top of page

ነገረ ቅዱሳን ማለት ምን ማለት ነው?


‹‹ነገር›› ማለት፡- በቤተ ክርስቲያን የአንድነት ትምህርት ሙሉ መግለጫ በመሆን ያገለግላል፡፡ በዚህ ነገር ስንል ስለአንድ ነገር የሚናገር፣ የሚያስረዳ፣ የሚተርክ ለዛ ለሚነገርለት ነገር እንደ መግለጫ አስረጂ ሆኖ የሚቀርብ ቃል ነው፡፡

‹‹ነገረ ቅዱሳን›› ማለት፡- ቅዱሳን ከልደታቸው እስከ እረፍታቸው ድረስ በሕይወታቸው ዘመን ሁሉ ሕገ እግዚአብሔርን አክብረው፣ ትእዛዙን ፈጽመው የኖሩና የሚኖሩ የእግዚአብሔር ልጆችን እንዲሁ የቅዱሳንን መላእክትን ነገር የምንማርበት ትምህርት ቤት ነው፡፡

አንድም ነገረ ቅዱሳን ስንል፡- ኃይማኖት ይዘው ምግባር ሠርተው በስርዓት ተጉዘው እስከሞት ድርስ ታምነው ለተገኙ የእግዚአብሔር ወዳጆች፣ ንጹሐን መላእክት ክብሩን እንደገለጸላቸውና እንደሚገልጽላቸው የሚያስረዳ ነው፡፡

ነገረ ቅዱሳንን መማር (ማወቅ) ለምን አስፈለገ?
ነገረ ቅዱሳንን ስንማር ከቅዱሳኑ ታሪክ ባሻገር የቅዱሳንን ሁሉ አስገኚ፣ የቅዱሳን ሁሉ ክብርና አክሊል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑን ላላወቁ ለማሳወቅ፣ ላወቁትም ለማጽናት መማር አስፈልጓል፡፡ ሮሜ. 8÷30 ‹‹አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአልና አስቀድሞም የወሰናቸውን እነዚህን ደግሞ ጠራቸው፡፡ የጠራቸውንም እነዚህን ደግሞ አጸደቃቸው፡፡ ያጸደቃቸውንም እነዚህን ደግሞ አከበራቸው ›› እንዲል፡፡ የከፈሉትን ሰማዕትነት፣ የተቀበሉትን መከራ፣ ያሳዩትን ትእግስትና ጽናት ለምዕመናን ያለውን አርአያነት በቃልና በጽሑፍ ለማስተማር ማንነታቸውን ለማሳወቅ መማር አስፈልጓል፡፡ ቅዱስ ኤፍሬም በውዳሴ ማርያም ዘሐሙስ ላይ፡- ‹‹ሰማዕታት የዚህችን ዓለም ጣዕም በእውነት ናቁ ደማቸውንም ስለ እግዚአብሔር አፈሰሱ ስለ መንግሥተ ሰማያትም መራራ ሞትን ታገሱ›› ብሏል፡፡ ከእግዚአብሔር ያገኙትን የቃል ኪዳናቸውን በረከት በተለያዩ መንገድ ለእኛ ለምእመናን እንድንጠቀምበት፡፡ ታሪካቸው የቤተ ክርስቲያን ታሪክ አካል በመሆኑ የነበሩበት ዘመን፣ ያበረከቱት አስተዋፅኦና አጠቃላይ ሁኔታዎች በወቅቱ የነበረውን የቤተ ክርስቲያን ሁኔታ ለማወቅ (ለመረዳት) እንማራለን፡፡ ቅዱሳን የቤተ ክርስቲያንን ትምህርተ ኃይማኖት፣ ሥርዓትና ትውፊት ለይተው በመንፈስ ቅዱስ አጋዥነት የጻፉትን መጻሕፍት እንድናውቅና ለሕይወት እንድንጠቀምበት ነገረ ቅዱሳንን እንማራለን፡፡

ቅዱሳንን ማወቃችን ምን ጥቅም አለው?
ሰይጣን የብርሃን መልአክ መስሎ እንዳይገባ መከላከያ ይሆኑናል
ተኩላዎች በጎችን መስለው እንዳይንቀሳቀሱ እውተኛ እረኛ ይሆኑናል
ቤተ ክርስቲያን መታሰቢያቸውን ለይታ ለመፈጸምና ለእኛ ለማሳወቅ ያስችላታል
ምዕመናን በክርስቶስ የወይን ግንድነት ላይ ቅርንጫፍ በመሆን ብዙ ፍሬ ያፈሩ የኃይማኖት አባቶቻቸውን አውቀው ከአታላዮች፣ ከአስመሳዮች፣ ከሐሳውያን ቅዱሳን እንድንጠበቅ ይረዱናል፡፡

ነገረ ቅዱሳን ማለት ምን ማለት ነው?
የባህሪ ቅድስናና የጸጋ ቅድስና

የባህሪ ቅድስናና የጸጋ ቅድስና
 

1. የባህሪ ቅድስና
የባህሪይ ቅድስና ገንዘብነቱ ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ቅዱስ የሚለው ቃል ከሁሉ በፊት የሚያገለግለው ለእግዚአብሔር ብቻ ነው፡፡ ይህም የእግዚአብሔር የባህሪዩ መገለጫ ሆኖ የሚጠራበት ስያሜ ሲሆን ቅድስናው ከእርሱ የማይለይ ከማንም ያልተቀበለው፣ ያልተዋሰው ማንም ሊወስድበት የማይችል የራሱ ገንዘብ ማለት ነው፡፡

‹‹እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተም ቅዱሳን ሁኑ›› እንዲል፡፡  ዘሌ. 19÷2

‹‹ወደ ቅዱስ መቅደስህ እሰግዳለሁ፤ ስለምህረትህና ስለ እውነትህ ስምህን አመሰግናለሁ፤ በሁሉ ላይ ቅዱስ ስምህን ከፍ ከፍ አድርገሀልና ›› እንዲል፡፡  መዝ. 137÷2


2. የጸጋ ቅድስና
‹‹ጸጋ›› ማለት፡- ቸርነት፣በጎነት፣ምህረት፣ያለብድራት፣ያለዋጋ የሚደረግ ስጦታ ማለት ነው፡ በመሆኑም የጸጋ ቅድስና ስንል ከእግዚብሔር በጸጋ (በስጦታ) የተሰጠ ወይም የተገኘ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ማንኛውም ከእግዚአብሔር የሚገኝ ሃብት ሁሉ የጸጋ ቅድስና፣ የጸጋ ሀብት ይባላል፡፡

‹‹ጽድቅና ፍርድን ይወድዳል የእግዚአብሔር ቸርነት ምድርን ሞላች››  መዝ. 32÷5

‹‹እግዚአብሔር ለሚወድዱት እንደ አሳቡም ለተጠሩት ነገር ሁሉ ለበጎ እንዲደረግ እናውቃለን ›› እንዲል፡፡ ሮሜ 8÷28

ከላይ የተጠቀሱት የመጽሐፍ ቅዱስ ኃይለ ቃላት ውስጥ ቸርነት፣ በጐነት እያለ የተጠቀሰው የእግዚአብሔር የባህሪይ ገንዘቡ ስለሆነውና ከእግዚአብሔር ለሰው ልጆች ስለሚሰጠው የጸጋ ቅድስና ነው፡፡ ስለዚህ የቅድስና ጥሪ ለሰው ዘር ሁሉ የተላለፈ ጥሪ ቢሆንም የተቀበሉትና በሕይወት የኖሩበት ጥቂቶች ናቸው፡፡

‹‹የተጠሩ ብዙዎች፣ የተመረጡ ግን ጥቂቶች ናቸውና›› እንዲል፡፡ማቴ. 22÷14

ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የምትላቸው እነማንን ነው?

ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን የምትላቸው እነማንን ነው?
ቅዱሳን መላእክት፡- ቅዱሳን መላእክት ከማንኛውም ነገር የራቁ፣ ሥርዓታቸውን የጠበቁ፣ እግዚአብሔርን ያወቁ፣ እግዚአብሔርን የሚቀድሱ ስለሆኑ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
‹‹አንዱም ለአንዱ፣ ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር ምድር ሁሉ ከክብሩ ተሞልታለች እያሉ ይጮሁ ነበር፡፡››  ኢሣ. 6÷3 ስለዚህ በባህሪዩ ቅዱስ የሆነውን እግዚአብሔርን ስለሚያመሰግኑ፣ ስለሚቀድሱ ቅዱሳን ተብለዋል፡፡

ቅዱሳን አበው፡- መጻሕፍት ሳይጻፍላቸው መምህራን ሳይላኩላቸው በሕገ ልቡና በቃል ብቻ የተላለፈላቸውን ይዘው እንዲሁም በሥነ ፍጥረት በመመራመር ፈጣሪያቸውን አምነው እርሱ የሚወደውን ሥራ የሠሩና በጣኦት አምልኮ ራሳቸውን ያላረከሱ አባቶች ቤተ ክርስቲያናችን ቅዱሳን ትላቸዋለች፡፡ ለምሣሌ አበው ብዙኃን አብርሃም ኩፋሌ 50÷42-44፣ 11÷1

ቅዱሳን ነቢያት፡- እግዚአብሔር ከማኅፀን ጀምሮ ጠርቶ መርጧቸው ሀብተ ትንቢትን አጐናጽፏቸው ያለፈውንና ወደፊት የሚሆነውን በእርግጠኝነት እየተናገሩ ሕዝቡን ይመክሩትና ይገስጹት የነበሩ ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ የምትጠራቸው አባቶች ናቸው፡፡
‹‹ትንቢት ከቶ በሰው ፈቃድ አልመጣምና፣ ዳሩግን በእግዚአብሔር ተልከው ቅዱሳን ሰዎችበ መንፈስ ቅዱስ ተነድተው ተናገሩ›› 2ኛጴጥ 1÷25 እንዲል፡፡

ቅዱሳን ሐዋርያት፡- በነቢያት የተነገረውን ቃለ ትንቢት መድረሱንና በዘመናቸው መፈጸሙን ለዓለም እንዲያስተምሩ ጌታችን ራሱኑ ተከተሉኝ ብሎ የጠራቸውና የመረጣቸው ናቸው፡፡
‹‹በእውነት ቀድሳቸው ቃልህ እውነት ነው፡፡ወደ ዓለም እንደላክኸኝ እንዲሁ እኔ ወደ ዓለም ላክኋቸው፤ እነርሱም ደግሞ በእውነት የተቀደሱ እንደሆኑ እኔ ራሴን ስለ እነርሱ እቀድሳለሁ›› ዮሐ. 17÷17-19

ቅዱሳን ጻድቃን፡- ቅዱሳን ጻድቃን ጌታን አርአያ አድርገው መላ ዘመናቸውን ከጣዕመ ዓለም ተለይተው ፈቃደ ሥጋቸውን ለፈቃደ ነፍሳዋው  አስገዝተው በጾም፣ በጸሎት፣ በስግደት፣ በምናኔ ጸንተው ድምጸ አራዊትን፣ ጸብአ አጋንንትን፣ ግርማ ሌሊትን ሳይሳቀቁ ዳዋ ጥሰው፣ ደንጊያ ተንተርሰው፣ ጤዛ ልሰው የኖሩ አባቶችን ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ማዕረግ ታከብራቸዋለች፡፡
‹‹ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ያገኛል ›› ማቴ 10÷42 እንዲል፡፡

ቅዱሳን ሰማዕታት፡-  ቅዱሳን ሰማዕታት ጌታችን በጲላጦስ ፊት ‹‹ እኔ እውነት ልመሰክር ስለዚህ ተወልጃለሁ ስለዚህም ወደ ዓለም መጥቻለሁ ›› ዮሐ 18÷37 ያለውን ምስክርነት በመከተል እግዚአብሔርን አንክድም ለጣኦት አንሰግድም በማለት በዓላውያን ነገስታት ፊት ሳይፈሩና ሳያፍሩ ቆመው የመሰከሩትን ቤተ ክርስቲያን በቅድስና ትጠራቸዋለች፡፡

ቅዱሳን ነገሥታት፡- እንደ አሕዛብ፣ ዓላማውያን ነገሥታት በሥልጣናቸው በሀብታቸው በሠራዊታቸው ሳይመኩ ኃይማኖት ይዘው ምግባር ሰርተው የተገኙ እንደ ዳዊት ያሉ ቅዱሳን አባቶችናቸው፡፡

ቅዱሳን ሊቃውንት፡- ቅዱሳን ሊቃውንት ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ያልተመሰለውን መስለው የተመሰለውን ተርጉመው በማስተማር መጻሕፍትን በመተርጐም መናፍቃንን ጉባኤ ሰርተው ረትተው ያስተማሩ ቅዱሳን ይባላሉ፡፡
‹‹መልካሙን የምስራች የሚያወሩ እግሮቻቸው እንዴት ያማሩ ናቸው›› ሮሜ 10÷15

ቅዱሳን ጳጳሳት፡- ቅዱሳን ጳጳሳት የካህናትና የምዕመናን፣ የሰማያውያንና የምድራውያን አንድነት የሆነችውን ቤተ ክርስቲያን በኃይማኖት በመምራት መንጋውን ከተኩላ በመጠበቅ የክርስቶስን ትዕዛዝ የፈጸሙ ቅዱሳን ናቸው፡፡

ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል)፡- ቅዱሳን መነኮሳት (ደናግል) ከሕገ እንስሳ ሕገ መላእክት ይበልጣል ብለው ራሳቸውን ለክርስቶስ አጭተው ከሴት ወይም ከወንድ ርቀው ስለ መንግሥተ ሰማያት ብለው ራሳቸውን ጃንደረቦች ያደረጉ ናቸው፡፡

ቅዱሳት አንስት፡- ጌታችን መርጦ ካስከተላቸው 120ው ቤተሰብ 36ቱ ቅዱሳት አንስት ጌታ ሲሰቀል ሳይሸሱ፣ በመቃብሩም በመገኘት፣ የትንሳኤው ምስክርም በመሆን መከራ በበዛበትና በጸናበት የክርስትና ጐዳና የተጓዙ እናቶች፣ እህቶች ሁሉ ቅዱሳት አንስት ይባላሉ፡፡

ቅዱሳት መካናት፡- ማለት የተለዩ፣ የተከበሩ ሥራዎች ቦታዎች እግዚአብሔር በመዝሙር፣ በቅዳሴ፣ በማኅሌት ይገለገልባቸው ዘንድ የመረጣቸው ገዳማትና አድባራት ቅዱሳት መካናት ይባላሉ፡፡
‹‹የእግዚአብሔር ሠራዊት አለቃ ኢያሱን፡- አንተ የቆምክባት ስፍራ የተቀደሰ ነውና ጫማህን ከእግርህ አውልቅ አለው›› ኢያሱ 5÷15

ቅዱሳት መጻሕፍት፡- ቅዱሳት መጻሕፍት የሚባሉት የብሉያትና ሐዲሳት፣ የመነኮሳትና ሊቃውንት፣ እንዲሁም አዋልድ መጻሕፍት ናቸው፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ስንል የተመረጡ፣ የተከበሩ የተወደዱና የተመሰገኑ መጻሕፍት ማለት ነው፡፡


ቅዱሳን መጻሕፍት ቅዱስ መሰኘታቸው የሰውን ልጅ መነሻና መድረሻ ታሪክ በሦስቱም ሕግጋት የተነሱ ቅዱሳን ጥንተ ክብራቸውን ገድላቸውን ከእግዚአብሔር የተቀበሉትን ጸጋ እግዚአብሔር ወልድ የሰውን ልጅ ለማዳን ያደረገውን ጉዞ የማዳን ሥራውን ስለያዙ ቅዱሳን ተባሉ፡፡

ቅዱሳትሥዕላት፡- በእግዚአብሔር ትእዛዝና ፈቃድ ተስለው የእግዚአብሔር ስም በሚጠራበት ቦታ የሚቀመጡና ከስዕሉ ባለቤት ተራዳኢነትና በረከትን ለማግኘት የሚጠቅሙ የእግዚአብሔር ልዩ ስጦታዎች ናቸው፡፡ ዘፀ. 25÷18-22፣ዘኁ. 7÷89


ሥጋዊውን ዓለም ከሚያንጸባርቁ ዓለማውያን ሥዕላት ፈጽመው የተለዩ በመሆናቸው ነው፡፡ የቅዲሳኑ ቅድስና ሥዕላቱንም ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል:: ሥዕላቱ በራሳቸው የሚያደርጉት ገቢረ ተአምራት ቅዱሳት አሰኝቷቸዋል፡፡

ቅዱሳት ንዋያት፡- በእግዚአሔር ቤት ውስጥ ለመንፈሳዊ አገልግሎት የሚውሉ ንዋያት ሁሉ የተቀደሱ ናቸው፡፡ ምክንያቱም አገልግሎቱ የሚፈፀመው ቅድስና የባህሪይ ገንዘቡ ለሆነ ለእግዚአብሔር ነውና፡፡

ቅዱስ መስቀል፡- የጌታችን ቅዱስ መስቀል ሕያው፣ አማናዊ በሆነው በክርስቶስ ደም ከመክበሩ የተነሳ ቅዱስ ተብሏል፡፡
(ቅዱስ ያሬድ ስለመስቀሉ በድጓ ዘክረምት ላይ እንዲህ ብሏል) ‹‹የቅዱሳን ክብራቸው የጻድቃን ሞገሳቸው የዕውራን ብርሃናቸው እነሆ ይህ መስቀል ነው›› ብሏል፡፡

ታቦት፡- ቤተክርሲያን ቅዱስ ብላ ከምታከብራቸው አንዱ ታቦተ ሕጉን ነው፡፡
ታቦት ማለት በግእዝ ቋንቋ ማዳሪያ፣ ማዳኛ ማለት ሲሆን በዚህ ታቦት ላይ እግዚአብሔር የሚያድርበትና የሚገለጥበት የጽላት ሕጉ ማዳሪያ ነው፡፡ ዘፀ. 25÷22

የቅዱሳኑ ክብራቸው በቤተ ክርስቲያን

 

ቤተክርስቲያን የቅዱሳንን ውለታ አትረሳም፡፡ በአጸደ ሥጋ ያሉትን በማገልገል ያረፉትን ቅዱሳንን ደግሞ በማክበር ገድላቸውን በመጻፍ መታሰቢያቸውን ታደርጋለች፡፡
‹‹እግዚአብሔር ቅዱሳንን ስላገለገላችሁ እስከ አሁንም ስለምታገለግሉአቸው ያደረጋችሁትን ሥራ ለስሙም ያሳያችሁትን ፍቅር ይረሳ ዘንድ አመጸኛ አይደለምና፡፡›› ዕብ. 6÷10 ዕብ. 11÷32……
ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳንን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በጸበል፣ ቤተ ክርስቲያን በማነጽጽላትበመቅረጽታስባቸዋለች፡፡

‹‹በቤቴና በቅጽሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋልሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ፡፡››ኢሣ. 56÷5
ቤተ ክርስቲያን በቅዱሳን የልደትና የእረፍት ዕለታት የመታሰቢያ በዓል በማድረግ በቅዳሴና በማኅሌት በማክበር በዓለ ንግሥ ታደርጋለች፡፡ በስማቸው ጠበል ጸዲቅ ታደርጋለች፡፡ ማቴ 10÷40-42
ሌላው ቤተክርስቲያን ቅዱሳንን የምታስበው የተጋደሉትን ተጋድሎ፣ የደረሰባቸውን ፈተና፣ ያደረጉትን ውጊያ፣ ጦርነት ድልና አክሊል እስካገኙበት ድረስ ያሉትን ገድላቸውን በመጻፍ ታስባቸዋለች፡፡ 2ኛጢሞ 6÷12፣ይሁዳ ቁጥር 3 ማጠቃለያ እግዚአብሔር ከ22ቱ ስነፍጥረት በቅድስና ማዕረግ ስሙን ቀድሰው ክብሩን እንዲወርሱ አድርገው የፈጠራቸውቅ ዱሳን መላእክትንና፣ የሰው ልጅን ነው፡፡

"ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚቀድስ ማነው? ቀዳማዊ ዜና መዋ 29:5
ከዚህ መልዕክት እንደምንረዳው እግዚአብሔርን ለማገልገል ራስን መለየት እንደሚገባ ነው:: ከቃሉ ትርጉም ስንነሳ "ቀደሰ" የሚለው ሐረግ የሚያመለክተው "ለየ" "አከበረ" መረጠ ሲሆን ስንተረጉመው "ዛሬ በፈቃዱ ራሱን ለእግዚአብሔር የሚለይ ማንነው?" የሚለው ይሆናል:: እግዚአብሔር ለቅዱሳኑ የሰጠውን ክብርና ጸጋ የሚገልጽባቸው  ብዙ መንገዶች አሉ:: እነዚህም የቅዱሳኑን ማንነት መግለጫና ለሰውጥቅም የተሰጡናቸው:: እነርሱም እንደሚከተለው ተዘርዝርዋል::

1ኛ.በስማቸው ቤተ ክርስቲያን ማነጽ


ቤተ ክርስቲያን የእግዚአብሔር ስም በማኅበር የሚጠራባት:እግዚአብሔርም ጸጋውንና በረከቱን የሚያድልባት የምህረት ግምጃ ቤት ናት::
ኢሳ 1:26 "...የጽድቅ ከተማ: የታመነች ከተማ ተብለሽ ትጠሪያለሽ" እንዲል::
መድኃኒታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስም ዕለት ዕለት በቤተ መቅደስ እየተገኘ ያስተምር ነበር:: ቤተክርስቲያን
"የአባቴ ቤት" ብሎታል: ሉቃ 2:49:: እግዚአብሔር አምላክ በዚህ ቤቱ ወዳጆቹ ቅዱሳን እንዲታሰቡበት እንዲህ ሲል አዞአል::
ኢሳ 56:4-7 "እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ። ያገለግሉት ዘንድ የእግዚአብሔርንም ስም ይወድዱ ዘንድ ባሪያዎቹም ይሆኑ ዘንድ ወደ እግዚአብሔር የሚጠጉትንም መጻተኞች፥ እንዳያረክሱ ትሰንበትን የሚጠብቁትን ቃል ኪዳኔንም የሚይዙትን ሁሉ፥ ወደ ተቀደሰ ተራራዬ አመጣቸዋለሁ፥ በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ" እግዚአብሔር ይህንን ቃል ኪዳን የገባው ለጃንደረቦች ነው:: ጃንደረባ የሚለውን ደግሞ ሲፈታው
ማቴ 19:10-12 "ይህ ነገር ለተሰጣቸው ነው እንጂ ለሁሉ አይደለም፤ በእናት ማኅፀን ጃንደረቦች ሆነው የተወለዱ አሉ፥ ሰውም የሰለባቸው ጃንደረቦች አሉ፥ ስለ መንግሥተ ሰማያትም ራሳቸውን የሰለቡ ጃንደረቦች አሉ። ሊቀበለው የሚችል ይቀበለው። ስለሆነም ቅዱሳን ስማቸው የማያልፍ: ሁልጊዜ የሚዘከርና የማይጠፋ እንደሆነ በማይታበል ቃሉ ተናገረ::
"በጸሎቴም ቤት ደስ አሰኛቸዋለሁ" ማለቱም ስማቸው የሚዘክረውና የሚጠራው በቤቱና በቅጥሩ ውስጥ በመሆኑ ነው:: ራሳቸውን ስለ እርሱ ፍቅር ሲሉ ጃንደረቦች ያደረጉት የወዳጆቹ የቅዱሳን ስም በራሱ ቤት ማለትም በቤተክርስቲያን እንዲጠራ ቅዱስ ፈቃዱ መሆኑን ራሱ እግዚአብሔር እንዲህ ነግሮናል::

ስለዚህ ቅድስትና ሐዋርያዊት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የእግዚአብሔርን ቤት በቅዱሳን ስም የምትሰይመው ይህን የፈጣሪዋን ትእዛዝ ይዛ እንጂ በልብ ወለድ አይደለም:: የቅዱሳኑ ስም የማይጠፋና የማያልፍ ዘለዓለማዊ በመሆኑ ከብዙ ጊዜ በፊት ገድላቸውን ፈጽመው ያረፉ ቅዱሳን ስም ቢሰየምም በውስጡ የሚሰራው ስራ ማኅሌቱ: ቅዳሴው: መሥዋዕቱ: አገልግሎቱ ሁሉ አንድ ነው:: የሚመሰገነው እግዚአብሔር ሲሆን የሚሰዋውም አንድ የክርስቶስ ሥጋና ደም ነው:: መታሰቢያነቱ ለቅዱሳን እንዲሆን ያዘዘ የቤቱ ባለቤት እግዚአብሔር ነው:: ይህንን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ የሰጠውን ክብር የሚቃወም ካለ ባለቤቱ ኢየሱስ ክርስቶስ

በማቴ  20:15 "በገንዘቤ የወደድሁትን አደርግ ዘንድ መብት የለኝምን? ወይስ እኔ መልካም ስለሆንሁ ዓይንህ ምቀኛ ናትን?":: ይለዋል::

2ኛ.በስማቸው ጸበልን: ጽላትን እና ሌሎችንም የተቀደሱ ነገሮች መሰየም


በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ጸበል ብለን የምንጠራው በእግዚአብሔር ኃይል ሕሙማን የሚፈወሱበትና ልዩ ልዩ ተአምራትን የሚደረግበት የተለየ (የተቀደሰ) ውኃ ነው:: የተለየ (የተቀደሰ) መባሉም በዓይነ ሥጋ ሲያዩት እንደማንኛውም ውኃ ሲሆን ነገር ግን እግዚአብሔር አምላክ ቸርነቱን የሚገልጽበትና ኃይሉን የሚያሳይበት ልዩ ውኃ ስለሆነ ነው::

ሲፈጠር ጀምሮ ዕውር የነበርውን ሰው አምላክችን ኢየሱስ ክርስቶስ መለኮት የተዋሃደውን ቅዱስ ምራቁን እንትፍ ብሎ በምራቁ ጭቃ አደረገና የዚያን ዕውር ዓይኑን ቀባው:: ከቀባውም በኃላ "ሒድና በሰሊሆም መጠመቂያ ታጠብ" አለው ዮሃ 9:1:: ዕውሩም ሄዶ ታጠበና እያየ ተመለሰ:: ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዕውሩን ጭቃ ከቀባው በኃላ ለምን በሰሊሆም መጠመቂያ እንዲጠመቅ አዘዘው? ያዳነው ራሱ ነው:: እርሱ ራሱ አግኝቶትና ፈውሶት ሳለ ሄዶ መታጠብ ለምን አስፈለገ? ጌታችን ይህንን ያደረገው ኃይሉን በጸበል ላይ ማሳደሩን ለመግለጽ ነው:: እግዚአብሔር ፈውስ የሚሰጥበት ቅዱስ ውኃ  "ጸበል"  መባሉም ጌታችን የዚህን ዕውር ዓይን የፈጠረው መለኮት በተዋሀደው ቅዱስ ምራቁ ለውሶ ጭቃ ባደረገው መሬትና ከሰሊሆም መጠመቂያ ከተገኘው ቅዱስ ውኃ ድብልቅ በመሆኑ ነው:: እንዲሁም በጭቃ በተዋሀደ ቅዱስ ምራቁ አማካይነት ኃይሉን ስላሳደረበት ነው:: ወደ መጠመቂያ ጸበል ሄዶ መጠመቅ ራሱ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያዘዘው መለኮታዊ ትእዛዝ እንጂ የፍጡር ትእዛዝ አይደለም::

3ኛ.የጸጋ ስግደት መስገድ


ስግደት የአክብሮት የተገዢነት እንዲሁም የትሕትና መግለጫ ነው:: አላማው የሚወሰነውም እንደሚሰገድለት አካል ማንነት ነው:: ለእግዚአብሔር የሚቀርብ ስግደት የአምልኮ መግለጫ ሲሆን ይህም ፈጣሪነቱን ከሃሊነቱንና ገናንነቱን እያሰቡ በፍጹም ሰውነትና ሕሊና መሬት ላይ በመውደቅ የሚፈጸም ስግደት ነው:: ይህ የአምልኮት ስግደት ለሌላ ለምንም አይቀርብም ነገር ግን እግዚአብሔር ለወዳጆቹ ለቅዱሳን የአክብሮት ስግደት እንዲሰገድላቸው ፈቅዶአል:: ይኽውም ስግደቱን የሚያቀርበው ሰው ለቅዱሳኑ ያለውን አክብሮት በተግባር ከሚገልጽባቸው መንገዶች አንዱ ነው::
"ሳኦልም ሳሙኤል እንደሆነ አወቀ፥ በፊቱም ተጐነበሰ፥ በምድርም ላይ እጅ ነሣ።" 1ኛሳሙ 28:14

"ከኢያሪኮም መጥተው በአንጻሩ የነበሩት የነቢያት ልጆች ባዩት ጊዜ። የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ ወደ ምድር ተደፉ።"2ኛ ነገ 2:15

"ዳዊትም ወደ ኦርና በመጣ ጊዜ ኦርና ተመልክቶ ዳዊትን አየ ከአውድማውም ወጥቶ ዳዊትን እጅ ሊነሣ በምድር ላይ ተደፋ።"1ኛዜና 21:21

"የዚያን ጊዜም ንጉሡ ናቡከደነፆር በግምባሩ ተደፍቶ ለዳንኤል ሰገደለት፥"ዳን 2:46

"በሦስተኛውም ቀን፥ እነሆ፥ ከሳኦል ሰፈር አንድ ሰው ልብሱን ቀድዶ በራሱም ላይ ትቢያ ነስንሶ መጣ ወደ ዳዊትም በመጣ ጊዜ በግምባሩ ተደፍቶ እጅ ነሣ።"2ኛሳሙ 1:1

"ያዕቆብም ዓይኑን አነሣ፥ እነሆም ዔሳውን ሲመጣ አየው፥ ...ሴቶች ባሪያዎችም ከልጆቻቸው ጋር ቀርበው ሰገዱ ደግሞም ልያና ልጆችዋ ቀርበው ሰገዱ ከዚያም በኋላ ዮሴፍና ራሔል ቀርበው ሰገዱ።" ዘፍ 33:1-8

"ጴጥሮስም በገባ ጊዜ ቆርኔሌዎስ ተገናኝቶ ከእግሩ በታች ወደቀና ሰገደለት።" ሐዋ 10:25

"እነሆ፥ አይሁድ ሳይሆኑ። አይሁድ ነን ከሚሉ ነገር ግን ከሚዋሹ ከሰይጣን ማኅበር አንዳንዶችን እሰጥሃለሁ እነሆ፥ መጥተው በእግሮችህ ፊት ይሰግዱ ዘንድ እኔም እንደወደድሁህ ያውቁ ዘንድ አደርጋቸዋለሁ።" ራዕ 3:9

የቅዱሳኑ ክብራቸው በቤተ ክርስቲያን

አማላጅነታቸው በአጸደ ሥጋ


1ኛ. የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ባለመስማቱ እግዚአብሔር ግብፅን በዕንቁራሪት /ጓጉንቸር/ አስወረራት፣ መላዋ የግብፅ አገር በእንቁራሪት ተሸፈነች፣ ፈርዖንም ይህን አስደንጋጭ መቅሰፍት አይቶ ሙሴና አሮንን ጠርቶ /ጓጉንቸሮቹ/ ከእኔና ከሕዝቤም እንዲርቁ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ አላቸው፡፡ ሙሴም ወደ እግዚአብሔር ጸለየ /አማለደ/ እግዚአብሔርም በሙሴ ምልጃ ጓጉንቸሮቹን በሙሉ ገደለ፣ ዘጸ. 8፡8-15፡፡


2ኛ. ተናካሽ የዝንብ መንጋ ዘጸ. 8፡25-31፡፡


3ኛ. እስራኤላውያን ጣዖትን በማምለክ ከባድ ኃጢአት በፈጸሙ ጊዜ እግዚአብሔር ሙሴን ጠርቶ ይህን ሕዝብ አጠፋለሁ /እደመስሳለሁ/ አንተም በታላቅ ሕዝበ ላይ እሾምሃለሁ ባለው ጊዜ ሙሴ ወደ ፈጣሪው ወደ እግዚአብሔር አጥብቆ ጸለየ /አማለደ/ በዚህ ጊዜ መሐሪ እግዚአብሔር በሙሴ ምልጃ ሊያደርገው ካሰበው መቅሰፍት በራሱ መሐሪነት ተመልሶ መቅሰፍቱን አስቀረ ሕዝቡንም በሙሉ ጸሎት ምልጃ ይቅር አለ ዘጸ. 32፡11-14፡፡


4ኛ. ሙሴ ኢትዮጵያዊትዋን ሴት ልጅ በማግባቱ ወንድሞቹ አሮንና ማርያም ሙሴን በመቃወም አሙት በዚህም ምክንያት እግዚአብሔር የነገሩ ቆስቋሽና ጀማሪ የነበረችውን ማርያምን በለምጽ በሽታ መታት /በረዶ መሰለች/ ነገር ግን ሙሴ ሰባት ቀን ወደ እግዚአብሔር ጸለየላት /ማለደላት/ እግዚአብሔርም በሙሴ ጸሎት /ምልጃ/ፈወሳት ዘኁል.12፡1-7፡፡
የነቢየ እግዚአብሔር አማላጅነት ስሙ በውል ያልተጠቀሰ ብእሴ እግዚአብሔር በሚል ስያሜ ብቻ የተጠቀሰው በመሰውያ ላይ ዕጣን እያጠነ በነበረው የኢዮርብዓም ላይና በመሰውያው ላይ ትንቢት በመናገሩ ንጉሱ ኢዮርብዓም ተው ያዙት ብሎ እጁን ዘረጋ በዚህ ጊዜ በትንቢቱ መሠረት በደቂቃ ውስጥ የተዘረጋች የንጉሡ እጅ እንደብረት ደርቃ እንደተዘረጋች ቀረች ሊያጥፋት ቢሞክርም አልቻለም፡፡
ከአቅሙ በላይ ሲሆንበት ኦብእሴ እግዚአብሔር ጸሊሊተ ኅበ እግዚአብሔር በማለት ንጉሡ ወደ እግዚአብሔር ሰው አማልደኝ ብሎ በመለመኑ የእግዚአብሔር ሰውም ወደ መሐሪ እግዚአብሔር በመለመኑ የደረቀችው ንጉሡ እጅ ወደእርሱ ተመለሰች ማለት /ታጠፈች/ እንደ ነበረችውም ሆናለች ይላል. 1ኛነገ. 13፡1-7፡፡


የነቢየ የኤልያስ ምልጃ ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ በምልጃው /በጸሎቱ/ ብዙ አስደናዊ ተአምራቶች ፈጽሞአል፡፡ ከእነርሱም መካከል፡፡


1ኛ. ሕገ እግዚአብሔርን የተው ወገኖችን ለመቅጣትና ለማሳፈር የሰማይ ዝናብ እንዳይዘንብ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ የሰማይ ዝናብም በኤልያስ ቃል ሦስት ዓመት ከስድስት ወር ሳይዘንብ ቀጥ አለ፡፡ ከእነዚህ ዓመታት በኋላ ግን ነቢዩ ኤልያስ ዝናብ እንዲዘንብ ወደ ፈጣሪው /ምልጃ/ ጸሎት አቀረበ፡፡ ዝናብም በሚገባ ዘነበ 1ኛነገ. 17፡1-7 እንደገና 1ኛነገ. 18፡30-46 በጸሎቱ መሥዋዕቱን ከሰማይ እሳት ወርዶ በላለት፡፡


2ኛ. ለሞተው ሕፃን ልጅ ስለእናቱ ሲል ኤልያስ ወደ እግዚአብሔር ጸልዮ /ምልጃ/ አቅርቦ የልጁም ነፍስ ተመልሳ ልጁም ከሞት ተነሳ 1ኛነገ. 17፡17-24፡፡


የነቢዩ ኤልሳዕ አማላጀነት


ገቢሬ ተአምር ኤልሳዕም በጸሎቱ /በምልጃው/ ብዙ ተአምራቶች አድርጎአል፡፡ ከተአምራቶቹም መካከል አንደኛው የሞተውን ልጅ ጸልዮ ማስነሳቱ ነው 2ኛነገ. 4፡18-37 ራሱ ታሞ የሞተው ልጅ ነው ያስነሳው፡፡
የዳዊት አማላጅነት "ምንተ ገብሩ እሉ አባግዕ እንዘኖላዊሆሙ አነ ዘአበስኩ" "ጠማማም ሥራ እኔ አድርጌአለሁ፡፡ እነዚህ በጐች ግን ምን አደረጉ እጅህ በእኔና በአባቴ ቤት ላይ እንድትሆን" በማለት ከአንጀቱ በአቀረበው ጸሎት /ምልጃ/ መቅሰፍቱ በፈጣሪ ቸርነት ተገታ 2ሳሙ. 24፡15-25፡፡


የነቢዩ ኤርምያስ ምልጃ

በአሥር ቀን ጸሎት /ምልጃ/ በእስራኤላውያን ታስቦ የነበረውን መቅሰፍት አንደተገታ ተገልጾአል ኤርምያስ. 42፡1-17፡፡ እስካሁን ድረስ ከሞላ ጎደል ያየነው የቅዱሳን ምልጃ በዘመነ ብሉይ ነው፡፡


ከዚህ ቀጥሎ ደግሞ የቅዱሳን ጻድቃን ምልጃ በዘመነ ሐዲስ እናያለን፡-


ይህ የአማላጅነት አገልግሎት ሳይቋረጥ በዘመነ ሐዲስም ማለት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በምድር ላይ በነበረበት ዘመንና በዘመነ ሐዋርያትም ይፈጸም እንደነበረ ከዚህ ቀጥለን እንመለከታለን፡፡ በወንጌል እንደ ተጻፈው "ልጄ ታሞ ለሞት ተቃርቦአልና ፈውስልኝ" በማለት ስለታመሙ ሰዎች ወጥተው በአቀረቡት ምልጃ እንኳን ሲታመሙ ሲሞቱ ሳይቀር ከሞት እያስነሳ በጥያቄአቸው መሠረት ይፈቅድላቸው እንደነበር ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል ማቴ. 9፡18-20፡፡


በዚህ ዓይነት ጌታችንን እየለመኑ ልጆቻቸውን ያዳኑ ብዙ ናቸው ማቴ. 15፡21፣ ማቴ. 17፡14፣ ማር. 5፡22-44፣ ሉቃ. 7፡1-10፡፡
ስለዚህ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አንዳንድ ጊዜ በሽተኞች በቀጥታ ሲለምኑት ይፈውሳቸው እንደነበረ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ ከዚህ በላይ እንዳየነው ስለበሽተኞቹ ሌሎች ሰዎች በማለዱላቸው ጊዜ ይፈውሳቸው ነበር፡፡ በዚህ መሠረት አማላጅነት ማለት አንዱ ስለሌላው መጸለይና መለመን፣ ማማለድ ማለት ነው፡፡


አማላጅነት በዘመነ ሐዋርያት

ሐዋርያት በተሰጣቸው የመንፈስ ቅዱስ ስጦታ መሠረት በሐዲስ አማንያንና በበሽተኞች ላየ እጃቸውን አያኖሩ መንፈስ ቅዱስን ሲያሰጡና ሕመምተኞች ሲፈውሱ ያየ ሲሞን ይህን ታላቅ የመንፈስ ቅዱስ ሥልጣን እንዲሰጠው ገንዘብ ይዞ ወደሐዋርያት ቀረበና እንዲህ አላቸው እጄን በምጭንበት ሁሉ መንፈስ ቅዱስን ይቀበል ዘንድ ለእኔ ደግሞ ይህን ሥልጣን ሰጡኝ አለ፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ ይህንን ሰምቶ ሲሞንን አጥብቆ ገሰጸው ንስሐም እንዲገባ መከረው፡፡ ሲሞን የመንፈስ ቅዱስን ስጦታ /ጸጋ/ በገንዘብ መግዛት /መለወጥ/ ታላቅ ስሕተት መሆኑን ከተገነዘበ በኋላ ቅዱስ ጴጥሮስን ካላችሁት ማለትም ከተናገራችሁት አንዳች እንዳይደርስብኝ እናንተው ወደ ጌታ ለምኑልኝ አማልዱኝ አላቸው ዮሐዋ. 8፡14-25፡፡


ከዚህ ላይ ከሲሞን አባባል የምንረዳው ዓቢይ ቁም ነገር አለ ይኸውም አንዳች ክፉ ነገር እንዳይደርስብኝ እናንተ ወደ እግዚአብሔር አማልዱልኝ /ለምኑልኝ/ ማለቱ በዚያን ጊዜ ሐዋርያት ስለበደሉ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ይጸልዩና ምልጃንም ያቀርቡ እንደነበረ ይረጋገጣል፡፡


ዘፍ 18:23 "አብርሃምም ቀረበ አለም።በውኑ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ታጠፋለህን? አምሳ ጻድቃን በከተማይቱ ውስጥ ቢገኙ በውኑ ሁሉን ታጠፋለህን? ከተማይቱን ስበ እርስዋስ ለሚገኙ አምሳ ጻድቃን አትምርምን? ይህ ከአንተ ይራቅ ጻድቁን ከኃጢአተኛ ጋር ትገድል ዘንድ፥ ጻድቁም እንደኃ ጢአተኛ ይሆን ዘንድ፥ እንደዚህ ያለው አድራጎት ከአንተ ይራቅ። የምድር ሁሉ ፈራጅ በቅን ፍርድ አይፈርድምን? እግዚአብሔርም፦ በሰዶም በከተማይቱ ውስጥ አምሳ ጻድቃን ባገኝ ስፍራውን ሁሉ ስለ እነርሱ እምራለሁ አለ።

ዘፍ 20:7 "እግዚአብሔርም በሕልም አለው፦ ይህን በልብህ ቅንነት እንዳደረግህ እኔ አወቅሁ፥ እኔም ደግሞ በፊቴ ኃጢአትን እንዳትሠራ ከለከልሁህ ስለዚህም ትነካት ዘንድ አልተውሁም። አሁንም የሰውዬውን ሚስት መልስ ነቢይ ነውና፥ ስለ አንተም ይጸልያል፥ ትድናለህም። ባትመልሳት ግን አንተ እንድትሞት ለአንተ የሆነውም ሁሉ እንዲሞት በእርግጥ እወቅ።"

ዘጸ 8:8 ፈርዖንም ሙሴንና አሮንን ጠርቶ። ጓጕንቸሮቹን ከእኔ ከሕዝቤም እንዲያርቅ ወደ እግዚአብሔር ጸልዩልኝ ለእግዚአብሔርም ይሠዋ ዘንድ ሕዝቡን እለቅቃለሁ አላቸው። ሙሴም ፈርዖንን፦ ጓጕንቸሮቹ ከአንተ ከቤቶችህም እንዲጠፉ፥ በወንዙም ብቻ እንዲቀሩ፥ ለአንተ ለባሪያዎችህም ለሕዝብህም መቼ እንድጸልይ አስታውቀኝ አለው። እርሱም፦ ነገአለ። ሙሴም፦ አምላካችንን እግዚአብሔርን የሚመስል እንደሌለ ታውቅ ዘንድ እንደ ቃልህ ይሁን። ጓጕንቸሮቹም ከአንተ ከቤቶችህም ከባርያዎችህም ከሕዝብህም ይሄዳሉ በወንዙም ብቻ ይቀራሉ አለ። ሙሴና አሮንም ከፈርዖን ዘንድ ወጡ ሙሴም በፈርዖን ላይ ስላመጣቸው ጓጕንቸሮች ወደ እግዚአብሔር ጮኸ። እግዚአብሔርም ሙሴ እንዳለ አደረገ ጓጕንቸሮቹም ከቤት ከወጀድም ከሜዳም ሞቱ።

ዘጸ 32:1-15 "እግዚአብሔርም ሙሴን፦ እኔ ይህን ሕዝብ አየሁት፥ እነሆም አንገተ ደንዳና ሕዝብ ነው። አሁንም ቍጣዬ እንዲቃጠልባቸው እንዳጠፋቸውም ተወኝ አንተንም ለታላቅ ሕዝብ አደርግሃለሁ አለው። ሙሴም በእግዚአብሔር በአምላኩ ፊት ጸለየ፥ አለም።አቤቱ፥ ቍጣህ በታላቅ ኃይልና በጽኑ እጅ ከግብፅ ምድር ባወጣኸው በሕዝብ ህላ ይስ ለምን ተቃጠለ?  ግብፃውያንስ። በተራራ መካከል ሊገድላቸው፥ ከምድርም ፊት ሊያ ጠፋቸው ለክፋት አወጣቸው ብለው ስለምን ይናገራሉ? ከመዓትህ ተመለስ፥ ለሕዝብህም በክፋታቸው ላይራራ። ዘራችሁን እንደ ሰማይ ከዋክብት አበዛለሁ፥ ይህችንም የተናገርኋትን ምድር ሁሉ ለዘራችሁ እሰጣታለሁ፥ ለዘላለምም ይወርሱአታል ብለህ በራስህ የማልህላቸውን ባሪያዎችህን አብርሃምንና ይስሐቅን እስራኤልንም አስብ። እግዚአብሔርም በሕዝቡ ላይ ሊያደርግ ስላሰበው ክፋት ራራ።"

2ኛ ነገ 4:32-35 "ኤልሳዕም ወደ ቤት በገባ ጊዜ እነሆ፥ ሕፃኑ ሞቶ በአልጋው ላይ ተጋድሞ ነበር። ገብቶም በሩን ከሁለቱ በኋላ ዘጋ፥ ወደ እግዚአብሔርም ጸለየ። መጥቶም በሕፃኑ ላይ ተኛ አፉንም በአፉ፥ ዓይኑንም በዓይኑ፥ እጁንም በእጁ ላይ አድርጎ ተጋደመበት የሕፃኑም ገላሞቀ። ተመልሶም በቤቱ ውስጥ አንድ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተመላለሰ ደግሞም ወጥቶ ሰባት ጊዜ በሕፃኑ ላይ ተጋደመ ሕፃኑም ዓይኖቹን ከፈተ።"

2ኛ ነገ 19:34 "ስለ ባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ አድናት ዘንድ እጋርዳታለሁ።"

2ኛነገ 20:6 "በዕድሜህም ላይ አሥራ አምስት ዓመት እጨምራለሁ አንተንና ይህችን ከተማ ከአሦር ንጉሥ እጅ እታደጋለሁ ስለእኔም ስለባሪያዬም ስለ ዳዊት ይህችን ከተማ እጋርዳታለሁ።

ኢዮ 42:7-11 "እግዚአብሔርም ይህን ቃል ለኢዮብ ከተናገረ በኋላ እግዚአብሔር ቴማናዊውን ኤልፋዝን፦ እንደባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅንን ነገር ስለእኔ አልተናገራችሁምና ቍጣዬ በአንተና በሁለቱ ባልንጀሮችህ ላይ ነድዶአል። አሁን እንግዲህ ሰባት ወይፈኖችና ሰባት አውራ በጎች ይዛችሁ ወደባሪያዬ ወደ ኢዮብ ዘንድሂዱ፥ የሚቃጠልንም መሥዋዕት ስለራሳችሁ አሳርጉ ባሪያዬም ኢዮብ ስለእናንተ ይጸልያል፥ እኔም እንደ ስንፍናችሁ እንዳላደርግባችሁ ፊቱን እቀበላለሁ እንደባሪያዬ እንደ ኢዮብ ቅን ነገር ስለ እኔ አልተናገራችሁምና።

መዝ 88:3 "ከመረጥሁት ጋር ቃል ኪዳኔን አደረግሁ፥ ለባሪያዬም ለዳዊት ማልሁ። ዘርህን ለዘላለም አዘጋጃለሁ፥ ዙፋንህንም ለልጅ ልጅ እመሠርታለሁ።

መዝ 106:23 እንዳያጠፋቸው ቍጣውን ይመልስ ዘንድ የተመረጠው ሙሴ በመቅሠፍት ጊዜ በፊቱ ባይቆም ኖሮ፥ ያጠፋቸው ዘንድ ተናገረ።

ማቴ 10:40-42 እናንተን የሚቀበል እኔን ይቀበላል፥ እኔንም የሚቀበል የላከኝን ይቀበላል። ነቢይን በነቢይ ስም የሚቀበል የነቢይን ዋጋ ይወስዳል፥ ጻድቅንም በጻድቅ ስም የሚቀበል የጻድቁን ዋጋ ይወስዳል።

ዮሃ 20:23 "ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው።"

ሐዋ 7:60 እስጢፋኖስም። ጌታ ኢየሱስ ሆይ፥ ነፍሴን ተቀበል ብሎ ሲጠራ ይወግሩት ነበር። ተንበርክኮም። ጌታ ሆይ፥ ይህን ኃጢአት አትቍጠርባቸው ብሎ በታላቅ ድምፅ ጮኸ።

ሐዋ 9:36-40 "በኢዮጴም ጣቢታ የሚሏት አንዲት ደቀ መዝሙር ነበረች፥ በዚያም ወራት ታመመችና ሞተች፤ አጥበውም በሰገነት አኖሯት።ልዳም ለኢዮጴ ቅርብ ናትና ደቀመዛሙርት ጴጥሮስ በዚያ እንዳለ ሰምተው፥ ወደ እነርሱ ከመምጣት እንዳይዘገይ እየለመኑ ሁለት ሰዎች ወደ እርሱ ላኩ። ጴጥሮስም ተነሥቶ ከእነርሱ ጋር መጣ፤ በደረሰም ጊዜ በሰገነት አወጡት መበለቶችም ሁሉ እያለቀሱ ዶርቃ ከእነርሱ ጋር ሳለች ያደረገቻቸውን ቀሚሶችንና ልብሶችን ሁሉ እያሳዩት በፊቱ ቆሙ። ጴጥሮስም ሁሉን ወደ ውጭ አስወጥቶ ተንበርክኮም ጸለየ ፥ወደ ሬሳውም ዘወር ብሎ። ጣቢታ ሆይ፥ ተነሺ አላት። እርስዋም ዓይኖችዋን ከፈተች ጴጥሮስንም ባየች ጊዜ ተቀመጠች።

1ኛቆሮ 6:1 "ከእናንተ አንዱ ከባልንጀራው ጋር ሙግት ቢኖረው በቅዱሳን ፊት በመፋረድ ፋንታ በዓመፀኞች ፊት ሊፋረድ ይደፍራልን? ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን? በዓለምስ ላይ ብትፈርዱ ከሁሉ ይልቅ ትንሽ ስለሚሆን ነገር ልትፈርዱ አትበቁምን? የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?

2ኛቆሮ 5:20 እግዚአብሔር በክርስቶስ ሆኖ ዓለሙን ከራሱ ጋር ያስታርቅ ነበርና፥ በደላቸውን አይቆጥርባቸውም ነበር፤ በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልክተኞችነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን።

ያዕ 5:14 "ከእናንተ የታመመ ማንም ቢኖር የቤተክርስቲያንን ሽምግሌዎች ወደ እርሱ ይጥራ፤ በጌታም ስም እርሱን ዘይት ቀብተው ይጸልዩለት።"

አማላጅነታቸው በአጸደ ሥጋ

 

አማላጅነታቸው በአጸደ ነፍስ


የቅዱሳን ታላቅ ዕውቀትና ምልጃ በአጸደ ነፍስ
ቅዱሳን በአካለ ሥጋ ሆነው ማንም ሳይነግራቸው እጅግ ምሥጢራዊ የሆኑ ነገሮችን ካወቁ የዚህን ዓለም ውጣ ውረድና ፈተና አልፈው በአካለ ነፍስ ሲሆኑማ ምን ያህል የጠለቀ እውቀት ይኖራቸው? ቅዱስ ጳውሎስ ዛሬስ በመስታወት በድንግዝግዝ እንደምናይ ነን በዚያን ጊዜ ግን ፊት ለፊት እናያለን "ዛሬስ በዐውቀት ከፍዬ አውቃለሁ በዚያን ጊዜ ግን እኔ ደግሞ እንደታወቅሁ አውቃለሁን" በማለት የቅዱሳን ዕውቀት በአጸደ ነፍስ ታላቅ እንደሆነ ተናግሯል 1ቆሮ. 13፡12፣ 1ሳሙ. 28፡8-21፣ሉቃ. 9፡30-32፡፡
ቅዱሳን በአካለ ነፍስ ሆነው በምድር የሚሰራውን ነገር ማወቅ እስከቻሉ ድረስ የኛን ልመና ሰምተው መግለጽ አይሳናቸውም፡፡
በአካለ ነፍስ ያሉ ቅዱሳን "ቅዱስና እውነተኛ ጌታ ሆይ እስከ መቼ ድረስ አትፈርድምን ደማችንንስ በምድር በሚኖሩት ላይ እስከመቼ አትቀበልምን?" በማለት በአካለ ነፍስ እንደሚከሱ ራዕይ. 6፡9-11፡፡ በአጸደ ነፍስ ስለሚያውቁ ለቀረቡት ጥያቄዎች በዚመልስነው፡፡ቅዱሳን በአካለ ነፍስ ተበቀልልን ብለው ከለመኑ ለበጎ ነገር አማልዱን ስንላቸውማ ምን ያህል አብዝተው ይለምኑልን?
እንኳን ቅዱሳን /ጻድቃን/ ይቅርና በበደልና በኃጢአት ይኖር የነበረው ባለጸጋ /ነዌ/ በአካለ ነፍስ ሆኖ የወንድሞቹን በንስሐ አለመመለስ አውቆ አልአዛርን ስደድላቸውና ያስትምራቸው ሲል አብርሃምን ለምኖላቸዋል ሉቃ. 16፡20-31፡፡
ጌታ ሐዋርያትን "አንትሙ ውእቱ ብርሃኑ ለዓለም" ያላቸው ብርሃንነታቸው በዚህ በኃላፊው ዓለም ብቻ ተወስኖ እንዲቀር አይደለም፣ አማላጅነታቸውም በሕይወተ ሥጋ ሳሉ ነው እንጂ ከሞቱስ በኋላ ማማለድ የለባቸውም እንዳይባልማ የሰው ልጅ በግርማ መንግሥት በክበብ ትስብዕት መጥቶ በጌትነቱ በተገኘ ጊዜ እናንተም በ12 መንበሮች ተቀምጣችሁ በ12ቱ ነገደ እስራኤል ላይ ትፈርዳላችሁ ብሎአቸዋል ማቴ. 19፡28 ማማለድና መፍረድስ የቱ ይቀላል?
ጠቢቡ ሰለሞንም ቅዱሳን ጻድቃን ከሞቱ በኋላ በኃጥአኑ ላይ እንደሚፈርድባቸው ለደጋጉ እንዲፈርድላቸው ሲያስረዳ "ወብእሲሰ ጻድቅ መዊቶ ይኴንን ረሲዓነ እንዘ ሀለሙ ሕያዋኒሆሙ" ጻድቅ ሰው ግን ከሞተ በኋላ በሕየወት ሳሉ እግዚአብሔርን የዘነጉ ሰዎችን ይገዛል /ይቀጣል/ ይላል፡፡ ጥበብ. 2፡20፣አማርኛው ግን 4፡16 ላይ ነው፡፡
በዚሁም መሠረት መሞት ማለት-


1ኛ የነፍስና የሥጋ መለያየት ሲሆን

2ኛ መሞት ማለት ደግሞ በአካለ ነፍስ ወደ መንፈሳዊ /ረቂቅ ዓለም መሄድ/ ወደ እግዚአብሔር መድረስ /መመለስ/ ማለት ነው፡፡በሞት ጊዜ ነፍስ ወደ እግዚአብሔር እንደምትሄድና ሟቹ ሰው በነፍሱ እግዚአብሔርን ማየት እንደሚችል መጽሐፍ ቅዱስ በሰፊው ያስረዳል፡፡
ጻድቁ ኢዮብ በነፍሱ ወደ እግዚአብሔር እንደሚሄድ ሲያስረዳ "ይህ ቁርበቴ ከጠፋ በኋላ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ፡፡ እኔ ራሴ አየዋለሁ፡፡ አይኖቼም ይመለከቱታል" ሲል ተናግሯል ኢዮብ. 19፡26፡፡
እንዲሁም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ መሞት ማለት በነፍስ ወደ ጌታ መሄድና ከጌታ ጋር በክብር መኖር ማለት መሆኑን ሲገልጽ "ለእኔ ሕይወት በክርስቶስ አምኖ መሞት ጥቅም ነውና ነገር ግን በሥጋ መኖር ለኔ ለሥራ ፍሬ ቢሆንም ምን እንደምመርጥ አላውቅም በእነዚህም በሁለቱ እጨነቃለሁ፡፡ ልሄድ ከክርስቶስም ጋር ልኖር እናፍቃለሁ፡፡ ከሁሉ ይልቅ እጅግ የሚሻል ይህ ነውና" በማለት አስረድቷል ፊልጵ. 1፡24-24፡፡
ነገር ግን በቅዱሳን ክብር የማያምኑ መናፍቃን ከዚህ በላይ የቀረበውን ማስረጃ ላለመቀበል ብዙ ማደናገሪያ ለመደርደር ይሞክራሉ፡፡ ይህም የሚያሳየው "አውቆ የተደበቀን ቢጠሩት አይሰማም" እንደሚባው እነሱ አውቀውና ወደው የቅዱሳንን አማላጅነት ስለካዱ ምንም ዓይነት ማስረጃ አይመልሳቸውም ይሁን እንጂ መጽሐፍ ቅዱስ ግን "መኑ ውእቱ ዘይትዋቀሶሙ ለሕሩያነ እግዚአብሔር" የእግዚአብሔር ምርጦች ቅዱሳንን አልበቃችሁምና አታማልዱም በማለት የሚከራከራቸው የሚወቅሳቸው ማን ነው? እርሱ ያከበራቸውንስ የሚያዋርድ ማንነው? በማለት አስተምሯል ሮሜ. 8፡30-31፡፡
ቅዱሳንም በሃይማኖትና በምግባር የጸኑ ስለሆነ የሚሳናቸው ነገር የለም፡፡ ተራራ ማፍለስ፣ ሙት ማስነሳት፣ ሕሙማንን መፈወስ እንደቻሉ ካወቅን፣ ማማለድ እንደማይሳናቸውም እናምናለን፡፡
እንግዲህ ክብረ ቅዱሳን እንዲሁ በአጭር ጊዜ ተነግሮ በአጭር ጽሑፍ ተጽፎ የሚያልቅ አይደለም፡፡ በአጭሩ ያልቃል ብሎ መገመት ወይም ማሰብ፣ አባይን በጭልፋ እንደሚባለው ይሆናል፡፡ ምክንያቱም የቅዱሳን ምልጃ በብሉይ ኪዳንና በሐዲስ ኪዳን፣ የቅዱሳን ምልጃ በአጸደ ሥጋና በአጸደ ነፍስ የቅዱሳን ረቂቅ እውቀት በሚል ርዕስ በአጭሩ ለመግለጽ ሞከርኩ እንጂ የእግዚአብሔርን ሕግጋት /ትእዛዝ/ የፈጸሙና በጾምና በጸሎት ተወስነው የኖሩ በነፍስና በሥጋ ከፈጣሪያቸው ክብር የተሰጣቸው ብዙ ናቸው፡፡
>ሄኖክ 9:22 "ከዚያም ቦታ ዓይኖቼን ከመላእክት ጋር የሚኖሩበት ማደሪያቸው ከቅዱሳንም ጋር በሚኖሩበት ቦታቸውን አየሁ። ስለ ሰው ልጆች ፈጽመው ይለምናሉ፥ ይጸልያሉ"

ሄኖክ 12:34 "በሰማይ የሚኖሩ ጻድቃን ባንድ ቃል ሆነው ተባብረው ያመሰግናሉ፥ ለሰውም ፈጽመው ይለምናሉ"

1ኛነገ 13:31  ከቀበረውም በኋላ ልጆቹን እንዲህ ብሎ ተናገራቸው። በሞትሁ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው በተቀበረበት መቃብር ቅበሩኝ አጥንቶቼንም በአጥንቶቹ አጠገብ አኑሩ በቤቴል ባለው መሠዊያ ላይ፥ በሰማርያም ከተሞች ውስጥ ባሉ በኮረብታዎቹ መስገጃዎች ላይ በእግዚአብሔር ቃል የጮኸው ነገር በእውነት ይደርሳልና።

2ኛነገ 13:20 "ኤልሳዕም ሞተ፥ ቀበሩትም። ከሞዓብም አደጋ ጣዮች በየዓመቱ ወደ አገሩ ይገቡ ነበር። ሰዎችም አንድ ሰው ሲቀብሩ አደጋጣዮችን አዩ፥ ሬሳውንም በኤልሳዕ መቃብር ጣሉት የኤልሳዕንም አጥንት በነካ ጊዜ ሰውዮው ድኖ በእግሩ ቆመ።"

ማቴ 22:32 እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ የሚል ከእግዚአብሔር ዘንድ ወደ እናንተ የተባለውን አላነበባችሁምን? የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም።

ሉቃስ16፥22 "ድሀውም ሞተ፥ መላእክትም ወደአብርሃም እቅፍ ወሰዱት፤ ባለጠጋው ደግሞ ሞተና ተቀበረ። በሲኦልም በሥቃይ ሳለ አሻቅቦ አብርሃምን በሩቅ አየ አልዓዛርንም በእቅፉ። እርሱም እየጮኸ። አብርሃም አባት ሆይ፥ ማረኝ፥ በዚህ ነበልባል እሣቀያለሁና የጣቱን ጫፍ በውኃ ነክሮ መላሴን እንዲያበርድልኝ አልዓዛርን ስደድልኝ አለ።"

2ኛየጴጥ 1:15 ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና። ከመውጣቴም በኋላ እነዚህን ነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ።

አማላጅነታቸው በአጸደ ነፍስ


ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል


ተቃዋሚዎች ቅዱሳን በአጸደ ነፍስ አያማልዱም ብለው እንደማስረጃ አድርገው ከሚያቀርቧቸው መካከል አንዱ " ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል" የሚለውን የመጽሃፍ ቅዱስ ክፍል ነው። መጽሃፍ ቅዱስን መሰረት በማድረግ ጠቢቡ ሰሎሞን ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል ሲል ምን ማለቱ እንደሆነ እንመለከታለን።
በቅዱስ መጽሃፍ ውሻም ሆኑ አንበሳ ለሃጥዓንም ለጻድቃንም እንደየሁኔታው ምሳሌ ተደረገው ቀርበዋል፡፡ ውሻ ለሃጥአን ምሳሌ ሲሆን፤ -
ኢሳ56-11 ‹‹መብል ወዳጆች ከቶ የማይጠግቡ ውሾች ናቸው››

ማቴ7-6 ‹‹የተቀደሰውን ለውሾች አትስጡ››

ፌልጵ 3-2 ‹‹ከውሾች ተጠበቁ››

2ጵጥ 2-22 ‹‹አውቀዋት ከተሰጣቸው ከቅድስት ትእዛዝ ከሚመለሱ የጽድቅን መንገድ ባላወቋት በተሻላቸው ነበርና።- ውሻ ወደ ትፋቱ ይመለሳል፥ ደግሞ። የታጠበች እርያ በጭቃ ለመንከባለል ትመለሳለች እንደሚባል እውነተኞች ምሳሌዎች ሆኖባቸዋል።››

ራዕ22-14 ‹‹ወደ ሕይወት ዛፍ ለመድረስ ሥልጣን እንዲኖራቸው በደጆችዋም ወደ ከተማይቱም እንዲገቡ ልብሳቸውን የሚያጥቡ ብፁዓን ናቸው። ውሻዎችና አስማተኞች ሴሰኛዎችም ነፍሰገ ዳዮችም ጣዖትንም የሚያመልኩት ውሸትንም የሚወዱና የሚያደርጉ ሁሉ በውጭ አሉ።››

ሌላው ለንጽጽር የቀረበው አንበሳ ነው፤ አንበሳም እንዲሁ በመጽሀፍ ለሃጥአንም ለጻድቃንም ተመስሎ እናገኝዋለን፡፡ አንበሳ ለዲያቢሎስ ምሳሌ ሲሆን፤
2ኛ ጵጥ 5-8 ‹‹በመጠን ኑሩ ንቁም፥ ባላጋራችሁ ዲያብሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሣ አንበሳ ይዞራልና››

አንበሳ ለጻድቃን ምሳሌ ሲሆን ደግሞ፤
ምሳ 28-1 ‹‹ኀጥእ ማንም ሳያሳድደው ይሸሻል፤ ጻድቅ ግን እንደ አንበሳ ያለፍርሃት ይኖራል።››

ጠቢቡ ሰለሞን ‹‹ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል ›› ብሎ የተናገረላቸው በውሻም ሆነ በአንበሳ የተመሰሉት ሁለቱም ሓጥአን ናቸው፡፡ ይህንን ለመረዳት ቀጥሎ ያለውን ሀይለ ቃል መረዳት ያሻል
መክብብ 9-4 ‹‹ ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው።፤ ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቷልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም።፤ ፍቅራቸውና ጥላቻቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቶአል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።››
ይህንን ቃል ለመረዳት የሙታንን እና የህያዋንን ምንነት ማንሳት ያሰፈልጋል፡፡ ሙታን የተባሉ እነማን ናቸው ‹‹ሙታን ›› የሚለው ቃል ነፍሳቸው ከስጋቸው ለተለየ እና ለሞተ ነፍስ (በሀጢያት ወድቀው ሕይወታቸው ከእግዚአብሄር ለተለዩት ) ይነገራል፡፡ ብዙውን ግዜ ቅዱሳን አረፉ ወይም አንቀላፉ ሲባል ሀጥአን ግን ሞቱ ይባላል (ማቴ 2-19፣ ሐዋ 5-5፤ 1 ነገ 2-10 ማቴ 27-52) ቅዱስ መጽሀፍ ሙታን የሚላቸው ቅዱሳንን ሳይሆን በዚህ አለም እያሉ ሀይማኖት እና ምግባር የሌላቸው እና ከእግዚአብሔር አንድነት የተለዩትን ነው፡፡ ጌታችን ከደቀመዛሙርቱ አንዱ
ማቴ 8-22  ‹‹ከደቀ መዛሙርቱም ሌላው። ጌታ ሆይ ፥አስቀድሜ እንድሄድ አባቴን እንድቀብር ፍቀድልኝ አለው። ኢየሱስም። ተከተለኝ፥ ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው አለው።››
ነፍሱ ከስጋው ተለይቶ ሊቀበር ያለው የደቀመዝሙሩ አባት ሲሆን ጌታችን ግን ከእርሱ የተለዩትን እና ወደ እርሱ ያለመጡትን ሁሉ ‹‹ሙታን›› ብሎቸዋል፡፡ ምክኒያቱም ከህይወት ባለቤት ከእየሱስ ክርስቶስ ጋር አንድነት የላቸውምእና፡፡ ‹‹ሙታን ሙታናቸውን ይቅበሩ›› ሲልም አንዱ አስከሬን ሌላውን የሚቀብር ሁኖ ሳይሆን ከእርሱ የተለዩ ሰወች ምንም እንኮን በሰው ዘንድ ሕያዋን (ሕይወትያላቸው ) ቢመስሉም በእርሱ ዘንድ ግን ሙታን መሆናቸውን ሲያስረዳ ነው፡፡ ሀዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፤  
1 ጢሞ 5-6  ‹‹ቅምጥሊቱ ግን በህይወት ሳለች የሞተች ናት›› ሲል ጽድቅን ረስታ በተድላ ስጋና በሃጢአት የምትኖር እረሱ በዚህ አለም እያለች ቢሆን ሙት መሆኗን የሚያሰረዳ ነው ስለዚህ መጽሃፍ ሙታን እያለ የሚረታቸው፤ ከእውነተኛዋ እምነት ውጭ ሆነው ወይም በዚህ አለም በሃጥያት ወድቀው ከህይወት ባለቤት ከእግዝአብሔር ተለይተው ይሉትን እንጅ በእረሱ አምነው ከሞት ወደ ሂወት፤ ከባርነት ወደ ልጅነት የተሸጋገሩትን አይደለም፡፡

ከዚይም ቀጥሎ ‹‹ፍቅራቸው፤ ጥላቸው፤ ቅንአታቸውም …›› ማለቱ ይህ ለሀጥአን የተነገረ መሆኑን የሚያስረግጥ ነው ምክንያቱም ጥላቻና ቅንአት ለጻድቃን ሳይሆን የሀጥአን ገንዘባቸው ናቸው:: በዚህ መሰረት አንዳች አይውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶ ከዚህ በኌላ ዋጋ የላቸውም የተባሉት ሃጥአን ናቸው፡፡ ሰለሆነም በውሻም ሆነ በአንበሳ የተመሰሉት ሁለቱም ሀጥአን መሆናቸውን ልብ ማለት ይገባል፡፡ ስለዚህ ‹‹ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላል ›› ማለት ‹‹ከሞተ ሓጥዕ ያልሞተ ሐጥዕ ይሻላል›› ማለት ነው፡፡
ምክኒያቱም ያልሞተ ሀጥእ ንስሀ የመግባት እድል ሲኖረው የሞተ ሀጥእ ግን ንስሀ ሳይገባ ስለሞተ የመዳን ተስፋ የለውም እናነው፡: ጌታችን እንደተናገረው ክርስቶስ የህያዋን አምላክ እንጂ የሙታን አይደለም፡፡ ስለዚህ ሁሉም ቅዱሳን ህያዋን ናቸው፡፡
ማቴዎስ 22፡32 "እኔ የአብርሃም አምላክ፥ የይስሐቅም አምላክ የያዕቆብም አምላክ ነኝ... የሕያዋን አምላክ ነው እንጂ የሙታን አይደለም"
መክብብ 9:4_6 ያልሞተ ውሻ ከሞተ አንበሳ ይሻላልና ሰው ከሕያዋን ሁሉ ጋር በአንድነት ቢኖር ተስፋ አለው። ሕያዋን እንዲሞቱ ያውቃሉና፤ ሙታን ግን አንዳች አያውቁም፤ መታሰቢያቸውም ተረስቶአልና ከዚያ በኋላ ዋጋ የላቸውም። ፍቅራቸውና ጥላቸው ቅንዓታቸውም በአንድነት ጠፍቷል፥ ከፀሐይ በታችም በሚሠራው ነገር ለዘላለም እድል ፈንታ ከእንግዲህ ወዲህ የላቸውም።
ፕሮቴስታንት ወንድሞቻችን ይህንን ጥቅስ በመጥቀስ ፃድቃን ከሞቱ በኋላ የማያማልዱና መታሰቢያቸው የተረሳ መሆኑን ይናገራሉ ነገር ግን ቅዱሳን መታሰቢያቸው ለዘላለም ነው።
መዝ.111-6 ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል።››
ይላል ይረሳል አላለም ጌታ እግዚአብሔር ለዘላለም የመታሰቢያ ስማቸው እንደማይጠፋ ተናግሯል
ኢሳ.56:4-54 ‹‹እግዚአብሔር ሰንበቴን ስለሚጠብቁ ደስ የሚያሰኘኝንም ነገር ስለሚመርጡ ቃል ኪዳኔንም ስለሚይዙ ጃንደረቦች እንዲህ ይላልና። በቤቴና በቅጥሬ ውስጥ ከወንዶችና ከሴቶች ልጆች ይልቅ የሚበልጥ መታሰቢያና ስም እሰጣቸዋለሁ፤ የማይጠፋም የዘላለም ስም እሰጣቸዋለሁ።››

እግዚአብሔር በቤቱ በቅድስት ቤተ ክርስቲያን በእኛ በእያንዳንዳችን የማይጠፋ ስም ሰጥቷቸዋል  ዳዊትም የጻድቅ መታሰቢያ ለዘላለም ይኖራል ያለው ለዚህ ነው:: መታሰቢያነቱ ለዘላለም ስለሆነ ጊዜያዊ ስላልሆነ የማይጠፋ ስም አላቸው ሀጥአን ግን የላቸውም ክፍዎች ግን የላቸውም ቅዱሳን ስማቸው ብቻ ሳይሆን በፅዋ እነሱን ያሰበ ዋጋው አይጠፋበትም:
ማቴ 10:42 ‹‹ማንም ከእነዚህ ከታናናሾቹ ለአንዱ ቀዝቃዛ ጽዋ ውኃ ብቻ በደቀመዝሙር ስም የሚያጠጣ፥ እውነት እላችኋለሁ፥  ዋጋው አይጠፋበትም።››
ምሳ 10-7 ‹‹የጻድቅ መታሰቢያ ለበረከት ነው፤ የኅጥኣን ስም ግን ይጠፋል።››
ይላል መታሰቢያቸውን ማድረግ በረከት እንዳለው መፅሃፍቅዱስ ያስረዳናል ስለዚህ መታሰቢያቸው የተረሳው የሀጢአን እንጂ የቅዱሳን አይደለም ይህ ለቅዱሳን የተነገረ ቢሆን ኖሮ ዳዊት መታሰቢያቸው ለዘለአለም ይኖራል ባላለን ኢሳያስም የዘላለም መታሰቢያ ስም እሰጣቸዋለሁ ብሎ እግዚአብሔር መናገሩን ባልፃፈልን ነበር:: ከሞተ ዘመናት ያለፉት ሙሴ ከኤልያስ ጋር በደብረ ታቦር በተገለጸ ጊዜ ኤልያስና ሙሴ ከጌታ ጋር ይነጋገሩ ነበር። ስለኢየሩሳሌምም ትንቢት ተናገሩ እንዲል
ሉቃ 9:30 ‹‹ሙሴ መናገር መቻሉና ትንቢት መተንበዩ ሕያው መሆኑን ያስረዳናል›› ከላይ የተመለከትነው መታሰቢያ ስም እንዳላቸው እነጂ የቅዱሳን መታሰቢያ የሚረሳ አለመሆኑን ነው ሀጢአን ግን መታሰቢያ የላቸውም ተረስተዋል:: እንዲሁም ቅዱሳን ከሞቱም በኋላ እንኳን ከፈጣሪያችን ጋር ያማልዱናል:: ሰማዕታት በታላቅ ድምጽ እየጮሁ
ራዕ 6:9 ‹‹ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስ ነው?›› አሉ
“በታላቅ ድምጽ መጮህ መቻላቸው” ሕያዋን መሆናቸውን ያስረዳናል። ደማችንን በከንቱ ያፈሰሱትን የማትበቀለው እስከመቼ ድረስነው? ማለታቸው ደማቸውን በከንቱ ያፈሰሱት ገና እንዳልተቀጡ ስለሚያውቁ ነው። ጌታም ሌሎች ሰማዕታት ስላሉ እንዲታገሱ ነግሯቸው የንጽህና ምልክት የሆነውን ነጭ ልብስ ሰጣቸው። “ሰማዕታት ደማቸውን በከንቱ ስላፈሰሱት ፍርድን ሲጠይቁ ስለ እኛ ደግሞ ይለምናሉ” በሞት ጊዜ ነፍስ ወደእግዚአብሔር እንደምትሄድ በነፍሱ እግዚአብሔርን ማየት እንደሚችል መጸሀፍ ቅዱስ ይነግረናል:
ኢዩብ 19:26-27 ይህ ቁርበቴም ከጠፋ በኋላ፥ በዚያን ጊዜ ከሥጋዬ ተለይቼ እግዚአብሔርን እንዳይ አውቃለሁ። እኔ ራሴ አየዋለሁ፥ ዓይኖቼም ይመለከቱታል፥ ከእኔም ሌላ አይደለም። ልቤ በመናፈቅ ዝሎአል። በአጸደ ነፍስ ያሉትን ቅዱሳን በድል አድራጊነት ያሉ በመሆናቸዉም ልጃቸዉን አጥብቀን እንለምናለን። እንዲህ በምናደርግበት ጊዜ በሰማይም ሆነ በምድር ያሉ አማኞች በአንድ አካል ላይ ያሉ ብልቶች መሆናቸዉን መናገራችንና ማመናችን ነው:: ከድልነሺ ቅዱሳን ጋር ያለን ግንኙነት ሥራህ ያውጣህ በሚል መርህ የተተበተበ አይደለም። ይህ ማለት ጭንቀታችንን ምኞታችንን ይረዳሉ ይጋራሉ ማለት ነው። ለዚህ ነው "አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል።" 1ቆሮ 12-26 ተብሎ ስለ አማኞች አንድነት የተነገረው። ይህ ስለሆነ ነው ቅዱስ ጴጥሮስ ወደ አጸደ ነፍስ ከወጣ በኃላ በአጸደ ሥጋ ላሉ ልጆቹ እንደሚተጋላቸዉ የነገራቸዉ:: ምክንንያቱም በየትም ቦታ ቢኖሩም አንድ አካል ላይ ያሉ ብልቶች ስለሆኑ ነው።

"ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንዳመለከተኝ ከዚህ ማደሪያዬ መለየቴ ፈጥኖ እንዲሆን አውቃለሁና። ከመውጣቴም በኋላ(ወደ ኣጸደ ነፍስ) እነዚህ ንነገሮች እንድታስቡ በየጊዜው ትችሉ ዘንድ እተጋለሁ(በጸሎት)።" 2ጴጥ 1-14
 

ከሞተ አንበሳ ያልሞተ ውሻ ይሻላል
bottom of page