top of page

ዜና አበው

 

ዜና አበው ማለት በግብጽ፣ በሶሪያና በዮርዳኖስ የቅዱሳን አበው አባባሎችን:ምስክሮችን የሕይወት ተሞክሮዎችንና ልዩ ልዩ ገድሎችን የያዘ ስብስብ ነው:: በአራተኛውና በአምስተኛው መቶ አመት ግብጽ፣ ሶርያና የዮርዳኖስ በረሃ በእነቅዱስ እንጦንዮስ፣ መቃርዮስ ፣ጳኩሚስና አሞን የተጀመረውን የብሕትውናና ገዳማዊ ሕይወት በተከተሉ ገዳማውያን ተሞልተው ነበር:: በገዳማትና በገዳማውያን : በባሕታውያንና በመነኮሳት ብዛት ግን ግብጽን የሚይስተካከል አልነበረም:: በአራተኛው መቶ ዓመት ግብጽ "የባህታውያን ሀገር" ተብላ እስከመጠራት ደርሳ ነበር:: አንዳንዶቹ የግብጽ ገዳማት እስከ ሠላሳ ሽህ የሚደርሱ ወንዶችና ሴቶች መነኮሳትስ ለነበሩባቸው "የመላእክት ከተሞች" እስከመባልም ደርሰው ነበር::

አንዳንድ ቅዱሳን አበው የጻፏአቸው መልእክታት በዘመናቸው ተጽፈው የነበረ ቢሆንም የአብዛኛዎቹ አበው አባባል ምስክርና ትሩፋታቸው በነበሩበት ዘመን ተጽፎ አይቀመጥም ነበር:: ስለሆነም ጳላድዮስና ይሩማሊስ የሚባሉ ቅዱሳን መነኮሳት በግብጽ ገዳማትና በረሃዎች እየዞሩ ያሉትን ከቃላቸው የሞቱትን ደግሞ ከደቀመዝሙሮቻቸው ብሂላቸውንና ምክራቸውን እንዲሁም የተለየ ሁኔታቸውን ጽፈዋል:: የአንዳንዶቹ አበው ብሂል /አባባል/ በቃል ከአንዱ መነኩሴ ወደ ሌላ ሲተላለፍ ይቆይና በኋላ ይጻፉ ነበር:: ይህ የአበው ዜና ሕይወት ከተጻፈ በኃላም በሁለት አይነት መልኩ ተዘጋጀ:: ይኸውም አንዱ በታወቁ በታላላቅ ቅዱሳን ስም ቅደም ተከተል መሠረት ሲሆን ሌላው ደግሞ አባባሎቹን መነኮሳቱ በሚፈልጉአቸው ርዕሰ ጉዳዮች ለምሳሌ እንደአርምሞ መታዘዝ ትህትና ራስን መግዛት እና በመሳሰሉት ዙሪያ የተሰባሰበና የተዘጋጀ ነው::

ዜና አበው በአምስተኛው መቶ ዓመት ገደማ በግብጽ ከተዘጋጀና ከተጻፈ በኃላ ወደ ፅርህ ቋንቋ ተተርጉሟል:: ከዚያም በእንግሊዘኛ ተተርጉሟል:: በእንግሊዘኛ የተተረጎመው በሁለት ክፍል ነው:: እነዚህ "The World of The Desert Fathers" እና 
"The Wisdom of the Desert Fathers" ናቸው::
እንዲሁም ወደ ፈረንሳይኛና ሌሎችም ቋንቋዎች ተተርጉሟል:: በእኛ ሀገር ግን ዜና አበው በግእዝ ተተርጉሞ በቤተክርስቲያን በትምህርት በጉባኤ ከሚሰጡት መጻሕፍት አንዱ ከሆነ ብዙ ዘመን ሆኖታል::
ዳሩማሊስና ጳላድዮስ ከግብጽ ተነስተው ሀገር ለሀገር እየዞሩ የአበውን ዜና ያሉትን ከቃላቸው የሞቱትን ከአርድእቶቻቸው እየጠየቁ ጽፈዋል:: መጽሐፉንም ሲጽፉት ቃለ አበው ዜና አበው ካልእ ዜና ሣልስ ዜና ራብዕ እያሉ ጽፈውታል:: እንዲሁም ሁሉንም አንድ አድርገው "መጽሐፈ ገነት" ብለውታል:: በገነት ብዙ ጣዕም ብዙ መዓዛ እንዲያገኝ በዚህም መጽሐፍ ደስ የሚያሰኝ ብዙ ምሥጢር ይገኝበታል::

Anchor 1

መጻሕፍተ መነኮሳት

 

መጻሕፍተ መነኮሳት የመነኮሳትን ሥራቸውን፣ ታሪካቸውን፣ ጸጋቸውንና ክብራቸውን የሚናገር መጽሐፍ ነው:: መጽሐፍተ መነኮሳት ተብለው የሚጠሩት ሦስት መጻሐፍት በአንድ ላይ ነው:: እነዚህም ማር ይስሐቅ ፣ ፊልክስዮስ እና አረጋዊ መንፈሳዊ ናቸው::

1.ማር ይስሐቅ
ማር ይስሐቅ የቅዱስ ኤፍሬም /ውዳሴ ማርያምን የደረሰው/ ደቀ መዝሙር የሆነና ብሉይና ሐዲስ ኪዳንን እንዲሁም ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ተምሯአል:: ከዚህ በኃላ ከአባ እብሎይ ገዳም ገብቶ ሃያ አምስት አመት በረዳትነት አገልግሏል:: አባ እብሎይ ሲያርፍ አናምርት አክይስት አቃርብት ካሉበት ነቅአ ማይ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት በረሃ ሄዶ ተባህትዎ ያዘ:: በብሕትውና እያለ እግዚአብሔር የገለጠለትን ከሶስቱ መጽሕፍተ መነኮሳት አንዱ የሆነውንና "ማርይስሐቅ" ተብሎ የሚጠራውን መጽሐፍ ጻፈ::

መጽሐፈ ማር ይስሐቅ የመነኮሳትን ፆር፣ትሩፋት ለመሥራት የሚያስፈልጉ ነገሮችና መንፈሳዊ ጥበብን፣ ሰይጣን ትሩፋት የሚሰሩ መነኮሳትን እንዴት እንደሚተናኮላቸውና እነርሱም እንዴት መዘጋጀትና መጠንቀቅ እንዳለባቸው፣ በአጠቃላይ ፈጣሪያቸውን ለማገልገል የገቡትን ቃል ኪዳን እንዴት አድርገው መጠበቅ እንዳለባቸው የሚገልጽ በድንቅ መንፈሳዊ ጥበብ የተዋበ መጽሐፍ ነው:: በውስጡም ልዩ ልዩ ንዑስ ክፍሎችን የያዘ ነው:: ለምሳሌም ስለ ትጋሃ ሌሊት ስለ ጾም ስለ ተጋድሎ ስለ ጸዋተ ወመከራ ስለ ጸሎት ስለ ትህትና ስለ አጽንኦ በዓት ስለ ትዕግስት እና ስለ ሌሎችም ብዙ ነገሮች የሚገልጽና ራሳቸውን ለመንፈሳዊ ሥራ ለማሰማራት ለሚፈልጉ ሁሉ ከእግዚአብሔር የተሰጠ መካሪ መጽሐፍ ነው::

2.ፊልክስዮስ
ፊልክስዮስ ከሦስቱ መጻህፍተ መነኮሳት አንዱ ሲሆን የሚገልጸውም ስለ ገዳማውያን ታሪክና ተጋድሎ ነው:: ፊልክስዮስ በዜና አበው ከተጻፈውና በቃል ሲነገር ከመጣው የአበው ብሂል ያልተተረጉመውን እየተረጎመ ያልተመሰለውን እየመሰለ ጽፏል:: አኃው ከቃለአበው የሚለያይና የሚቃረን የሚመስላቸውን እየጠየቁት እንዲሁም እርሱ መተርጎምና መታረቅ ያለበትን ከብሉይና ከሐዲስ እየጠቀሰ አስማምቶ ተርጉሟል:: ሲተረጎምም በመጀመሪያ ከብሉይና ከሐዲስ ማስረጃ እያወጣ ካስረዳ በኃላ ከዚያ ደግሞ ከቃለ አበው እየጠቀሰ ነው::

3.አረጋዊ መንፈሳዊ 
አረጋዊ መንፈሳዊ ዮሐንስ ከሚባል የአንድ ገዳም አበምኔት ከነበረ ወንድሙ ጋር ይኖር ነበር:: አረጋዊ ከገዳሙ ሲኖር በትሕትና ነበር:: ጽሕፈት ያውቃልና ጻፍ ሲሉት እኔስ ብእሩን ቀርጬ፣ ቀለሙን በጥብጬ  ብራናውን ዳምጬ አቀርባለሁ እናንተ ጻፉ ይላል:: ንባብ ያውቃልና አንብብ ሲሉት እኔስ አትሮኖስ አቀርባለሁ፤ መጽሀፍ አወጣለሁ፤ መብራት አበራለሁ እናንተ አንብቡ ይላል:: ቅዳሴ ያውቃልና ቀድስ ሲሉት እኔስ ጥላ አሰፍራለሁ ፤ቃጭል እመታለሁ፤ማዩን ቀድቼ፣ መሥዋዕቱን ሠርቼ አቀርባለሁ እናንተ ቀድሱ ይል ነበር::ከእለታት አንድ ቀን ቀዳሽ ጠፋና ቀድስ ብለውት ሊቀድስ ገባ:: ጸዋትውን ጨርሶ ከፍሬ ቅድሴው ሲደርስ መሥዋዕቱን እንደ ደብረ ሲና በአምሳለ እሳት፣ እንደ ደብረታቦር በአምሳለ ብርሃን፣ በአምሳለ በግዕ፣ በአምሳለ ሕጻን ተለውጦ አየው:: ከዚህ በኃላ ከራዕዩ ተመልሶ ቅዳሴውን ቀድሶ ወጥቶ ከሰው ሳልለይ እንዲህ ያለ ምሥጢር የተገለጠልኝ ከሰው ብለይማ እንደምን ያለ ምሥጢር በተገለጠልኝ ብሎ ከገዳሙ ወጥቶ አክይስት፣አቃርብት አናምርት ካሉበት፣ነቅዓ ማይ ልምላሜ ዕፅ ከሌለበት ዘር ተክል ከማይገኝበት ከጽኑ በረሃ ሂዶ ተቀመጠ::

ዮሐንስም ወንድሙ ጠፍቶበት እያዘነ ሲኖር በኃላ ያለበትን ቦታ በማወቁ ወደ ገዳም እንዲመጣ ላከበት:: አረጋዊ ግን ተባሕትዎን ትቶ ለመምጣት ፈቃደኛ ስላልሆነ ዮሐንስም የማትመጣ ከሆነ ባይሆን ከዚያው ካለህበት ሲደክምህ የምታርፍበት ጎጆ ላሰራልህ ቢለው 
"ምዕራፈ ኩሉ ጌታ ለእኔ ማደርያ አነሰኝን?እሱ ይበቃኛልና ይህንንስ አልፈልግም" አለው::
እንኪያስ ብቻህን ስትሆን የሚያነጋግርህ አንድ ሰው ልላክልህ ቢለው
"ለኑዛዝየስ የአክሉኒ ዕፅወ ዝንቱ ደብር- ለመነጋገርስ የዚህ የበርሃው ዕፅዋት ይበቁኛል" አለው::
ወንድሙ ዮሐንስም ይህ ቢቀር ስትታመም የሚያስታምምህ ስትሞትም የሚያሟሙትህ ሰው ልላክልህ ቢለው 
"ከእግዚአብሔር ዘንድ የምመኘው ይህንን ነው። ብታመም የሚያስታምመኝ፣ ብሞትም የሚያሟሙተኝ አጥቼ ባፌ፣ በግንባሬ ተደፍቼ ጉንዳን ፈልቶብኝ፣ ጭጫን ወርሶኝ እንድናገኝ ነውና ፈቃዴ ለዚህም አታስብ" አለው:: ያንም ያንም ቢለው ሁሉንም የማይቀበል ሆነ::

ከዚህ በኃላ ሁሉም በያሉበት ሆነው ሲላላኩ ኖረዋል:: ዮሐንስ ያየውን ራዕይና የሚጠይቀውን ጥያቄ ይልክለታል:: አረጋዊ ደግሞ የሚተረጉመውን እየተረጎመ ይልክለታል:: ይልቁንም ራዕይን አትመነው እውነትም አለ ሐሰትም አለ እያለ ይጽፍለት ነበር:: ሲጽፍለትም "ከምድረ በዳ አውሬ የተላከ መልእክት " እያለ ነበር::
ዮሐንስ ግን ለውጦ "አረጋዊ መንፈሳዊ እንጂ የምድረ በዳ አውሬ ሊሉህ አይገባም" ብሎታል::
ስለዚህ የመጽሐፉም ስም "አረጋዊ መንፈሳዊ" ተብሏል:: ዮሐንስም አርጋዊ የላከለትን ተመልክቶ ሲያበቃ እየሰበሰበ ያስቀምጠዋል:: ኃላም መልእክታቱን ሁሉ ከአንድ ላይ ሰብስቦ ሠላሳ አምስት ድርሳን አርባ ስድስት መልእክታት አድርጎታል::

አረጋዊ መንፈሳዊ በአጠቃላይ የሚናገረው ቅዱሳን ከዚህ ዓለም ተለይተው ትሩፋት ሠርተውና መከራ ተቀብለው የሚያገኙትን ጸጋና የሚቀምሱትን ጣዕመ መንፈስ ቅዱስ ነው:: አረጋዊ መንፈሳዊ በቤተ መንግስት ያደገ ሰው ይመስላል:: በቤተመንግስት ያደገ ሰው የተመከረውን ምክርና የሰማውን ምሥጢር ሰምቶ ይወጣና ለሚመስሉት ለወዳጆቹና ለባልንጀሮቹ ያጫውታል:: አረጋዊ መንፈሳዊም እርሱ ከብቃት ደረጃ ደርሶ ያየውንና የሰማውን ረቂቅ ምሥጢር በዚህ ዓለም ላሉት ለደጋጎቹ ያስረዳልና:: በመጠኑም ቢሆን የጸጋ እግዚአብሔርን ሁኔታ ላላወቀና ጣዕመ መንፈስ ቅዱስን ላልቀመሰ ሰው አረጋዊ መንፈሳዊን ለመረዳት ያስቸግራል::

Anchor 2
Anchor 3

ገድላት

ገድል፡- “በቁሙ ትግል ፈተና ውጊያ ሰልፍ ድልና አክሊል እስኪገኝ ድረስ  የሚደክሙት ድካምየ ሚሠሩት ሥራ የሚቀበሉት መከራ ማለት ነው” 
ልበ አምላክ ዳዊት "አቤቱ ወዳጆችህ ከፊት ይልቅ በዙ ፤ ብቆጥራቸውም ከአሸዋ ይልቅ ይበዛሉ" መዝ 138:17 እንዳለ የእግዚአብሔር ወዳጆች ቅዱሳን ብዙዎች ናቸው:: የእነዚህም ተጋድሎና ጸጋ የአንዱ ካንዱ የተለየ ነው:: 

ቅዱስ ዮሐንስ ሐጺር እንዲህ አለ:- "ቅዱሳን በአንድ የተክል ቦታ እንዳሉና ከአንድ ምንጭ እንደሚጠጡ ነገር ግን የተለያየ አበባና ፍሬ እንዳላቸው አትክልት ናቸው:: የአንዱ ቅዱስ ሥራ ተጋድሎ ሕይወትና አኗኗር ከሌላው ይለያል : ነገር ግን በሁሉም የሚሠራው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው::"

የገድል መጻሕፍት ጻድቃን፣ሰማዕታት ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ትእዛዘ እግዚአብሔር እንዲከበር ሥርዐተ ቤተክርስቲያን እንዲጠበቅ ከአላውያን ነገሥታት፣ከቢጸሐሳውያን፣ከጠላት ዲያብሎስና ከፈቃደ ሥጋ ጋር ያደረጉትን ተጋድሎ የሚያወሱ መጻሕፍት ናቸው፡፡ሃይማኖታቸው በኑሮአቸው እንዴት እንደተገለጠ የሚያሳዩን የሕይወታቸው መስተዋቶች ናቸው፡፡ስለዚህ ገድል ስንል የቅዱሳን ታሪክ፣ተአምራት፣ቃልኪዳንና መልእክት የያዘ መጽሐፍ ነው፡፡ይህ እንዲህ ይሆናል ይቻላል ተብሎ የተነገረው ቃል በእውነት የሚኖር በቃልና በሥራም የሚገለጥ እንደሆነ የምናየው በቅዱሳን ገድል ነው፡፡ ማቴ.10፥37፣ሉቃ.14፥27፣ 1ቆሮ.11፥26-28
ገድል መጽሐፍ ቅዱሳዊ መሠረት አለው።2ቆሮ.11፥23-22  ዕብ.11፥32-40 ራሱ የሐዋርያት ሥራ የምንለው የመጽሐፍ ቅዱስ ክፍል የሐዋርያትን ግብር /ሥራ/ ገድልና ዜና የሚያስረዳ መጽሐፍ ነው፡፡ከብሉይ ኪዳንም መጽሐፈ ጦቢት፣መጽሐፈ አስቴር፣መጽሐፈ ሶስና፣የመሳሰሉት በሰዎቹ ኑሮ የተገለጠውን የእምነታቸውን ፍሬ የሚያሳዩ የገድል መጻሕፍት ናቸው፡፡


ገድላት በ3 ይከፍላሉ እነሱም፡-
ገድለ ሰማዕታት፡- ለምሳሌ ገድለ ጊዮርጊስ፣ገድለ ፋሲለደስ፣ገድለ ኢየሉጣ
ገድለ ሐዋርያት፡- በአንድነት የተሰበሰቡ የሐዋርያት አገልግሎት ተአምራት መከራ የያዙ መጽሐፍት
ገድለ ጻድቃን፡- ገድለ አቡነ ተክለሃይማኖት፣ገድለ ገብረመንፈስቅዱስና የመሳሰሉትን ነው፡፡

ስለሆነም የእያንዳንዱ ቅዱስ ሥራ ተጽፎ ከትውልድ ወደ ትውልድ ቢተላለፍ ከዚያ ቅዱስ በረከት ከማሰጠቱም ጋር ለሕይወት አስተማሪ ነው:: ስለዚህ ይህንን የእያንዳንዱን ቅዱስ ሥራ የሚገልጸው መጽሐፍ "ገድል" ይባላል:: ይህውም ከፍትወት፣ እኩያትና ከአጋንንት ጋር ያደረጉትን ተጋድሎና ያሸነፉበትን ሁኔታ የሚያሳይ ነው:: ጠላት ሰይጣን እያንዳንዱን ሰው የሚፈትነው ሊያሸንፈው በሚችልበት መልኩ ስለሆነ የእያንዳንዱን ቅዱስ ገድል ማንበብ የሰይጣንንን ልዩ ልዩ አመጣጥ ያስተምራል:: ታሪክ መጻፍ ካለፈው ለመማር ነውና ከቅዱሳንም ሕይወት ጠቃሚ ትምህርት ይገኛል::

አንድ ሀገርና ሕዝብ በታሪኩ ውስጥ የነበሩትን ባለውለታዎቹን ስማቸው እንዳይረሳና ለተተኪ ትውልድም አርአያ እንዲሆኑ ሥራቸውን በመጻፍና በማስተማር ከትውልድ ወደ ትውልድ ያስተላልፋል:: ለስማቸው መታሰቢያ እንዲሆን መንገዶችን ፣አዳራሾቹን፣ሕንጻዎችንና የመሳሰሉትን በስማቸው ይሰይማል:: ሐዋርያዊትና ቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋህዶ ቤተክርስትያንም ቅዱሳን ልጆቿን በሃይማኖት ያፈሩትን ፍሬ ለመታሰቢያቸው እንዲሁም ለትውልድ ትምህርት እንዲሆንና በረከትም እንዲያስገኝ ጽፋ ታስቀምጣላች::

ይህን የሚቃወሙ ቢኖሩ ሲሰርቅ ሄዶ ጅራቱን ወጥመድ የቆረጠበት ቀበሮ ሌሎቹም እንደርሱ ይሆኑ ዘንድ "ጅራት ትርፍ አካል ስለሆነ አይጠቅምምና ከዛሬ ጀምሮ ሁሉም ቀበሮ ጅራቱን ይቆረጥ" አለ የሚባለውን ይመስላላሉ:: ከሥጋዊ ዓለም መር ብለው ወጥተው መንፈሳዊ ተጋድሎ የተጋደሉ "ቅዱሳን" ስለሌሉአቸው እኛ ከሌለን እነርሱ ስለምን ይኖራቸዋል? የሚል ቅንዓትና ምቀኝነት የጨፈናቸው ናቸው::

ድርሳን

ድርሳን  የሚለውን ቃል በቁሙ “የተደረሰ፣የተጣፈ፣ቃለ ነገር፣ሰፊ ንባብ፣ረዥም ስብከት፣ትርጓሜ፣አፈታት፣ጉሥዐተ ልብ፣መዝሙር፣ምሥጢሩ የሚያጠግብ፣ቃሉ የተሳካ፣ጣዕመ ቃሉና ኃይለ ቃሉ ደስ የሚያሰኝ ልብ የሚነካ” ማለትነው፡፡

“የኑሮአቸውን ፍሬ እየተመለከታችሁ በእምነት ምሰሏቸው” ዕብ.13፥7 እንደ ተባለው በሃይማኖትና በምግባር ለመጠንከር ገድለ ቅዱሳንን የያዙ መጻሕፍትን እናነባለን፤እንጸልይባቸዋለን፡፡የቅዱሳን መላእክትንም ጠባቂነት፣የሊቃውንትን ተግሣጽ ትርጓሜና ምክር የዕለተ ሰንበትን ክብር እና የኢየሱስ ክርስቶስን የቤዛነት ሥራ የሚናገሩ ድርሳናትን ሁልጊዜ እናነባለን እናደርሳለን፡፡

ድርሳን ስለቅዱሳን መላእክት ተራዳኢነት፣ ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት፣ክብርና ጸጋ፣ስለ ዕለተ ሰንበት ክብርና ስለኢየሱስክርስቶስ የማዳን ሥራ የሚናገሩ /የሚያትቱ/ መጻሕፍት ማለታችን ነው፡፡

እስከ 2000 ዓ.ም በተደረገው ጥናት ወደ 138  የሚሆኑ በድርሳን ስያሜ የሚጠሩ መጻሕፍት እንዳሉ ታውቋል፡፡ከእነዚህም ውስጥ 11የሚሆኑት የመላእክት ድርሳናት ሲሆኑ የ11ዱ መላእክት ስምም ቅዱስ ሚካኤል፣ቅዱስ ገብርኤል፣ቅዱስ ሩፋኤል፣ቅዱስ ራጉኤል፣ቅዱስ ዑራኤል፣ቅዱስ አፍኒን፣ቅዱስ ፋኑኤል፣ቅዱስ ሳቁኤል፣ቅዱስ ሱርያል፣ቅዱስ ሱራፌልና ቅዱስ ኪሩቤል ናቸው፡፡

የመላእክት ድርሳናት በአብዛኛው ተመሳሳይነት ባሕርይ አላቸው፡፡የውስጥ ይዞታቸውም በ5 ይከፈላል፡፡እነሱም መቅድም፣ድርሳን፣ተአምራት፣አርኬና መልክእ ናቸው፡፡ከእነዚህ ክፍሎች ውስጥ ድርሳን የምንለው የባለድርሳኑን መልአክ ግብር በፈጣሪው ዘንድ ያለውን ሞገስ የሠራቸውን ተአምራት ከመጽሐፍ ቅዱስና ከሌሎች ቅዱሳት መጻሕፍትጋር እያጣቀሰ የሚያብራራ ክፍል ነው፡፡በአጠቃላይ ድርሳንን በ5 መክፈል ይቻላል፡፡

1. ድርሳነ መላእክት የሚባለው ድርሳነ ሚካኤል፣ ድርሳነ ገብርኤልን የመሳሰሉትን ነው፡፡
2. ድርሳነ ሰንበት ስለ ዕለተ ሰንበት ክብር የሚያብራራ መጽሐፍ

3. ድርሳነ መስቀል ደግሞ የመስቀሉን ታሪክና አመጣጥ ይተርካል፡፡
4. ድርሳነ ሊቃውንት ደግሞ የእነ ቅዱስ አትናቴዎስ የእነ ቅዱስ ኤፍሬም ድርሳን የሚባለው ነው፡፡እንዲሁም ድርሳን ዘቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ፣ድርሳን ዘቅዱስ ቄርሎስንም ያጠቃልላል፡፡
5.ድርሳነ ማኅየዊና ድርሳነ መድኀኔዓለም የመሳሰሉት ድርሳናት የኢየሱስ ክርስቶስን ጸዋትወ መከራ የሚያዘክሩ ድርሳናት ናቸው፡፡

Anchor 4

ስንክሳር

ስንክሳር ማለት ስብስብ ማለት ነው:: ስብስብ የተባለበትም ምክንያት የብዙ ቅዱሳንን ገድልና ዜና ሕይወት በአንድ ላይ የያዘ መጽሐፍ ስለሆነ ነው:: ስንክሳር በእያንዳንዱ ቀን የሚዘከረውን ቅዱስ ታሪክ ጠቅለል ባለመልኩ የያዘ ነው:: ከታሪኩም መጨረሻ ታሪኩን ጠቅለል አድርጎ የሚያስረዳ በግጥም መልክ የተዘጋጀ ድርሰት አለ ይህም "አርኬ" ይባላል:: 
ስንክሳር ከገድል የሚለየው ገድል የሚይዘውን የእያንዳንዱን ጻድቅ ወይም ሰማዕት ሥራ በዝርዝር ሲሆን ስንክሳር ግን የሁሉንም ቅዱሳን ሥራ ጠቅለል ባለመልኩ በዕለት የያዘ ነው:: ስንክሳር ቅዱሳኑን የሚያነሳው የተወለዱበት ዕለት፣ያረፉበትን ቃልኪዳን የተቀበሉበትን ወይንም በዚያ ዕለት እንዲዘከሩ የሚያደርጋቸው ሥራ የሠሩበት ዕለት ከሆነ ነው:: ስለሆነም በአንድ ቀን ብዙ ቅዱሳን ይዘከራሉ:: እንዲሁም ስንክሳር አንዱን ቅዱስ በተለያዩ ቀናት ሊያዘክረው ይችላል:: የቅዱሳንን ዜናቸውንና ሥራቸውን በየዕለቱ መስማት እነርሱን ወደ መምሰል የሚያነሳሳና ረድኤታቸውንና በረከታቸውንም የሚያስጎበኝ ነው:: ስለዚህ ቤተክርስቲያን ሳይሳለሙ ዜና ቅዱሳንን ሳይሰሙ መዋል እንደማይገባ አበው ተናግረዋል::

የቅዱሳን ገድል ጌታ በወንጌል የተናገረው ቃልና ያዘዘው ትእዛዝ ሊፈጽም የሚችልና አማናዊ መሆኑን የሚያስረዳ ነው:: ወንጌል ትእዛዝ ሲሆን የቅዱሳን ሥራ ደግሞ ገቢራዊ ትርጓሜ ነው:: ለምሳሌም የሚከተሉትን እንመልከታለን::


"ዓይንህ ብታሰናክልህ ከአንተ አውጥተህ ጣላት" ማቴ 18:9::
ይህ የክርስቶስ ቃል መፈጸሙን በቅዱስ ገድል እናገኛለን:: ስምዖን ጫማ ሰፊ የሚባል ጻድቅ በዓይኑ ምክንያት ፈተና ስለመጣበት ጌታችንና አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከተናገረው ከዚህ ቃል የተነሳ ዓይኑን በሚሰፋበት መስፊያ አውጥቶ ጥሏታል::

 


"የሰናፍጭ ቅንጣት የሚያህል እምነት ቢኖራችሁ ይህንን ተራራ ከዚህ ወደዚያ እለፍ ብትሉት

ያልፋል::" ማቴ 17:20
አረማውያን ይህንን ቃል ይዘው የክርስቲያኖች መጽሐፍ የማይቻል ነገር ይናገራል ብለው ክርስቲያኖችን ስለተከራከሮአቸው ቅዱስ ስሞዖን ሕዝበ ክርስቲያኑን ንጉሡንና አህዛብን ሰብስቦ ተራራውን ሶስት ጊዜ ወደ ላይና ወደ ታች አሰግዶታል:: ተራራው ሲነሳም በዚህና በዚያ በኩል የነበረውን ሕዝብ በውስጡ ተለያይቷል:: ተራራውንም ከነበረበት ቦታ አንስቶ ሕዝቡን እየመጣ የሚያስቸግራቸው ውኃ ነበርና ሂደህ ተጋረድላቸው ብሎት ቦታውን ለቆ ሄዶ ተጋርዶላቸዋል:: ይህም ተራራ በግብጽ ሀገር ዛሬ ድረስ ያለ ህያው ምስክር ነው::

በአጠቃላይ የቅዱሳን ገድሎች የክርስቶስ ቃል የሚፈጽምና እውነተኛ መሆንኑን በተግባር የሚያሳዩ ናቸው:: እነዚህን የሚጠራጠር ኢየሱስ ክርስቶስ ተናገረውን ማሳበሉ ነውና ይህ የክርስቶስ ተቃዋሚ መንፈስ ነው:: መፈጸሙን የሚያምን ደግሞ ይህንን የሚያገኘው በቅዱሳን ታሪክና ገድል ነው:: ቅዱሳን ራሳቸውን ክደዋልና የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም ችለዋል:: የራሱን ፈቃድ የካደ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ መፈጸም አይከብደውም:: ምክንያቱም “ትእዛዛቱን ልንጠብቅ የእግዚአብሄር ፍቅር ይህ ነውና: ትእዛዛቱም ከባዶች አይደሉም" 1ኛ ዮሐ 5:3  ዘዳ 30:11-14

Anchor 5
bottom of page