top of page
  • ክብረቅዱስመስቀል

    • ክርስቶስበመስቀሉ

    • ለቅዱስመስቀልክብርይገባል

    • ማማተብ

    • መስቀልመሳለም (መሳም)

    • በመስቀልመባረክ

    • ማዕተብ

    • መስቀልየአባታችንገዳይነው? እንዴት?

ክርስቶስበመስቀሉ

·       

  1. ቅዱስ መስቀል ስንል ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከሞተ ኃጢአት ለማዳን በቀራንዮ የተሰቀለበት የተመሳቀለ ዕጽ ማለታችን ነው። መስቀል ለክርስቲያኖች የሕይወትና የድኅነት ምልክት ነው። ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዓለሙን ከኃጢአትና ከሞት ለማዳን በቀራኒዮ የተሰቀለበትን ዕፀ መስቀል ከሌላው መስቀል የሚለየው ቅዱስ መሆኑ ነው። ይህም መስቀል ቅዱስ መስቀል ይባላል ድኅነትን አግኝተንበታልና ስለዚህም የድህነት ምልክት ነው። የነጻነታችን አርማ አድርጎ መመኪያችን መዳኛችን ትምክህታችን አድርገን እንይዘዋለን። ነገር ግን ከዚያን በፊት መስቀል የእርግማን ምልክት የኾነ የወንጀለኞች መቅጫ ነበር።


"በእንጨት ላይ የተሰቀለ በእግዚአብሔር ዘንድ የተረገመ ነው "ዘዳ 21:23 
"በእንጨት የሚሰቀል ሁሉ የተረገመ ነው ተብሎ ተጽፎአልና ክርስቶስ ስለእኛ እርግማን ሆኖ ከሕግ እርግማን ዋጀን፤ "ገላ 3:13 

  1. መስቀል የክርስቶስ ምልክት ነው:: ጌታችን ስለዓለም መጨረሻ ሲናገር "የሰው ልጅ ምልክት በሰማይ ይታያል" ብሎአል የሰው ልጅ ምልክት የተባለ መስቀል መሆኑን ዮሐንስ አፈወርቅ እና ቅዱስ ቄርሎስ ዘኢየሩሳሌም አስተምረዋል:: ማቴ 24:30 

  2. ጌታችን በትምህርቱ መስቀልን ከክርስቲያኖች ሕይወት እና ጉዞ ጋር አያይዞ አስተምሮአል "ማንም ሊከተለኝ የሚወድድ ቢኖር መስቀሉን ተሸክሞ ይከተለኝ" ማቴ 16:24 "ማንም መስቀሉን ተሸክሞ በኃላዬ የማይመጣ ደቀመዝሙሬ ሊሆን አይችልም" ሉቃ 14:26 

  3. ጌታችን ከሙታን በተነሳ ጊዜ በመቃብሩ አካባቢ የነበሩት መላእክት ጌታችንን የጠሩት በመስቀሉ ነው "እናንተስ የተሰቀለውን  ኢየሱስን እንድትሹ አውቃለሁ" ማቴ 28:5 

  4. ሐዋርያትምጌታችንንበመስቀሉይገልጡትነበር
    "ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት: እኔም ለዓለም ከተሰቀልኩበት ከጌታችን መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ገላ 6:14 

  5. በመስቀል ስናማትብ የእግዚአብሔርን የማዳን ሥራ እንመሰክራለን:: በኒቂያ ጉባኤ በ325 ዓም በተወሰነው መሠረት ከግንባራችን ወደ ሆዳችን ስናማትብ የጌታችንን ከሰማየ ሰማያት ወርዶ ከድንግልማርያም መወለዱን: ከግራ ወደ ቀኝ ስናማትብ ደግሞ ከሲዖል ወደ ገነት እኛን ማስገባቱን እንመሰክራለን::

  6. "በእንጨት ምክንያት ለዕዳ ተሰጠን: በእኝጨትም ምክንያትም ከዕዳችን ነጻ ሆንን" በማለት ቅዱስ ሄሬኔዎስ እንዳስተማረው መስቀል ከዕዳ ነጻ የሆንንበት ነው::

  7. በብሉይ ኪዳን ሕዝበ እሥራኤል ከአማሌቃውያን ጋር በሚዋጉ ጊዜ ሙሴ እጁን ዘርግቶ በመስቀል አምሳል ቆሞ ነበር
    "ሙሴ እጁን ባነሳ ጊዜ እሥራኤል ድል ያደርግ ነበር: እጁን ባወረደ ጊዜም አማሌቅ ድል ያደርግ ነበር" መስቀል በሙሴ እጅ በምሳሌው ይህንን ያህል ኃይል ከነበረው በክርስቶስ ደም ከተዋጀ በኃላማ አማናዊውማ እንዴት ታላቅ የሆነ ኃይል አያደርግ:: ዘጸ 17:16 

  8. "እግዚአብሔር በከተማይቱ በኢየሩሳሌም መካከል እለፍ: በመካክልዋም ስለተሰራው ርኩሰት ሁሉ በሚያለቅሱና በሚተክዙ ሰዎች ግምባር ላይ ምልክት ጻፍ አለው" በአማርኛ "ምልክት"  የተባለው በግሪኩ "tau" የተባለው ምልክት ነው:: ይህም በእንግሊዘኛው የ "ተ" ቅርጽያለው ምልክት ነው:: ሕዝ 9:4 

  9. ጣት የመንፈስ ቅዱስ ምሳሌ ነው:: በሉቃስ ወንጌል 11:20 ላይ 
    "እኔ ግን በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን የማወጣ ከሆንኩ" ያለውን የማቴዎስ ወንጌል ግን በእግዚአብሔር መንፈስ" ብሎታል ማቴ12:28 እኛም በጣታችን ስናማትብ በመንፈስ ቅዱስ ኃይል ሰይጣንን ድል ለመንሳት ማማተባችን ነው::

  10. አስቀድሞ ልበ አምላክ ዳዊት "ከቀስት ፊት ያመልጡ ዘንድ ለሚፈሩህ ምልክትን ሰጠሃቸው " መዝ 59:4 ብሎ የተናገረለት ከዲያብሎስ ቀስት የምናመልጥበት ምልክት መስቀል ነው::
    ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀሉ ላይ ባፈሰሰው ቅዱስ ደሙ ሰላምን አወጀ:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ስለዚህ ታላቅ ምስጢር ሲናገር:-
    ቆላ 1:18  "በመስቀሉ ደም ሰላም አደረገ በሰማያትም በምድርም ላሉት እርቅን: ሰላምን አደረገላቸው"

ጌታችን በመስቀሉ ጠላት ዲያቢሎስን እንደገደለ ማለት እንዳሸነፈና ተለያይተው የነበሩትንም ሕዝብንና አሕዛብን አንደ ማድረጉን አስመልክቶ በሌላው መልእክቱ ሲናገር:-

ኤፌ 2:13 "አሁን ግን እናንተ በፊት ርቃችሁ የነበራችሁ በክርስቶስ ኢየሱስ ሆናችሁ በክርስቶስ ደም ቀርባችኋል: እርሱ ክርስቶስ ሰላማችን ነው: እርሱ ሁለቱን ያዋሐደ: የትእዛዙንም ሕግ (ሕዝብንና አሕዛብ የመባል ትእዛዝ) ሽሮ በመካከል የነበረውን የጥል ግድግዳ በሥጋው አፈረሰ: ይኅውም ከሁለታችሁ አንድ አዲስ ሰውን ይፈጥር ዘንድና ሰላምንም ያደርግ ዘንድ: ጥልን በመስቀሉ ገደለ: በእርሱም ሁለታችሁን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር አስታረቀን: መጥቶም ርቃችሁ ለነበራችሁትና ቀርበው ለነበሩትም ሰላምን ሰጣቸው" ማለት ነው::


ከዚሁ በላይ እንደተመለከትነው ጌታችን ስለ ዓለሙ ቤዛ የተሠዋበት ቅዱስ መስቀል ክቡር ነው: ጠላትዲያብሎስን ያሸነፈበት ቅዱስ መስቀል ክቡር ነው: በደሙ በከበረው ቅዱስ መስቀል ለምድራውያንና ለሰማያውያን ሰላም አውጆአል:: ሐዋርያው እንዳለው: ቅዱስ መስቀል የሰላምን የደኅንነት ንጉስ የሆነው የኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ነው:: በእግዚአብሔር አብ ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስስ ለሰው ሁሉ ሞትን ይቀምስ ዘንድ ከመላእክት ይልቅ በጥቂት አንሶ (በሞተአንሶ) የነበረውን ከሞት የተነሣ የምስጋናን ዘውድ (አክሊለ ስብሐት) ጭኖ (ደፍቶ) እነሆ እናየዋለን" ዕብ 2:8-9

ስለዚህ ቅዱስ መስቀል ንጉስ ስብሐት ክርስቶስ (የምስጋናን ንጉስ ክርስቶስ) የተሰዋበት: ክርስቶስ አምላካችን በቅዱስ ደሙያከበረውና መለኮታዊ ደሙም የፈሰሰበት ስለሆነ በአማን (በእውነት) ክብር: በእውነት ቅዱስ ነው:: በመሆኑም በእውነት ክርስቶሳውያን የሆን ሁሉ በጌታችንና በክቡር መስቀሉ እንመካለን:: ሐዋርያው ጳውሎስ ሲያስተምር

ገላ 6:14 "እኔስ ጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ" ብሎአል:: በዚሁ መሠረት የክርስቶስ ተከታይ ነኝ የሚል ሁሉ ክርስቶስን ከልብ ማመንና መውደድ: መስቀሉንም ማክበር ይገባዋል:: እንደ ሐዋርያው እንደ ቅዱስ ጳውሎስም በክርስቶስ መስቀል መመካት ግዴታ ነው::

2ጴጥ 2:24 "ለኃጢአት ሞተን ለጽድቅ እንድንኖር፥ እርሱ ራሱ በሥጋው ኃጢአታችንን በእንጨት ላይ ተሸከመ፤ በመገረፉ ቁስል ተፈወሳችሁ። እንደ በጎች ትቅበዘበዙ ነበርና፥ አሁን ግን ወደ ነፍሳችሁ እረኛና ጠባቂ ተመልሳችኋል።
ቆላ 2፥14 "በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።"
ኤፌ 2፥16 "ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው።"
ቆላ 1:20 "...በመስቀል ባፈሰሰው ደሙም ሰላምን አደረገ"
1ኛቆሮ 1:18 "የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። "
ፊል 3:18 "ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶቹ ሆነው ይመላለሳሉና፤ ብዙ ጊዜ ስለእነርሱ አልኋችሁ፥ አሁንም እንኳ እያለቀስሁ እላለሁ። "

ለቅዱስ መስቀል ክብር ይገባል

 

"ወደ ማደሪያዎቹ እንገባለን እግሮቹ በሚቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን።"መዝ 132:7 
በዘባነ ኪሩብ ላይ የቆሙት እግሮቹ የሰውን ልጅ ለማዳን ተቸንክረው የዋሉበት የመድኃኒተ ዓለም ኢየሱስ ክርስቶስ ዙፋን ነውና የአክብሮት ስግደትን አንሰግድለታለን። እናከብረዋለን መስቀልን በብዙ ምክንያት እናከብረዋለን። በአጠቃላይ መስቀል:-


1ኛ. የእግዚአብሔርን ፍቅር የምናስብበት ነውና።

"እርሱ ስለእኛ ነፍሱን አሳልፎ ሰጥቶአልና በዚህ ፍቅርን አውቀናል "1ኛዮሐ 3:16 
"ነፍሱን ስለወዳጆቹ ከመስጠት ይልቅ ከዚህ የሚበልጥ ፍቅር ለማንም የለውም።"ዮሐ 15:13

2ኛ.ዲያብሎስ ያፈረበት፥ ሞተ ነፍስን ድል የተነሳበት ነውና 

ጌታ ከመስቀሉ :- "አቀድሞ ሞት በሰው ላይ ነግሦ ይኖር ነበር። "ሮሜ 5:12 
ነገር ግን ጌታችን በመሰቀል ላይ ተሰቅሎ ጠላታችን ዲያብሎስን ከመንገዱ አስወገደ በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል።
"በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዛት የተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው። እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል። "ቆላ 2:14 
ሞትንም ከእኛ ስላስወገደው እንዲህ ብለን ለመናገር በቃን።
"ሞት ሆይ፥መውጊያህ የት አለ? ሲኦል ሆይ፥ድል መንሣትህ የት አለ?" 1ኛ ቆሮ 15:54 
ስለዚህ ዛሬ በመስቀል ስናማትብ ጥንተ ጠላት ዲያብሎስ እንደ ጢስ ተንኖ ይሸሻል፤ ኃይሉን ያጣበት፤ ያፈረበትና የተዋረደበት ነውና።

3ኛ. የጌታን ውለታ የእመቤታችንን እናትነት የምናስብበት ስለሆነ 

"እርሱ በእግዚአብሔር መልክ ሲኖር ሳለ ከእግዚአብሔር ጋር መተካከልን መቀማት እንደሚገባ ነገር አልቈጠረውም፥ ነገር ግን የባሪያን መልክ ይዞ በሰውም ምሳሌ ሆኖ ራሱን ባዶ አደረገ፥ በምስሉም እንደ ሰው ተገኝቶ ራሱን አዋረደ፥ ለሞትም ይኸውም የመስቀል ሞት እንኳ የታዘዘ ሆነ።ፊል 2:6

"በመስቀል ሳለ... ኢየሱስም እናቱን ይወደው የነበረውንም ደቀመዝሙር በአጠገቡ ቆሞ ባየ ጊዜ እናቱን። አንቺ ሴት፥ እነሆ ልጅሽ አላት። ከዚህ በኋላ ደቀ መዝሙሩን። እናትህ እነኋት አለው።"ዮሐ 19:26

4ኛ.መንፈሳዊ ኃይል የምናገኝበት ነውና

"የመስቀሉ ቃል ለሚጠፉት ሞኝነት፥ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነውና። "1ኛቆሮ 1:18

5ኛ.የሰው ልጅ ከሲኦል ነጻ የወጣበት ነውና

"እርሱ ሰላማችን ነውና፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ፥ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው። ኤፌ 2:14

6ኛ. ቅዱስ መስቀል መመኪያችን ነውና

"ነገር ግን ዓለም ለእኔ የተሰቀለበት እኔም ለዓለም የተሰቀልሁበት ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል በቀር ሌላ ትምክህት ከእኔ ይራቅ። "ገላ 6:14 
ማቴ 10:38 "መስቀሉንም የማይዝ በኋላዬም የማይከተለኝ ለእኔ ሊሆን አይገባውም። "ማቴ 16:24 "ኢየሱስ ለደቀመዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ። "

ማማተብ

 

"አማዕተን" አመሳቀለ: አማተበ: ባረከ ካለው ግሥ የወጣ ቃል ነው:: ትርጉሙ ምልክት ማድረግ ማመሳቀል መባረክ ማለት ነው:: ማዕተብ ማለትም ምልክት ማለት ነው:: "ማዕተበ ክርስትና" ሲል የክርስትና ምልክት (መስቀል) ማለት ነው:: ባረከ ሲልም "ዮሴፍ አባቱ እሥራኤል ይባርካቸው ዘንድ ልጆቹን አቀረበ:: እሥራኤልም እጆቹን በራሳቸው ላይ አመሳቀለ" (ዘፍ 48:13)
ስለዚህ በቀኘ እጅ በጣቶች በመስቀል ምሳሌ (በአርአያ መስቀል) ማማተብ ተገቢ መሆኑን ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ታዛለች:: ፍትሕ መንፈሳዊ (ፍትሐ ነገስት) በተባለውና የቀኖና (የሕግ) መጽሐፍ በአንቀጽ 10 ላይ ማማተብ የሚገባ መሆኑን ተደንግጎል::
"በመስቀል አምሳል (በመስቀል ምሳሌ) ከላይ ወደ ታች (ከግንባራችን ወደ ደረታችን) : ከግራ ወደ ቀኝ በጣት ማማተብ ነው:: በጣቶች የማማተብ አጋንንትን (ሰይጣናትን) ለማራቅ ነው:: ጌታችን "እኔ በእግዚአብሔር ጣት አጋንንትን (ሰይጣናትን) አስወጣሁ ብሎ እንደ ተናገረ (ሉቃ 11:20)::

ከላይ ከግንባራችን እስከ ታች ማለት እስከ ደረታችን ማማተባችን ግን ጌታችን መድኃኒታችን ከሰማየ ሰማያት መውረዱን: መስቀሉን መሞቱንና ከሙታን ተለይቶ በመነሳት እኛን ከግራ ወደ ቀኝ የመመለሱ ምልክት ነው:: በመስቀል አምሳል ማማተብ ድኅነታችን የተፈጸመው በመስቀል ነውና: ሰይጣን ከእኛ የይርቅ ዘንድ በተረዳች ሃይማኖት (ኦርቶዶክሳዊት ሃይማኖት) ዘወትር በመስቀል አምሳል ፊታችንን እናማትብ ዘንድ ከጥፋትም እንድንበት ዘንድ ይህንን ምልክት (ማማተብ) ሐዋርያት ለእኛ አደረጉ: ይሕውም የግብጻውያንን በኩር እንደገደለ: በኩራቸውን እንዳይገድልባቸው እግዚአብሔር በፋሲካ የታረደውን የበግ ደም ከእስራኤላውያን ልጆች ቤት የሚያርቅ ምልክት እንዳደረገው ነው:: በትምህርት መስቀል ማለት ምልክት የምናማትብባቸው ጊዜያቶችም:

አንደኛ-  ጸሎት ስንጀምር
ሁለተኛ- ነገር መስቀልን የሚያነሳ ቃል ስናነብ ነው:: (ፍትሐ መንፈሳዊ አንቀጽ 14) ::

እንደሚታወቀው ወደ ቤተክርስቲያን ደርሰን ስግደት ስናደርግ እጃችን በዘፈቀደ ሥርዓትና ምስጢር በሌለው ሁናቴ ማወዛወዝ ሳይሆን: በመካከለኛው ጣታችንና ባመልካቹ ጣታችን የመስቀል ቅርጽ በመስራት ከግንባራችን ወደ ደረታችን: ከዚያም ከግራ ትከሻችን "በስመአብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ"
እያልን ማማተብ ተገቢ ነው:: ይህውም ከላይ እንደተገለጸው ጌታችን በመስቀል ተሰቅሎና ሞቶ በትንሳኤው አዳምንና የልጅ ልጆቹን ከግራ (ከዲያኒሎስ) ወደቀኝ ማለት ገነት የመመለሱ ምሳሌ ነው::

የማማተብ ጊዜያትም ከላይ ከተገለጸው ሌላ በተጨማሪ ጸሎት ስንጨርስ እግዚኦ ተሣሃለነ (ኪርያላይሶን) ስንል ከምግብ በፊት ምግብ ተመግበን ስንፈጽም: ስንተኛ: ከመኝታችንም ስንነሳ: ከቤታችን ስንወጣ ወደ ቤታችን ስንገባ: ሥራ ስንጀምርና ስንጨርስ: ክፉና አስደንጋጭ ነገር ስንሰማ ወይም ስናይ ከጸሎት ጋር ማማተብ ይገባናል::
ቀደም ብለን እንደ ገለጽነው በትምእምርተ መስቀል (በመስቀል ምሳሌ) ማማተብ ክፉን ለማራቅና መንፈሳዊ ኃይልን ለማግኘት ነው:: ምክንያቱም የክርስቶስ ቅዱስ መስቀል መንፈሳዊ አጥራችን: ኃይላችንና ጽናታችን ነውና::

መስቀል ኃይልና ጽንእ በመሆኑ: ይኅውም እግዚአብሔር ሰውን ሲፈጥር በመስቀል ምሳሌ ነው::  ማለት የሰው ቅርጽ የመስቀል ቅርጽ ነው:: አእዋፍና አሞሮችም የተፈጠሩት በመስቀል ቅርጽ ነው:: መስቀል ኃይልና ጽንእ በመሆኑ ትምርተ መስቀል (የመስቀል ምሳሌ) በሁሉም ፍጥረቶች ዘንድ ትገኛለች: ጸሐይ በመስቀል አምሳል ብርሃንዋን ካልዘረጋች ልታበራ አትችልም:: ጨረቃም እንደዚሁ:: የሰማይ ወፎችም ክንፉን በመስቀል አምሳያ ካልዘረጋች ለመብረር አትችልም ሲል ቅዱስ አትናቴዎስ አረጋግጦል (መጽ. ግብረ ሕማማት ዘዓርብ)

መስቀል መሳለም (መሳም)

 

መስቀል በጌታችን ደመመለኮት ስለተቀደሰ እንስመዋለን እንቀደስበታለን የተቀደሰውን ነገር እንኮአንስ መሳም ብንዳሰሰው እንደምንቀደስ ቅዱስ መጽሐፍ ያስተምረናል:: ዘጸ 30: 29 እኛ ክርስቶሳውያን የክርስቶስን መስቀል የምንሰመው ወይንም የምንሳለመው ስለክርስቶስ ያለንን ፍቅር ለመግለጽና በረከተ ክርስቶስንም ለመቀበል ነው:: ነገር ግን የክርስቶስን መስቀል መሳማችንን ወይም መሳለማችንን የሚነቅፉ እንደሞኝነትም አድርገው የሚያስቡ ወይም የሚቆጥሩ ወገኖች አሉ:: በመሆኑም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እነዚህን አጽራረ መስቀል አስመልክቶ ለእውነተኞቹ ክርስቲያኖች እንዲህ ሲል ጽፎአል...
"የመስቀሉ ቃል (ነገር) ለሚጠፉት ሞኝነት: ለእኛ ለምንድን ግን የእግዚአብሔር ኃይል ነው..."  ብሎአል 1ኛ ቆሮ 1:8 ::በሌላ መልእክቱም... ፊልጵ "ብዙዎች ለክርስቶስ መስቀል ጠላቶች ሆነው የመላለሳሉና ብዙ ጊዜ ስለእንሱ ነግሬያችኃለው: አሁንም እንካ እያለቅስሁ እላለሁ: እነሱ መጨረሻቸው ጥፋት ነው: ሆዳቸው አምላካቸው ነው: ክብራቸው በነውራቸው ነው:  አሳባቸው ምድራዊ ነው..." ሲል አስተምሮአል::

መስቀል መሳለምና ማክበር በእርግጥ ፍቅርን ለመግለጽ: በረከትም ለመቀበል ነው:: መሳለም ወይም መሳም የአክብሮት: የፍቅርና የናፍቆት መግለጫ መሆኑም በሁሉም ዘንድ የታወቀ ነው:: ለምሳሌ ታሪኮ በቅዱስ ወንጌል ተምዝግቦላት የሚገኝ አንዲት ኃጢአተኛ ሴት እጅግ ብዙ የሆነውን ኃጢአትዋን ጌታ እንዲተውላት እጅግ አድርጋ ጎጋች:: ጌታችንንም አጥብቃ ፈለገች:: ባገኘችው ጊዜ ሽቱ የሞላበት የአልባጥሮስ ብልቃጥ አመጣች ከጌታም በስተኃላው በእግሩ አጠገብ ቆማ ትሰመው (ታጥበው) ጀመረች: እንደዚህም በማድረጎ ጌታችን ኃጢአትዋን ይቅር ብሎ ልጄ በሰላም ሂጂ ብሎ አሰናበታት: ሉቃ 7::

በዚሁ አይነት ጌታችንን የሚወድና ትእዛዙን የሚጠብቅ ክርስቲያን ሁሉ ስለ ጌታ ያለውን መንፈሳዊ ፍቅር ለመግለጽ: እንዲሁም ሥርየተ ኃጠአትንና በረከትን ለመቀበል የጌታ እግሮች የቆሚበትን ቅዱስ መስቀል ይስማል (ይሳለማል:: የጌታ እግሮች ከቆሙበት ቦታ መስገድ እንደሚገባን ቅዱስ መጽሐፍ ያረጋግጣል::
"የጌታ እግር በቆሙበት ስፍራ እንሰግዳለን" ሲል ንጉስ ዳዊት መስክሮአልና::መዝ 132:7 

የተቀደሰውን ነገር ወይም ቦታ መሳለም ደግሞ በሃይማኖት ሥርዓት የተለመደ ነው:: በቤተ መቅደስ ወይም በምኩራብ ለጸሎት ይሰበሰቡ የነበሩ እስራኤላውያን መጽሐፈ ሕግ ማለት ኦሪት (ቶራ) ከተነበበበ ኃላ ለጸሎት የሚሰበሰቡትን ሰዎች በሙሉ መጽሐፈ ኦሪቱን ይሳለሙ ወይም ይስሙ እንደነበር መጽሐፈ ታልሙድ ይመሰክራል:: ይህን ሥርዓት አሁንም በምኩራባቸው እየሰሩበት ነው:: እኛም እንደ ጥንቱ ሥርዓት ቅዱስ ወንጌልን: መስቀልንና ሥዕልን እንሳለማለን:: በቅርብም ሆነ በሩቅ ያለውን ቅዱስ ቦታ ወይም ቅዱስ መስቀል መሳም (መሳለም) ስለሱ ያለንን አክብሮትና ፍቅር ለመግለጽ ነው:: ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ስለዚሁ ሲገልጽ
"እነዚህ ሁሉ አምነው ሞቱ: የተሰጣቸው የተስፋ ቃል አላገኙም: ዳሩ ግን ከሩቅ ሆነው አዩትና ተሳለሙት" ይላል ዕብ 11:13  የወደዱትንና ያፈቀሩትን ነገር እንኮንስ በቅርብ ተገኝተው መሳለም (መሳም) ይቅርና በሩቅ ሆነው እንኮ አንመሳለም እንጂ መንሳት እንደሚገባ ሐዋርያው የጻፈው ቃል ታላቅ ምስክር ነው::

ከዚሁ መጽሐፍ ቅዱሳዊ ሥርዓት የተነሳ በሀገራችን በኢትዮጵያ በተለይም በገጠሩ ክፍል በየመንገዱ መሳለሚያ እየተባለ የሚጠራ ልዩ ቦታይገኛል:: በዚሁ ቦታ መስቀል መሰል የድንጋይ ካብ ይገኛል:: ሕዝበ ክርስቲያኑ በየመንገዱ ሲያልፍ ከዚያ ቦታ እንደደረሰ ቀጥ ብሎ የቆመና በተተከለው የዕንጨት መስቀል ወይም በተቆለለው መስቀል መሰል ካብ አቅጣጫ ወደ ሚገኘው ቤተክርስቲያን ራሱን ዝቅ አድርጎ እጅ ይነሳል: ማለትም ይሳለማል:: ይኅውም እምነቱንና ፍቅሩን ለመግለጽ ነው::

ነብዩ ዳንኤል የጸሎት ቤቱን መስኮቶች ወደ ኢየሩሳሌም አቅጣጫ አድርጎ በመሥራት: በቀን ሥስት ጊዜ መስኮቶችን እየከፈተ በቀን ሥስት ጊዜ ተንበርክኮ ይጸልይ እንደነበር መጽሐፍ ቅዱስ ያስረዳል (ዳን 6:10):: ስለዚህ መስቀል መሳለም ወይም ወደ መስቀልና ወደ ቤተክርስትያን: እንደዚሁም ወደ ቅዱሳን ሥዕሎች ዞሮ መስገድ የሚገባ መሆኑን ኦርቶዶክስ ቤትክርስቲያን ታስተምራለች::

በመስቀል መባረክ

 

ሥልጣነ ክህነት ያላቸው ካህናት በቅዱስ መስቀል እንዲባረኩና ምእመናንም እንዲባረኩ ኦርቶዶክሳዊ ቤተክርስትያን ታዛለች::

በቅዱስ መስቀል የመባረክና የመባረክ ምስጢር

1ኛ. በጌታችን ቅዱስ መስቀል አማካይነት ሥርዓት ኃጢአትን ለመቀበል:
2ኛ. በጌታችን ቅዱስ መስቀል አማካይነት ቡራኬን ማለት መንፈሳዊ ክብርንና ጸጋን ለመቀበል ነው::

 

በመስቀል ምሳሌ በረከትንና ምርቃትን መስጠት በዘመነ ኦሪትም የትለመደ ነው:: በእርግጥ በኦሪት ዘመን መስቀል አልነበረም:: ስለዚህም አበው በመስቀል ምሳሌ እጃቸውን እየዘረጉ ልጆቻቸውን ይባርካ እንደ ነበር መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል:: ለምሳሌ ከዚሁ ቀጥሎ ያለውን እንመልከት:: ያዕቆብ በሸመገለ ጊዜ የልጅ ልጆቹን ኤፍሬምንና ምናሴን ሊባርካቸው ፈለገ: አባታቸው ዮሴፍም ሁለቱን ልጆቹን በያዕቆብ ቀኝና ግራ አቆማቸው: ያዕቆብም እጆቹን አመሳቅሎ ባረካቸው: መረቃቸውም (ዘፍጥ 48:13)

በዚሁ ዓይነት ካህናተ ኦሪት እጆቻቸውን በማንሳትና በማመሳቀል ሕዝቡን ይባርኩ ነበር:: የቡራኬም ሥርዓት ከእግዚአብሔር የተነገረ ነው:: እግዚአብሔር ለሙሴ እንዲህ ብሎ ነግሮት ነበር::

"እግዚአብሔርም ሙሴን እንዲህ ብሎ ተናገረው። ለአሮንና ለልጆቹ ንገራቸው። የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩአቸው እንዲህ በሉአቸው። እግዚአብሔር ይባርክህ፥ ይጠብቅህም እግዚአብሔር ፊቱን ያብራልህ፥ ይራራልህም እግዚአብሔር ፊቱን ወደ አንተ ያንሣ፥ሰላምንም ይስጥህ። እንዲሁ ስሜን በእስራኤል ልጆች ላይ ያደርጋሉ እኔም እባርካቸዋለሁ። "ዘኁ 6:22

የበረከት ባለቤተና የበረከት መገኛ የሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ወንጌል በሚያስተምርበት  ጊዜ የተቀደሱ እጆቹንን እያነሳ (እያመሳቀለ) ምእመናንን ይባርክ ነበር:: ለምሳሌ ጌታችን በስንከተ ወንጌል ጊዜ ለመባረክ ወደ እሱ የመጡትን ሕጻናት ተቀብሎ እንዳቀፋቸውና እጆቻቸውንም አንስቶ እንደባረካቸው ቅዱስ ወንጌል ይመሰክራል (ማር 10:10):: ከሞት ተለይቶም ከተነሳም በኃላ ወደ ሰማያት ከማረጉ በፊት ደቀ መዛሙርቱን ሰብስቦ እጆቹን አንስቶ (አመሳቆሎ) ባረካቸው: እንደ ባረካቸውም ወደ ሰማያት ማረጉን ሉቃስ መስክሮአል (ሉቃ 24:50)::


ስለዚህ ጌትችን በሠራው ሥርዓት መሠረት የጌታችን ተከታዮች የሆኑት ሊቃነ ጳጳሳት: ኢጲስ ቆጶሳትና ካህናት (ቀሳውስት) በቅዱስ መስቀልና እጆቻቸውን በማመሳቀል ምእመናንንና ምእመናትን እንዲባርኩ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ታስተምራለች:: ካህናት አባቶቻችንም እግዚአብሔር ለሙሴና ለአሮን የእስራኤልን ልጆች ስትባርኩ እንዲህ በሉአቸው በተባሉበት የቡራኬ ቃል መሠረት ይባርኩናል::  ዘፍ 6:22

ማዕተብ

 

ማዕተብ ማለት ቀጥተኛ ትርጉሙ ምልክት ማለት ነው:: እኛም ክርስቲያኖች በአንገታችን የምናስረው የመስቀል ምልክት ማዕተባችን ነው:: ማዕተብ "አተበ" ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ዋና ትርጉሙም አመለከተ ማለት ነው:: ማንኛውም ኃይማኖት የመለያ ምልክት አላቸው:: ለምሳሌ በኦሪት ዘፍጥረት ስለአብርሃም ያለውን ታሪክ ስንመለከት እግዚአብሔር ግዝረትን ምልክት እንዳደረገለት እና ያለን ለዚህም ሳይገዘር እግዚአብሔር አብርሃምን በእምነት እንዳጸደቀው በእርሱ ላይ ይታወቅ ዘንድ ግዝረትን የጽድቅ ማህተም ትሆነው ዘንድ ምልክት አድርጎ ሰጠው ብሎ ቅዱስ ጳውሎስ ሮም ለሚኖሩ ክርስቲያኖች እንዳስተማራቸው መጽሐፍ ቅዱስ ይነግረናል:: እስላም አርማቸው ሆነ ምልክታቸው ጨረቃ እንደሆነ ሁሉ እኛ ክርስቲያኖች በክርስቶስ አምላክነት እና ፈጣሪነት ስለምናምን ደግሞም ጌታችን መድኃኒታችን እየሱስ ክርስቶስ የተሰቀለበት መስቀል ለኛ ለምናምን ኃይላችን ስለሆነ ምልክታችንም አርማችንም ነው ስለዚህም በአንገታችን እናስረዋለን ማለት ነው:: ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ገላትያ ሰዎች በምዕራፍ 6 ቁጥር 14 ላይ እኔ ግን በጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስክርስቶስ መስቀል እንጂ በሌላ አልመካም ብሎ ለገላትያ ሰዎች የነበረባቸውን መከራም ሆነ በክርስትና እምነት የተነሳ ከሚደርስባቸው እንግልት እንዲጽናኑ እና በእምነታቸው እንዲጸኑ ደግሞም በሌላ ትምክህት እንዳይመኩ ትምክህታቸው ክርስቶስ በተሰቀለበት መስቀል እንዲሆን አጥብቆ ሲመክራቸው እና ያለን ስለዚህ እኛም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳስተማረን ትምክህታችን የክርስቶስ መስቀል ስለሆነ መስቀሉን ማዕተብ አድርገን እናስራለን ማለት ነው::

መጽሐፈ ምሳሌ 3፥3 ምሕረትና እውነት ከአንተ አይራቁ በአንገትህ እሰራቸው በልብህ ጽላት ጻፋቸው።

ታሪክ እንደሚነግረን ከሐዋርያት ጀምሮ ያሉት አባቶች ይህችን የክርስትና ኃይማኖት ፈተናውን; ስድቡን; መከራውን; ግርፋቱን; ስቅላቱን; ሞቱን ሁሉንም ሆነው ይህችን ልጫ ዓለም በወንጌል እንዳጣፈጡ አትሁሉ በአንጻሩም የሚኖሩበት ቦታ በዋሻና በጣሻ ስለነበር ከሞት ራሳቸውን ለማዳን ሲሉ ከሚያሳድዱአቸውና ለግድያ ከሚፈልጉአቸው ሰዎች ራቅ በማለት በድብቅ ወንጌልን ያስተምሩ እንደ ነበር ታሪክ ያስረዳናል:; ክርስቲያኖች ከአህዛብ የሚለዩበት ዋናው ምክንያት መስቀልን ማዕተባቸው አድርገው በማሰራቸውና መለያቸው በመሆኑ ብዙ እንግልት እስከ ግድያ ድረስ የሚደርስባቸው ብዙ ቅዱሳን አባቶች እና እናቶችም እንደ ነበረ ታሪክ ያስረዳናል:: ቤተክርስቲያንም ሲሰራ ከጉልላቱ ላይ የመስቀል ምልክት የሚሆንበት ምክንያት የክርስቲያን ዋና አርማና መለያ ስለሆነ ነው:: በተጨማሪም በእኛ በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀልን ማዕተብ አድርገን ማሠራችንና የመስቀሉ ምልክት በክርስቲያኖች ዘንድ ዋና መለያ እና አርማ ሆኖ ጸንቶ ለመኖር የቻለበት ዋና ምክንያት ከጉዳቱ ጥቅሙ በዝቶ ስለሚታይ እና ሆኖም በመገኘቱ ነው:: ማንኛውም ሀገር በመንግስት ደረጃ ስንመለከት ሰንደቅ ዓላማ የሌለው የለም ምክንያቱም ያ ሰንደቅ ዓላማ ሃገሪቱንና ሰውን ይወክላል ደግሞም ለሃገሪቱም አርማቸው እና ምልክታቸው ስለሆነም ነው:: በአንጻሩም ደግሞ እኛ ከርስቲያኖች መስቀልን ማዕተብ አድርገን የምናስርበት ዋና ምክንያታችን መስቀሉ የክርስትና መለያችን ስለሆነ ነው ስለዚህም ማዕተብ አድርገን እናስረዋለን ማለት ነው:: 

ተዘከረኒ እግዚኦ አመት መፅእ በመንግስት ከ“ በመንግስት በመጣህ ጊዜ አሰበኝ ወአውስ ኦ እግዚእ ኢየሱስ ለፊያታዊ ወይቤሎ በከመትቤ አማን አማን እብልከ ከመዮም ትሄሉ ምስሌ የውስተ ገነት ”

ጌታ ኢየሱስም እውነት እውነት እልሃለሁ ዛሬ ከእኔ ጋራ በገነት ትኖራለህ” የብርሀን መክፈቻ ውሰድ፡፡ ተድላ ደስታ ወደ ሚገኝበት ወደ ገነት ሂድ፡፡ ለብርሀንን ጉስም መንገዱን ጥረግ፡፡ ለመላእክት ሰራዊት ሁሉ ንገራቸው፤ ድሉንም ስበክ፡፡ በገነት ውስጥም የሰላምን አዋጅ ንገር፡፡ ወንጀለኛው አዳም ወደ ቀድም መኖሪያው እንደተመለሰ ንገራቸው፡፡ ከዚህም በኋላ ጌታችን ለፊታዊ የሕይወት መፅሐፍን ፃፈ፡፡ያቺንም መፅሐፍ በከበረ ደሙ አተማት ...አከበራትም፡፡ ፊያታዊም በጌታችን ደም ከበረ፤ ሕይወትም አገኘ፤ ልጅነትንም ተቀበለ፡፡ ከጌታ ጎን በፈሰሰው ደምና ውሃ በመጠመቅ ፊያታዊ ነፃ፤ ብርሀንና ክብር ያላትን ልጅነትን ተጎናፀፈ፡፡ የገነት መክፈቻ ያችንም መፅሐፍ ተቀብሎ የእሳቱን ባህር ተሻገረ፡፡ ነበልባሉም አላቃጠለውም፡፡ ከእሳቱም መካከል ካለው መንገድ በደረሰ ጊዜ መልአክ አገኘው፤ በቁጣ መረመረው አንተ ማነህ? ንገረኝ ከወዴት መጣህ? በእሳት ውስጥስ እንደምን አለፍክ? ነፋሳቱስ በቃጠሎው ውስጥ እንዴት በኃይላቸው ተሸከሙህ? ደካማ አንተንስ እንዴት አላቃጠሉህም?

  • የእሳቱን ባህር እንዴት አለፍክ? ወይም ትህዛዛቱን የጠበቀ የእግዚአብሄር አገልጋይ የተባለ መልከ ፄዴቅ አንተ ነህን?

  • አንተ እግዚአብሄር በእጁ የፈጠረው አዳም ነህን? ወይስ ትሩፋቱ ብዙ የሆነ ፃድቁ ሴት ነህን? ወይስ የጥፋት ውሃ ማዕበልን ድል የነሳና በንፁህ መስዋህቱ እግዚአብሄርን ደስ ያሰኘ ኖኅ አንተ ነህን?

  • የአባቶች አባት አብርሀም ወይስ በሾተል ከመታረድ የዳነው ይስሀቅ አንተ ነህን?

  • እግዚአብሄርን ፊት ለፊት ያየው ያዕቆብ ወይስ የሰይጣንን ጦር ድል ያደረገ ዮሴፍ አንተነህን?

  • በሕዝብ ፊት ባህረ ኤርትራን የከፈለ ማዕበሉን ፀጥ ያደረገ ከእግዚአብሄር ጋር የተነጋገረ ሙሴ ወይስ ፀሐይን ያቆመ የነዌ ልጅ ኢያሱ አንተነህን?

  • የእግዚአብሄርን መውረድ በመስክ ከባዘቶ ላይ እንደሚወርድ ጠል የመሰለ ጌዴዎን ወይስ ስለስእለቱ ሴት ልጁን ለእግዚአብሄር የሰዋ ዮፍታኤ አንተነህን?

  • በትንቢቱ ጌታን መንክር ብሎ የሰየመው ነብዩ ኢሳይያስ ወይስ እግዚአብሄርን በሰረገላው ላይ ሆኖ ያየው ሕዝቅኤል አንተ ነህን?

የአንበሶችን አፍ የዘጋ ዳንኤል ወይስ የእሳት ወላፈን ያልነካቸው ከሰለስቱ ደቂቅ አንዱ አንተ ነህን? በባህር ላይ የሄደ ስምዖን ጴጥሮስ ወይስ በጌታ ኢየሱስ አጠገብ የተቀመጠ ዮሀንስ ወይስ ጌታን ያጠመቀ መንፈስ ቅዱስ በላዩ ሲወርድ የየና የምወደው ልጄ የሚለውን የአብን ቃል የሰማ የዘካርያስ ልጅ ዮሃንስ አንተነህን?
አንተ ሰው ሆይ ንገረኝ አንተ ማነህ? የእሳት ባህሮችን የተሻገርህ አቃጥለው ያላጠፉህ ብሎ ጠየቀው ፌያታዊ ዘየማንም መለሰ ተወዳጅ መልአክ ሆይ አትቆጣ እኔ ማን እንደሆንኩኝ እነግርሃለሁ፡፡ የላከኝም ማን እንደሁነ እነግርሃለሁ፡፡ መላዘመኔን በክፉ ስራ ያሳለፍኩ ወንበዴ ነኝ የሰውንደም ተቀባሁ፡፡ እቀማ ዘንድ በመንገድ እሸምቅ ነበር፡፡ መልአክ ሆይ እነሆ ሰማያዊ ንጉስ ጌታህ ሕይወትን የሰጠኝ እርሱ ነው፡፡ አምኜበታለሁና በአመንኩበት ጊዜ ወደ ሕያዋን እገባ ዘንድ የይቅርታውን በር ከፈተልኝ፡፡
የጌታ ምህረት ከጥፋት ወደ ሕይወት መለሰኝ፤ በኃጥያት የኖረኩበትን ዘመን ሳይመለከት በፍቅሩ ማረከኝ፤ በርህራሄው ተመልክቶኝ እንደ ባለማዕረግም ቆጠረኝ፡፡ በቸርነቱ ያደፈ ታሪኬን ለውጦ ከበደሌ ሁሉ አነፃኝ፡፡በሞቱ ሕይወቴን ታደገኝ፡፡ግብረ ሕማማት

መስቀል የአባታችን ገዳይ ነው? እንዴት?

 

ሰይጣን ምንግዜም የሚሸነፍበትን መሣሪያ ማውገዝ ልማዱ ነው:: ዛሬ የመስቀሉ ጠላቶች ፊል 3:18 መስቀል ጣዖት እንደውም የአባታችን ገዳይ ነው ሲሉ ይሰማሉ::

መስቀል የገደለው ማንን ነው?


"ጥልን በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታችንን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው::ኤፌ 2:16

ጥል የጥልም አባት ዲያብሎስ በመስቀል ላይ በተደረገው ቤዛነት ራስ ራሱን ተቀጥቅጦ ወድቆ አልተገድሎአልም::

"በእኛ ላይ የነበረውን በትዕዛዛትየተጻፈውን የዕዳ ጽሕፈት ደመሰሰው:: እርሱንም በመስቀል ላይ ጠርቆ (አስጨንቆ) ከመንገድ አስወግዶታል:: ቆላ 2:14 
አለቅነትና ሥልጣናትን ገፎ ድል በመንሳት በእርሱ እያዞራቸው በግልጽ አሳያቸው::

በመስቀል ቤዛነት ተጠርቆ ከመንገዳችን የተወገደው ሰይጣን ነው:: አለቅነትና በሰው ልጆች ላይ የነበረውን ሥልጣን በቀራኒዮ አደባባይ ተገፎ ሽንፈት ንተከናንቦል::

መስቀል የአባታችን ገዳይ ነው የሚሉ ሰዎች ሳያውቁት መንፈስ ቅዱስ አባታቸው ዲያብሎስ መሆኑን እየመሰከራቸው ነው:: ምክንያቱም በመስቀል የሞተው (የተቀጠቀጠው) ዲያብሎስ እንጂ ክርስቶስ አይደለምና:: ክርስቶስማ በፈቃዱ የሞተ የባህርይ አምላክ ነው::

ሊቀ ካህናት ሐና ብዙዎች ከሚሞቱ አንድ እርሱ ይሙት ብሎ ሳያውቀው እውነት እንደተናገረ: እነርሱም ሳያውቁት በመስቀል የተጠረቀው ዲያብሎስ የግብር አባታቸው እንደሆነ እውነቱን እያናገራቸው ነው::

  • መስቀል ጠላታችን አይደለም:: ጠላትነት ለሰይጣን እንጂ::

  • መስቀል ጌታችንን አልገደለውም ዲያብሎስን እንጂ::

  • መስቀልን አክበርን እንጂ አላመለክነውም (ጣዖት ሊባልም አይገባም)::

የሚገርመን ግን መስቀልን እንደ ጣዖት በተጸየፉበት አንደበታቸው የጸሎት ቤታችን ነው በሚሉት አዳሳሾቻቸው ጣሪያ ላይ መስቀል መሰካታቸው ነው:: እንደ ጣዖት ከተመለከቱት ለምን እንደ አርማ ይተክሉታል? የቅዱስ መጽሐፍን ትርጉም እንደማያውቁት ሁሉ ለሚናገሩትንም አያውቁም ማለት ነው:: የተከሉትም ሊድኑበት ሳይሆን ለማስመሰል እንደሆነ ግልጽ ነው::

bottom of page