የቅድስት ድንግል ማርያም የትውልድ ሐረግ

እግዚአብሔር አምላክ ማደሪያው ሁሉ ንጹሕና ቅዱስ ፍጹምም ነው።ስለሆነም እርሱ ያደረበት ሰውም ሆነ ቦታ ወይንም ንዋይ ሁሉ ቅዱስ ይባላል።እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የአምላክ ማደሪያ ሆና ስለተገኘች ቅድስት ትባላለች።የተገኘችውም እግዚአብሔር ካደረባቸው ቅዱሳን ስለሆነ ምጭምር ቅድስት ተብላለች።ቅዱሳን የተባሉ ዘሮቿ እነማን ናቸው? ቢባል ከዚህ እንደሚከተለው ዋና ዋናዎቹን እናያቸዋለን፦

አዳም ----> ሴት ---> ኖኅ ---> ሴም ---> አብርሃም ---> ይስሐቅ ---> ያዕቆብ ---> ይሁዳና፣ሌዊ ---> ዳዊት ---> ሰሎሞን ---> ጰጥርቃና/ቴክታ ---> ኢያቄም/ሐና ---> ድንግልማርያም ---> ኢየሱስክርስቶስ።

ሀ. አብርሃም፦

አባታችን አብርሃም ቅዱስ የእግዚአብሔር ሰው ነበር እግዚአብሔር አምላክም አስቀድሞ ቃል የገባለት ወይንም የመረቀው ሰው ነው  “ዘርህንም እንደ ሰማይ ከዋክብት በባሕርዳር እንዳለ አሸዋ አበዛዋለሁ” ብሎ እግዚአብሔር ቃልኪዳን የሰጠው ጻድቅ ሰው ዘፍ.፳፪፥፲፯። በዕብራውያን መልዕክቱ ፩፥፲፮ ላይ ቅዱስ ጳውሎስ ስለኢየሱስ ክርስቶስ ሲናገር  “የአብርሃምን ዘር ይዟል እንጂ የመላእክትን አይደለም” በማለት ከአብርሃም ዘር በወረደው የሰው ዘር በኩል እንደተወለደ መስክሯል።

ለ. ዳዊት፦

ወንጌላዊው ቅዱስ ማቴዎስ የኢየሱስ ክርስቶስን የትውልድ ሐረግ በፃፈበት በምዕራፍ ፩ ላይ “የዳዊት ልጅ የአብርሃም ልጅ የኢየሱስ ክርስቶስ የትውልድ መጽሐፍ” ብሎ ይጀምራል፤ ስለቅዱስ ዳዊት እግዚአብሔር ሲመሰክርለትም  “እንደልቤ የሆነ ሰው ፈቃዴንም ሁሉ የሚያደርግ የእሴይን ልጅ ዳዊትን አገኘሁ” ሐዋ.ሥራ፲፫፥፳፪ ብሎ የጠራው ታላቅ ቅዱስ የእግዚአብሔር ባለሟል ነው

ሐ. ኢያቄም እና ሐና፦

የቅድስት ድንግል ማርያም አባትና እናት ናቸው እነዚህ ባልና ሚስት ሕይወታቸውን በተቀደሰ ኑሮ እየመሩ በኢየሩሳሌም አካባቢ ይኖሩ የነበሩ ሰዎች ናቸው ፤ሕይወታቸው በእግዚአብሔር የሚመራ ቅዱሳን ቢሆኑም ልጅ አልነበራቸውም፤በዚህ ምክንያት በተለይ ቅድስት ሐና ከጎረቤቶቿና ከአካባቢው ሴቶች ሽሙጥና መገለል ይደርስባት ነበር፤ይህም በዚያን ጊዜ ያልወለደች ሴት እንደኃጢአተኛ ትቆጠር ስለነበር ነው።በዚህ የተነሣ ቅድስት ሐና ዘወትር ወደ ፈጣሪዋ ልጅ ይሰጣት ዘንድ ትጸልይ ነበር፤ብጽአትም ወይም ስእለት ገብታ አምላኳን ተማጸነች፤ብጽአቷም ወንድ ልጅ ከሰጣት ካህን ቀዳሽ የእግዚአብሔርን ቤት አገልጋይ እንዲሆን ፤ሴትም ብትሆን ውሃ ቀድታ ፤ ፈትል ፈትላ ፤ቤተእግዚአብሔርን እንድታገለግል ለቤተመቅደስ ልትሰጣት ነበር ።የሰዎችን ልመና የማይንቅ እግዚአብሔርም ልመናዋን ሰማት ፤ልጅም ፀነሰች ፤ይህም የሆነው ነሐሴ ፯ ቀን ከክርስቶስ ልደት በፊት ፲፮ ዓመት ላይ ነበር እመቤታችንም ግንቦት ፩ ቀን ፲፭ ዓመት ቅድመ ክርስቶስ ሊባኖስ በተሰኘ ቦታ ተወለደች ።በአጠቃላይ እንደነዚህ ካሉ ቅዱሳን ዘር የተገኘች በመሆኗ እመቤታችን ቅድስት ተብላለች።ነብዩ ዳዊት በመዝሙር ፹፮፥፩ ላይ  “መሠረቶቿ በተቀደሱ ተራሮች ናቸው” ሲል ስለትውልዷ ይመሰክራል።

 

ንጽሕናዋና ቅድስናዋ ድንቅ ነው።

“ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም” /መኃ.4፥7/፡፡

እግዚአብሔር ቅዱስ አምላክ ነው፤ ማደሪያውም ሁሉ ቅዱስ ነው እግዚአብሔር በበረከትና በረድኤት ያደረባቸው ሰዎች ቦታዋችና ነዋያት ሁሉ ቅዱስ የሚል ቅጽል ይሰጣቸዋል።እመቤታችን ድንግል ማርያም ደግሞ እግዚአብሔር በበረከትና በረድኤት ብቻ ሳይሆን በሥጋም ያደረባት ናትና ቅድስት /ቅድስተቅዱሳን ትባላለች፤ ቅድስናዋም በሥጋ ፣በነፍስና በሕሊናዋም ጭምር ነው።ነብዩ ዳዊትም “ልዑል ማሪያውን ቀደሰ” መዝ. ፵፭፥፬-፭ በማለት አስቀድሞ በፈጣሪ ዘንድ የተቀደሰች መሆኗን ይናገራል ።መልአኩ ቅዱስ ገብርኤልም  “ከሴቶች ተለይተሽ የተባረክሽነሽ የማኅጸንሽም ፍሬ የተባረከነው” ሉቃ. ፩፥፳፰  በማለት ቅድስናዋን መስክሯል።

እግዚአብሔር ዓለምን ሁሉ ላዳነበት ጥበቡ ምስጢር መፈጸሚያ መቅደስ ፣የመለኮት ማደሪያ ለመሆን የበቃች ንጽሕት ቅድስት ናት ።ክርስቶስ ከቅድስት ድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ተወልዶ ዓለምን ከጥፊት እንደሚያድን "እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደሰድም በሆንን እንደገሞራም በመሰልን ነበረ፡፡” ኢሳ. 1፥14 ብሎ ተናግሮ ነበር፡፡ዘርን የሚለው ቃል ለጊዛው በእግዚአብሔር ርኅራኄ ጨርሶ ከመጥፊት የዳኑትን ቱሩፊንን ቢሆንም  (እነዙህም ከጥፊት የዳኑ ደጋግ የእስራኤል ሕዝቦች ናቸው)  ፍጻሜው ግን ለቅድስት ድንግል ማርያምና ለክርስቶስ የተነገረ ነው፡፡ቅድስት ድንግል ማርያም ራሷን በንጽሕናና በቅድስና በማኖር የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያ በመሆንዋ ምክንያት ከራስዋ ቅድስና ጋር ታክል መንፈስ ቅዱስ ፍጽምትና ቅድስት እንድትሆን አድርጓታል፡፡ እግዚአብሔር ባወቀ በዙህ ምክንያት ነው እርሷን ለተዋሕድ የመረጣት፡፡መጽሐፍ ቅዱስን አስተውለን ብንመለከት የእግዚአብሔር ማደሪያ ወይም እግዚአብሔር የመረጣቸው ወይም የእግዚአብሔር ክብር የተገለጠባቸው ቅደሳን እንዱሁ በከንቱ ቅድስ የተባለ እንዳልሆኑ እንረዳለን፡፡

ነገር ግን እግዚአብሔርን በመውደድ እርሱ ደስ የሚያሰኘውን ሥራ በመሥራት ራሳቸውን ከዓለም ጉድፍ በመጠበቅ በትልቅ ተጋድል እንደሆነ የታወቀ ነው፡፡ከዙያ በኋላ በእነርሱ እግዚአብሔር ሥራውን ለመሥራት አያፍርም ስለዙህም ቅደስ ዳዊት  “እግዚአብሔር በጻድቁ እንደተገለጸ እወቁ” መዝ.4፥3 ብሎ በመንፈስ ተሞልቶ መሠከረ ፡፡ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም “የሚወደኝ ቃሌን ይጠብቃል አባቴም ይወደዋል ወደእርሱም እንመጣለን በእርሱም ዘንድ መኖሪያ እናደርጋለን” /ዮሐ.14፥24 ብሎ አስተማረን፡፡

ቅድስት እናታችንንም እግዚአብሔር ለተዋሕድ ሲመርጣት የንጽሕና የቅድስና ሕይወቷን ተመልክቶ ነው ፡፡ቅድስናዋም ከቅደሳን ሁለ ስለሚበልጥ እግዚአብሔር ለአንዳ የሚያደርገውን ወደፉትም ለላልች የማያደርገውን ሥራ በእርሷ ለመሥራት የፈቀደው ፡፡እኛም ኦርቶድክሳውያን የቅድስት ድንግል ማርያምን ንጽሕና እንዱህ በማለት እንመሰክራለን፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም በሐልዮ በነቢብ በገቢር ከሚሠራ ኃጢአት ሁለ ንጽሕት ናት፡፡መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚያስረዳን “ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው ነውርም የለብሽም”  እንዳለ  /መኃ.4፥7/፡፡

ይህንን ስንል ኃይለ አርያማዊት ናት ወይም ከሰው ወገን አይደለችም ማለታችን ሳይሆን በአዳምና በሓዋን በኃጢአት መተላለፍ በሰው ሁለ ላይ ያለው የውድቀት ባሕርይ /fallen nature/  እርሱም መራብ ፣መጠማት ፣መድከም ፣መሞት እንደማንኛውም ሰው የሚስማማት ሲሆን ነገር ግን ከኃጢአት ሁለ ራሱዋን ጠብቅ የተገኘች ንጽሕት ናት ማለታችን ነው፡፡ በዙህም ምክንያት ነው ቅደሳን አባቶች ከኃጢአት በቀር ክርስቶስ የሰውን ባሕርይ ባሕርይው አደረገ ብለው ማስተማራቸው ፡፡ራሱም ጌታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም በነሣው ሥጋና ነፍስ ተርቧል ፥ደክሟል ፥መከራ ተቀብለል ፣ሞቷል ፡፡ራሱንም የሰው ልጅ ብሎ መጥራቱም የሰውንባሕርያትን ገንዘቡ እንዳደረገ ለማጠየቅ ነው፡፡ /ዮሐ.3፥14-15/ እግዚአብሔር አምላክ ሰው ሆኖ ሰውን ሉቤዤ በፈለገ ጊዛ በቅድስና ፣በንጽሕና ፣በታማኝነት ፣በትሕትና ፣እግዚአብሔርን ተስፊ በማድረግና በፍቅር በመመላለስ የመልካም ነገር ሁለ ግምጀ ቤት በመሆን እንደቅድስት ድንግል ማርያም ላላሴት አላገኘም ነበር፡፡እንዱህም ስለሆነ  “አንቺ ከሴቶች መካከል የተባረክሽ ነሽ /ለቃ.1፥28/ ብሎ ቅደሱ መልአክ መሠከረላት፡፡

 

ሲራክም “….ብቻዬንበአድማስ ዝርኩ በውቅያኖስም ዝርኩ በባህርም ማዕበል መካከል ተመላለስኩ…. ከዙህም በኋላ ዕረፍትን ፈለግሁ እንግዱህስ የማንን ሥጋ አዋሐዳለሁ …. በእርሱ ፈቃድ በከበረ በማርያም ማኅፀን ሥጋን ተዋሐድኩ በምኩራብም አስተማርኩ” /ሲራ.24፥1-10/ ብሎል፡፡ አባ ሕርያቆስም በቅዳሴው “እግዚአብሔር አብ በሰማይ ሆኖ ምስራቅንና ምዕራብን ሰሜንና ደቡብን ዳርቻዎችን ሁለ በእውነት ተመለከተ ተነፈሰ አሸተተም እንደ አንቺ ያለ አላገኘም የአንቺን መዓዚ ወደደ ደምግባትሽንም ወደደ የሚወደውን ልጁንም ወደአንቺ ሰደደ፡፡”ብሎ ከፍጥረታት ሁለ በቅድስና  የሚስተካከላት እንደላለ መስክሯል፡፡ ስለዙህም እኛም ቅድስት ድንግል ማርያም በእውነት ንጽሕት ፍጽምት ክብርት ናት ብለን እንመሰክራለን፡

እመቤታችን ንጽሕተ ንጹሕን ፣ቅድስተ ቅዱሳን ፣ከተለዩ የተለየች ፣ከተመረጡም የተመረጠች ፤መትሕተ ፈጣሪ ፣መልእልተ ፍጡራን ፣ከፈጣሪ በታች፣ከፍጡራን በላይ እየተባለች የምትመሰገን ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና አላት ።የወላዲተ አምላክ ንጽሕናና ቅድስና ልዩ ነው። ‹‹ከቅዱሳን ክብር የማርያም ክብር ይበልጣል ፤የአብን ቃል ለመቀበል በተገባ ተገኝታለችና መላእክት የሚፈሩትን ትጉኀን በሰማያት የሚያመሰግኑትን ድንግል ማርያም በማኀጸኗ ተሸከመችው ።ይህች ከኪሩቤል ትበልጣለች ፣ከሱራፌልም ትበልጣለች ፣ከሦስቱ አካል ለአንዱ ማደሪያ ሆናለችና። ›› እያሉ ላቃውንት ያመሰገኗትም ድንቅ ከሆነ ቅድስና ዋና ንጽሕናዋ የተነሣ ነው። /ውዳሴ ማርያም ዘረቡዕ ፤ራዕ .4፥ 7-9/። ኢትዮጵያዊው ላቅ ቅዱስ ያሬድም በምስጋናው ‹‹ጸጋን የተመላሽና የደስታ መገኛ ሆይ … ዓይኖቻቸው ስድስት ከሆኑ ከሱራፌል ግርማ የሚበልጥ የመወደድ ግርማ አለሽ ።እነዚያ ፊታቸውን ይሸፍናሉ። .. ከልጅሽ መለኮት ከሚወጣው እሳት ይድኑ ዘንድ ፣አንቺ ግን ለመለኮት ማደሪያ ሆንሽ የመለኮት ባሕርይም አላቃጠለሽም ።የእሳት ነበልባልን ተሸከምሽ ። ›› በማለት ንጽሕናዋን ከመላእክት ንጽሕና ጋር እያነጻጸረ እጹብ ድንቅ እያለ ያመሰግናታል።

የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና በቅዱሳን አንደበት ሲመሰገን ድንቅ ነው።መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ምልዕተ ጸጋ›› ቅድስት ኤልሳቤጥ  ‹‹የጌታዬእናት›› እያሉ ያመሰገኗት ምስጋና ድንቅ ነው ።ከሰው ወገን እንዲህ ያለውን ምስጋና የተቀበለ የለምና ።የእግዚአብሔር እናቱ የቅድስት ድንግል ማርያም የንጽሕናዋን የቅድስናዋን ድንቅነት ላቁ ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ‹‹ከቅዱሳን ሁሉ ክብር ይልቅ የማርያም ክብር ይበልጣል …›› ሲል በብዙ ምሳሌ ያመሰገናት ላቁ አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው  ‹‹በምን በምን ልመስልሽ›› በማለት ምሳሌ የታጣላት ድንቅ ንጽሕናና ቅድስና ያላት መሆኑን መስክሯል። የንጽሕናዋ የቅድስናዋ ምስክር ስሟ ድንቅ ነው። ማርያም ማለት በዕብራይስጥ ቋንቋ ፍጽምት ማለት ነውና። ለጊዜው መልክ ከደም ግባት ያላት ስለሆነ ውበቷ ድንቅ ነው። ‹‹ወዳጄ ሆይ ሁለንተናሽ ውብ ነው፤ነውርም የለብሽም። ›› እንዲል /መኃ.መኃ 4፥ 7/።ሔዋን ንጽሐ ጠባይ ሳያድፍባት እንደነበረችው በእግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ከጥንት ጀምሮ በጥንተ ተፈጥሮ ንጽሐ ጠባይ ሳያድፋባት ጥንተ አብሶ ሳይደርስባት ተጠብቃ የኖረች ድንቅ ናት። ነቢዩ ‹‹ንጉሥ ውበትሽን ወደደ›› ያለበት ምክንያቱ ከዚህ ድንቅ ንጽሕናዋ የተነሣ አይደለምን? ከአካላዊ ውበቷ ይልቅ ውስጣዊ ንጽሕናዋ ቅድስናዋ ምን ይደንቅ! የእመቤታችን ቅድስናና ንጽሕና አፍአዊ ብቻ አይደለም።ንጉሥ እግዚአብሔር የወደደው ውበት እመቤታችንንም ድንቅ የሚያሰኛት ሌላም አለ። ንጽሐ ሥጋ ፣ንጽሐ ልቡናና ንጽሐ ነፍስን አስተባብራ የያዘች ፍጽምት መሆኗ።ስለዚህ ከቅዱስ ዳዊት ጋር ሆነን በአማን ነኪር ነገሩ በእንቲ አኪ፣በእውነት በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው ልንላት ይገባል።

 

ዘላለማዊ ድንግል ነች

 

መጽሐፍ ቅዱስና ሌሎች የቤተክርስቲያን አባቶች ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል እንደሆነች አስረግጠው ይስተምራሉ፡፡ እርሱዋ ቅድመ ወሊድ፣ ጊዜ ወሊድ፣ድኅረ ወሊድ ድንግል ናት፤ ሃሳቡዋም ሰውነቱዋን ለእግዚአብሔር አምላኩዋ ቀድሳ በድንግል መኖር ነበር፡፡ ይህን ከንግግሩዋ ማረጋገጥ ይቻላል፡፡መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ለቅድስት ድንግል ማርያም “ ደስ ይበልሽ ጸጋን የሞላብሽ ሆይ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው፡፡… ማርያም ሆይ በእግዚአብሔር ፊት ጸጋን አግኝተሻልና አትፍሪ እነሆ ትጸንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ…” ባላት ጊዜ የሷ መልስ “ወንድ ስለማላውቅ ይህ እንዴት ይሆናል” ነበር፡፡/ሉቃ. 1፥27-36/ ይህም በድንግልና ለመኖር እንደቆረጠች ያስረዳናል፡፡ አግብታ ልጅ የመውለድ ፈቃዱ ቢኖራት ኖሮ መልአኩን ከማን? ብላ በጠየቀችው ነበር፡፡ በተጨማሪም ወንድ ስለማላውቅ ማለቷ ወደፊትም ወንድ ባለማወቅ በድንግልና ለመኖር ለእግዚአብሔር ስለተሳልኩ እንዴት ይሆናል? ማለቷ ነበር፡፡

ቅዱስ ገብርኤልም የእርሷ የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን መውለድ በተፈጥሮዋዊ ልማድ ሳይሆን፣ ያለወንድ ዘር በመንፈስ ቅዱስ ግብር እንደሆነና እናትም ድንግልም ሆና እንደምትቀጥል ከነገራት በኋላ ድንግል በመስማማቷ የእግዚአብሔርን ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስን በኅቱም ድንግልና ፀንሳ ወለደችው፡፡ ወደፊትም እም ወድንግል በመባል ትኖራለች፡፡ነገር ግን ቀደም ብሎ በእግዚአብሔር የተነገረው ቃል “በአንተና /በሰይጣን/ በሴቲቱ /በድንግል ማርያም በቤተክርስቲያን/ መካከል በዘርህና በዘሯ መካከል ጠላትነትን አደርጋለው” የሚለው ቃል /ዘፍ.3፥15/ ይፈጸም ዘንድ በተለይ ከሁለተኛው እስከ አምስተኛው መቶ ክፍለ ዘመን ውስጥ በድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግልና ላይ የተለያዩ መናፍቃን ተነሥተው ነበር፡፡ ለምሳሌ ያህል ቱርቱሊያን /160-220/ ሄልፊደስ  /ሄልቪደስ/  /383/ ጆቬንያን  /390/ ይገኙበታል፡፡ እነዚህም ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል አትባል ልጆችንም ወልዳለች እያሉ ያስተማሩ ናቸው ፡፡በአሁኑ ጊዜም የተነሡ አንዳንድ የፕሮቴስታንት እምነት አራማጆች ጥንት በሐሰተኛ ትምህርታቸው ቤተክርስቲያንን ያውኳት የነበሩትን ከሃዲያን ፈለግ በመከተል ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል አትባልም፣ ልጆችንም ወልዳለች እያሉ ያስተምራሉ፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ድንግልናን ከእናትነት ጋር እናትነትንም ከድንግልና አስተባብራ ይዛለች በመውለድ ክብር ላይ ድንግልናን በሥራና በሀሳብ ድንግል ሆና በመገኘታ ያለወንድ ዘር አምላክ ጸንሳ ወልዳለች ከዚህም የተነሳ ድንግልናዋ ዘለዓለማዊና ልዩ ሆኖ ተገኝታል። ሴቶች በሃሳብ ንጹህ ባይሆኑ በሥጋ ይነጹ ይሆናል እመቤታችን ግን በሃሳብም በሥጋዋም ድንግል ናት ለዚህ ነው መልአኩ ቅዱስ ገብርኤል ሲይበስራት:

 

ስለእመቤታችን ድንግልና በመጽሐፍ ቅዱስ በብዙ ቦታ ተጠቅሶ እናገኛለን።

  • በኢሳያስ 7:14"ስለዚህ ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ ፥ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።" ከዚያም በኃላ ባል አግብታ ልጆች ተውልዳለች አላለም ልጅ ተወልዳለች አለ እንጂ:: እንዲሁም

  • ሕዝቅኤል 44:1-2 " ወደ ምሥራቅም ወደሚመለከተው በስተውጭ ወዳለው ወደመቅደሱ በር አመጣኝ ተዘግቶም ነበር። እግዚአብሔርም፦ይህ በር ተዘግቶ ይኖራል እንጂ አይከፈትም ፥ሰውም አይገባበትም የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ገብቶበታልና ተዘግቶ ይኖራል። "ብሎ የአመቤታችንን ዘላለማዊ ድንግልና ይነግረናል: እመቤታችን ስለምን በምስራቅ ትመሰላለች ቢሉ የፀሐይ መውጫ ምሥራቅ ነው:: እመቤታችንም የአማናዊው የፀሐየ ጽድቅ የኢየሱስ ክርስቶስ እናት ነችና::

  • በተጨማሪም ደግሞ በማቴዎስ 2:16 ሰበአ ሰገል በመጡበት ጊዜ ጌታ ከተወለድ ሁለት አመት ሆኖት ነበር ማለት ነው:: ዮሴፍን የምታገባ ቢሆን ኖሮ ይህን ያህል አመት ባልጠቀች ነበር:: በግብጽ ስደት መልስም ያላገባች መሆንዋ በሚከተሉት ጥቅሶች ማወቅ ይቻላል::

  • ማቴዎስ 2:13 "...ሕጻኑን ከእናቱ ጋር " አለው እንጂ ሕጻኑን ከሚስትህ ጋር አላለውም:: እንግዲሁም በዚሁ ምዕራፍ ቁጥር  20 ላይ ዮሴፍን ከግብጽ ወደ እሥራኤል እንዲመለስ ሲነግረው  "ሕጻኑን እናቱንም..."ነው ያለው:: እጮኛ የሚለውን ስም እንካ ጌታችንን ከወለደች በኃላ አልተጠራችበትም::ይህ ሁሉ የሚያስረዳን ዮሴፍ እመቤታችንን እንዲጠብቅ እንጂ እንዲያገባት አለመሆኑን ነው:

  • እንዲሁም በዮሃ 19:26 "ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን አንቺ ሴት፥እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀመዝሙሩን እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀመዝሙሩ ወደቤቱ ወሰዳት።" ሌላ ልጅ ከእርሱ በስተቀር እንደሌላት የሚያስረዳ ነው::

  • ሰሎሞንም በመኃልየ መኃልይ 4:12 " እኅቴ ሙሽራ የተቈለፈ ገነት፥ የተዘጋ ምንጭ የታተመም ፈሳሽ ናት።" ብሎ የእመቤታችንን ዘለዓለማዊ ድንግልና ይነግረናል::

 

እመቤታችን ለዮሴፍ ለምን ታጨች?

ማቴ 1:20 እጮኛ የሚለው ቃል ለብዙ ነገር ይሆናል። ይኸውም:-

1.በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስና በምዕመናን መካከል ያለው አንድነት እጮኝነት ተብሎ ተገልጻል። 1ኛቆሮ11:23 "ለአንድ ክርስቶስ ላቀርባችሁ አጭቻችኃለሁ።"

2.ከጋብቻ ስርዓት በፊት የሚፈጽሙት ውል ቃልኪዳን መተጫጨት ይባላል።

3.አንድ ሰው ለትልቅ ሥር ሹመት ሲመረጥ እጩ ሰው ለሹመት የታጨ ይባላል።

4.ለክብር ለቅድስና መመረጥም መታጨት ይባላል። ይኸውም እግዚአብሔር ኢየሩሳለምን 1ኛ መቃ 12:35  "እኔ ለክብር አጭቼሽ ነበር አንቺ ግን ለዲያብሎስ ሆንሽ" ብላል።

 

ስለዚህ ቅዱስ ዮሴፍ የማርያም እጮኛ ተብሎ የተጠራው ጠባቂዋ አገልጋይዋ ለማለት ነው። ዮሴፍ እጮኛ የተባለበት ምክንያት:-

1ኛ. ዮሴፍ ከዳዊት ዘር ነውና ክርስቶስ በዮሴፍ የዳዊት ልጅ ተብሎ እንዲቆጠር። ማቴ1:16, ሉቃ2:4።

2ኛ. ሴት ልጅ ናትና ጠባቂ ስለሚያስፈልጋት እንዲጠብቃት ነው።

3ኛ.ከሰው ዘር ከሰው ወገን መሆና እንዲታወቅ ከሰማይ የመጣች ኃይል ናት እንዳይሉ ነው።

4ኛ. እንዲያገለግላት ተላኪዋ እንዲሆን ለምሳሌ በስደታ ጊዜ።ማቴ 13:19

5ኛ. ከመደብደብ እንድትድን /ተወግራ እንዳትገደል/ ነው።ዘኅ 5:19:23

ማጠቃለያ ከላይ በዝርዝር ለመመልከት እንደሞከርነው እመቤታችን ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል ናት፡፡ ለዚህም መጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ሆኖናል፡፡ ይበልጡኑ ግን ብናስተውል ለምሳሌ ሙሴ የእግዚአብሔርን ክብር በሲና ተራራ ላይ ተመልክቶት ዳሩን ትቶ በፍጹም እግዚአብሔርን እንደተከተለ ሐዋርያትም የዓለም መድኃኒት የሆነው ኢየሱስ ክርስቶስ ከጠራቸው በኋላ እነርሱም ጨርቄን ማቄን ትዳሬን ሳይሉ ስለ ለጌታ ለኢየሱስ ክርስቶስ ነፍሳቸውን እስከ መስጠት ደርሰው ሁሉን ትተው ከተከተሉት እንዴት የዓለም መድኃኒት የሆነውን ስሙም ፍቅር የሆነ ቅዱሳንን በፍቅሩ ማርኮ ሁሉን ጥለው እንዲከተሉት ያደረገ ኢየሱስ ክርስቶስን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያም እንዴት ወደሥጋዊ ግብር ተመለሰች ልንል እንችላለን? ዮሴፍስ የአምላክ ማደርያን፣ የቅዱሳን እናት፣ የመላእክት እኅት የሆነችውን ክብርት፣ ቅድስት ድንግል ማርያምን ለሌላ እንዴት ሲያስባት ይችላል? ይህንን መጽሐፍ ቅዱስም ሆነ የገዛ ሕሊናችን የማይቀበለው አመለካከት ነው፡፡ ስለዚህም እኛ መጽሐፍ ቅዱስና የገዛ ሕሊናችን እንደሚመሰክርልን ቅድስት ድንግል ማርያም ዘለዓለማዊ ድንግል ናት ብለን እናምናለን፡ ፡

 

እመቤታችን የአምላክ ነች

እመቤታችን ወላዲተ አምላክ ናት፡፡ይህ እንደምን ያለድንቅ ነው?! ወላጆች ሁሉ በዘመን የሚቀድሟቸውንና የሚከተሏቸውንም ሕፃናት ይወልዳሉ፡፡ የእመቤታችን እናትነት ድንቅ ነው፡፡ ከእናቱ ልደት አስቀድሞ የነበረውን አምላኳን ወልዳለችና፡፡ ‹ድንግል ፈጣሪዋን ወለደችዉ››  እንዲልሊቁ፡፡ በብሥራተ መልአክ የወለዱ ብዙ አንስት ቢኖሩም እመቤታችን የወለደችው በብሥራተ መልአክ፣ ምክንያተ ፅንስ የሆነ ዘርን ያለመቀበል /እንበለዘር/፣ ያለተፈትሖ ማኀጸን  /ድንግልናን ባለማጣት/ ነውና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ ‹‹ያለዘርዐ ብእሲ የወለደችው እናቱናት በሥጋ ከእርሷ መወለዱም እንደሴቶች መጽነስ ሥርዓት ልማድ አይደለም፡፡ ድንግል ቃልን በሥጋ ያለዘርዐ ብእሲ ወለደችው፡፡ ›› /ሃይ.አበው ዘቄርሎስ 70፥ 25/፡፡ ለዚህ ነው ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት ‹‹በአንቺ የተደረገው ነገር ድንቅ ነው›› ሲል ያመሰገናት፡፡ እግዚአብሔር የድንቅ ጥበቡ ማደሪያ አድርጓታልና፡፡

 

‹‹በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ›› /ሉቃ.119/፡፡ በማለት ድንግል ማርያምን እንደምትፀንስና እንደምትወልድ ያበሰረ መልአከ መበሥር ቅዱስ ገብርኤል ‹‹ይህ እንዴት ሊሆን ይችላል?››  ለሚለው የድንግል ማርያም ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ‹‹መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፡፡ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ፣ ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል፡፡ › ›  በማለት የአምላክ እናቱ መሆኗን መስክሯል፡፡ /ሉቃ.1፥35/ ፡፡ እናትነቷን ድንቅ የሚያደርገው ለልደቱ ዘር ያልቀደመውን ፣ሁለት ልደታት ያሉትን ጌታ መውለዷ ነው፡፡ ቅድመ ዓለም ያለ እናት የተወለደውን እመቤታችን ድኀረ ዓለም ያለአባት ወልዳልናለችና እናትነቷ ድንቅ ነው፡፡ ሊቁ አባ መቃርስ ስለዚህ ድንቅ እናትነት እንዲህ ብሏል፡፡

‹‹ከማይመረመር ልደቱ በኋላ ማኀተመ ድንግልናዋ አልተለወጠም፡፡ ስለዚህ ወላዲተ አምላክ እንደሆነች አመንን ፤ሕጻን ሆኖ ተወለደ በጨርቅም ተጠቀለለ በጎል ተጣለ፡፡ ይህን ጊዜ ተገኘ የማይባል ከአብ ከመንፈስቅዱስም ጋር የነበረ ያለ ለዘለዓለም እርሱ ዘመን ተቆጠረለት ጊዜ ተነገረለት እርሱ አንድ ወልድ ሲሆን በየጥቂቱ አደገ፡፡ ›› /ሃይ.አበው ዘመቃርስ  98*13/፡፡  እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በፍጹም ንጽህና ያጌጠች ፥ የከበረች፥ ከሰማይና ከምድር ፍጥረታት ሁሉ የላቀች ድንግልናን ከእናትነት እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ በሥራና በሃሳብ ድንግል የሆነች፥ በአጠቃላይ ከፈጣሪ ከእግዚአብሔር በታች ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የገነነች። ሱራፌልና ኪሩቤል የሚሰግዱለትንና የሚያመሰግኑትን፥ ሊነኩትና ሊዳስሱት የማይቻላቸውን እሳት መለኮት ኃያል ጌታ በማህጸኖ የተሸከመች ክብርት እናት ነች። ድንግል ማርያም እመቤታችን የወለደችው ኢየሱስ እርሱ አምላክ ነው። ቀድሞ በነብዩ ያለትንቢት ተነግሮ ነበር።

 

"ሕጻን ተወልዶልናልና ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙ ምድንቅ መካር ኃያል አምላክ የዘላለም አባት የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል ኢሳ 9:6 ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም በሮሜ 9:5 ከሰማይ ወርዶ ከድንግል የተወለደው የሁላችን ቤዛ ኢየሱስ እኛን ለማዳን ሰው ይሁን እንጂ እርሱ  "ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው አሜን" ይላልኢሳ 7:14    "ጌታ ራሱ ምልክት ይሰጣችኋል እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች፥ ወንድ ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ብላ ትጠራዋለች።" "የድንግሊቱም ስም ማርያም ነበረ።" ሉቃ 1:27 ስለዚህ እግዚአብሔር አምላክ የወደቀውን አዳም ለማዳን ከድንግል ማርያም ከሥጋዋ ሥጋን ከነፍስዋ ነፍስን ተዋህዶ ሰው ሆነ። ይህ ሰው የሆነው አምላክ ነው።

 

"ሕፃን ተወልዶልናልና ፥ ወንድ ልጅም ተሰጥቶናልና አለቅነትም በጫንቃው ላይ ይሆናል ስሙም ድንቅ መካር፥ ኃያል አምላክ፥ የዘላለም አባት፥ የሰላም አለቃ ተብሎ ይጠራል ።"ኢሳ 9:6 "እነሆ፥ ድንግል ትፀንሳለች ልጅም ትወልዳለች፥ ስሙንም አማኑኤል ይሉታል የተባለው ይፈጸም ዘንድ ይህ ሁሉ ሆኖአል፥ ትርጓሜውም።እግዚአብሔር ከእኛ ጋር የሚል ነው።"ማቴ 1:23 "መልአኩም እንዲህ አላት፦ ማርያም ሆይ ፥በእግዚአብሔር ፊት ጸጋ አግኝተሻልና አትፍሪ። እነሆም፥ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ፥ስሙንም ኢየሱስ ትዪዋለሽ ።እርሱ ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ፥ጌታ አምላክም የአባቱን የዳዊትን ዙፋን ይሰጠዋል ፤በያዕቆብ ቤትም ላይ ለዘለላም ይነግሣል ፥ ለመንግሥቱም መጨረሻ የለውም።" ሉቃ 1:30 "የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል?" ሉቃ 1:43 "የተባረከውን ተስፋችንን እርሱም የታላቁን የአምላካችንንና የመድኃኒታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን " ቲቶ 2:12 "ነገር ግን የዘመኑ ፍጻሜ በደረሰ ጊዜ እግዚአብሔር ከሴት የተወለደውን ከሕግም በታች የተወለደውን ልጁን ላከ ፤" ገላ 4:4 "ክርስቶስ በሥጋ መጣ፥እርሱም ከሁሉ በላይ ሆኖ ለዘላለም የተባረከ አምላክ ነው ፤ አሜን።" ሮሜ 10:9 "ከዚህም ሰው ዘር እግዚአብሔር እንደተስፋው ቃል ለእስራኤል መድኃኒትን እርሱም ኢየሱስን አመጣ። " ሐዋ 13:23 "የአብርሃምን ዘር ይዞአል እንጂ የያዘው የመላእክትን አይደለም። ስለዚህ የሕዝብን ኃጢአት ለማስተስረይ ፥ ለእግዚአብሔር በሆነው ነገር ሁሉ የሚምርና የታመነ ሊቀ ካህናት እንዲሆን፥ በነገር ሁሉ ወንድሞቹን ሊመስል ተገባው።" ዕብ 2:17 "የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህት ቆማለች። ልጄ ሆይ ፥ ስሚ እዪ ጆሮሽንም አዘንብዪ ወገንሽን ያባትሽንም ቤት እርሺ ንጉሥ ውበትሽን ወድዶአልና፥እርሱ ጌታሽ ነውና። የጢሮስ ሴቶች ልጆች እጅ መንሻን ይዘው ይሰግዱለታል ። የምድር ባለጠጎች አሕዛብ በፊትህ ይማለላሉ። " መዝ 45:9

 
 

እጮኛ : ሳይገናኙ

1. እጮኛ

በመጽሐፍ ቅዱስ ድንግል ማርያም ለዮሴፍ እንደታጨች ይናገራል ነገር ግን መናፍቃን እንደሚያስቡት ሳይሆን ከእነርሱ አስተሳሰብ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ምክንያቶችም አሉት ምክንያቶቹን እንደሚከተለው ቀርበዋል፡፡

1.ድንግል ማርያም ኃይለ አርያማዊት ወይም ከሰው ወገን አይደለችም ብለው አንዳንዳንድ የስህተት ትምህርት አራማጆች እንደሚነሡ እግዚአብሔር ስለሚያውቅ የእነዚህን የመናፍቃንን አፍ ለማዘጋትና ሰው እንደሆነች ለማመልከት እርሱ ባወቀ ለዮሴፍ እንድትታጭ አድርጓታል፡፡

ይህንን ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ በማለት ያብራራዋል፡፡ “And this Isaiah pointed to in his prophecy in the word behold the virgin (Is 7:14) while st. Gabrial is sent to her not simply to virgin but to virgin betrothed to a man, in order that by means of bretrothed man he might show that may was really a human being” ሲተረጎም  “ነቢዩ ኢሳይያስ በትንቢቱ  “እነሆ ድንግል ትፀንሳለች” ማለቱና ወንጌላዊው ምስለ ቅዱስ ገብርኤል ወደ ድንግል መላክ ሲያስተምር  “ከዮሴፍ ወደ ታጨች ከአንዲት ድንግል ተላከ”  ማለቱ  “እጮኛ”  በሚለው ቃል እርሱዋ ፍጹም ሰው መሆኑዋን ለማሳየት ነው”  ብሏል፡፡ በዚህም ምክንያት ቅድስት ድንግል ማርያም ከሰዎች ወገን ስለመሆኑዋ ለማስገንዘብ ሲባል እግዚአብሔር ባወቀ ለዮሴፍ ታጨች፡፡'

2.በመንፈስ ቅዱስ ግብር ጌታን በመፀነሷ ምክንያት ከአይሁድ አላዋቂነት የተነሣ ከሚመጣባት ከድንጋይ ውግረት ለመጠበቅ ዘዳ. 22፥20-21

3. በአይሁድ የዘር ሐረግ የሚቆጠረው በወንድ በኩል ስለሆነ በዮሴፍ አመካኝቶ /አስጠግቶ ወንጌላዊው የድንግልን የዘር ሐረግ ለመናገር ስለፈለገ ነው፡፡

4.ዮሴፍ ድንግል ማርያም ወደ ግብጽ በተሰደደች ጊዜ ጠባቂና አገልጋይ እንዲሆናት ሲባል ለዮሴፍ እንድትታጭ ሆናለች፡፡

በእነዚህ ምክንያቶች የተነሣ እግዚአብሔር ባወቀ ሄልፊደስና ግብረአበሮቹ እንደሚሉት ሳይሆን ድንግል ማርያም ለዘመዷ ዮሴፍ እንድትታጭ ሆናለች፡፡

5. ሳይገናኙ  /Before they came together/

መናፍቃን  “ሳይገናኙ” የሚለውን ቃል ይዞ ጌታን ከወለደች በኋላ ቃሉ እንደሚመሰክረው በግብር አውቋታል ብሎ ይከራከራል፡፡ ይህ ግን ፈጽሞ ስሕተት ነው፡፡ ወንጌላዊው እንዲህ ለማለት የፈለገው ጌታን የፀነሰችበትን ጊዜ ለመጠቆምና ከዚያም በኋላ ጋብቻ እንዳልተመሠረተ ለማስረዳት ነው፡፡ ቅዱስ ጀሮም ለዚህ መልስ ሲሰጥ በምሳሌ እንዲህ ብሏል፡፡  “Helvedius, Before he repent, was cut off by death” “ሄልፊደስ ንስሐ ከመግባቱ በፊት በሞት ተወግዷል፡፡”  ብንል ይህ ማለት  “ከሞተ በኋላ ንስሐ ገብቶአል” ማለትነውን ? አይደለም ነገር ግን ንስሐ ጨርሶ እንዳልገባ የሚያስረዳ ነው፡፡እንዲሁ ወንጌላዊው ሳይገናኙ (before they came together) ማለቱ ትጭጭቱ ወደጋብቻ እንዳልተቀየረ በተቃራኒው ግን ድንግል ማርያም በእናትነት ዮሴፍ ደግሞ በጠባቂነትና በአገልጋይነት በባል ሽፋን አብረው መኖራቸውን የሚያሳይ ነው፡፡  

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም ስለዚህ ጉዳይ ሲናገር  “ወንጌላዊው  “ሳይገናኙ”  ማለቱ ወደ ሙሽራው ቤት  /ጫጉላቤት/ ሳትወሰድ በፊት ማለቱ አይደለም፡፡ በእርግጥ ጌታን ከፀነሰች በኋላ ቅድስት ድንግል ማርያም ከዮሴፍ ቤት ኖራለች፡፡ ይህ ደግሞ አግብታዋለች ማለት ግን አይደለም ፡፡ ምክንያቱም የድሮ ሰዎች የታጨችላቸውን ድንግል በቤታቸው የመጠበቅ ልምድ ነበራቸውና ነው፡፡  /ዘፍ.19፥8-14/ የሎጥ አማቶች ከሎጥ ሴት ደናግላን ልጆች ጋር በአንድ ቤት እንደነበሩ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል”  ብሏል፡፡ ይህም ድንግል ማርያም ከዮሴፍ ጋር አብራ ኖራለች መባሉ ሌላ ትርጉም የሚያሰጥ አይደለም፡፡

የበኩር ልጅዋን እስክትወልድ ድረስ...

የበኩር ትርጉም

"የበኩር ልጅዋን ወለደች "የሚለው ቃል ብዙ ሰዎችን አሳስቶል ::ይህም ሊሆን የቻለው በተለምዶ የበኩር ልጅ የሚባሉ የግድ ተከታይ ያላቸው መሆን አለባቸው የሚል አስተሳሰብ በእያንዳንዱ ህሊና ስለተቀረጸ ነው:: መጽሐፍ ቅዱስ ግን የበኩርን ትርጉም ብዙሃኑ ከተረዳው ለየት ባለ አተረጋጎም ይተረጉመዋል:: እግዚአብሔር ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው:

ዘጸአት 13:1-2 "በእሥራኤል ልጆች ዘንድ ከሰውም ከእንሰሳትም ማኅጸንን የሚከፍት በኩር ሁሉ ለእኔ ቀድስልኝ የእኔ ነው :"

በመጽሐፍ ቅዱስ እንደተገለጸው በኩር የሚባሉት ለመጀመሪያ ጊዜ ከእናታቸው ማህጸን የወጡ መሆናቸውን እንጂ የግዴታ ተከታይ ሊኖራቸው እንደማይገባ ይገልጻል:: አንድም ብቻም ቢሆን የእናቱን ማህጸን ለመጀመሪያ ጊዜ ከፍቶ ከወጣ ተከታይ ባይኖረውም በኩር ነው:: የክርስቶስ በኩርና ግን በዚህ ብቻ የሚፈታ አይደለም:: ክርስቶስ በኩር መባሉ የእመቤታችንን ብቸኛ ልጅ መሆኑን ለመግለጽ ብቻም አይደለም:: ተቀዳሚ ተከታይ የሌለውን የአብ የባሕርይ ልጅ መውለዳዋን ለመግለጽ ወንጌላዊው ማቴዎስ "የበኩር ልጅዋን..."ብላል:: በተጨማሪም ክርስቶስ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በተለያዩ ቦታዎች ላይ በኩር ተብሎ ተጠርታል:: ጥቂቶችን እንመልከት:

ቆላስይስ 1:17 "...ከፍጥረት ሁሉ በፊት በኩር ነው: ሁሉ በእርሱና ለእርሱ ተፈጥሮአል: እርሱም ከሁሉ በፊት ነው" እዚህ ላይ በኩር የሚለው ቃል ተወዳዳሪ ላላቸው ነገሮች የሚጠቀስ ሆኖ ከቀረ በጌታን ፍጡር አድርጎ ከፍጡራን ጋር አነጻጽሮ እርሱ ከፍጥረታት በፊት ቀደም ብሎ የተፈጠረ ፍጡር ነው እንደማለት ይሆናል:: ይህ ደግሞ የክርስትናን ትምህርት ሥር መሰረት የሚያናጋ የተረፈ አርዮሳዊያን ትምህርት ስለሆነ ከቅድስት ቤተክርስቲያን እምነት ውጪ ነው:: አባባሉ የገባው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከፍጥረታት በፊት ያለ :ፍጥረታትንም አሳልፎ የሚኖር መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው መሆኑን ፈጣሪነቱን ለመግለጽ የተጠቀሰ ነው::

ዕብራውያን 1:6 "...በኩርን ወደ ዓለም ሲገባ"  እዚህም ላይ የክርስቶስ በኩር ተብሎ መጠራት አብ ተቀዳሚ ተከታይ የሌለው የባህርይ ልጁን ወደ መሬት ሂድ:  ውረድ ተወለድ : ሙት ተሰቀል ብሎ እንደላከው መግለጹ መሆኑ በክርስቶስ ክርስቲያን ተሰኝተናል የሚሉ ሁሉ የማይክዱት ነው ::እንግዲህ አብ በኩሩን ወደ ዓለም ሲልክ...ስለአለ በኩር የሚለው ቃል ተጠቅሳልና አብ ከክርስቶስ (ከወልድ) ሌላ ልጅ አለው ማለቱ ነውን?  ይህማ እንዳይባል ፍቁረ እግዚ ዮሐንስ በምዕ. 1:18 ላይ "መቼም ቢሆን እግዚአብሔርን ያየው አንድስንኳ የለም፤ በአባቱ እቅፍ ያለ አንድ ልጁ እርሱ ነገረን። "ብሎ ወልድ ብቻ የአብ የባህርይ ልጁ እንደሆነ አስረግጦናል::

እንግዲህ  "የበኩር ልጅዋን " መባሉ መጻሕፍት በኩር በኩር ብለው የተናገሩለት : ዓለም ከመፈጠሩ በፊት የነበረ : ዓለምና በውስጥዋ ያሉት ፍጥረታትን የፈጠረ: መጀመሪያና መጨረሻ የሌለውን አምላክ አዶናይ: ልዑል ባሕርይን ወለደች ለማለት ተፈልጎ ነው::

"እስከ............"

በሌላ አንጻር እስከን ተገን አድርገው  "እስክትወልድ ድረስ አላወቃትም " የሚለውን እስከን ፍጻሜ ላለው ነገር አስገብተው ከዚያ በኃላ በግብር አወቃት የሚል ትርጋሜ ቢሰጡትም : የተሳሳቱ መሆናቸው ራሱ መጽሐፍ ቅዱስ ይነግራቸዋል::  "እስከ " ፍጻሜ ላለው ነገር እንደሚገባ ሁሉ ፍጻሜ ለሌለው ነገርም ይገባል:: የሚከተሉት ከመጽሃፍ ቅዱስ የወጡ ሲሆኑ የ "እስከን" አገባብ ግልጽ ያደርጉታል::

2ኛሳሙ 6:23 "የሣኦል ልጅ ሜልኮል እስከ ሞተችበት ቀን ድረስ ልጅ አልወለደችም"  ይህ ማለት እስከ መቼም አልወለደችም ለማለት ነው እንጂ ከሞተች በኃላ ወለደች ለማለት አለመሆኑ ግልጽ ነው::

ኢሳያስ 22:14 "ይህም ነገር በሰራዊት ጌታ በእግዚአብሔር ጆሮ ተሰማ እስከ ሞቱም ድረስ ይህ በደል በእውነት አይሰረይላችሁም "ይላል::  ከሞቱ በኃላ ይሰረይላችሃል ማለት ይሆን? የዚህ ትርጉሙ ለዘለዓለም ለማለት ነው::

ሮሜ 4:14 "ከአዳም ጀምሮ እስከ ሙሴ ድረስ ሞት ነገሠ" ይላል:: ከሙሴ በኃላ ሞት ቀረ ማለቱ ነውን?አይደለም:: "ሞት ሆይ መውጊያ የታለ?" የተባለው ክርስቶስ ሞትን ድል አድርጎ ከተነሳ በኃላ ነው::

መዝሙር 110:1 "እግዚአብሔር ጌታዬን ጠላቶችህን ለእግርህ መረጋገጫ እስካደርግልህ ድረስ በቀኜ ተቀመጥ አለው ሲባል ጠላቶቹን ካሻነፈ በኃላ በቀኝ መቀመጡ ቀረ ማለት አይደለም ::ወደ ቆላስይስ ሰዎች በተላከው በሐዋርያው የጳውሎስ መልእት ምዕ 2:14-15  ጌታችን በመስቀሉ ድል የነሣ መሆኑ የተነገረ ሲሆን: በሐዋርያት ሥራ ምዕ 7:55 ላይ ደግሞ እስጢፋኖስ በመንፈስ ቅዱስ ተሞልቶ ጌታ ኢየሱስ በእግዚአብሔር አብ ቀኝ ሆኖ ያየው መሆኑን ተናግሮአል::  ይህም የሆነው ጌታ ጠላቶቹን ድል ከነሣ በኃላ በመሆኑ እዚህ ላይ የተጠቀሰው "እስከ" ፍጻሜ የሌለው እስከ ነው::

ማቴ 28:20 ላይ "እነሆ እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ" ያለው ከዓለም ፍጻሜ በኃላ ከእነርሱ ይለያል ለማለት አይደለም:: እስከ ዘለዓለም ድረስ ከእናንተ ጋር ነኝ ለማለት እንጂ::

ዘፍጥረት 8:7 "ቁራውን ሰደደው እርሱም ወጣ ውሃው ከምድር እስከ ሚደርቅ ድረስ ወዲያና ወዲህ ይል ነበር " ሲል ከደረቀ በኃላስ ወዲያና ወዲህ ማለቱን ተወ ማለቱ ነውን?

እንግዲህ ከላይ በተጠቀሰው መሠረት በማቴ 1:25 የተጠቀሰው ፍጻሜ የሌለው "እስከ" መሆኑን ያስረዳናል:: ስለዚህም ዮሴፍ እመቤታችንን እስከ ፍጻሜው በግብር አላወቃትም የሚል ትርጉምን ይሰጠናል::

አላወቃትም

“አላወቃትም” የሚለውን ቃል አንድ ትርጉም ብቻ ሰጥቶት ያስተምራል፡፡ነገር ግን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃላት መተርጎም የሚገባቸው እንደ ዐረፍተ ነገሩ ይዘት ነው፡፡ ለምሳሌ “የዐሥራ ሁለት ዓመት ልጅ በሆነ ጊዜ እንደ በዓሉ ሥርዐት ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ ቀኖቹንም ከፈፀሙ በኋላ ሲመለሱ ብላቴናው ኢየሱስ በኢየሩሳሌም ቀርቶ ነበር፤ ዮሴፍም እናቱም “አላወቁም” ነበር፡፡” /ሉቃ.2፥41-43/ የሚለው ቃል እንደ ሄልፊደስ ብንተረጉመው በቀጥታ ስህተት ውስጥ እንወድቃለን፤ ነገር ግን እንደ ዐረፍተ ነገሩ ይዘት ከተረጎምነው ትክክለኛ ፍቺ ይሰጠናል፡፡እንደዚሁ እስክ ትውልድ ድረስ አላውቃትም ማለቱ ድንግል ማርያም ጌታችንን ወልዳ የሰማይ መላእክት ሲያመሰግኑት፣ ሰብአ ሰገል እጅ መንሻ ይዘው ሲሰግዱለት፣ እረኞች የምሥራቹን ቃል ሰምተው ለምስጋና እስኪ ሲታደሙ ድረስ ዮሴፍ በነቢዩ የተነገረላት ድንግል እርሷ መሆኗን በቅጡ አልተረዳም ለማለት ፈልጎ ነው፡፡ እንዲህም ሲል እምነቱ ፍጹም ሆነለት ማለቱ ነው፡፡ ከመስማት ማየት ይበልጣልና ስለዚህም ወንጌላዊው “አላወቃትም” አለ፡፡

 

የጌታ ወንድሞችና እህቶች

የጌታ ወንድሞች

ሀ. “ገና ለሕዝቡ ሲናገር አነሆ እናቱና ወንድሞቹ ሊያነጋግሩት ፈልገው በውጭ ቆመው ነበር፡፡” /ማቴ.12፥46/

ለ. “ከዚህ በኋላ ከእናቱና ከወንድሞቹ ከደቀ መዛሙርቱ ጋር ወደ ቅፍርናሆም ወረደ፡፡” /ዮሐ.2፥12/

ሐ. “እንግዲህ ወንድሞቹ ደቀመዛሙርትህ ደግሞ የምታደርገውን ሥራ እንዲያዩ ከዚህ ተነሣና ወደ ይሁዳ ሂድ…. ወንድሞቹስ እንኳ አላመኑበትም ነበር /ዮሐ.7፥3-5/

መ.“ወደ ገዛ አገሩም መጥቶ እስኪገረሙ ድረስ በምኩራባቸው ያስተምራቸው ነበር፡፡ እንዲህም አሉ ይህ ጥበብና ተአምራት ከወዴት አገኘው? ይህ የፀራቢው ልጅ አይደለምን? እናቱስ ማርያም ትባል የለምን? ወንድሞቹስ ያዕቆብና ዮሳ ስምዖንም ይሁዳም አይደሉምን? እኅቶቹስ ሁሉ በእኛ ዘንድ ያሉ አይደሉምን?” /ማቴ.13፥54-55/

ሠ. “እነዚህ ሁሉ ከሴቶች እና ከኢየሱስ እናት ማርያም ከወንድሞቹም ጋር በአንድ ልብ ሆነው በጸሎት ይተጉ ነበር፡፡” /ሐዋ.1፥14/

ረ. “ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በከሐዋርያት ሌላ አላገኘሁም” /ገላ.1፥19/

ሰ. “ልበላና ልንጠጣ መብት የለንምን? እንደ ሌሎቹ ሐዋርያትና እንደጌታ ወንድሞች እንደ ኬፋም እኅታችንን ይዘን ልንዞር መብት የለንምን?”

መናፍቅን እነዚህ የጌታ ወንድሞች የተባሉት በትክክል የድንግል ማርያም ልጆች መሆናቸውን የሚያረጋግጡልን እነዚህ ናቸው ብሎ ከታች የተዘረዘሩትን ጥቅሶች ይጠቅሳል ፡፡እነዚህ ማርያም የያዕቆብና የዮሳ እናት እንደሆነች ይገልጻሉ ብሎ ይከራከራል፡፡

ሀ. “ኢየሱስን እያገለገሉ ከገሊላ የተከተሉት ብዙ ሴቶች በሩቅ ሆነው ሲመለከቱ በዚያ ነበሩ፡፡ ከእነርሱም መግደላዊት ማርያም የያዕቆብና የዮሶ እናት ማርያም የዘብዴዎስም ልጆች እናት ማርያምነበሩ፡፡” /ማቴ.27፥55-56/

ለ. “ሴቶችም ደግሞ በሩቁ ሆነው ይመለከቱ ነበር ከእነርሱም በገሊላ ሳለ የከተሉትና ያገለግሉት የነበሩ መግደላዊት የታናሹ የያዕቆብና የዮሳ እናት ማርያም ሰሎሜም ነበሩ፡፡ /ማር.15፥40-41/

ሐ. “ይህንንም ለሐዋርያት የነገሯቸው መግደላዊት ማርያምና የዮሳና የያዕቆብም እናት ማርያምከእነርሱ ጋር ነበሩ፡፡” ፡፡

መናፍቅን እነዚህን ከላይ የጠቀስናቸው ጥቅሶች መሠረት አድርጎ እንደሚለው ከሆነ ድንግል ማርያም በስቅለቱ ጊዜ ከነመግደላዊት ማርያም ጋር ነበረች፡፡ ወንጌላውያኑም እርሷን የያዕቆብና የዮሳ እናት ብለው ጽፈዋል፡፡ ይህም ድንግል ማርያም ሌላ ልጅ እንዳላት ማርጋገጫ ነው ብሎ ይከራከራል፡፡ የሚገርመው ግን እርሱ የሚረታበትን ወንጌላዊው ዮሐንስ የጻፈውን ሊጠቅስ አለመውደዱ ነው፡፡ ኃይለ ቃሉም  

“ነገር ግን በኢየሱስ መስቀል አጠገብ እናቱ ፣ የእናቱም እኅት የቀለዮጳም ሚስት ማርያም ፣ መግደላዊት ማርያም ቆመው ነበር” /ዮሐ.19፥25/ የሚለው ነው፡፡

በዚህ ጥቅስ ውስጥ ወንጌላዊው ድንግል ማርያምን እናቱ ብሎ ሲጠራት ከእርሷ ጋር ሌሎች ሴቶችም እንዳሉ ጠቅሶልናል፡፡ ከእነዚህም ሁለት ሴቶች መካከልም የድንግል ማርያም እኅት የምትባል የቀለዮጳ ሚስት የሆነች ማርያም የተባለች ሴት እንዳለች ገልጾልናል፡፡ ይህች ናት ታዲያ የያዕቆብ፣ የዮሳ፣ የይሁዳ እናት የተባለችው፡፡ ይህ ግልጽ እንዲሆንልን ከታች ያለውን ማብራሪያ በእርጋታ እናንብበው፡፡

ወንጌላዊው ማርቆስ የእልፍዮስን ልጅ ያዕቆብን ታናሹ ያዕቆብ ብሎ ይጠራዋል፡፡ /ማር.15፥40-41/ ይህም የዘብዴዎስ ልጅ ከሆነው ከዮሐንስ ወንድም ከሐዋርያው ያዕቆብ ለመለየት ብሎ የተጠቀመበት ቃል ነው፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ከሐዋርያት ጋር ለመገናኘት ወደ ኢየሩሳሌም በሄደ ጊዜ መጀመሪያ የተገናኘው ከታናሹ ያዕቆብ ጋር ነበር፡፡ ታላቁ ያዕቆብ ግን በጊዜው ሞቶ ነበር፤ ገዳዩም ሄሮድስ ነው፡፡ /የሐዋ.12፥2/

ቅዱስ ጳውሎስም “ከዚያ ወዲያ ከሦስት ዓመት በኋላ ኬፋን ልጠይቅ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቼ ከእነርሱ ጋር ዐሥራ አምስት ቀን ሰነበትኩ፤ ነገር ግን ከጌታ ወንድም ከያዕቆብ በቀር ከሐዋርያት ሌላ አላገኘሁም፡፡” /ገላ.1፥19/

በማለት የጌታ ወንድም የተባለውንና በቅዱስ ማርቆስ ታናሹ ያዕቆብ የተባለውን ሐዋርያ ብሎ መጥራቱን እንመለከታለን፡፡ እርሱን ቅዱስ ጳውሎስ ከነጴጥሮስና ከነዮሐንስ ጋር አዕማድ ብሎ መጥራቱንም እናስተውላለን፡፡

መጽሐፍ ቅዱስም ደግሞ ሁለት ያዕቆብ የሚባሉ ሐዋርያት እንዳሉ ገለጾ ጽፎልናል፡፡ /ማቴ.10፥3-5/ አንደኛው የዘብዴዎስ ልጅና የዮሐንስ ወንድም የሆነው ያዕቆብ ሲሆን ሌላኛው ደግሞ የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብ ነው፡፡ ከእነዚህ ውጭ ሌላ ያዕቆብ የሚባል ሐዋርያ የለም፡፡ሦስተኛ አለ የምንል ከሆነ ግን ቅዱስ ማርቆስ የጌታ ወንድም የተባለውን ያዕቆብን ከዘብዴዎስ ልጅ ያዕቆብ ለመለየት ሲል ታናሹ ያዕቆብ ማለት ባላስፈለገው ነበር፡፡ ታናሽና ታላቅ የሚሉት ቃላት ለሁለት እንጂ ለሦስት ነገር መለያነት አንጠቀምባቸውም፡፡ ስለዚህም በሐዋርያት ዝርዝር ውስጥ የተካተተው ፣ በቅዱስ ጳውሎስ ሐዋርያ የተባለው (ገላ.1፡19) የያዕቆብ አባት እልፍዮስ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ  "... የእልፍዮስ ልጅ ያዕቆብም፣.."(ማቴ.10፡3) በማለት ያረጋግጥልናል፡፡ የጌታ ወንድም ለተባለው ያዕቆብ አባቱ እልፍዮስ ከሆነ የእመቤታችን እኅት የተባለችው ፣በመስቀሉም ሥር የነበረችው የያዕቆብና የዮሳ የይሁዳም እናት የሆነችው ማርያም የተባለችው ለያዕቆብ እናቱ ናት ማለት ነው፡፡ /ማቴ.27፥55-56/ ወንጌላዊው ዮሐንስም ቀለዮጳ ያለው እልፍዮስን መሆኑን በዚህ ማረጋገጥ እንችላለን፡፡ አንድን ሰው ሁለትና ከዚያም በላይ ስም ሰጥቶ መጥራት ደግሞ በዕብራውያን ዘንድ ልማድ ነው፡፡ በዚህም መሠረት ቀለዮጳ የእልፍዮስ ሌላኛው ስሙ መሆኑን እናረጋግጣለን፡፡

        ለምሳሌ፡-

የሙሴ አማት የነበረው ራጉኤል ሌላ ጊዜ ዮቶር  /ዘጸ.18፥6፣ዘኁል. 10፥24/  ተብሎ ተጠርቶ እንመለከታለን፡፡

ንጉሥ ዖዝያን በሌላ ቦታ አዛርያስ ተብሎ ተጠርቷል፡፡

ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ ስምዖን ናኬፋ ተብሎ ተጠርቷል፡፡

• ቀናተኛው ይሁዳም ታዴዎስ ተብሎ ተጠርቷል፡፡

እነዚህን የመሰሉ ብዙ ምሳሌዎችን እንደማስረጃ ማቅረብ ይቻላል ፡፡በዚህ መሠረት መጽሐፍ ቅዱስም እንደሚያስረዳን የጌታ ወንድሞች የተባሉት የቀለዮጳ ወይም የእልፍዮስ እና የድንግል ማርያም እኅት የተባለችው ማርያም ልጆች ሲሆኑ ለጌታ ደግሞ የአክስት ልጆች እንደማለት ናቸው ፡፡ የአክስት ልጅን ደግሞ በአይሁድ ወንድም ብሎ መጥራት የተለመደ ነው፡፡ ይህም የአይሁድ እምነት ተቀብላ በነበረች በአገራችን የሚታይ እውነት ነው፡፡

መጽሐፍ ቅዱስ ዐራት ዓይነት ወንድምነት እንዳለ ይገልጽልናል፡፡

   ሀ.በመወለድ ወንድምነት

እንዲህ ዓይነት ወንድምነት ከአንድ እናትና አባት መወለድን በእናት ወይም በአባት አንድ መሆንን ይጠይቃል፡፡ ለምሳሌ ያዕቆብና ኤሳው /ዘፍ.4፥1-2/ ዐሥራ ሁለቱ የያዕቆብ ልጆች /ዘፍ.34፥23/ ሐዋርያው እንድርያስና ሐዋርያው ጴጥሮስ /ዮሐ.1፥4/ ወዘተ….. መጥቀስ ይቻላል፡፡

   ለ. የወገን ወንድምነት

ይህ ዓይነት ወንድምነት በወገን አንድ መሆንን ይጠይቃል፡፡ አይሁድ ከአንድ ከአብርሃም ወገን ስለሆኑ ወንድማማቾች ተብለዋል፡፡ ለምሳሌ፡-

“አንተም ወንድምህን ዕብራዊውን ወይም ዕብራዊቱን ብትገዛ ስድስት ዓመት ያገልግልህ” /ዘዳ.15፥12/

“የወንድምህ በሬ ወይም በግ ጠፍቶ ብታይ ቸል አትበል” /ዘዳ.15፥12/

“አምላክህ እግዚአብሔር የመረጠውን በላይህ ታነግሣለህ ከወንድሞችህ መካከል የሆነውን በአንተ ላይ ወገን ሰው በላይህ ንጉሥ ታደርግ ዘንድ አይገባህም፡፡ /ዘዳ.17፥15/

“በሥጋ ዘመዶቼ ስለሆኑት ስለወንድሞቼ ከክርስቶስ ተለይቼ እኔ ራሴ የተረገምኩ እንድሆን እጸልይ ነበር፡፡” /ሮሜ.9፥1-3/

ሐ. በሥጋ ዝምድና ወንድምነት

የቅርብ የሥጋ /የዘር/ ቁርኝት ካለወንድማማች ተብለው ይጠራሉ፡፡ ለምሳሌ፡-

ሎጥ የአብርሃም ወንድም ልጅ ነው፤ ማለትም አብርሃም ለሎጥ አጎቱ ነው፤ ነገር ግን ወንድሜ ብሎ ጠርቶታል፡፡ /ዘፍ.12፥3-5፣ 13፥8፣ 14፥14/

እንደዚሁ ሐዋርያው ታናሹ ያዕቆብ፣ ይሁዳ፣ ስምዖንና ዮሳ የእመቤታችን እኅት ለተባለችው ማርያም ልጆች በመሆናቸው ለጌታችን ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ወንድሞች ተባሉ ምክንያቱም የአክስት ልጆች ናቸው፡፡

መ. የፍቅር ወንድምነት

የፍቅር ወንድምነት መንፈሳዊ አንድነትን የሚጠቁም ነው፡፡ ለምሳሌ  

“ወንድሞች በሕብረት ቢቀመጡ እነሆ መልካም ነው ፡፡ እነሆም መልካም ፣ ያማረነው፡፡” መዝ.132፥1

“ስምህን ለወንድሞቼ እነግራቸዋለሁኝ፡፡ በጉባኤም መካከል አመሰግንሃለሁ ” መዝ.22፥22/

“ኢየሱስም ገና ወደ አባቴ አላረኩም፤ አትንኪኝ ነገር ግን ወደ ወንድሞቼ ሄደሽ እኔ ወደ አባቴና ወደ አባታችሁ ወደ አምላኬና ወደ አምላካችሁ አርጋለሁ ብለሽ ንገሪአቸው አላት” /ዮሐ.20፥1/

“አሁን ግን ወንድሞች ከሚባሉት አንዱ ሴሰኛ ወይም ገንዘብን የሚመኝ ወይም ጣኦትን የሚያመልክ ወይም ነጣቂ ቢሆን ከእርሱ ጋር እንዳትተባበሩ እጽፍላችኋለሁ” /1ኛቆሮ.5፥11/

 
 

የእመቤታችን አማላጅነት

 

ነገረ እግዚአብሔር በሚገባ ለሚያውቅና ለተገነዘበ ሰው የአማላጅነት ትምህርት የሚያስደንቀውና የሚያጠራጥረው ሊሆን አይገባም::  የአማላጅነት ትምህርት ከጊዜ በኃላ ድንገት የመጣ ሳይሆን በዘመነ ኦሪት በመጻሕፍተ ብሉያት በዘመነ ሐዲስ በመጻሕፍተ ሐዲሳት የነበረና አሁንም ያለና ወደፊትም የሚቀጥል ነው::

ያዕ 5:16 "ትፈወሱም ዘንድ እያንዳንዱ ስለሌላው ይጸልይ፤ የጻድቅ ሰው ጸሎት በሥራዋ እጅግ ኃይል ታደርጋለች።"

2ኛቆሮ 5:20 "በእኛም የማስታረቅ ቃል አኖረ። እንግዲህ እግዚአብሔር በእኛ እንደሚማልድ ስለክርስቶስ መልክተኞች ነን፤ ከእግዚአብሔር ጋር ታረቁ ብለን ስለክርስቶስ እንለምናለን።"

ቅዱሳኑ የመለመንና የማስታረቅ ስራ ብቻ ሳይሆን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለቅዱሳኑ በፍጡራኑ ላይ የመፈረድ ስልጣንም ሰጥቶአቸዋል

1ኛቆሮ 6:2 "ቅዱሳን በዓለም ላይ እንዲፈርዱ አታውቁምን?"

ማቴ 12:42 "ንግሥተ ዓዜብ በፍርድ ቀን ከዚህ ትውልድ ጋር ተነሥታ ትፈርድበታለች"

1ኛቆሮ 6:3 "የትዳር ጉዳይ ይቅርና በመላእክት እንኳ እንድንፈርድ አታውቁምን?"

ይህንን ሁሉ ከተመለከትን ዘንዳ ቅዱሳኑ ይህን ያህል ክብር ካገኙ የእመቤታችንማ ምን ያህል ይሆን እንድንል ያደርገናል:: ምክንያቱም እመ አምላክ የእግዚአብሔርን ቃል ለመቀበል በተገባ የተገኘች መልእልተ ፍጡራን በመሆና ነው::  ድንግልናን ከእናትነት እናትነትን ከድንግልና አስተባብራ በሥራና በሃሳብ ድንግል የሆነች፥ በአጠቃላይ ከፈጣሪ ከእግዚአብሔር በታች ከፍጥረታት ሁሉ በላይ የገነነች። ሱራፌልና ኪሩቤል የሚሰግዱለትንና የሚያመሰግኑትን ፥ሊነኩትና ሊዳስሱት የማይቻላቸውን እሳት መለኮት ኃያል ጌታ በማህጸኖ የተሸከመች ክብርት እናት ነች። የነብያት ትንቢታቸው:  የመላእክት እህታቸው፥ የጻድቃን የሰማዕታት እናታቸው ለደካሞች ለእኛ ብርታታችን መመኪያችን እማላጃችንና ተስፋችን ናት። እንግዲህ ምን እንላለን ፈጣሪ ይህንን ሁሉ ክብር የሰጣትን እኛ ምን ያህል ልናከብራት ይገባትሆን? ጌታችን በወንጌል እንዲህ ይለናል

ዮሐ 14:12 "በእኔ የሚያምን እኔ የማደርገውን ሥራ እርሱ ደግሞ ያደርጋል፤ ከዚህም የሚበልጥ ያደርጋል፥" ብሎ በማያልፈው ቃሉ ተናግሮአል እመቤታችን ደግሞ እንዲ ተብሎላታል

ሉቃ1:45  "ከጌታ፤ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብፅዕት ናት።"

ታዲያ እንግዲህ እመቤታችን እንዲህ ማድረግ ትችላለች እንዲህ ማድረግ ግን አትችልም ሊል የሚቻለው ማነው?

መጽሐፍ ውስጥ የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት ደግሞ በገሃድ የታየበት የቃና ዘገሊላ የሰርግ ቤት ነው ውኃው ወደ አማረ የወይን ጠጅ የተቀየረው በእርሷ አማላጅነት ነው።

ዮሃ 2:1-11 "በሦስተኛውም ቀን በገሊላ ቃና ሰርግ ነበረ ፥የኢየሱስም እናት በዚያ ነበረች፤ ኢየሱስም ደግሞ ደቀ መዛሙርቱም ወደሰርጉ ታደሙ። የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት። የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም፦አንቺ ሴት፥ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት። እናቱም ለአገልጋዮቹ። የሚላችሁን ሁሉ አድርጉ አለቻቸው። ኢየሱስም፦ጋኖቹን ውኃ ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሙሉአቸው አላቸው። እስከ አፋቸውም ሞሉአቸው።አሁን ቀድታችሁ ለአሳዳሪው ስጡት አላቸው፤ ሰጡትም። አሳዳሪውም የወይን ጠጅ የሆነውን ውሃ በቀመሰ ጊዜ ከወዴት እንደመጣ አላወቀም፤ ውኃውን የቀዱት አገልጋዮች ግን ያውቁ ነበር። ኢየሱስ ይህን የምልክቶች መጀመሪያ በገሊላ ቃና አደረገ፤ ክብሩንም ገለጠ፥ ደቀ መዛሙርቱም በእርሱ አመኑ።"

በተጨማሪም መጽሐፍ ቅዱስ የእመቤታችንን ክብር መጽሐፍ ቅዱስ እንዲይገልጻል

መዝ45:9  የንጉሦች ሴት ልጆች ለክብርህ ናቸው በወርቅ ልብስ ተጐናጽፋና ተሸፋፍና ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች።

የወርቅ ልብስ የተባለው ንጽሐ ሥጋ ንጽሐ ነፍስ ሲሆን ከጌታ ቀኝ በመሆን በእርሳ ለሚተማመኑ ለምኝልን ኃጢአታችንን አስትተሰርይልን ለምኝልን ለሚሉ የቃል ኪዳን ልጅቾ አማላጅ መሆንዋን ያሳያሉ:: ጌታችን በመልዕልተ መሰቀል ላይ ሆኖ ለወዳጁ ቅዱስ ዮሐንስ እነኃት እናትህ በማለት የሰጠውም ለዚህ ነው  

ዮሐ 19:27 "ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀመ ዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው። ከዚህም ሰዓት ጀምሮ ደቀ መዝሙሩ ወደቤቱ ወሰዳት።"

እንግዲህ ልበ አምላክ የተባለው ዳዊት

መዝ 129:5 "ጽዮንን የሚጠሉ ሁሉ ይፈሩ ፥ወደኋላቸውም ይመለሱ።

እንዳለ መንፈሰ ጽርፈት (ስድብ) አድሮባቸው ዲያብሎስ ሔዋንን ባሳተበት ምላስ በሐሰት ትምህርት የሚመሩ የቅዱሳንን የመላዕክትን የእመቤታችንን ስምና ቅድስና የሚያጎድፉ የጌታችንመ ለኮታዊ ብርሃን ሳይበራላቸው በሻማ ድንግዝግዝ የሚጋዙ በሽንገላ አንደበት በማመሳሰል የበግ ለምድ ተጀቡነው ውስጣቸው ግን ነጣቂ ተኩላዎች የሆኑ ተረፈ አርዮሳውያን መንፍቃን ሊያፍሩ ይገባቸውል ይልቁንስ ስህተትን አምኖ በንሰሐ መመለስ ከጥበብ ሁሉ የበለጠ ነውና ወደልባቸው እንዲመለሱ የሁላችንም ጸሎት ነው::

እኛ ግን የተዋህዶ ልጆች

መዝ 48:12 "ጽዮንን ክበቡአት፥ በዙሪያዋም ተመላለሱ፥ ግንቦችዋንም ቍጠሩ በብርታት ዋልባችሁን አኑሩ አዳራሽዋን አስቡ ለሚመጣው ትውልድ ትነግሩ ዘንድ።" እንደ ተባለን ጽዮን የተባለች እናታችን ማርያምን አንድም ቅድስት ቤተክርስቲያንን ከብበን ንጹህ ነገር ሃይማኖትን በመማር ራሳችንን ከሚነፍሰው የጥርጥር ክህደት ከሚወረውርው የኑፋቄ ቀስት ከሚሰነዝረው የክህደት ፍላጻ ሁሉ መጠበቅ መቻል አለብን የትውልድ ባላደራዎች ነንና:: ቅዱስ ጳውሎስ

ዕብ 13:9 "ልዩ ልዩ በሆነ እንግዳ ትምህርት አትወሰዱ ኢየሱስ ክርስቶስ ትናንትና ዛሬ እስከ ዘለዓለም ያው ነው::" በማለት እንዳስተማረን በአንዲት ርትዕት ሃይማኖት እንድንጎዝ እግዚአብሔር ይርዳን::

 

አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ አላት

 

"የወይን ጠጅም ባለቀ ጊዜ የኢየሱስ እናት።የወይን ጠጅ እኮ የላቸውም አለችው። ኢየሱስም፦አንቺ ሴት፥ከአንቺ ጋር ምን አለኝ? ጊዜዬ ገና አልደረሰም አላት።" የዮሐንስ ወንጌል 2፥4

ጌታ ለእመቤታችን አንቺ ሴት ከአንቺ ጋር ምን አለኝ አላት፤ ይህ ምግሩም የሆነ ሚስጢርን በውስጡ ይዟል; እስቲ ቃሉን ለሁለት ከፍለን እንየው፦

“አንቺ ሴት”፦

ይህን ቃል ለመጀመሪያ ግዜ የተጠቀመው አዳም ነበር። አዳም በግብረ ሥላሴ ከህቱም ድንግል መሬት  (ከአፈር) ተፈጠረ፤ ከባድ እንቅልፍ ተኝቶ ሳለ ከግራ ጎን ዐጥንቱ ሔዋን ተፈጠረች። አዳም ከእንቅልፉ ነቅቶ ሔዋንን ከጎኑ ቢያት

ዘፍ 2:23 “ይህች ሥጋ ከሥጋዬ ይህች አጥንት ከአጥንቴ ናት ሲል ሴት” አላት።

ጌታችንም እመቤታችንን ከሥጋሽ ሥጋ ከነፍስሽ ነፍስ ነስቼ ከአንቺ ተወልጄ ዓለምን ኹሉ አዳንኩ ሲል  “አንቺ ሴት” አላት።

አንድም አዳም ከህቱም ድንግል መሬት ወይም ከአፈር መፈጠሩ እመቤታችን በህቱም ድንግና ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም ከአዳም ጎን ዐጥንት ሲነቀል አዳም ህመም አለ መሰማቱ እመቤታችን ያለህመም ጌታን የመውለዷ ምሳሌ ነው። አንድም እግዚአብሔር አዳምን ከፈጠረ በኋላ ከእኛ እንደ አንዱ ሆነ አለ ፤ ይህም አዳምን ሳይሆን እመቤታችንን ነው;  እንዴት ቢሉ ወልድ “ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍሷ ነፍስ ነስቶ ከሶስቱ አካል አንዱ ስለሚሆን ነው”

“ከአንቺ ጋር ምን አለኝ”፦

መፅሐፉ አጋንንት ያምናሉ ይንቀጠቀጣሉም ይላል; ነገር ግን ጌታን  

ማቴዎስ 8:29 "በታላቅ ድምፅም እየጮኸ። የልዑል እግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ሆይ፥ከአንተ ጋር ምን አለኝ? እንዳታሠቃየኝ " “ከአንተ ዘንድ ምን አለን” አሉት፤አጋንንት ይህን ሲሉ ጌታን ንቀውት እንዳልሆነ ግልፅ ነው።

አንድም ሱናማዊቷ ሴት ልጇን ከሞት እንዲያስነሳላት ነብዩ ኤልዕን መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ  17:18 ጌታዬ ሆይ “ከአንተ ዘንድ ምን አለኝ” አለችው።

አንድም ዳዊት ልጁን አቤሴሎምን ሊገድሉበት ሲሉ እናንተ ሰዎች  “ከእናንተ ዘንድ ምን አለኝ”አላቸው።

ስለዚህም ከላይ ባየናቸው ማስረጃነት ከአንቺ ዘንድ ምን አለኝ ማለት የአክብሮት እንጂ የመናቅ ንግግር አለመሆኑ ግልጽ ነው።

ቅድስት ድንግል ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ

    ፩. በብሉይ ኪዳን

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በብዙ ቦታዎች በብዙ ምሳሌና በግልጽ የተነገረላት እመቤት ናት፤ በብሉይ ኪዳን ከተነገሩላት ምሳሌዎች መካከል ጥቂቶቹን ብቻ ከዚህ ቀጥሎ እንመለከታለን፦

ሀ. የመጀመሪያይቱ ምድር

እግዚአብሔር አምለክ በመጀመሪያ ምድርን ከፈጠረ በኋላ ለሰው ሕይወትን የሚሰጥ ፍሬ ያፈራችው ዘር ተዘርቶባት ሳይሆን እንዲሁ በቃሉ ብቻ መልካም የሆነውን ፍሬእ ንድታፈራ ይሁን ስላለ ነው። ዘፍ.፩፥፲፩ ቅድስት ድንግል ማርያምም ልጇን ኢየሱስ ክርስቶስን የጸነሰችውና የወለደችው፤ እውነተኛውን የሕይወት ፍሬ ያፈራችው በመልአኩ ቅዱስ ገብርኤል የብስራት ቃል ብቻ ስለሆነ የመጀመሪያይቱን ምድር ትመስላለች።

ለ.የኖህ መርከብ {ዘፍጥረት 7:1-24}

የኖህ መርከብ በመጽሐፍት ቅዱስ ውስጥ በቤተ ክርስቲያን ተመስላ ብትገለጽም አባቶች የእመቤታችንም ምሳሌ እንደሆነች ይናገራሉ። እግዚአብሔር በኖህ ጊዜ የነበሩትን ሰዎች በኃጥአታቸው ተቆጥቶ ሊያጠአቸው ሲያስብ ለኖህ መርከብ እንዲሠራ አዘዘው። ኖህም መርከብ ሠርቶ ገባ። እግዚአብሔርም ምድርን ውስጥ ውሃን በማዝነም በምድርን ላይ ያሉቱን ሰዎች አንድ ሳይቀሩ ፈጃቸው።ኖህን ግን መርከብዋን ምክንያት አድርጎ አዳነው ኖህ ሊድን የቻለው ከሠራት መርከብ ጥንካሬና ብቃት አለመሆኑ ከማንኛውም ክርስቲያን ያልተሰወረ ነው። እግዚአብሔር ምክንያት ይሻልና መርከብዋን ምክንያት አድርጎ የእግዚአብሔር ጥበቃ እንደሆነ የታወቀ ነው። እንግዲህስ ባይሆን ኖሮ ያን መአት እግዚአብሔር እንኮን የኖህ መርከብ ቀርቶ በአሁኑ ጊዜ በከፍተኛ ቴክኖሎጂ የተሠሩት ታላላቅ መርከቦችም ሊቆቆሙት አይችሉም። እንደዚሁም ጌታ የአዳምን ልጆች ሊያድን ሲሻ እመቤታችንን ምክንያት አድርጎ ከእርስዋ ተወለደ። ሁለተኛም የኖህ መርከብ በውስጥዋ ያሉትን ሰዎች ከመከራ ሥጋ እንዳዳናቸው ሁሉ እመቤታችንም በአማላጅነትዋ የሚያምኑትን ሰዎች ከሞት ሥጋና ከሞት ነፍስ ታድናቸዋለች። ከመርከብዋ ውጭ ያሉትን በንፍር ውሃ እንደጠፉ በእመቤታችን አማላጅነት የሚያምኑትም በሥጋም በነፍስም ለዘለዓለም ይጠፋሉ።

ሐ.በቀስተ ደመና

ከጥፋት ውሃ በኃላ እግዚአብሔር ዳግመኛ ምድርን በንፍር ውሃ እንዳያጠፋት ለኖህ ቃል ኪዳን ገባለት። የቃል ኪዳኑ ምልክትም ቀስተ ዳመና ነበር። እግዚአብሔርም ለኖህ የገባለትን ቃል ማጽናቱን ሊገልጽ ከአማናዊቶ ቀስተ ደመና ከእመቤታችን ተወለደ አስቀድሞ ነብዩ በመንፈስ ቅዱስ ተቀኝቶ ኢሳ 1:9 "እግዚአብሔር ዘርን ባያስቀርልን ኖሮ እንደሰዶም እንደገሞራም በመሰልንም ነበር" ሲል የእናት አማላጅ እውነተኛ መድህን እንደሆነልን ነገረን። ስለሆነም እግዚአብሔር በሃጥያታችን ተቆጥቶ እንዳያጠፋን የባህሪያችን መመኪያ የምትሆን እመቤታችንን ከጎኑ አደረገልን።

መ.ያዕቆብ ባያት በፍኖተ ሎዛ

{ዘፍጥረት 28:10-12}

እመቤታችን ያዕቆብ ሎዛ በተባለችው ሥፍራ በራዕይ ያያትን መሰላል ትመስላለች። መላዕክት ይወጡባትና ይወርዱባት ነበር። ጌታችን ከእመቤታችን ሰው ከመሆኑ አስቀድሞ ለተልእኮ አይወጡም አይወርዱም ነበር። ጌታ ከእመቤታችን ሰው ከሆነ በኃላ ግን ለተልእኮ የሚወጡና የሚወርዱ ሆነዋል። ሁለተኛም እርሳለ ቃል መውረድ ለሥጋ እርገት ምክንያት ሆናለችና አንድም አረገ መባሉ ከእርሳ የነሳው ሥጋ ነውና: አንድም ቅዱሳን ማረጋቸው ከእርሳ የነሳው ሥጋ በኩር አድርገው ነውና። እንዲሁም ከምድር አስከ ሰማይ እግዚአብሔር መንበር የምትደርስ በላይዋም መላዕክት ሲወጡባት እንደነበር እንዲሁ ደግሞ በቅድስት ድንግል እመቤታችን የአማላጅነት መሰላልነት የሰው ሁሉ ልመና ወደ ባሕርይ አምላክ ወደ እግዚአብሔር ይደርሳል።

ሠ.የጌድዮን ጸምር

{መጽ.መሳፍንት 6:36-40}

ለወቅቱ ጸምር የእሥራኤል ጠልየ ረድኤተ እግዚአብሔር ምሳሌ ነው። ጠሉ በጸምሩ ላይ መውረዱ አግዚአብሔር እሥራኤል በረድኤተ የመርዳቱ በዳርና በዳር ባለው መሬት ላይ አለመውረዱ ረድኤተ እግዚአብሔር አህዛብን የማይጠብቅና ከእነርሱ የራቀ መሆኑ ምሳሌ ነው። በሌላ በኩልም ጸምር የእሥራኤል ጠል የመቅሰፍቱ ምሳሌ ነው። ጠሉ ከጸምሩ ላይ አለመውረዱ እሥራኤል እግዚአብሔር ከመቅሰፍት ይጠብቃቸው የነበረበ መሆኑ በዳር ባለው ምድር ላይ መውረዱ እግዚአብሔር አሕዛብን በየጊዜው በመቅሰፍት ያጠፋ የነበረለ መሆኑ ምሳሌ ነው ።ፍጻሜው: ጸምር የእመቤታችን ጠል የጌታ ምሣሌ ሲሆን ጠል በጸምሩ ላይ መውረዱ ከሶስቱ አካላት አንዱ አካል ወልድ ከእመቤታችን ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ለመንሳቱ በእርሳ የማደሩ ምሳሌ ነው። ጠልበ ጸምሩ ዳር ባለው ምድር ላይ አለ መውረዱ አካላዊ ቃል ኢየሱስ ክርስቶስ በሌሎች ሴቶች ያለማደሩ ምሣሌ ነው ።ጠሉ በጸምሩ ላይ አለመውረዱ እመቤታችን ያለወንድ ዘር በድንግልና ጸንሣ በድንግልና የመውለድዋ ሲሆን በዳርና በዳር ባለው ምድር ላይ መውረዱ ሌሎች ሴቶች በዘርዐ ብእሲ በሩካቤ የመውለዳቸው ምሣሌ ነው። እንግዲህ እመቤታችን ከአንስት ዓለም ተለይታ ያለ ወንድ ዘር ያለ ሩካቤ ጸንሳ በመውለድዋ በጌድዮን ጸምር ተመስላለች

ረ. ዕጸሳቤቅ

እግዚአብሔር የአብርሃምን የእምነት ጽናት ለመለካት ልጁን ይስሐቅን ይሰዋለት ዘንድ አዘዘው፤ አብርሃምም አምላኩን እግዚአብሔርን በእውነትና በፍጹም ያመልክ ስለነበር የፈጣሪውን ትእዛዝ ሊፈጽም ወደ ሞሪያ ተራራ ልጁን ይስሐቅን ይዞ ወጣ ፤ ሰይፋንም መዝዞ ልጁን ይስሐቅን ለማረድ ሲዘጋጅ በእግዚአብሔር መልአክ እጅ የተያዘ በዕጸ-ሳቤቅ (ሐረግ) የታሰረ በግ እንዲሠዋ ይስሐቅን እንዳይገድል ከእግዚአብሔር ቃል መጣ ከዚያም በጉን ሰዋው ይስሐቅም ዳነ። ዘፍ. ፳፪፥፩-፲፫ በዚህ ታሪክ ውስጥ ብዙ ምሳሌዎች ተነግረዋል፤ ቅድስት ድንግል ማርያም የተመሰለችው በእጸ-ሳቤቅ (ሐረግ) ነው፤በበጉ ደግሞ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ በጉ በሐረጉ ታስሮ እንደተገኘ ኢየሱስ ክርስቶስም በእርሷ ማኅፀን ተወስኖ ሰው በመሆኑ በእጸ-ሳቤቅ ትመሰላለች።

ሰ. ሰላማዊት ርግብ

በኖኅ ዘመን በደረሰው የጥፋት ውሃ ኖኅና ቤተሰቦቹ ሊድኑ የቻሉት በመርከብ ተሸሽገው ነበር፤ከዚያም ለመውጣት የጥፋት ውሃው መድረቁንና አለመድረቁን ለማወቅ ርግብን ላኳት እርሷም በአፏ የቄጠማ ዝንጣፊ ይዛ ተመለሰች፤ ውሃውም እንደጎደለ አወቁ ከመርከቢቱም ወጥተው እንደገና ሰላማዊ ሕይወት መኖር ጀመሩ የላኳት ርግብ ይዛ የመጣችውና ያበሰረቻቸው ሰላምን ነው ጥፋት መወገዱን ነው፤ እንደዚህም ሁሉ እመቤታችን ይዛ የመጣችው ኢየሱስ ክርስቶስን ነው የሰላሙን መሪ ከሰይጣን እስራት የፈታንን ስለሆነም እርሷ በርግቧ፤ ልጇ ደግሞ በቄጠማው ይመሰላሉ።

ሸ. እጸ-ጳጦስ ዘሲና (የሲና ሐመልማል)

በኦሪት ዘጸአት ፫፥፩-፮ ላይ እንደተጻፈው ሙሴ በጎች በመጠበቅ ላይ እንዳለ በኮሬብ ተራራ ላይ ቁጥቋጦው በእሳት ሲነድ ነበልባሉ ሐመልማሉን ሳያቃጥለው አየ፤ እርሱም ወደዚያለ መቅረብ በፈለገ ጊዜ ከቁጥቋጦው ውስጥ የእግዚአብሔር ድምጽ ተሰማ፤ለሙሴም እንዲህ አለው፦ ወደዚህ ስፍራ ከመምጣትህ በፊት ጫማህን ከእግርህ አውጣ እኔ የአባትህ የአብርሃም የይስሐቅ የያዕቆብ አምላክ ነኝ ፤ሙሴም በፍርሃት ተውጦ ፊቱን ሸፈነ፤ ነበልባሉ ያላቃጠላት ያቺ የሲና ቁጥቋጦ ሐመልማል ምሳሌነቷ ለእመቤታችን ነው እሳተ መለኮት የሆነ ጌታ እግዚአብሔር ወልድን በማሕፀኗ ይዛለችና።

ቀ. የኤልሳዕ ማሰሮ

ኤልሳዕ መምህሩ ኤልያስ በእሳት ሰረገሎች ተነጥቆ በአውሎ ንፋስ ወደሰማይ ከወጣ በኋላ በኢያሪኮ ተቀምጦ ሳለ የከተማይቱ ሰዎች እንዲህ አሉ፥ እነሆ ጌታችን ሆይ የዚህች ከተማ ኑሮዋ ጥሩ ነበር ነገር ግን ውሃዋ መራራ ነው ያረገዙ ሴቶች ሲጠጡ ትይጨነግፋሉ፤ እርሱም አዲስ ማሰሮ አምጡልኝ ጨውም ጨምሩበት አላቸው። እነርሱም እንዲሁ አደረጉ ፤ እርሱም ወደውሃው ሄዶ ጨውን ጨመረበት፤ ከዚህ በኋላ እግዚአብሔር ይህንን ውሃ ፈውሶታል፤ ሞትና ጭንገፋ በዚህ ውሃ ምክንያት አይሆንም አላቸው። ፪ነገ፪፥፲፱-፳፩ በአዲስ ማሰሮ የተመሰለቸው እመቤታችን ነች፤ በጨው የተመሰለው ደግሞ ልጇ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ በመራራው ውሃ የተመሰለችው ደግሞ ይህቺ ዓለም ነች፤ ከማሰሮው የወጣው ጨው ውሃውን እንዳጣፈጠው ከድንግል ማርያም የተገኘው እግዚአብሔር ወልድ ዓለሙን ከመራራ ኃጢያት ታድጎታል ::

   ፪. በአዲስ ኪዳን

ሀ. የቅዱስ ገብርኤል ብስራት

“በስድስተኛው ወር መልአኩ ገብርኤል ናዝሬት ወደ ምትባል ወደ ገሊላ ከተማ ከዳዊት ወገን ለሆነ ዮሴፍ ለሚባል ወደ ታጨች ወደ አንዲት ድንግል ከእግዚአብሔር ዘንድ ተላከ”  ሉቃ. ፩፥፳፮ እርሱም “...ጸጋን የተመላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ...” እያለ በማመስገን አምላክን እንደምትወልድ አበሰራት በዚህ የቅዱስ ገብርኤል ብስራት ውስጥ ስለ እመቤታችን ድንግልናና ጸጋ የሞላባት ስለመሆንዋ፣ የምትወልደውም አምላክ ስለመሆኑና ይህም የሚሆነው ከመንፈስ ቅዱስ የተነሣ እንደሆነ መስክሯል።

ለ. የኤልሳቤጥ ሰላምታ

የዘካርያስ ሚስት  እርስዋም የመጥምቁ ዮሐንስ እናት ቅድስት ኤልሳቤጥ ወዳጇና ዘመዷ የሆነች ድንግል ማርያም ልትጠይቃት ወደ ቤቷ በሄደች ጊዜ የማርያምን የሰላምታ ቃል ስትሰማ በማኅጸኗ ውሰጥ ያለው ጽንስ ዘለለ፤ እርሷም (ኤልሳቤጥም) “የጌታዬ እናት ወደ እኔ ትመጣ ዘንድ እንዴት ይሆንልኛል? እነሆ የሰላምታሽ ድምጽ በጆሮዬ በመጣ ጊዜ ጽንሱ በማኅጸኔ በደስታ ዘሎአልና ከጌታ የተነገረላት ቃል ይፈጸማልና ያመነች ብጽእት ናት ” አለች።ሉቃ.  ፩፥፴፱-፵፭ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የጌታ እናት መሆኗን መንፈስ ቅዱስ ለኤልሳቤጥ ገለጸላትና የጌታዬ እናት አለች፤ በማኅጸኗም ያለው ጽንስ ከእርሱ በኋላ ለሚወለደው ለጌታውና ለእናቱ በደስታ ዘለለ /ሰገደ ራሷ ድንግል ማርያምም የመልአኩን ብስራት ከተቀበለች በኋላ  “ትውልድ ሁሉ ብጽዕት ይሉኛል” ሉቃ .፩፥፵፱ በማለት ተናግራለች። ስለዚህ ቅድስት ድንግል ማርያም በእግዚአብሔር የተመሰከረላት የሰው ልጆች የድኅነት መሠረት ናት፤ እኛም ጸጋን የተመላሽ ድንግል ሆይ ለምኝልን እያልን ዘወትር እንጠራታለን።

ሐ. የመስቀል ስጦታ

ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለሰው ልጆች ሲል በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ሳለ በወዳጁ በቅዱስ  ዮሐንስ አማካኝነት ለሰው ሁሉ የሰጠው ታላቅ ስጦታ እመቤታችንን ነው። ዮሐ. ፲፱፥፳፮-፳፯ ሰዎች ዛሬ በጌታችን የልደት ዘመን የተለያዩ ስጦታዎችን ይሰጣጣሉ፤ ለነፍስ የማይጠቅም አላቂ ሃላፊ ቁሳቁስ ይሰጣጣሉ፤ የሚኮነን ልምድ ባይሆንም ከጌታ የተሰጠችንን ታላቅ ስጦታ ግን ከሁሉ አስቀድሞ መቀበል ይገባል፤ እመቤታችን በልጇ ልደት ጊዜ አብራው ነበረች፤ በስደቱ ጊዜም አብራው የተንገላታችነች፤ በመጨረሻው ሰዓት በአስጨናቂው ጊዜ በመስቀሉም አጠገብ የተገኘች እርሷ ናት፤ ስለዚህ ለኛም ዘወትር የማትለየን እናታችን መሆኗን መረዳት ይገባናል።

 
 

ዕረፍቷ፣ትንሣኤዋና ዕርገቷ

መጽሐፍ ቅዱስን እና አዋልድ መጻሕፍትን ተጠቅመን ፅንሰቷን ነሐሴ 7፣ልደቷን ግንቦት 1፣ እረፍቷን ጥር 21፣ ትንሣኤዋንና ዕርገቷን ነሐሴ 16 ቀን ነው እንላለን፡፡ እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም በልጇ ዓርአያነት በሦስተኛው ቀን  (እሑድ ተቀብራ ማክሰኞ )ተነሥታ ወደሰማይ ዐርጋለች ፡፡ወንጌላዊው ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ላይ እንዳሰፈረው

“ታላቅ ምልክትም በሰማይ ታየ ፀሐይን ተጐናፅፋ ጨረቃ ከእግሮቿ በታች ያሏት አሥራ ሁለት ከዋክብት የሆነላት አንዲት ሴት ነበረች ” ራዕይ 12÷1 ፡፡

እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም ያረፈችው በ49  ዓ.ም ሲሆን ቅዱስ ዮሐንስ ደግሞ ይህንን ራዕይ የተመለከተው እርሷ ካረፈች ከብዙ ዓመታት በኋላ ነው፡፡ምን አልባትም እመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም እንደ አርዮሳውያን (መናፍቃን) አባባል ሞታ ቀርታ ቢሆን ኖሮ ቅዱስ ዮሐንስ በሥላሴ ዙፋን እንዴት ተመለከታት??? ያስተውሉ “ታላቅ ምልክት በሰማይ ታየ ” ነው ያለው :: በሰማይ ማለቱ እመቤታችን ሞትን ድል አድርጋ መነሣቷንና በሠማያት በክብር ዙፋን መቀመጧን ለመግለፅ ነው፡፡ ደግሞም ከርሷ ውጪ በእንዲህ ባለ ልዩ ክብር ያጌጠች ሴት በሠማያት የለችም !!! ምንም በማያሻማ መልኩ ቅዱስ ዮሐንስ በራዕዩ ድንግል ማርያምን ተመልክቷታል፡፡ በተጨማሪም

“በወርቅ ልብስ ተሸፋፍናና ተጐናፅፋ ንግሥቲቱ በቀኝህ ትቆማለች” መዝ 44(45)÷9 ::

በማለት የመንፈስ አባቷ ቅዱስ ዳዊት አስቀድሞ እንደ ተነበየ በክብር ተነሥታ በልጇ ቀኝ መቀመጧን ተናግሯል፡፡ እኛም እንናገራለን፤እንመሰክርማለን ! እንደገናም

‹‹ተንሥእ እግዚኦ ውስተ ዕረፍትከ፤ አንተ ወታቦተ መቅደስከ›› “አቤቱ ወደዕረፍትህ ተነሥ አንተና የመቅደስህ ታቦት ” መዝ 131(132)÷8 ይላል::

የዚህ የመዝሙረ ዳዊት አንድምታም ይህን ቃል እንዲህ ይተረጉመዋል፡- ‹‹አንተ›› ሲል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ሲሆን  ‹‹የመቅደስህ ታቦት›› ማለቱ ደግሞ አማናዊት ማደሪያውን ድንግል ማርያምን ነው ፡፡ ‹‹ወደ ዕረፍትህ ተነስ›› ሲል ደግሞ አማናዊት ማደሪያህ ከሆነችው ከእናትህ ከድንግል ማርያም ጋር ‹‹ ከሞት ››ተነሥ ማለቱ ነው፡፡ ምን አልባትም ይህንን ቃል ለታቦት እንጂ ለድንግል ማርያም አይደለም የሚሉ ወገኖች(መናፍቃን) ይኖራሉና ጥቂት ማስረዳቱ ተገቢ ነው፡፡ በእርግጥ ቤተክርስቲያናችን እንዲህ ዓይነት ምስጢር አዘል ቃላቶችን በመመርመር ለጊዜው እና ለፍጻሜው ለተለያዩ አካላት መነገሩን ታምናለች፣ ትመሰጥር ማለች፡፡ በመሰረቱ ሁለቱም (ታቦትና ድንግልማርያም)  የእግዚአብሔር ማደሪያዎች ናቸው፡፡ ነገር ግን በታቦትና በድንግል ማርያም መካከል የማይተመን (የማይለካ፣ የማይወሰን፣ የማይወዳደር) ልዩነት አለ፡፡ እግዚአብሔር በታቦት ላይ ቢያድር በመንፈስ ብቻ ነው !!! በድንግል ማርያም ላይ ያደረው ግን ‹‹በመንፈስም በሥጋም ››ነው!!! ይሄ  ልዩነት ከገባን ይሄ ቃል ለጊዜው ለታቦት፤ ለፍጻሜው ግን ለድንግል ማርያም መነገሩን ልብ ይሏል፡፡ እንደገናም የዳዊት ልጅ ሰሎሞን ትንሳዔዋን በገሃድ ሲመሰክር  ‹‹ወዳጄ ሆይ፥ተነሺ ውበቴ ሆይ፥ ነዪ›› በማለት በግልጽ ተናግሯል፡፡

‹‹ የድንግል ማርያም ትንሳዔ እና ዕርገት ማረጋገጫዎች  ››

1ኛ)ጌቴ ሴማኒ (የእመቤታች መካነ መቃብር) ባዶ መሆን፡፡

ለምሳሌ ከጌታችን ትንሳዔ ማረጋገጫዎች መካከል አንዱ የጎሎጎታ (የጌታችን መካነ መቃብር) ባዶ መሆን ሲሆን የእመቤታችን መካነ መቃብር ጌቴ ሴማኒም ባዶ ነው፡፡ ቅዱስ ሥጋዋ በቦታው የለም!!! ዛሬም ድረስ ከተለያዩ ዓለማት የሚመጡ ብዙ ምእመናን በቦታው እየተገኙ የድንግልን ትንሳዔ እየመሰከሩና እየተባረኩ ይገኛሉ፡፡ ቦታውንም በዶክመንተሪ ፊልም ለማየት እንደቻልኩት ብዙዎች እመቤታችን ተቀብራ በነበረበት ቦታ ላይ ስለት እየተሳሉ ላደረገችላቸው ተአምር ለክብሯ መግለጫ የሚሆኑ የተለያዩ ስጦታዎችን እና የብር ኖቶችን በመካነ መቃብሯ እያስቀመጡ ይሄዳሉ፡፡

2ኛ) በተለያዩ ጊዜአት እና ቦታዎች የድንግል ማርያም በአካል መገለጥ፡፡

ለምሳሌ በግብጽ ደብረ ቁስቋም፣ ዘይቱን ማርያም እንዲሁም በኢንዶኔዢያ፣ በኮትዲቯር፣ በኢራቅ እና በሌሎች አገራት ላይ ዛሬም ድረስ እየተገለጠች ለሕዝብ እና ለአሕዛብ በገሃድ ትታያለች ፡፡ +++ በዚህች ዕለት ይህ የእመቤታችን የቅድስት ድንግለ ማርያም ትንሳዔ የሚታሰበው (የሚከበረው) በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን በሌሎቹም እህት አቢያተ ክርስቲያናት (oriental church's) ጭምር ነው፡፡ ከዚህ ባለፈም የካቶሊክ ቤተ እምነትን ጨምሮ በሌሎቹም ‹‹ኦርቶዶክስ መለካውያን›› ተከታዮች ምዕርገቷን በማመን ይህችን ቀን ያከብሯታል ፡፡(ኦርቶዶክስ መለካውያን የሚባሉት እንደግሪክ እና ሩሲያ ኦርቶዶክስ አብያተ ክርስቲያናት ናቸው)፡፡

በመሠረቱ የድንግል ማርያም ትንሳዔ እና ዕርገት የሚያስደንቅ ነገር አይደለም! እንኳን የአምላክ እናት ቅድስተ ቅዱሳን ድንግል ማርያም ይቅርና ነቢየ እግዚአብሔር ኤልያስ እንኳ በእሳት ሠረገላ ወደ ሰማይ ዐርጐ የለም እንዴ? ጸሐፍተ ትዕዛዛት ሔኖክስ በሃይለ ነፋሳት ወደ ብሔረ ሕያዋን ተሰውሮ አይደል እንዴ? ኧረ እንደውም በሐዲስ ኪዳን ወንጌላዊው ዮሐንስ፣ጃንደረባው አቤላክባኮስ፣ቅዱስ ያሬድ እና ጻድቁ አቡነ አረጋዊ ዘደብረ ዳሞ ሞትን ሳይቀምሱ ተሰውረው አይደል እንዴ? ታዲያ የድንግል ማርያም ትንሳዔ የሚያስደንቀው ምኑ ላይ ነው?  ሞትን የሻረ ልጅ እያላት ሞት እርሷ ላይ ይሰለጥን ይሆን? ለነገሩ ክፋተኛና አመንዝራ ትውልድ ምልክትን ይሻል!(ማቴ 12፥38) አንድም ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹መቼም አይሁድ ምልክትን ይለምናሉ የግሪክ ሰዎችም ጥበብን ይሻሉ›› ብሎ እንደተናገረ የዛሬዎቹም መናፍቃን እንዲሁ በምልክት የታጠሩናቸው (1ኛቆሮ1፥22) ፡፡

የእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት ትውፊት ወይም የቤተክርስቲያንን ትውፊት የማትቀበሉ ከሆነ ለመሆኑ መጽሐፍ ቅዱስን ከየት አገኛችሁት? ማን ሰጣችሁ? ምዕራፍና ቁጥሩንስ ከየት ተቀበላችሁት? ነቢያት ሐዋርያት እንደጻፉትስ በምን ታረጋግጣላችሁ? በእነማንስ በኩል ተጠብቆ ደረሳችሁ? ለመሆኑ ተነሣች ዐረገችን ለመቀበል ከቸገራችሁ አልተነሣችም አላረገችምን ለምን አመናችሁት? የተነገረውንና ሲተላለፍ የኖረውን ለማመን የምትቸገሩ እናንተ ልብወላዳችሁን ለማመን የሚያፋጥናችሁ ማን ነው? መቼና እንዴት እንደተፈጸመ ወይም የዕረፍቷንና የአቀባበሯ ሌላ ትውፊት እንኳ ሳትይዙየነበረውን ለማቃለል ብቻ የሚያጣድፋችሁ እንዴት ያለ ክፉ መንፈስ ነው? እናንተ የተረጋገጠ ጽሑፍ ብቻ ነው የምንቀበልስ ካላችሁ ትንሣኤና ዕርገቷ የተመለከተውን ጽሑፍ ማን እንደጀመረው፣ እንዴት እንደተሸጋገረና እንዴት ስሕተት እንደሆነ ስለ ምን አልመረመራችሁም? ጥላቻ ጊዜ አይሰጥማ፤ክህደት የእውነተኛ ዐውቀት ጭላንጭል የለውማ፡፡እንግዲህ እናነተን በምን መርዳት ይቻል ይሆን? ትንሣኤዋና ዕርገቷ ለክርስቲያኖች ሊቀበሉት የማያስቸገረው ግን የተረጋገጠ ትውፊት በመኖሩ ብቻም አይደለም፡፡ትልቁና ዋናው ምሥጢር ያለው ደግሞ እመቤታችን  ‹‹ልዩ›› መሆኗ ላይ ነው፡፡ዕድገቷና ሕይወቷ ልዩ ነበር፡፡በእርሷ የተደረገው የአካላዊ ቃል ጽንስና ወሊድም እስካሁን ሊገልጹት ቀርቶ ሲያስቡትም ይከብዳል፡፡

አባ ሕርያቆስ በቅዳሴው ‹‹ ይህንም ባሰብኩ ጊዜ ኅሊናዬ የልጅሽን የባሕሩን ጥልቅነት ሊዋኝ ይወዳል፤ የወዳጅሽ የመሰወሪያው ማዕበልም ያማታዋል፡፡ ... አሁንም ገናንቱን አንመርምር፤ ጥልቅነቱንም አንጠናቀቅ፤የገናንቱን መጠን ለማመስገን የነቢያትና የሐዋርያት አንደበት የማይቻለው ነው››

እንዳለው ለማንም የሚቻል አይደለም፡፡ ለዚህ የታደለችው ነገሩን ሁሉ በልቧ ትጠብቀው የነበረችው እራሷ ድንግል እመቤታችን ብቻ ናት፡፡ ለዚህም ነው ቅዱስ ገብርኤልም ቅድስት ኤልሳቤጥም ‹‹ ልዩ›› መሆኗን አስቀድመው ምስጋናቸውን ያስከትሉላት፡፡ ታዲያ እመቤታችን ልዩ በሆነ መንገድ ከጸነሰችና ከወለደች ልዩ በሆነ መንገድስ የማትነሣው የማታርገው ለምንድንነው?  መነሣቷና ማረጓ አድሎ ያስመስላል የሚባለው በድንግልና ጸንሳ በድንግልና መውለዷን ስለምን አድሎ ነው አይባልም? ጽንሱ ልደቱ ሰለእርሱ ነው የምትሉ ከሆነስ ትንሣኤውና ዕርገቷ ምን የሚያረጋግጥ ይመስላችኋል?  የእርሱን ትንሣኤና ዕርገት ተሰርቆ ነው ሲሉ የነበሩ አይሁድ በእርሷ ትንሣኤና ዕርገት ሲያፍሩ ብዙዎቹም ከእነርሱ ወደ ክርስትና ሲመለሱ እናንተ ይህን ከማለት የማትመለሱ የክርስቶስን ትንሣኤም ሳታውቁ ታቃልላላችሁን? የእናንተ ክሳደ ልቡናበ እውነቱ እንደምን ከዚያ ዘመን አይሁድ ይልቅጸና? በውኑ አድሎን ለእመቤታችን ትንሣኤና ዕርገት የምትጠቅሱት በደብረ ታቦር በዓል ሙሴን ከሙታን ኤልያስን ከብሔረ ሕያዋን አምጥቶ ከደቀ መዛሙርቱ ሦስቱን ብቻ ይዞ መውጣቱንስ አድሎ ትሉታላችሁን? በእውነቱ ስንቱን ተመሳሳይ ታሪክ ልንጠቅስ ስንቱንስ ልናስታውሳችሁ እንችላለን? በእውነት የቀደሙትን አበው ትምህርትና ትውፊት እንዳትቀበሉ የእግዚአብሔርንስ የማይታወቅ መንገድ የደረሳችሁበት አስመስሎ ያሞኛችሁ ወይንም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው አዚም ያደረገባችሁ ማን ነው? የእመቤታችን ልዩ መሆን ካልገባችሁ በትንሣኤዋና በዕርገቷም ልዩ መሆኗን እንዴት ልትረዱ ትችላላችሁ? ማስተዋላችሁን የጋረደውን የስድብና የስም ማጥፋት ግብር ያሰደረባችሁን ከፉን መንፈስ ትቃወሙትና ከዚህም ነጻ ትወጡ ዘንድ በእውነት እግዚአብሔር ይርዳችሁ ከማለት በቀር ምን ልንል እንችላለን፡፡ድንግልማ በእውነት ተነሥታለች ዐርጋለችም፤ክብር ምስጋና ለተወደደ ልጇ ይሁን፤አሜን፤በረከቷም ይደረብን፡፡

 

ቤተክርስትያን ስለድንግል ማርያም ለምን ታስተምራለች?

 

ቤተክርስቲያናችን ለምን ስለእመቤታችን ዘወትር እንደምታስተምር አንዳንድ ሰዎች ግር ሲላቸው ይታያል፡፡ እንዲያውም ስለእመቤታችን ማስተማር ስለጌታችን እንዳታስተምር አድርጓታል ብለው የሚናገሩም አሉ፡፡ቤተክርስቲያናችን ግን ስለእመቤታችን ቅድስት ድንግል ማርያም የምታስተምረው ለርሷ ካላት ልዩ ፍቅር ብቻ ወይም ስለጌታችን የምታስተምረው አልቆባት አይደለም፡፡

በቅዳሴያችን፣ በዘወትር ጸሎታችን፣ በመዝሙራችን፣ በሥርዓታችን፣ በትውፊታችን፣ በአለባበሳችን ሳይቀር ስለኢየሱስ ክርስቶስ ትምህርት የሌለበት የለም፡፡ ሰዎች ዐረፍተ ዘመናቸው ደርሶ ወደመቃብር ሲሸኙ እንኳን በምናደርግው ጸሎተ ፍትሐት ለክርስቲያኑ በሚደረገው የቀብር ሥነ ሥርዓት ሁሉ ኢየሱስ ክርስቶስ ይሰበካል ይገለጣል፡፡

ቤተክርስቲያን ነገረ ማርያምን ዘወትር ለምእመናን የምታስተምረው ከነገረ ድኀነት ጋር የተያያዘ ጥልቅ ምሥጢር ስላለው ነው፡፡ ነገረ ድኀነትን ለመማር፣ ለመረዳትና ለማመን ነገረ ማርያም መሠረትና መቅድም ነው፡፡ ያለ ነገረ ማርያም ነገረ ድኀነት፣ ያለ መሠረት ቤት ማለት ነው ፡፡ጥቂት ምሳሌዎችን እንመልከት፡፡

   1. የሔዋን ካሣ

ሀ. እናታችን ሔዋን ምክንያተ ስህተት፣ ምክንያተ ሞት በመሆኗ ፍዳ መርገም ደርሶባት ነበር፡፡ያበላችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ከገነት የሚያስወጣ በመሆኑ ትውልድ ሁሉ ሲወቅሳት ይኖር ነበር፡፡ ዳግማዊት ሔዋን እመቤታችን ግን ምክንያተ ድኂን ሆነች፡፡የሰጠችን ፍሬ ሞትን የሚያመጣ ሳይሆን ተበልቶ ተጠጥቶ የዘላለም ሕይወት የሚያሰጥ ነው /ዮሐ6፡35/:: ትውልድ ሁሉ ሔዋንን ሲወቅስ ኖረ፡፡ እመቤታችንን ግን ትውልድ ሁሉ ያመሰግናታል  /ሉቃ 1፡48/:: ሶሪያዊው ቅዱስ ኤፍሬም በሐሙስ ውዳሴው  ‹‹ስለ… ሔዋን የገነት በር ተዘጋ ዳግመኛም ስለድንግል ማርያም ተከፈተልን፡፡ከዕፀ ሕይወት እንበላ ዘንድ አደለን ›› ብሏል፡፡

ለ. ሔዋን በዲያቢሎስ ተመክራ ኃጢአትን ጸነሰች፡፡ ሞትንም ወለደች፡፡ እመቤታችን ግን በሊቀመላእክት ቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ሕይወትን ፀነሰች፣ ትንሣኤን ወለደች /ሉቃ 1፡28-38/፡፡በሴት የመጣ ሞት በሴት ድል ተመታ፡፡ ‹‹እመቤታችንን የሔዋን መድኃኒቷ›› ያሰኛትም ይኼው ነው፡፡ይኼንን ድንቅ ምሥጢር ካልተረዳንና ካላመንን ሔዋን መካሥዋን፣የሴቶች ክብራቸው መመለሱን በምን ተረድተን እንዴትስ ልናምን እንችላለን?

    2. የአዳም ካሣ

ሀ. አዳም የተወለደው ከኀቱም ምድር ነው፡፡ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ምድር ሌላ ልጅ የላትም፡፡አዳምን ያስገኘችው በጥበበ መንፈስ ቅዱስ በፈቃደ ሥላሴ እንጂ ዘር አላስፈለጋትም፡፡ ያ በዚህ ግሩም ድንቅ ምሥጢር የተገኘ አዳም ግን ሞትን በራሱ ላይ በማምጣቱ ወደቀ፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወደዚህ ዓለም የመጣበትም አንዱና ዋነኛው ምክንያት ለቤዛ ዓለም ፣ለካሣ ዓለም ነው፡፡ይኸንንም በመዋዕለ ሥጋዌው በሠራውሥ ራ ሁሉ ገልጦታል፡፡ ጌታችን ሲወለድ ያለ ወንድ ዘር ፣ በግብረ መንፈስ ቅዱስ በኀቱም ድንግልና ከእመቤታችን ነው፡፡የእመቤታችንን ድንግልና ካልተቀበልን የመጀመሪያው አዳም ከኋለኛው አዳም ይበልጣል ማለት ነው ፡፡ያነሰው ደግሞ የበለጠውን ሊያድን እንዴት ይቻለዋል? እኛስ እንዲህ አናምንም፡፡ከኀትምት ምድር ተወልዶ የወደቀውን አዳም ያነሣው ዘንድ ያለ ወንድ ዘር ከድንግል ማርያም ተወለደ፡፡ ምድር ከአዳም በፊትም ሆነ በኋላ ሌላ ልጅ እንዳላስገኘች እመቤታችንም ከጌታችን በፊትም ሆነ በኋላ በድንግልና ኖረች፡፡በዚህም ዘላለማዊት ድንግል ትባላለች፡፡ልበ አምላክ ዳዊት ይኼንን በምሳሌ ሲያስረዳን፡- ‹‹እውነት ከምድር በቀለች ጸድቅና ሰላም ተስማሙ›› ብሏል (መዝ 85፡10-11)፡፡እውነት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው  /ዮሐ14፡6/፡፡እውነት የበቀለባት ምድር ደግሞ እመቤታችን ናት፡፡ጽድቅና ሰላም የተስማሙትም በልደተ ክርስቶስ ነው፡፡

ለ. አዳም የተገኘው መርገም ካልደረሰባት ምድር ነው፡፡ምድር መርገምን ያመጣችው በልጅዋ በአዳም በደል ነው፡፡ አምላክን የወለደች ቅድስት ድንግል ማርያምም በደል መርገም ያልደረሰባት ንጽሕት ቅድስት ናት፡፡አስቀድማ በደል /ጥንተአብሶ/ ነበረባት ካልን ከኋለኛው ምድር የቀደመችው ትበልጣለች ያሰኝብናል፡፡ይኸ ከሆነ ደግሞ አዳም በአዳም ተዋጀ ፣ተካሠ ወደ ክብሩ ተመለሰ ማለት አይቻልም ፡፡ያነሰው የበለጠውን ሊያከብረው አይችልምና፡፡ስለዚህም ቤተክርስቲያናችን እመቤታችን የአዳም ኃጢአት ያልደረሰባት ናት ብላ የምታስተምረው ርቱዕ እንደሆነ በዚህ ይታወቃል፣ እምነቷ እንደሌሎቹ አይጣላምና፡፡ የሌሎቹ ግን የሚናገሩትም ሆነ የሚጽፉት እርስ በርሱ የሚጋጭ ነው፡፡

    3. የሕያዋን እናት

አዳም ለሚስቱ የሕያዋን እናት ብሎ ስም አውጥቶ ነበር፡፡ ሔዋን ማለት የሕያዋን እናት ማለት ነውና  /ዘፍ 3፡20/ ፡፡ ነገር ግን የሕያዋን እናት በርግጥ አልነበረችም፡፡እርስዋም ልጆችዋም የሞት ባሮች ነበሩና፡፡ ‹‹ከአዳም እስከ ሙሴ ሞት ነገሠ ›› እንዲል (ሮሜ 5፡19)፡፡ታዲያ የሕያዋን እናት ማን ናት?

የሰው ልጅ በጥፋቱ እናትም አባትም አጥቷል፡፡ አባታችን አዳምና እናታችን ሔዋን ከገነት ተባረሩ፡፡ ለኛ ቤዛ መከታ ፣ አለኝታ ሊሆኑን ቀርቶ ለነርሱም አስፈልጓቸው ነበር፡፡ በዚህም ምክንያት ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአዳም ተገብቶ በሥጋ ብዕሲ መጣ፡፡ወንዶቹ እኛ ብቻ ተካስን የሔዋን ነገር ግን መና ቀረ እንዳይሉ እመቤታችንን መርጦና ቀድሶ አዘጋጀ፡፡አባትም እናትም ያጣው የሰው ዘር አባት አገኘ፡፡ ‹‹አባ አባት ብለን የምንጠራበት የልጅነት ጸጋ ተሰጠን››  እንዳለ ቅዱስ ጳውሎስ ‹‹አባታችን ሆይ›› በሉ የተባልነውም ይኸ ክብር ስለተመለሰልን ነው (ሮሜ 8፡15)፡፡ስለሔዋን ደግሞ የሕያዋን እናት ትሆነን ዘንድ እመቤታችንን አገኘን፡፡የሰው ልጅ ገነትንም እናቱንም ያጣው ባንድ ጊዜ እንደነበረው ሁሉ ገነትንም እናቱንም ያገኘው ደግሞ በአንድ ጊዜ ነው፡፡ እመቤታችን በጸሎታችን ብዛት፣ በቅድስናችን ብቃት ያገኘናት ሳትሆን ስለምታስፈልገን የተሰጠችን እናት ናት፡፡ይህም ጌታችን በመልዕልተ መስቀል የሚወደውን ደቀመዝሙሩን ቅዱስ ዮሐንስን ‹‹እነኋት እናትህ›› ባለው ጊዜ ታውቋል /ዮሐ 19፡27/፡፡ነቢዩ ዳዊትም አስቀድሞ ‹‹ሰው እናታችን ጽዮን ይላል››  ሲል ተናግሮላት ነበር  (መዝ 87፡5)፡፡ቤተክርስቲያናችን ነገረ ማርያምን አዘውትራ የምታስተምረው ያለጥርጥርና ያለነቀፋም የምታምነው ለድኅነት መሠረት መሆኑን ስላወቀች ነው፡፡ በሥዕሎቻችን፣ በጸሎታችን፣ በመጻሕፍቶቻችን፣ በዝማሬዎቻችን፣ በሥርዓታችንና በትውፊታችን ምስለ እመቤታችን የሚነሣው ለዚህ ነው፡፡

 

ኪዳነምህረት

ኪዳን የሚለው ቃል ‹‹ቃል›› ከሚለው ጋር እየተዜረፈ በብሉይ ኪዳን ለ280 ጊዜ ያህል ሲጠቀስ በአዲሰ ኪዳንደ ግሞ ከ32  ጊዜ በላይ ተጠቅሷል፡፡ ‹‹ኪዳን›› ቃሉ ‹‹ተካየደ›› ተማማለ፣ቃል ተገባባ ከሚለውየ ግእዝ ግሥ የተገኘ ነው፡፡ ‹‹ምሕረት›› የሚለው ቃል ደግሞ ማብራሪያ ሳያሻው ምሥጢሩ ከነዘይቤው ከግእዝ የተወረሰ ነው፡፡ስለዝህ ኪዳነምሕረት ማለት የምሕረት፣ የይቅርታ ውል፣ ስምምነት፣ መሐላ ማለት ነው፡፡ ኪዳን ከተራ ውሎችና ስምምነቶች የበለጠ ጽኑና ቀዋሚ ነው፡፡ ከፍ ያለ ክብደትም አለው፡፡

‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አድርጋለሁ›› ተብሎ በዳዊት መዝሙር እንደተጻፈ እግዝአብሔር ከመረጣቸው ቅዱሳኑ ሁሉ ጋር ቃልኪዳን አድርጓል፡፡ ወደፊትምያደርጋል፡፡ (መዝ 88.3) ቃልኪዳኑም የምሕረት ቃልኪዳን ነው፡፡

በቅዱሳን አበውና በቅዱሳት እማት እናቶች ታሪክ፣ ገድልና ድርሳን እንደምናነበው እግዝአብሔር ለቅዱሳን ከመሞታቸው አስቀድሞ ይገለጥላቸውና የምሕረት ቃልኪዳን ይሰጣቸው ነበር ፡፡የእግዝአብሔር የምሕረት ቃል ኪዳን በቅዱሳኑ ሕይወት ዘሪያ ብቻ የሚያተኩር አይደለም፡፡ለስማቸው፣ ለመስቀላቸው፣ ለልብሳቸው ገድላቸውን ከትቦ ለያዘ መጽሐፍ፣ አልፎ ተርፎም ለረገጡትና አፈርና ለተጋደለበት ቦታ ሁሉ ተርፎላቸዋል፡፡ ስለዝህ ልዩ ልዩ ቃልኪዳን የተገባላቸው ቅዱሳት መካናት ሞልተዉናል፡፡

ለቅዱሳን ከሞትአ ስቀድሞ የእግዝአብሔር መገለጥ ወይም የሚሞቱበትን ጊዜና የአሟሟታቸውን መንገድ ገልጦ መንገር በቅዱሳት መጻሕፍት የተለመደ ነው እንጂ እንግዳ ነገር አይደለም፡፡ ጌታ ለቅዱስ ጴጥሮስ እንዳት ባለ አሟሟት እንደሚሞት ነግሮታል፡፡  (ዮሐ 21.19 2ጴጥ 1.14) ቅዱስ ጳውልም ስለሚሞትበት ጊዜ ተነግሮታል፡፡ (የሐዋ20.25 የሐዋ21.10-13) ‹‹ከሞቱ አስቀድሜ እገለጥለታለሁ›› እንዱል፡፡ (ሰኔጎልጎታ) እግዝአብሔር ከሞታቸው አስቀድሞ በመገለጥ ለቅዱሳን የምሕረት ቃልኪዳን የሚሰጣቸው በእነርሱ በጎ ሥራ ከእነርሱ በኋላ ያለ የሰው ልጆችን ለመጥቀም ፈልጎ ነው፡፡ ተጠቃሚዎቹ ራሳቸው ናቸው እንዳይባል ወደ ሞት አፋፍ የተጠጉ ከመሆናቸውም ባሻገር ለቃልኪዳን የበቁት የሚጠቀሙበት በጎ ሥራ በመሥራታቸው ነው፡፡ የሰው ልጆች ያለፉ ቅዱሳንን በመዘከር የቃልኪዳናቸው ተጠቃሚ ሲሆኑ ቅዱሳኑ ግን ከመታሰብ በቀር በሰው በኩል የሚያገኙት ምንም ጥቅም የለም፡፡ ቅዱሳን የምሕረት ቃልኪዳን ሲቀበሉ ለወገናቸው መትረፋቸውን ያመለክታሉ፡፡

የምሕረት ቃልኪዳን ለምን ያስፈልጋል ቢባል ሕግ መተላለፍ ካለ ሁልጊዜ ተጠያቂነት ወይም ቅጣት ይኖራል፡፡ይህም በአዳም ይታወቃል፡፡የሰው ልጆች ደግሞ ከተጠያቂነት ነጻ የሚያደርግ ፍጽምና ይዘው አይገኙም፡፡በዝህ ምክንያት ቅጣት እንዳያገኛቸው የሚድኑበትን በርካታ መንገድች እግዝአብሔር አዘጋጀ ፡፡ከእነዝህም ውስጥ አንደ የምሕረትቃልኪዳንነው፡፡

የምሕረት ቃልኪዳን ሁሉ በጎ እንድንሠራ የሚያበረታታ ነው፡፡ይህም ዘወትር ከቃል ኪዳኑ ጋር ተያይዘው በሚቀመጡ ግዳታዎች ይታወቃል፡፡ ለበጎ ሥራ ምክንያት የማይሆን ባድ የምሕረት ቃልኪዳን የለም፡፡ ‹‹ስምሽን (ስምህን) የጠራውን፣ ዝክርያዘከረውን፣ የተራበያበላውን፣ የተጠማያጠጣውን፣ የታረዘ ያለበሰውን፣ እንግዳ በስምህ (በስምሽ) የተቀበለውን፣ ገድልህንያነበበውን፣ የሰማውን፣ የተረጎመውን ወዘተ ኃጢአቱን ይቅር እለዋለሁ፣እምረዋለሁ››

የሚሉ ቃልኪዳናት በሙሉ ከባደ መልካም ሥራ ባይቻለን እንኳን ቀላሉን መሥራት እንዳለብን ግዳታ የሚጥሉ ናቸው እንጂ አንዳንድቸ እንደሚያስቡት መልካም እንዳንሠራ የሚያሳንፉ አይደሉም፡፡ ከዝህ ይልቅ ለበጎ ሥራ የሚያነሣሡና የታዘዘትን መሥራት ያልተቻላቸውን ሰዎች ተስፋ ሳይቆርጡ እስከ መጨረሻው ሰዓት የሚድኑበት መንገድ እንዳለ አውቀው የተቻላቸውን እንዱያድርጉ የሚጠቁሙ ናቸው፡፡

የእግዝአብሔር ቸርነት ከአእምሮ በላይ ነው፡፡ ይህም ሰዎች በእግዝብሔር ቸርነት ላይ በሚያነሡት ጥያቄ ይታወቃል፡፡ ለምሳላ፡ እግዝአብሔር በዜና ገድላቸው እንደምናነበው ለብዘ ቅዱሳን ‹‹እስክአሥር ፣ሠላሳ ፣ሃምሳ አምስት ወዘተ ትውልድ ድረሰ እምርልሃለሁ›› እያለ የምሕረት ቃልኪዳን ሰጥቷቸዋል፡፡ ይህን በማንበብ እምነት የጎደላቸው አንዳንድች  ‹‹ይህ እንዳት ይሆናል?›› እያሉ ይጠይቃሉ፡፡ ይህ ብቻ በራሱ የፈጣሪ ቸርነት ከሕሉና በላይ መሆኑን አያስረዳም?

ፈጣሪ ስለፈራጅነቱና ስለመሐሪነቱሲናገር ‹‹በሚጠሉኝ እስከ ሦስተኛና አራተኛ ትውልድ ድረስ የአባቶችን ኃጢአት በልጆች ላይ የማመጣ ለሚወደኝ ትእዚዜን ለሚጠብቁ እስከ ሺህ ትውልድ ድረስ ምሕረትን የማደርግ እኔ እግዝአብሔር አምላክህ ቀናተኛ አምላክ ነኝ፡፡›› ይላል፡፡ (ዘጸ20.2-6)

ይህ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እስከ ሺህ ትውልድ የሚደርስ የእግዝአብሔርን ምሕረት በመናገሩ በአዋልድ መጻሕፍት ላይ ያለው የሠላሳና የሃምሳ ትውልድን ምሕረት የሚያወሳው ኃይለ ቃልሉስ ተባበል አይቻልም፡፡ያን ማክፋፋት ይህን የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል እንደመቃወም ይቆጠራልና፡፡

ዓለም ከተፈጠረች ሰባት ሺህ አምስት መቶ ዓመት ገደማ ሉሆናት ነው፡፡የሰው ልጅን አማካይ እድሜ እጅግ አሳንሰን በመቁጠር የአንድ ትውልድ ዘመን ሠላሳ ዓመት ነው ብንል እንኳን ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ ያለው ትውልድ ከሁለት መቶ ሃምሳ አይበልጥም፡፡ በዝህ ዓይነት ደግሞ እስከ ዓለም ፍጻሜም ብንቆጥርና ብናሰላም የትውልድ ቁጥር እንኳን አንድ ሺህ ሉደርስ ወደ አምስት መቶምአ ይጠጋም ፡፡ነገር ግን ፈጣሪ የሚወደውና ትእዚዘን የሚጠብቅ እውነተኛ ሰው ከተገኘ ያን ያህል ትውልድ አይኖርም እንጂ ‹‹እስከ ሺህ ትውልድ›› ድረስ እንኳን ይቅር ሉል ቃልኪዳን ገብቷል፡፡ይህ የሚያሳየው የእግዝአብሔርን የቸርነት ስፋት ነው፡፡ሺህ ትውልድ ስለላ ለእግዝአብሔር ሺህ ትውልድ ሉምር አይችልም አይባልም፡፡ከዝህ አንጻር የፈጣሪን ቃልኪዳን ከመሐሪነቱ አንጻር እንጂ ከተፈጻሚነቱ አንጻር ሉመለከቱት አይገባም፡፡ፈጣሪ ለቅዱሳኑ በየዕለቱ ብዘ ነፍሳትን ከሲዖል እንዱ ያወጡ የምሕረት ቃልኪዳን ሉሰጣቸው ይችላል፡፡ የተሰጣቸውም ቅዱሳን አሉ፡፡ ነገር ግን ተፈጻሚነቱን ስንመለከት በቀን የተባለውን ያህል ነፍሳት ከሲዖል ሉወጡ ወይም አንድም ነፍስ ከሲዖል ላትወጣ ትችላለች፡፡ ይህ ግን በተገባላቸው ቃልኪዳን ላይ ምንም ዓይነት አሉታየለውም፡፡ ምክንያቱም ለቅዱሳኑ ይህ ቃል ኪዳን ሲሰጥ ሲዖል ካለችው ነፍስ ደግሞ የሚጠበቅ ነገር ይኖራልና፡፡ ያን የምታሟላ ነፍስ ካልተገኘች ቃልኪዳኑ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡ ይህም በመሆኑ ቃልኪዳኑ ከንቱ ነው አይባልም፡፡ከላይ እንዳየነው ተፈጻሚ ሉሆን ባለመቻሉ ብቻ ለሺህ ትውልድ የተገባው ቃልኪዳን ከንቱ ነው ሉባል አይቻልምና፡፡

‹‹ከመረጥኳቸው ጋር ቃልኪዳኔን አደርጋለሁ›› ባለው መሠረት ጌታ ከእመቤታችን ጋር ብዘ ቃልኪዳን አድርጓል፡፡ እርሷ የተመረጠች ብቻ ሳትሆን ከተመረጡትም ሁሉ የተመረጠች ናትና፡፡ ከቅዱሳን ሁሉ እመቤታችን ድንግል ማርያም በሁሉም ረገድ እንደምትበልጥ ከተሰጣቸውም የምሕረት ቃል ኪዳን ለሷ የተሰጣት ኪዳን በእጅጉ ይበልጣል፡፡ በዝህም ምክንያት ድንግል ማርያም በተሰጣት ቃልኪዳን ተለይታት ታወቃለች፡፡ማለትም ትጠራበታለች ኪዳነምሕረት ትባላለች፡፡ስለዝህ የኃጥአን ሁሉ ዓይን የእርሷን የምሕረት ቃልኪዳን ተስፋ ያደርጋል፡፡

4901 W Indian School Rd

Phoenix, AZ 85031

(602) 328-0992

  • Facebook Social Icon