top of page

ደብረ መዊዕ ቅድስት ሥላሴ ወቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሰ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን

የቤተክርስቲያናችን ታሪክ

Anchor 1

"ይህ ሥፍራ እንዴት ያስፈራ፤ ይህ ሥፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም፤ ይህም የሰማይ ደጅ ነው።" (ዘፍ ፳፰፥፲፯)

በሰሜን አሜሪካ በአሪዞና እስቴት ብቸኛ የሆነችው ደብረ መዊዕ ቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጳጉሜን ፬ ቀን ፲፱፻፺፱ ዓ.ም. በወቅቱ የካሊፎርኒያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹዕ አቡነ ማርቆስ ተመሠረተ። ሕንጻ ቤተ ክርስቲያኑ ደግሞ የካቲት ፲፩ ቀን ፪ሺ፬  ዓ.ም በብጹዓን ሊቃነ ጳጳሳት ዶ/ር አቡነ ገሪማ እና አቡነ አትናቴዎስ ተባርኮ ተመረቀ። በቀድሞው የካሬቢያንና አካባቢው ሊቀ ጳጳስ አቡነ ይስሐቅ መጥቶ ለበርካታ ዓመታት ስካትስዴል አሪዞና በሚገኘው ቅዱስ ማርቆስ የግብጽ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በአደራ ተቀምጦ የነበረው የቅድስት ሥላሴ ታቦት ግንቦት ፳፭ ቀን ፪ሺ፬ ዓ.ም. ወደ ቤተክርስቲያናችን ገብቷል። ሰኔ ፳፭ ቀን ፪ሺ፱ ዓ.ም. በብጹዕ አቡነ ፋኑኤል የዲሲ እና አካባቢው እንዲሁም የካሊፎርኒያ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ፈቃድ የቤተክርስቲያናችን ስያሜ ደብረ መዊዕ ቅድስት ሥላሴ ወቅዱስ እስጢፋኖስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተብሎ እንዲስተካከል ተደርጓል።

የቤተክርስቲያኗ አመሰራረት መነሻው ቅዱስ ሲኖዶስ ባስተላለፈው ቃለ ውግዘት ምክንያት በቁጥር እጅግ አነስተኛ ነገር ግን በሐይማኖት ጠንካራ በሆኑ (ቁጥራቸው ከ20 ያልበለጡ በአንድ ካህንና በሁለት ዲያቆናት ብርቱ ጥረት ብጹዕ አብነ ማርቆስ በማስጠራትና የነበረውን ችግር በግልጽ በማስረዳት ሲሆን ብጹዕነታቸውም ጉዳዩን በጥሞና ከተመለከቱ በኃላ በጸሎታቸውና በእግዚአብሔር መልካም ፈቃድ ቤተክርስቲያኑ እንዲመሠረት አድርገዋል።።

ቤተክርስቲያኗ ስትመሰረት የራሷ ህንጻ ቤተክርስቲያን ስላልነበራት እግዚአብሔር የሌሎችን ልብ አራርቶ በ 6750 N. 7th AVE PHOENIX,AZ 85013 አድራሻ የሚገኘውን በነጻ እሁድን ለቤተክርስቲያን አገልግሎት በመፍቀዳቸው ለአራት ዓመታት በተሰጣት ቦታ አገልግሎት ስትሰጥ ቆይታለች በኃላም የሰበካ ጉባኤው እና ካህናት አባቶች ቤተክርስቲያኗ የራሷ የሆነ ህንጻ ቤተክርስቲያን እንዲኖራት ካላቸው ብርቱ ሃሳብና ምኞት የተነሳ የህንፃ ግዥ ኮሚቴ በማቋቋም ስራው ከሰበካ ጉባኤ አባላት ጋር ተጀምሮ የቤተክርስቲያንኗ የገንዘብ መጠን በመጠኑ ከጨመረ በሃላ በአጋጣሚ አሁን ያለንበት ህንፃ ቤተክርስቲያን ለገቢ (ለሽያጭ) ቀርቦ ስለነበር ቦታውን ለማየት ቀጠሮ ተያዘ ።

በእግዚአብሔር ፈቃድ የቤተክርስቲያኗ መስራች ብፅዕ አባታችን አቡነ ማርቆስ እኛ ልጆቻቸውን ለመባረክ ከኢትዮጵያ መጥተው ስለነበርና በዚህ ወቅት ከሳቸው መምጣት ጋር በመገጣጠሙ የተመረጠው ኮሚቴ ካህናት አባቶችንና ብጽዕነታቸው ይዞ ቦታውን ጎበኘ። በዚህ ወቅት ብጹዕነታቸው‘’እንግዲህ መጠንከርና መጨከን ያስፈልጋል ሊቀጳጳስ የረገጠው ቦታ ስለሆነ እንዳያመልጣችሁ’’ በማለት ከማበረታታቸውም በተጨማሪ ኮሚቴውንና ካህናት አባቶችንና በማሰባሰብ ምክር ከሰጡ በኃላ በወቅቱ የነበረውን ምዕመንና ኮሚቴ ቃል በማስገባት በእሳቸው አነሳሽነት ከ68ሺህ ደላር በላይ ቃል ተገባ።

ቀጣዩ ሂደት አበዳሪ ባንኮችን ማነጋገር ስለነበር በተወካዮች ያስፈልጋል የተባለውን ዶክመንት ተሟልቶ አበዳሪ ባንኮች በተጠየቁበት ወቅት የተሰጠው ምላሽ ግን የገንዘብ አቅማችሁ አነስተኛ ነው ያላችሁ አባላት በቁጥር ጥቂት ከመሆናችሁ በተጨማሪ ቤተክርስቲያኑን ከመሰረታችሁ ትንሽ አመታት ብቻ ስላስቆጠራችሁ በማለት እንደማይፈቅዱ አሳወቁ የተመረጠውም ኮሚቴ ምዕመናን ተስፋ እንዳይቆርጡ የአበዳሪዎችን መልስ በምስጢር በመያዝ የተለያዩ ሙከራዎችን በማድረግና ፈቃደ እግዚአብሔርን በመጠየቅ ቆየ በዚህ መካከል ለመግዛት የተሞከረው ቤተክርስቲያን መያዙ(ከገበያ) ላይ መነሳቱ ስራውን ይከታተሉ የነበራት ለኮሚቴው ገለፁ።

ከጥቂት ወራት ቆይታ በኃላ የእግዚአብሔር ተአምር አያልቅምና ከገበያ ላይ የተነሳው ቤተክርስቲያን 40ሺህ ደላር ቀንሶ እንደገና ለሽያጭ ቀረበ በዚህ ወቅት ጉዳዩን እንደ አዲስ መከታተል የጀመሩት በቀጥታ የቤተክርስቲያን ሻጮችን በግማሽ ከፍሎ እና ቀሪውን በ5ዓመታት ውስጥ ከፍሎ ለማጠናቀቅ ጠየቀ። እግዚአብሔር ልባቸውን አራርቶ ከስምምነት ከመድረስ አስፈላጊውን ነገር በሙሉ ተከናውኖ በአጭር ጊዜ ውስጥ አልቆ ታህሳስ 12 ቀን 2004 (12/25/11) ለቤተክርስቲያኗ አስተዳዳር በታላቅ ደስታ አስረከበ።

በአጭር ጊዜ የጥገና ስራና አስፈላጊው የሆኑ ነገሮች ተሞልቶ ለመጀመሪያ ጊዜ የጥምቀትን በዓል በራሱ ህንፃ ቤተክርስቲያን ተከብሮ ዋለ በነገሮች ሁሉ እግዚአብሔር ስለነበር ለእርቅ ሽምግልና ሊቃነጳጳሳት መጥተው ስብሰባው በዚሁ በፊኒክሰ ከተማ ስለነበር የካቲት 10 ቀን 2004 ዓ.ም:-

    1ኛ ብፅዕ አቡነ አትናቲዮስ የወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና የቅዱስ ሲኖዶስ አባል 
    2ኛ ንቡረዕድ ኤልያስ 
    3ኛ ሊቀካሕናት ኃይለሥላሴ በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ ሀገረ ስብከት ዋና ስራ አስኪያጅ 
    4ኛ ሊቀ ጉባኤ ኃይለሥላሴ በካልፎርንያ የቅድስት ሥላሴ ወገብረክርስቶስ ቤተክርስትያን አስተዳደዳሪ እና ሎሎች ተጋባዥ አባቶች በተገኙበት ቤተክርስትያኗ ተባረከች።

ሌላው ተዓምር ለብዙ አመታት በግብጽ ቤተክርስትያን ተቀምጦ የኖረ የሥላሴ ታቦት ግንቦት 25ቀን 2004 ዓ.ም (06/02/12) በክብር ወደ ቤተክርስቲያኗ በመግባቱ የምዕመናንም ሆነ የካህናት ደስታ ለመግለጽ ቃላት ያጥራል። "በአንተ አለትነት ላይ ቤተክርስትያንን አንፃለሁ የገሐነም ደጆች አይችሏትም"

በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ደም የተመሰረተችውን ቤተክርስትያን ለመጠበቅና ለመጭው ትውልድ ለማስረከብ የተጣለብንን አደራ እንወጣለን።

እግዚአብሔር በቸርነቱ ድንግል ማርያም በአማላጅትዋ ቅዱስ እሥጢፋኖስ በምልጃው ይጠብቁን።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

Anchor 2
የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስተዳደር
bottom of page