top of page

የ አስተዳዳሪው መልዕክት

  በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን !

           

      “እኔ ከአንተ ጋር ነኝ…….ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል ፤ በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና አለው።”    የሐዋ᎐፲፰፥፲

 

   “ከሕሊና አስቀድሞ ሁሉን የሚያውቅ ከአሳብ አስቀድሞ የሚመረምር ሳንለምነው የምንሻውን አውቆ የሚሰጠን የማይመረመር ብርሃን”(ኪዳን ዘነግህ) ልዑል እግዚአብሔር በምሕረቱ ፣ በይቅርታው ስላደረገልን ቸርነቱ በጎ ስጦታው ሁሉ የተመሰገነ ይሁን።

    እንደሚታወቀው አባቶቻችን ጥንታዊት ሐዋርያዊት ዓለም አቀፋዊት የሆነችውን አሐቲ ቅድስት ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያንችንን “ወነአምን በአሐቲ ቅድስት ቤተክርስቲያን እንተ ላዕለ ኩሉ ጉባዔ ዘሐዋርያት” ሐዋርያት ባነጽዋት ከምኩራበ አረሚ ከምኩራበ አይሁድ በላይ በምትሆን ክብርት ንጽሕት ጽንዕት ልዩ በምትሆን በአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን እናምናለን በማለት ስለሚያምኑት ሃይማኖት ስለ አንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ሳያፍሩና ሳይፈሩ በአላውያንና በነገስታቱ ፊት በመመስከር ስለተዋሕዶ እምነታቸው ስለቅድስት ቤተክርስቲያናቸው ብዙ መከራን በመቀበል ፣ በመጋዝ በመሰንጠቅ፣ በመገረፍ፣ በድንጋይ በመወገር ፣ በምድረ በዳ በመንከራተት፣ ራሳቸውን እስከሞት ድረስ አሳልፈው በመስጠት ለእኛ ለልጆቻቸው ሳይበረዝ አስረክበዋል።

    ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች---ከላይ በመግቢያዬ እንደጠቀስኩት ቅዱስ ጳውሎስን አምላካችን እግዚአብሔር በራእይ እኔ ከአንተ ጋር ነኝ ማንም ክፉ ሊያደርግብህ የሚነሳ የለምና አትፍራ በማለት ቃሉን እንዲሰብክና እንዲያስተምር ዝምም እንዳይል እንዲህ ብሎታል ”ነገር ግን ተናገር ዝምም አትበል በዚህ ከተማ ብዙ ሕዝብ አሉኝና” በማለት አጽናንቶታል አሳስቦታል። እኛም እግዚአብሔር አምላክ ለኢያሱ  “በምትሄድበትም ሁሉ እንዲከናወንልህ ወደ ቀኝም ወደግራም አትበል::” መጽ ኢያሱ ፩፥፯ ያለውን አምላካዊ ቃል ለመፈጸም፣የአባቶቻችንን ፈለግ ለመከተል እግዚአብሔርን አጋዥ በማድረግ ቃሉን ለማስተማር እግዚአብሔርን አጋዥ አድርገን ይህን ዌብሳይት ለመጠቀም ተነሳን። ቅዱስ ጳውሎስ ለመንፈስ ልጁ ለጢሞቴዎስ “ቃሉን ስበክ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና፥ፈጽመህ እየታገሥህና እያስተማርህ ዝለፍና ገሥጽ ምከርም” ፪ኛ ጢሞ᎐፬፥፪ ብሎ እንዳስተማረው ሕያውና ዘላለማዊ ቅዱስ ቃሉን እንድንሰብክ የቤተክርስቲያንን መልእክት እንድናስተላልፍበት፤ በተለይም በዚህ በአለንበት አገር የቤተክርስቲያን ልጆቻችን ያለባቸውን የኑሮ ሁኔታ የስራ ጫና ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በየእለቱ በቤተክርስቲያን ተገኝተው ቃለ እግዚአብሔርን መማር ባይሆንላቸው ባሉበት ሆነው በጽሑፍም ሆነ በምስል የተደገፉ ትምህርቶችን መማር እንዲችሉ በማሰብ ከመቼውም በበለጠ ትኩረት በመስጠት ቀድሞ የነበረውን ቤተክርስቲያናችንን ዌብሳይት በድጋሚ በአዲስ ዌብሳይት በማሻሻል ስራውን አጠናቀን ለዚህ በቅተናል።በዚህ አጋጣሚ እኔም በግሌ በተለይም በፊኒክስና አካባቢዋ ለምትኖሩ ብርቅዬ ውድ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ልጆቼ በሙሉ እንኳን ደስ አላችሁ በማለት መልእክቴን ለማስተላለፍ እወዳለሁ።

    ውድ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች---በተለይም ከአገር ርቀን መኖራችን ለመለያየት ምክንያት ሳይሆነን ቅዱስ ጳውሎስ ለገላትያ ምእመናን በላከው መልእክቱ በገላ᎐ ም᎐ ፫፥፳፮ - ፳፰  “በእምነት በኩል ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ የእግዚአብሔር ልጆች ናችሁና ከክርስቶስ ጋር አንድ ትሆኑ ዘንድ የተጠመቃችሁ ሁሉ ክርስቶስን ለብሳችኋልና:: አይሁዳዊ ወይም የግሪክ ሰው የለም ባሪያ ወይም ጨዋ ሰው የለም ወንድም ሴትም የለም ሁላችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ አንድ ሰው ናችሁና” ብሎ ያስተማረውን የእግዚአብሔርን ቃል አብነት አድርገን በአንድነት ስለአንዲት ቅድስት ቤተክርስቲያን ከመቼውም በበለጠ  “መጠራታችሁንና መመረጣችሁን ታጸኑ ዘንድ ከፊት ይልቅ ትጉ” ፪ኛ ጴጥ᎐ ም᎐ ፩፥፲ ብሎ ሊቀ ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ እንዳስተማረን በትጋት በጋራ እንድንሰራ በእግዚአብሐር ስም ለማሳሰብ እወዳለሁ።

      በመጨረሻም ሁላችንም በዚህ በምንኖርባት አገር በአሜሪካ የወለድናቸውን ልጆቻችን በዚህ አገር ባህል እንዳይወሰዱብንና ሃይማኖታቸውንም ሆነ ባህላቸውን እንዲጠብቁ እናት አባት ወገናቸውን አክባሪ አገራቸውን አፍቃሪ ለሃይማኖታቸው ተቆርቋሪ እንዲሆኑ ትልቁን ድርሻ በመወጣት ላይ ያለችውን ቤተክርስቲያናችንን በሚያስፈልገው ሁሉ ከጎን በመሆን በተለይም ይህ ዌብሳይት ለልጆቻችን ምን ያህል ጠቀሜታ እንደሚሰጥ በመረዳት ሁላችንም የበኩላችንን ድጋፍ እንድናደርግ ለማሳሰብ እወዳለሁ። ከዚህም ጋር ተያይዞ ይህንን ዌብሳይት እዚህ ለማድረስ የደከሙትን ሁሉ ከልብ አመሰግናለሁ። በመቀጠልም ሁላችንም ሃላፊነታችንን እንድንወጣና የምናገለግለውም አገልግሎት የተቃና እንዲሆንል በጸሎታችሁ እንድታስቡን ለማሳሰብ እወዳለሁ።

ስለሁሉም የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት የሰማዕቱ የቅዱስ እስጢፋኖስ በረከት አይለየን አሜን!

                  መልአከመዊዕ ቀሲስ ዮሐንስ ቀለመወርቅ

                   የደብረመዊዕ ቅድስት ሥላሴ ወቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን አስተዳዳሪ

bottom of page