስጋና ቢያቀርብ የፈጣሪን ምስጋና ለእርሷ ለምን እንሰጣለን የሚል ጥያቄን ማንሣት ይችሉ ነበር፡፡ይህ ግን አልተደረገም ሊደረግም አይችልም፡፡

ፍጥረት ሁሉ እመቤታችንን ለማመስገን ተፈጠረ
bottom of page