top of page

መግቢያ

ምንጭ፦ትምህርተ ተዋሕዶ አፕ

ሥርዓት ምንድን ነው? ለምንስ አስፈለገ?

 

ሥርዓት “ሠርዐ” ሠራ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም ደንብ፣ አሠራር፣ መርሐ ግብር ማለት ነው። ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ስንልም የቤተ ክርስቲያን ዕቅድ፣ የቤተ ክርስቲያን አሠራር መርሐ ግብር ወይንም ደንብ ማለታችን ነው።

 

ሥርዓት የሚከተሉት ጥቅሞች አሉት፦

 

 

ሥራን ወጥ በሆነ መልኩ ለመፈጸም

ማንኛውንም ነገር ወጥና ዘላቂ በሆነ መልኩ ለመሥራት ከየት ተጀምሮ በየት በኩል ሄዶ በየት በኩል እንደሚጠናቀቅ ወጥ የሆነ የአሠራር ሥርዓት ይዘጋጅለታል። የአንድ ሥራ አሠራር በትክክል ካልተነደፈና አካሄዱ ካልተስተካከለ፤ ሥራው የተዘበራረቀ ይሆናል ፍጻሜውም አያምርም።

አንድ ሃሳብና አንድ ልብ ለመሆን

አንድ መሥሪያ ቤት በመሥሪያ ቤቱ ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ተግባብተውና ተረዳድተው እንዲሠሩ ሥርዓት ሊኖረው ይገባል። ያ ሥርዓት ነው ሠራተኞቹን እንደመመሪያ ሆኖ ፈር እየቀደደ የሚመራቸውና የሚያስተዳድራቸው። ይህ ካልሆነ ግን እርስ በእርሷ እንደምትለያይ መንግሥት ሳይግባቡ ይቀሩና የመሥሪያ ቤቱንም ራዕይ ማሳካት ሳይችሉ ይቀራሉ። ለዚህ ነው በየአህጉራቱ፣ በየማኅበረሰቡ፣ በየማኅበሩ፣ በየቤተሰቡ የመተዳደሪያ ሥርዓት ማውጣት ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ የሆነው። እንደውም አንዳንድ መሥሪያ ቤቶች ሥራቸውን ከመጀመራቸው በፊት ሊኖራቸው ከሚገቡ ነገሮች መካከል ሥርዓት አንዱና ዋነኛው እንደሆነ ሲነገር ሁላችንም እንሰማለን።

ማኅበረ ምዕመናንም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንደጻፈው የመንፈስን አንድነት ለመጠበቅ አንድ ዓይነት ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ያስፈልገናል። ብዙ ስንሆን አንድ ልቡና አንድ ሃሳብ የሚያደርገን ሥርዓት ነውና። /ኤፌ. ፬፥፫፤ የሐዋ. ፬፥፴፪፤ ሮሜ. ፲፭፥፮/።

የሃይማኖትን ምሥጢራት ለመጠበቅ

ሥርዓት የሃይማኖት መገለጫ ነው። ጥምቀት፣ ቁርባን፣ ጾም፣ ጸሎት፣ ሥግደት፣ ወዘተ በማመን ብቻ የሚያበቁ ሳይሆን የአፈጻጸምና አተገባበር መንገድ /ሥርዓት/ ያስፈልጋቸዋል። የእነዚህ ሁሉ ዝርዝር አፈጻጸም በሥርዓት ውስጥ ይካተታል። ስለዚህ በአንዲት ርትዕትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እምነት ሥር ያሉ ሁሉ ያቺን አንዲት እምነት የሚገልጹት አንድ ዓይነት በሆነ ሥርዓት ነው። ሥርዓት በመሠረተ እምነት /ዶግማ/ የምናምናቸውን በተግባር የምንገልጽበትና ተግባራዊ የምናደርግበት መንገድ ስለሆነ ሥርዓቱ ሲሠራና ሲፈጸም ሃይማኖታዊ አንድምታና ነጸብራቅ ይኖረዋል።

  

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን​

ቤተ ክርስቲያን ማለት ሕንፃው፣ የክርስቲያኖች አንድነት /ጉባኤ/ እና የምዕመኑ ሰውነት በመሆኑ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን የምንለውም በእነዚህ በሦስቱ ላይ የተሠራውን ሥርዓት ነው። አንዳንዶቻችን ቤተ ክርስቲያንን ከራሳችን አርቀን ሌላ አካል አድርገን ስለምንመለከት ሥርዓቱ እኛን የሚመለከት አይመስለንም። ሥርዓቱ ግን የተሠራው ለሦስቱም የቤተ ክርስቲያን ትርጓሜዎች መሆኑን ማወቅ ተገቢ ነው።

ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን ምንጩ ወይንም መሠረቱ መጽሐፍ ቅዱስ፣ የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት ውሳኔ /ሲኖዶስ/ እና አባቶቻችን ሊቃውንት በተለያዩ ጊዜ ያደረጓቸው ጉባኤያት ውሳኔዎች ናቸው።

ሰንበትን ማክበር፣ በጻድቃን ስም አብያተ ክርስቲያናትን ማነጽ፣ የቁርባን ሥርዓት፣ የመሳሰሉት ከመጽሕፍ ቅዱስ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው። /ዘፍ. ፳፰፥፳-፳፪፤ ዘጸ. ፲፮፥፳፱፤ የሐዋ. ፩፥፲፪/።

ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባውንና የተቀደሰውን ንዋየ ቅድሳት እንደገና ወደውጭ አውጥቶ ለሥጋዊ ጥቅም ማዋል እንደማይገባ /ፍትሐ ነገሥት አንቀጽ ፩ ረስጣ ፳፰/፣ ጥምቀት በፈሳሽ ውኃ መፈጸም እንዳለበት፣ ወንዶች ሴቶችን ሴቶች ደግሞ ወንዶችን ክርስትና እንዳያነሱ፣ ሥጋ ወደሙ ለመቀበል ፲፰ ሰዓት መጾም እንደሚገባ፣ ሥጋ ወደሙ በምድር ላይ እንዳይወድቅ /እንዳይነጥብ/፣ ያላመኑ ሰዎች ሥጋ ወደሙን መቀበል እንደሌለባቸው፣ ወዘተ ያሉት ደግሞ በሲኖዶስ /የቅዱሳን አባቶቻችን ጉባኤያት/ የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

ከእናቱ፣ ከእህቱ፣ ከአክስቱ ወይንም እንደዚህ ባለ ሁኔታ ከምትታሰብ ሴት ጋር ካልሆነ በቀር አንድ ኤጲስ ቆጶስ፣ አንድ ቄስ፣ አንድ ዲያቆን፣ ወይንም ሌላ የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ ከማንኛውም ሴት ጋር አብሮ እንዳይኖር፤ ስለ መናፍቃን ጥምቀት፣ ስለ ትንሣኤ በዓል አከባበር፣ ስለ ድንግልና ኑሮ፣ ወዘተ ደግሞ በተለያዩ ጉባኤያት አባቶቻችን ያስተላለፏቸው ውሳኔዎችና ቀኖናዎች የተገኙ ሥርዓቶች ናቸው።

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

ምንጭ፦ማኅበረ ቅዱሳን የአውሮፓ ማእከል

Anchor 1
Anchor 2

ሥራ ወይስ እምነት ነው የሚያጸድቀው?

 

ሥራ ወይስ እምነት ነው የሚያጸድቀው? ተብሎ ብዙ ጊዜ ይጠየቃል።ጥያቄውን በአጭሩ ለመመለስ ያህል የሚያጸድቀው ሁለቱንም በጥምረት መያዝ ነው። የሰው ልጅ ከተጥመቀ ዮሃ 3:5 “ሰው ዳግመኛ ከውሃና ከመንፈስ ካልተወለደ በስተቀር ወደ መንግስተ ሰማያት አይገባም” እንደተባለ 
ስጋወደሙን ከተቀበለ ዮሃ 6:54 “ስጋዬንም የሚበላ ደሜንም የሚጠጣ የዘላለም ሕይወት አለው” እንደተባለ በኋላ እምነቱን በሥራው መግለጽ የግድ ነው።ጌታም በማቴ 25 ላይ ስለ ሙሽራው፤ዘይትና መብራት አጣምረው ስለያዙት ደናግላን በምሳሌ ያስተማረውን አንብበን መረዳት እንችላለን።በተጨማሪም 
በያዕቆብ መልእክት ምእ 2 ቁ 14 ላይ “ ወንድሞቼ ሆይ እምነት አለኝየ ሚል፤ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን?” ብሎ አስቀምጦታል።በቁጥር 17 ላይም እንዲሁ “ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው።” ብሎ ገልጾልናል።ይህ ምእራፍ ስለእምነትና ሥራ በደምብ የሚያስረዳን ሲሆን መናፍቃኑ “አብርሃምም አመነ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት” ስለሚል መጽሀፍ ቅዱስ እምነት ብቻ በቂ ነው ብለው ለሚያስተምሩት ትምህርትም አጥጋቢ ምላሽ ይሰጣል።እንዲህ በማለት “ አባታችን አብርሀም ልጁን ይስሀቅን በመሰዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደነበር በሥራም እምነት እንደተገለጸ ትመለከታለህን? መጽሀፍም አብርሀምም አመነ፤ ጽድቅም ሆኖ ተቆጠረለት ያለው ተፈጸመ፤ የእግዚአብሔርም ወዳጅ ተባለ።ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ።” 
ሥራ አያስፈልግም፣ማመን ብቻ ያድናል የምትሉ እስኪ እነዚህን ጥቅሶች አንብቡ፡፡ ተጻፉ? እውነት ነው የጽድቅ በርየ ተከፈተልን በጌታችን በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡የጽድቃችን መሰረትም በሩም እርሱ ነው፡፡ይህ ማለት ግን በማመን ብቻ መዳን እንደሚቻል ተደርጎ ሊወሰድ ኣይገባውም፡፡መልካም ሥራ ካልሰራን የክርስቶስ መሆናችንስ በምን ይታወቃል? በማመናችን ብቻ ለእርሱ ልንሆን አንችልም፡፡ማመን ብቻውን አያድንም፡፡መታመንን መጨመር አለብን፡፡መታመን ማለት ደግሞ ላመኑት መገዛት፣የታዘዙትን መፈጸም ማለት ነው፡፡ይኸውም የሚገለጸው በመልካም ሥራ ነው እንጅ አምናለሁ እያሉ በመናገር ብቻ አይደለም፡፡ለማንኛውም የሚከተሉትን ጥቅሶች አንብቡና ፍረዱ፡፡ጽድቅ በእምነት ብቻና እምነት ብቻውን ቢያድን ኖሮ እነዚህ ለምን ተጻፉ?

የዮሐንስ ራእይ 

20፥13  ባሕርም በእርሱ ውስጥ ያሉትንሙታን ሰጠ፥ሞትና ሲኦልም በእነርሱ ዘንድ ያሉትን ሙታን ሰጡ፥እያንዳንዱም እንደሥራው መጠን ተከፈለ። 
22፥12 እነሆ፥በቶሎ እመጣለሁ፥ለእያንዳንዱም እንደ ሥራው መጠን እከፍል ዘንድ ዋጋዬ ከእኔ ጋር አለ። 

የያዕቆብ መልእክት 
1፥4 ትዕግሥትም ምንም የሚጎድላችሁ ሳይኖር ፍጹማንና ምሉዓን ትሆኑ ዘንድ ሥራውን ይፈጽም። 
1፥25 ነገር ግን ነጻ የሚያወጣውን ፍጹሙን ሕግ ተመልክቶ የሚጸናበት ሥራንም የሚሠራ እንጂ ሰምቶ የሚረሳ ያልሆነ፥በሥራው የተባረከ ይሆናል። 
2፥14 ወንድሞቼ ሆይ፥እምነት አለኝ የሚል፥ሥራ ግን የሌለው ሰው ቢኖር ምን ይጠቅመዋል? እምነቱስ ሊያድነው ይችላልን? 
2፥17 እንደዚሁም ሥራ የሌለው እምነት ቢኖር በራሱ የሞተ ነው። 
2፥18 ነገር ግን አንድ ሰው አንተ እምነት አለህ እኔም ሥራ አለኝ፤እምነትህን ከሥራህ ለይተህ አሳየኝ፥እኔም እምነቴን በሥራዬ አሳይሃለሁ ይላል። 
2፥20 አንተ ከንቱ ሰው፥እምነት ከሥራ ተለይቶ የሞተ መሆኑን ልታውቅ ትወዳለህን? 
2፥21 አባታችን አብርሃም ልጁን ይስሐቅን በመሠዊያው ባቀረበ ጊዜ በሥራ የጸደቀ አልነበረምን? እምነት ከሥራው ጋር አብሮ ያደርግ እንደነበረ፥በሥራም እምነት እንደተፈጸመ ትመለከታለህን? 
2፥24  ሰው በእምነት ብቻ ሳይሆን በሥራ እንዲጸድቅ ታያላችሁ። 
2፥25 እንደዚሁም ጋለሞታይቱ ረዓብ ደግሞ መልእክተኞቹን ተቀብላ በሌላ መንገድ በሰደደቻቸው ጊዜ በሥራ አልጸደቀችምን? 
2፥26 ከነፍስ የተለየ ሥጋ የሞተ እንደሆነ እንዲሁ ደግሞ ከሥራ የተለየ እምነት የሞተ ነው። 
3፥13 ከእናንተ ጥበበኛና አስተዋይ ማን ነው? በመልካም አኗኗሩ ስራውን በጥበብ የዋህነት ያሳይ። 
3፥16 ቅንዓትና አድመኛነት ባሉበት ስፍራ በዚያ ሁከትና ክፉ ስራ ሁሉ አሉና። 
5፥16 እርስ በርሳችሁ በኃጢአታችሁ ተናዘዙ።ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለሌላው ይጸልይ፤የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች። 

የጳውሎስ መልእክት ወደ ሮሜ ሰዎች 
2፥6 እርሱ ለእያንዳንዱ እንደ ሥራው ያስረክበዋል፤ 

1ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 
3፥13 በእሳት ስለሚገለጥ ያ ቀን ያሳያልና፥የእያንዳንዱም ሥራ እንዴት መሆኑን እሳቱ ይፈትነዋል። 
3፥14  ማንም በእርሱ ላይ ያነጸው ሥራ ቢጸናለት ደመወዙን ይቀበላል፤ 

1ኛ የዮሐንስ መልእክት 
3፥12  ከክፉው እንደነበረ ወንድሙንም እንደገደለ እንደ ቃየል አይደለም፤ስለምንስ ገደለው? የገዛ ሥራው ክፉ፥የወንድሙም ሥራ ጽድቅ ስለነበረ ነው። 

1ኛየጳውሎስ መልእክት ወደተሰሎንቄ ሰዎች 
1፥2-3  በጸሎታችን ጊዜ ስለእናንተ ስናሳስብ፥የእምነታችሁን ስራ የፍቅራችሁንም ድካም በጌታችንም በኢየሱስ ክርስቶስ ያለውን የተስፋችሁን መጽናት በአምላካችንና በአባታችን ፊት ሳናቋርጥ እያሰብን፥እግዚአብሔርን ሁልጊዜ በሁላችሁ ምክንያት እናመሰግናለን፤ 

2ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደተሰሎንቄ ሰዎች 
2፥16-17 ራሱ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስና የወደደን በጸጋም የዘላለምን መጽናናት በጎንም ተስፋ የሰጠን እግዚአብሔር አባታችን ልባችሁን ያጽናኑት በበጎም ሥራና በቃል ሁሉ ያጽኑአችሁ። 
3፥11 ሥራ ከቶ ሳይሠሩ፥በሰው ነገር እየገቡ፥ያለ ሥርዓት ከእናንተ ዘንድ ስለሚሄዱ ስለ አንዳንዶች ሰምተናልና። 
3፥13  እናንተ ግን ወንድሞች ሆይ መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። 

የጳውሎስ መልእክት ወደ ፊልሞና 
1፥7  የቅዱሳን ልብ በአንተ ሥራ ስለ ዐረፈ፥ወንድሜ ሆይ፥በፍቅርህ ብዙ ደስታንና መጽናናትን አግኝቼአለሁና። 

1ኛ የጴጥሮስ መልእክት 
1፥17  ለሰው ፊትም ሳያደላ በእያንዳንዱ ላይ እንደ ሥራው የሚፈርደውን አባት ብላችሁ ብትጠሩ በእንግድነታችሁ ዘመን በፍርሃት ኑሩ። 
2፥12  ስለሚመለከቱት ስለ መልካም ሥራችሁ፥ክፉ እንደምታደርጉ በዚያ እናንተን በሚያሙበት ነገር፥በሚጎበኝበት ቀን እግዚአብሔርን ያከብሩት ዘንድ በአሕዛብ መካከል ኑሮአችሁ መልካም ይሁን። 

የማቴዎስ ወንጌል 
3፥10  አሁንስ ምሳር በዛፎች ሥር ተቀምጦአል፤እንግዲህ መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቈረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 
5፥44-45  እኔ ግን እላችኋለሁ፥በሰማያት ላለ አባታችሁ ልጆች ትሆኑ ዘንድ ጠላቶቻችሁን ውደዱ፥የሚረግሙአችሁንም መርቁ፥ለሚጠሉአችሁም መልካም አድርጉ፥ስለሚያሳድዱአችሁም ጸልዩ፤እርሱ በክፉዎችና በበጎዎች ላይ ፀሐይን ያወጣልና፥በጻድቃንና በኃጢአተኞችም ላይ ዝናቡን ያዘንባልና። 
7፥18  መልካም ዛፍ ክፉ ፍሬ ማፍራት፥ወይም ክፉ ዛፍ መልካም ፍሬ ማፍራት አይቻለውም። 
7፥19  መልካም ፍሬ የማያደርግ ዛፍ ሁሉ ይቆረጣል ወደ እሳትም ይጣላል። 
12፥12  እንግዲህ ሰው ከበግ ይልቅ እንደምን አይበልጥም! ስለዚህ በሰንበት መልካም መሥራት ተፈቅዶአል አላቸው። 
12፥33  ዛፍ ከፍሬዋ ትታወቃለችና ዛፍዋን መልካም፥ፍሬዋንም መልካም አድርጉ፥ወይም ዛፍዋን ክፉ ፍሬዋንም ክፉ አድርጉ። 
12፥34  እናንተ የእፉኝት ልጆች፥ክፉዎች ስትሆኑ መልካም ለመናገር እንዴት ትችላላችሁ? በልብ ሞልቶ ከተረፈው አፍ ይናገራልና። 
12፥35  መልካም ሰው ከልቡ መልካም ነገርን ያወጣል፥ክፉ ሰውም ከክፉ መዝገብ ክፉ ነገርን ያወጣል። 
13፥23  በመልካም መሬት የተዘራውም ይህ ቃሉን ሰምቶ የሚያስተውል ነው፤እርሱም ፍሬ ያፈራል አንዱም መቶ አንዱም ስድሳ አንዱም ሠላሳ ያደርጋል። 
13፥24  ሌላ ምሳሌ አቀረበላቸው እንዲህም አለ፦መንግሥተ ሰማያት በእርሻው መልካም ዘርን የዘራን ሰው ትመስላለች። 
26፥10  ኢየሱስም ይህን አውቆ እንዲህ አላቸው፦መልካም ሥራ ሠርታልኛለችና ሴቲቱንስ ስለምን ታደክሙአታላችሁ? 

የዮሐንስ ወንጌል 
5፥28-29  በመቃብር ያሉት ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ። 


የጳውሎስ መልእክት ወደ ገላትያ ሰዎች 
4፥17  በብርቱ ይፈልጉአችኋል፥ለመልካም አይደለም ነገር ግን በብርቱ ትፈልጉአቸው ዘንድ በውጭ ሊያስቀሩአችሁ ይወዳሉ። 
4፥18  ነገር ግን ከእናንተ ዘንድ በምኖርበት ጊዜ ብቻ ሳይሆን ሁልጊዜ በመልካም ነገር ተፈላጊ ብትሆኑ መልካም ነው። 
5፥7 በመልካም ትሮጡ ነበር፤ለእውነት እንዳትታዘዙ ማን ከለከላችሁ? 
6፥6 ነገር ግን ቃሉን የሚማር ከሚያስተምረው ጋር መልካምን ነገር ሁሉ ይከፋፈል። 
6፥9  ባንዝልም በጊዜው እናጭዳለንና መልካም ሥራን ለመሥራት አንታክት። 
6፥10  እንግዲያስ ጊዜ ካገኘን ዘንድ ለሰው ሁሉ ይልቁንም ለሃይማኖት ቤተሰቦች መልካም እናድርግ። 
6፥12  በሥጋ መልካም ሆነው ሊታዩ የሚወዱ ሁሉ እንድትገረዙ ግድ አሉአችሁ፥ነገር ግን ስለ ክርስቶስ መስቀል እንዳይሰደዱ ብቻ ነው። 

የጳውሎስ መልእክት ወደ ኤፌሶን ሰዎች 
4፥28  የሰረቀ ከእንግዲህ ወዲህ አይስረቅ፥ነገር ግን በዚያ ፈንታ ለጎደለው የሚያካፍለው እንዲኖርለት በገዛ እጆቹ መልካምን እየሠራ ይድከም። 
6፥2-3  መልካም እንዲሆንልህ ዕድሜህም በምድር ላይ እንዲረዝም አባትህንና እናትህን አክብር፤እርስዋም የተስፋ ቃል ያላት ፊተኛይቱ ትእዛዝ ናት። 
6፥8  ባሪያ ቢሆን ወይም ጨዋ ሰው፥እያንዳንዱ የሚያደርገውን መልካም ነገር ሁሉ ከጌታ በብድራት እንዲቀበለው ታውቃላችሁና። 

የጳውሎስ መልእክት ወደ ፊልጵስዩስ ሰዎች 
1፥6  በእናንተ መልካምን ሥራ የጀመረው እስከ ኢየሱስ ክርስቶስ ቀን ድረስ እንዲፈጽመው ይህን ተረድቼአለሁና፤ 
4፥8 በቀረውስ፥ወንድሞች ሆይ፥እውነተኛ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ጭምትነት ያለበትን ነገር ሁሉ፥ጽድቅ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ንጹሕ የሆነውን ነገር ሁሉ፥ፍቅር ያለበትን ነገር ሁሉ፥መልካም ወሬ ያለበትን ነገር ሁሉ፥በጎነት ቢሆን ምስጋናም ቢሆን፥እነዚህን አስቡ፤ 
4፥14  ሆኖም በመከራዬ ከእኔ ጋር ስለተካፈላችሁ መልካም አደረጋችሁ። 


1ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደ ተሰሎንቄ ሰዎች 
3፥6  አሁን ግን ጢሞቴዎስ ከእናንተ ዘንድ ወደ እኛ መጥቶ ስለእምነታችሁና ስለፍቅራችሁ የምስራች ብሎ በነገረን ጊዜ፥እኛም እናያችሁ ዘንድ እንደምንናፍቅ ታዩን ዘንድ እየናፈቃችሁ ሁልጊዜ በመልካም እንደምታስቡን በነገረን ጊዜ፥ 

2ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደተሰሎንቄ ሰዎች 
3፥13  እናንተ ግን፥ወንድሞች ሆይ፥መልካም ሥራን ለመሥራት አትታክቱ። 

1ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደ ጢሞቴዎስ 
1፥8  ነገርግን ሰው እንደሚገባ ቢሰራበት ሕግ መልካም እንደሆነ እናውቃለን፤ 
1፥18  ጢሞቴዎስ ልጄ ሆይ፥አስቀድሞ ስለ አንተ እንደተነገረው ትንቢት፥በእርሱ መልካም ጦርነት ትዋጋ ዘንድ ይህችን ትእዛዝ አደራ እሰጥሃለሁ፤ 
2፥3-4  ሰዎች ሁሉ ሊድኑና እውነቱን ወደ ማወቅ ሊደርሱ በሚወድ በእግዚአብሔር በመድኃኒታችን ፊት መልካምና ደስ የሚያሰኝ ይህ ነው። 
2፥9-10 እንዲሁም ደግሞ ሴቶች በሚገባ ልብስ ከእፍረትና ራሳቸውን ከመግዛት ጋር ሰውነታቸውን ይሸልሙ፤እግዚአብሔርን እንፈራለንለ ሚሉት ሴቶች እንደሚገባ፥መልካም በማድረግ እንጂ በሽሩባና በወርቅ ወይም በዕንቍ ወይም ዋጋው እጅግ በከበረ ልብስ አይሸለሙ። 
3፥1 ማንም ኤጲስ ቆጶስነትን ቢፈልግ መልካምን ሥራ ይመኛል የሚለው ቃል የታመነ ነው። 
3፥4  ልጆቹን በጭምትነት ሁሉ እየገዛ የራሱን ቤት በመልካም የሚያስተዳድር፤ 
3፥7  በዲያብሎስ ነቀፋና ወጥመድም እንዳይወድቅ፥በውጭ ካሉት ሰዎች ደግሞ መልካም ምስክር ሊኖረው ይገባዋል። 
3፥12  ዲያቆናት ልጆቻቸውንና የራሳቸውን ቤቶች በመልካም እየገዙ እያንዳንዳቸው የአንዲት ሴት ባሎች ይሁኑ። 
3፥13  በዲቁና ሥራ በመልካም ያገለገሉ ለራሳቸው ትልቅ ማዕርግና በክርስቶስ ኢየሱስ ባለው እምነት ብዙ ድፍረት ያገኛሉ። 
4፥4  እግዚአብሔር የፈጠረው ሁሉ መልካም ነውና፥ከምስጋናም ጋር ቢቀበሉት የሚጣል ምንም የለም፤ 
4፥6  ስለዚህ ወንድሞችን ብታሳስብ፥በእምነትና በተከተልኸው በመልካም ትምህርት ቃል የምትመገብ የኢየሱስ ክርስቶስ መልካም አገልጋይ ትሆናለህ። 
5፥4  ማንም ባልቴት ግን ልጆች ወይም የልጅ ልጆች ቢኖሩአት፥እነርሱ አስቀድመው ለገዛ ቤተሰዎቻቸው እግዚአብሔርን መምሰል ያሳዩ ዘንድ፥ለወላጆቻቸውም ብድራትን ይመልሱላቸው ዘንድ ይማሩ፤ይህ በእግዚአብሔር ፊት መልካምና የተወደደ ነውና። 
5፥10  ልጆችን በማሳደግ እንግዶችንም በመቀበል፥የቅዱሳንንም እግሮች በማጠብ፥የተጨነቁትንም በመርዳት በጎንም ሥራ ሁሉ በመከተል፥ይህን መልካም ሥራ በማድረግ የተመሰከረላት ልትሆን ይገባል። 
5፥17 በመልካም የሚያስተዳድሩ ሽማግሌዎች፥ይልቁንም በመስበክና በማስተማር የሚደክሙት፥እጥፍ ክብር ይገባቸዋል። 
5፥25  እንዲሁ መልካም ሥራ ደግሞ የተገለጠ ነው፥ያልተገለጠም ከሆነ ሊሰወር አይችልም። 
6፥2  የሚያምኑም ጌቶች ያሏቸው፥ወንድሞች ስለሆኑ አይናቋቸው፥ነገር ግን በመልካም ሥራቸው የሚጠቅሙ የሚያምኑና የተወደዱ ስለሆኑ፥ከፊት ይልቅ ያገልግሉ። 
6፥12  መልካሙን የእምነት ገድል ተጋደል፥የተጠራህለትንም በብዙም ምስክሮች ፊት በመልካም መታመን የታመንህለትን የዘላለምን ሕይወት ያዝ። 
6፥18-19  እውነተኛውን ሕይወት ይይዙ ዘንድ፥ለሚመጣው ዘመን ለራሳቸው መልካም መሠረት የሚሆንላቸውን መዝገብ እየሰበሰቡ፥መልካምን እንዲያደርጉ በበጎም ሥራ ባለጠጎች እንዲሆኑ፥ሊረዱና ሊያካፍሉም የተዘጋጁ እንዲሆኑ ምከራቸው። 

2ኛ የጳውሎስ መልእክት ወደ ጢሞቴዎስ 
3፥3  ቅድስና የሌላቸው፥ፍቅር የሌላቸው፥ዕርቅን የማይሰሙ፥ሐሜተኞች፥ራሳቸውን የማይገዙ፥ጨካኞች፥መልካም የሆነውን የማይወዱ፥ 

የጳውሎስ መልእክት ወደቲቶ 
2፥7-8  የሚቃወም ሰው ስለእኛ የሚናገረውን መጥፎ ነገር ሲያጣ እንዲያፍር፥በነገር ሁሉ መልካምን በማድረግህ ምሳሌ የሚሆን ራስህን አሳይ፤በትምህርትህም ደኅንነትን፥ጭምትነትን፥ጤናማና የማይነቀፍ ንግግርን ግለጥ። 
3፥8  ቃሉ የታመነ ነው።እግዚአብሔርንም የሚያምኑት በመልካም ሥራ በጥንቃቄ እንዲጸኑ፥እነዚህን አስረግጠህ እንድትናገር እፈቅዳለሁ።ይህ መልካምና ለሰዎች የሚጠቅም ነው፤

bottom of page