top of page
አቡነ አረጋዊና ዘንዶ

ገድላትና ድርሳናት ላይ ጥያቄ ከሚያቀርቡ ልብሳቸው  የተዋህዶ ውስጣቸው ግን መናፍቃንና የመናፍቃን ተላላኪ ተሃድሶ ነን ባዮች ራእ 12:3 {ታላቅ ዘዶ} በመጥቀስ አቡነ አረጋዊ ይህንን እንደታቀፉ አድርገው ሲያቀርቡ ትንሽ አይዘገንናቸውም የተጠቀሰው ዘንዶ ሰይጣንን ነው እንጂ ተፈጥሮአዊውን እባብ ወይም ዘንዶ አይደለም ::
በራእ 13:4 ላይ"ለዘንዶው ሰገዱለት " ያለው እመቤታችንን ሲያሳድድ የነበረው ሰይጣንን መሆኑን ለመረዳት በግድ ወደ ራእ 13:1 ላይ "አስር ቀንዶችና ሰባት ራሶች ነበሩት" የተባለው በራእ 12:3 ላይ "እነሆም ታላቅ ቀይ ዘንዶው ሰባት ራሶችና አሥር ቀንዶችም ነበሩት" የሚለውን በማነጻጸር እና በራእይ 12 ቁጥር 9 ላይ "ዓለሙንም ሁሉ የሚያስተው ዲያብሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ ወደ ምድር ተጣለ መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ" ብሎ የሚገልጸው ሰይጣንን መሆኑን ማወቅ እንችላለን። 

ስለዚህ በዚህ አገላለጽ ዘንዶው ሰይጣን እንጂ ተፈጥሮአዊ ዘንዶ አይደለም።ዘንዶማ እግዚአብሔር ከፈጠራቸው ፍጥረታት መካከል የሆነ እራዊት ነው።አራዊትም ሆነ ሌሎች ፍጥረታት 
ዘፍ 1:31 "እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ እነሆም እጅግ መልካም ነበር" ከተባለው መልካም የሆነፍ ጥረታት መካከል አንዱ ነው። 
ማንኛውም አውሬ ሌላውን ይበላል: አራዊቶች:-በግን በሬን እንዲሁም ሰውን ይበላሉ ዘንዶም እንዲሁ ስለሚያደርግ በሰው ሕሊና ክፉ ምሳሌ ተደርገው እንደተቀመጡ እናስባለን እንጂ ተፈትሮአዊ ዘንዶ ሁሉ ሰይጣን አይደለም። 
ለምሳሌ አንበሳ በሰይጣን ተመስሎአል 
1ኛጴጥ 5:8 "ባላጋራችሁ ዲያቢሎስ የሚውጠውን ፈልጎ እንደሚያገሳ አንበሳ ይዞራል" ስለዚህም ከአራዊት ጋር የነበረውን ሁሉ ከሰይጣን ጋር ነበር ብሎ ማመሳሰል ተገቢ አይደለም። 
ማር 1:13 "ኢየሱስ ክርስቶስ ...ከአራዊትም ጋር ነበር" 
እንዲሁም ቅዱሳን በዱር በጫካ በበርሃ ከአራዊት ጋር ተስማምተው ይኖራሉ።እና ከሰይጣን ጋር ተስማሙ ብሎ ቢናገር የጤነኛ ንግግር ነውን? አይሆንም።ጌታ ክርስቲያኖችን እንደ እባብ እንዲሆኑ ምክር ሰጥቶአል። 
ማቴ 10:16 "እንደ እባብ ልባሞች እንደ እርግብም የዋሆች ሁኑ" 
ይህ ማለት እንደ ሰይጣን ለማለት ነው ቢሉን ትክክል ይሆናሉን? አይሆንም።አቡነ አረጋዊ ተፈጥሮአዊውን ዘንዶ የያዙትን ከሰይጣን በተመሰለ ዘንዶ ጋር ማገናኘት ማለት ኃጥአን በፍየል ተመስለዋልና የፍየል ሥጋ እንዳትይዙ እንዳትመገቡ እንደማለት ነው የሚሆነው።ስለዚህ ማስተዋል ይገባል። 

አቡነ አረጋዊ ተፈጥሮአዊ እባብን ያዙትና በጌታ ስም አዘዙት መላኩም ዘንዶውን እንዳይበላቸው እየገሰጸው ወደ ተራራው አወጣቸው።ይህ ባይሆን ኖሮ በዚያ ተክኖሎጂ ባልተራቀቀበት ዘመን ግዙፉን ተራራ በምን ወጡት? መልሱ በእግዚአብሔር ጥበብ በተፈጥሮአዊው ዘንዶ እንዲሆን ፈቀደ ጌታም አደረገው። 
ይህ እየታወቀ እባብ ወይንም ዘንዶ የሰይጣን ምሳሌ ነውና እንዴት ያቅፉታል ብሎ ማጣጣል ከሚያምን ሰው እንዴት ይጠበቃል? ከተጠራጣሪ እንጂ ከሚያምን ሰው በፍጹም አይጠበቅም።ምክንያቱም ያመኑ ሰዎች እባብን እንደሚይዙ በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ተጠቅሷል:- 
ማር 16:17 "ያመኑትም እነዚህ ምልክቶች ይከተሉአቸዋል በስሜ...እባቦችን ይይዛሉ" አቡነ አረጋዊ እባብን ወይንም ዘንዶውን በእጃቸው ያዙት እንጂ አላመለኩትም። 

የእኛ አምላክ ተራራን እንዲወጡ በፈለገው መጠቀም የእርሱ ፈቃድ ነው። 
ኢዮብ 42:2 "ሁሉን ታደርግ ዘንድ ቻይ እንደሆንህ አሳብህም ይከለከል ዘንድ ከቶ እንደማይቻል አወቅሁ" እንዳለው እንኳንስ ተራራ ይቅርና 
ናሆ 1:3 "እግዚአብሔር በወጀብና በዓውሎ ነፋስ ውስጥ መንገድ አለው" 
2ኛነገ 2:11 እግዚአብሔር ሲፈልግ እንደ ነብዩ ኤልያስ በእሳት ሰረገላ ወደ ላይ ማውጣት ይችላል።ሐሳቡ ስለማይከለከል ያለምንም መጓጓዣ እንደ ሔኖክ ሊሰውርም የሚችልበት ጥበብ አለው ዘፍ5:24 
ወይንም ሐዋርያው ፊልጶስን መንፈስ ቅዱስ ነጥቆ እንደወሰደው ሐዋ 8:39 ማድረግ እንደሚችል በመጽሐፍ ቅዱስ ተመዝግቧል።አቡነ አረጋዊንም በዘንዶ ወገብ ታዝለው እንዲወጡ በማድረግ ጥበቡን ገልጾአል። 
ቅዱስ ጳውሎስ ከአንበሳ አፍ እንዳዳነው እርሱም 
2ኛጢሞ 4:17 "ከአንበሳ አፍም ዳንሁ።" እንዳለው እንዲሁ አቡነ አረጋዊን 
ያዕ 3:7 "አራዊት...የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይነገራል ደግሞ ተገርቷል" ባለው መሠረት አራዊት የሆነው ዘንዶ ሊገሩት ሊይዙት ይቻላቸዋል።እንኳን የተፈጥሮ ዘንዶ አይደለም በዘንዶ የተመሰለውን ሰይጣንን እምነት ላለው እንደሚታዘዝ ማወቅ አለብን። 
ማቴ 17:20 "የሚሳናችሁም ነገር የለም" ብሎ ቃል ገብቷልና። 


ዘንዶ ወይንም ሌሎች አራዊትን መግራት ይቻላ፤; አሁን መግራት ያልተቻለው 
"የአምልኮ መልክ ያላቸውን ነገር ግን ቅዱሳን መላእክትን እና ቅዱሳን ሰዎችን ለማዋረድ ሌት ተቀን የሚሰሩ የእግዚአብሔር አገልጋይ የሆኑትን በሰማይ የሚያድሩት ቅዱሳንን የሚያቃልሉ መናፍቃንን አፋቸውን መግራት አልተቻለም። 
ምክንያቱም 
ራዕ 13:6 "በሰማይም የሚያድሩትን ሊሳደብ አፉን ከፈተ" የሚለው አውሬ አቡነ አረጋዊ የያዙት ተፈጥሮአዊ ዘንዶ ሳይሆን ረቂቁ አውሬ ሰይጣን ዘንዶ ሳይሆን ረቂቁ አውሬ ሰይጣን ትንቢት እንዲፈጸም እየሰራላቸው ነውና" 
በአጠቃላይ ቀጥሎ ቅዱስ ያዕቆብ እንዲህ አውሬን መግራት እንደሚቻል የኃጢአተኛን አፍ ግን መግራት እንደማይቻል እንዲህ ይጽፋል: 
ያዕ 3:7 "የአራዊትና የወፎች የተንቀሳቃሾችና በባህር ያለ የፍጥረት ወገን ሁሉ በሰው ይገራል: ደግሞ ተገርቷል አንደበትን ሊገራ ማንም ሰው አይችልም። የሚገድል መርዝ የሞላበት ወላዋይ ክፋት ነው። 
በእርሱ ጌታንና አብን እንባርካለን በእርሱም እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠሩትን ሰዎች እንረግማለን። ከአንድ አፍ በረከትና መርገም ይወጣሉ።ወንድሞቼ ሆይ ይህ እንዲህ ሊሆን አይገባም።" 
ለክርስቲያኖች በሙሉ አራዊትን ከገሩት ከአቡነ አረጋዊ በረከት ረድኤትን                                                                                                                                                                 ያሳትፈን፤ ለመናፍቃን ደግሞ ልብ ይስጥልን።

 

bottom of page