top of page

ሃይማኖት

“ሃይማኖት” የሚለው ቃል አምነ፣ አመነ ከሚለው የግዕዝ ግሥ የወጣ ሲሆን መዝገበ ቃላዊ ትርጓሜውም “ማመን፣ መታመን” ማለት ነው። በምሥጢራዊው ትርጕሙ ግን “ሃይማኖት” ማለት ፍጥረትን ኹሉ ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ አንድ እግዚአብሔር እንዳለ፣ ለሚታየውም ለማይታየውም ፍጥረት ሠራዒውና መጋቢው ርእሱ ብቻ እንደሆነ፣ ልዩ ሦስትነት እንዳለው፣ በዚህ አለ በዚያ የለም የማይባል ምሉዕ በኵለሄ እንደሆነ ማመን መታመን ማለት ነው። 

 

ማመን ማለት ከሁሉ በፊት የነበረ፣ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር፣ ፍጥረትን ሁሉ የፈጠረ፣ ማንኛውንም ነገር ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣ ያስገኘ፤ ለእርሱ ግን አምጪ፣ አስገኚ፣ አሳላፊ የሌለው፣ ምንም ምን የሚሳነው የሌለ፣ በአንድነት በሦስትነት ጸንቶ ያለ ሁሉን ቻይ የማይለወጥ አምላክ መኖሩን ማመን ነው። መታመን ማለት በልብ /በረቂቅ አእምሮ/ ያመኑትን በአንደበት መመስከር መናገር፤ ማመስገን ማምለክ፤ መስገድ፤ መገዛት ለቃሉ ታዛዥ፤ ለመንግስቱ ተገዥ መሆን በስራ ሁሉ መግለጥ ማለት ነው።  (ሮሜ 10፡9) ተአማኒነት  ማለት ይደረግልኛል ይሆንልኛል ይፈፀምልኛል ብሎ በፍፁም ልብ በእግዚአብሔር ላይ ተአማኒነትን ማድረግ ነው። አመኔታ  የሚለው ተአማኒነት ከሚለው ጋር በትርጉም ተወራራሽነት አለው።

“ማመን” ማለትም ይኾንልኛል ይደረግልኛል ብሎ መቀበል፤ ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ተስፋ ማድረግ፤ አለመጠራጠር ማለት ሲኾን፤ “መታመን” ማለት ደግሞ ያመኑትን እውነት በሰው ፊት በአንደበት መመስከርና በተግባራዊ ሕይወት መግለጥ ማለት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስም ይኽን በተመለከተ፡- “ይኽም የምንሰብከው የእምነት ቃል ነው። ኢየሱስ ጌታ እንደኾነ በአፍህ ብትመሰክር እግዚአብሔርም ከሙታን እንዳስነሣው በልብህ ብታምንት ድናለህና፤ ሰው በልቡ አምኖ ይጸድቃልና በአፉም መስክሮ ይድናልና” ብሎ አስተምሯል (ሮሜ.10፥8-10)። ዳግመኛም በሌላ አንቀጽ፡- “የእግዚአብሔር ጸጋ እንደተሰጠኝ መጠን እንደ ብልሃተኛ የአናጺ አለቃ መሠረትን መሠረትኹ፥ ሌላውም በላዩ ያንጻል” በማለት ከኹሉ አስቀድሞ እምነት እንደሚያስፈልግ ያስረዳናል። ቀጥሎም “ማንም ግን በዚኽ መሠረት ላይ በወርቅ ቢኾን በብርም በከበረ ድንጋይም በእንጨትም በሣርም ወይም በአገዳ ቢያንጽ የእያንዳንዱ ሥራ ይገለጣል።” በማለት ምግባር ትሩፋት እንደሚያስፈልግ ያስረዳል /1ኛ ቆሮ.3፥10-12/። ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅም የዕብራውያንን መልእክት በተረጐመበት 9ኛው ድርሳኑ ላይ  “እምነት መሠረት ናት፤ ሌሎች ግን ሕንፃና ግንብ ናቸው” በማለት ምግባርና ትሩፋት ከመሥራት በፊት እምነት እንደሚቀድም አስተምሯል  /ቁጥር 80-81/። 

 

ይኸውም ሃይማኖት ማለት ቅድመ ዓለም የነበረ ፍጥረታትን ሁሉ የፈጠረ ፈጥሮም የሚገዛ ማዕከለ አለም ያለ፤ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ምንም የሚሳነው የሌለ ለእርሱ ግን አምጪ፣ አስገኚ፣ አሳላፊ የሌለው በአንድነት፤በሦስትነት የሚመለክ ዘለዓለማዊ ሁሉን ቻይ አምላክ እንዳለ ማመን ነው። /ዕብ 11፥1-40/

ሃይማኖት ማለት ፍጡር ፈጣሪውን ለማወቅ ባሰበ ጊዜ፤ እንደ መላእክት በአእምሮ ጠባያዊ፤ እንደነ አብርሃም በሥነፍጥረት ተመራምሮ እንደነቢያትና እንደሐዋርያት ፊቱን አይቶ ቃል በቃል ተነጋግሮ፤ እንደ ቅዱስ ጳውሎስ በተአምራት ተገልጾለት ተመልሶ እንደሌሎች ምእመናንም በአእምሮ መጽሐፋዊና በተስፋ አረጋግጦ አምላክ እንዳለ የሚያምኑበት እውነተኛ ትምህርት ነው እንጂ እንደ እቃ በእጅ የሚጨበጥና የሚዳሰስ እንደልብስም የሚለበስ፤ እንደ መብልና መጠጥም የሚቀመስ አይደለም። /ዕብ 11/

ስለ እግዚአብሔር በመጽሀፍ ቅዱስ የተነገረውን ሁሉ በልባችን የምናምንበት፤በአፋችን የምንታመንበት መግለጫ ሃይማኖት ነው።ሃይማኖት ማለት በአይን የማይታየውን በእጅ የማይዳሰሰውን የልዑል እግዚአብሔርን ነገር ይህ እንዴት ይሆናል? ማለት ሳይኖርበ እግዚአብሔር ዘንድ ሁሉ ይቻላል ብሎ በሙሉ ልብ ማመን፤ይህንንም በአፍም በመጽሐፍም መመስከር ነው።

ስለዚኽ “ትምህርተ ሃይማኖት” ስንል ስለዚኹ ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው ማለት ነው፡፡ “ስለምናምነው አምላክ የምንማማርበት የትምህርት ዘርፍ ነው” ሲባል ግን በፍልስፍናና በዚኽ ዓለም እንደምናደርገው በምርምርና በሙከራ እንደርስበታለን ለማለት ሳይኾን እግዚአብሔር ራሱ በተለያየ መንገድ የገለጠውንና እንድናውቀው የፈቀደውን ብቻ እንማማራለንለ ማለት ነው፡፡በዚኹ ዙርያ ስለ ሀልዎተ እግዚአብሔር ስንማማርበ ስፋት እንመለስበታለን፡፡በፍልስፍናው ዓለም ፍልስፍናን ለመማር የራሱ የኾነ ቅድመ ኹኔታ (Axiom) እንዳለ ኹሉ በትምህርተ ሃይማኖትም ስለ ፈጣሪ ለማወቅ “ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልገዋል” ተብሎ እንደ ተጻፈ አስቀድሞ እምነት ያስፈልጋል /ዕብ.11፡6/፡፡እምነት ማለትም ለመለኮታዊው መገለጥ የምንሰጠው ምላሽ ነው፡፡በትምህርተ ሃይማኖት የመዠመሪያው ቅድመ ኹኔታ ይኽ እምነት ነው፡፡እምነት ሳይኖረን ትምህርተ ሃይማኖትን መማር አይቻለንም፤ትምህርተ ሃይማኖት የአዕምሮ ጨዋታ አይደለምና፡፡ትምህርተ ሃይማኖትን ስናጠና ኹል ጊዜ እምነት ሊኖረን ያስፈልጋል፡፡እምነት ምንም እንኳን የእግዚአብሔር ስጦታ ቢኾንም ፈቃዳችንን ይጠይቃል፡፡ይኽ አካሔድም በቤተክርስቲያን ቋንቋ “ፍኖተ አሚን” ይባላል፡፡ 

ቀጥሎ የሚመጣው ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “እኛስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ክርስቶስ አንተ እንኾንኽ አምነናል፤ዐውቀናልም” እንዳለው ዕውቀት ነው /ዮሐ.6፡69/፡፡ኾኖም አኹንም ጥንቃቄ ያስፈልገናል፡፡ይኸውም ይኽ ስለ ፈጣሪ የምናውቀው እውነት መጨረሻ የለውም፡፡ለምን? እግዚአብሔር ወሰን የለውምና/ኤር.23፡23/፡፡ተጠንቶ የሚያልቀው ውስንነት ስላለው አካል (ፍጡር) ብቻ ነው፤ያውም አብዛኛው አያልቅም፡፡ስለኾነም ስለ እግዚአብሔር የምንማረው ኹሉ በጥቂት ቃላት ብቻ ታጥሮ የሚያበቃ አይደለም፡፡ይኽ አነጋገር በኦሬንታል ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተክርስቲያናት አነጋገር “Apophatism -አፖፋቲዝም” ይባላል፡፡በኢ/ኦ/ተ/ቤ/ክ. “አንድም፣አንድምታ” እያልን የምናውቀው ነው፡፡ “ታድያ መማራችን ምን ፋይዳ አለው?” የሚል ጥያቄ ሊነሣ ይችላል፡፡
1ኛ) የተገለጠውን እውነት ለመረዳት ይጠቅማል፤
2ኛ) የቀደመችውን አንዲቷን መንገድ መያዝ ስለሚያስፈልግ እውነትን ከሐሰት ለመለየት ይረዳናል፤

ምንም እንኳን ክርስትና የመገለጥ ሃይማኖት ቢኾንም፥ምንም እንኳን እግዚአብሔር ሰዎች ፈልገው የማያገኙት ቢኾንም፥በመጽሐፍ ቅዱስና በሥነፍጥረት የተገለጠውን ግልጽ ትምህርት መማርን ግን አያወግዝም፡፡ኹል ጊዜ እውነትን ለማወቅ ከመጠየቅ ዕረፍት የሌለው የሰው ልጅ አዕምሮንም በአመክንዮ(By Reason) ማስረዳትን እንዲኹ አያወግዝም፡፡ይልቁንም አመክንዮን በትክክለኛው መንገድ እንድንጠቀምበት ያግዛል እንጂ፡፡

ሃይማኖት

ዶግማ እና ቀኖና

ትምህርት ሃይማኖት (የሃይማኖት ትምህርት) በሁለት ይከፈላል። ይኸውም፦

1ኛ፡- ዶግማ 
2ኛ፡- ቀኖና በሚል ነው።


ዶግማ ፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ፍችውም እምነት ማለት ነው።
ቀኖና፡- ቃሉ የግሪክ ሲሆን ሥርዓት ማለት ነው።

ከእነዚህ ከሁለቱ ዶግማ ወይም እምነት አይጨመርበትም፤ አይቀነስበትም፤ አይሻሻልም፤ ችግርና ፈተናም ቢመጣ እስከ ሞት ድረስ አጥብቀን የምንይዘው ነው። ለምሳሌ ያህል ይህን ዓለም ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፤ ቢመረምር እንጂ የማይመረመር ሁሉን ቻይ አምላክ፤ የሚሳነው ነገር የሌለ ፈጣሪ፤ የሰማይና የምድር ባለቤት የሠራዊት ጌታ ሕያው እግዚአብሔር ነው።

እግዚአብሔር (ፈጣሪ) የአካል ሦስትነት አለው። በመለኮት፣ በመፍጠር፣ በሥልጣን፣ በአገዛዝ፣ በፈቃድ ግን አንድ ነው። በሦስትነቱ አብ፤ ወልድ፤ መንፈስ ቅዱስ ሲባል በአንድነቱ አንድ መለኮት አንድ እግዚአብሔር ይባላል። በአዳም ምክንያት ከመጣው የዘለዓለም ሞትና ከዲያብሎስ ባርነት ነጻ የወጣነው ከሦስቱ አካላት በአንደኛው አካል ማለትም በወልድ በኢየሱስ ክርስቶስ ነው። ይህ ዶግማ ወይም እምነት ይባላል።

ቀኖና ግን በአምላካችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምነው ያደጉ ክርስቲያኖች የሚመሩበት ሥርዓት ስለሆነ፤ በሃይማኖት አባቶች ወይም በቅዱስ ሲኖዶስ አማካኝነት እንደ ጊዜው ሁኔታ የሚሻሻል በመሆኑ የሚጨመርበት፤ የሚቀነስለት ነው። ለምሳሌ ያህል  እኛ ኦርቶዶክሳውያን የምንጠመቀው ሴት በሰማንያ ወንድ በአርባ ቀናችን ነው። የተወለዱ ሕጻናት ሴቷ ሰማንያ ወንዱም አርባ ቀን ሳይሞላቸው ቢታመሙና በሽታው አስጊ ከሆነ በ10፣ በ20፣ በ30…ቀናቸው መጠመቅ ይችላሉ፣ ቀኖና ነውና። በቤተ ክርስቲያናችን የቀዳስያን ብዛት መነሻው አምስት ነው። ምናልባት ከአምስቱ አንዱ፤ ሁለቱ፤ ሦስቱ ቢታጡና ሌላም ተፈልጎ እስከመጨረሻ የማይገኝ ከሆነ ከአቅም በላይም የሆነ ችግር ከገጠመ ሁለቱ ወይም አንዱ ብቻ ቀድሰው ማቁረብ ይችላሉ፣ ቀኖና ነውና። በቤተ ክርስቲያናችን ታቦት ሲከብር ቤተ ክርስቲያኑን የሚዞረው ሦስት ጊዜ ነው ችግር ካለ አንድ ጊዜ ብቻ ዑደት ተፈጽሞ ሊገባ ይችላል፣ ቀኖና ነውና። ስለ ቀኖና (ስለ ሥርዓት) ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ እንዲህ ሲል ጽፏል። ‹‹ነገር ግን ሁሉን በአግባብና በሥርዓት አድርጉ።”  (1ኛ ቆሮ. 14፥40)”ወንድሞች ሆይ በሠራንላቸው ሥርዓት ሳይሆን በተንኮል ከሚሄዱት ወንድሞች ሁሉ ትለዩ ዘንድ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ስም እናዝዛችኋለን። እኛን ልትመስሉ እንደሚገባችሁ እኛም በእናንተ መካከል ያለሥራ እንዳልኖርን ራሳችሁ ታውቃላችሁ።“ (2ኛ ተሰ. 3፥6-7)

 

ቀኖና (ሥርዐት) የሚወሰነው በሃይማኖት አባቶች እንደሆነና ወንጌልን የሚያስተምር ሰው ለሚያስተምራቸው ክርስቲያኖች በሃይማኖት አባቶች የተወሰነ ቀኖናን ማስተማርና መስጠት እንዳለበት መጽሐፍ ቅዱስ እንዲህ ሲል ያስረዳል። “በየከተማውም ሲሄዱ፥ ሐዋርያትና ቀሳውስት በኢየሩሳሌም ያዘዙትን /የወሰኑትን/ ሥርዓት አስተማሯቸው። አብያተ ክርስቲያናትም በሃይማኖት ጸኑ። ዕለት ዕለትም ቁጥራቸው ይበዛ ነበር።” (ሐዋ. 16፥4-5)በዚህ የእግዚአብሔር ቃል መሠረት ቅዱስ ጳውሎስ ደርቤንና ልስጥራን በተባሉ ቦታዎች ለነበሩ ክርስቲያኖች ወንጌልን ከሰበከ በኋላ ሐዋርያት የወሰኑትን ቀኖና (ሥርዓት) እንደሰጣቸው እንረዳለን። ስለዚህ ቀኖና ወይም ሥርዓት ቤተ ክርስቲያንን ይጠቅማል እንጂ አይጎዳም። በመሆኑም ዶግማንና ቀኖናን ወይም እምነትንና ሥርዓትን ጎን ለጎን ይዞ መጓዝ ሐዋርያትን መከተል ነው። እንግዲህ ሥርዓተ ቤተ ክርስቲያንን የሚቃወሙ ሰዎች ሁሉ የሚቃወሙት በቀኖና (በሥርዓት) የሚመሩትን ክርስቲያኖች ሳይሆን የእግዚአብሔር ቃል የሆነ መጽሐፍ ቅዱስን በመሆኑ እንዳይሳሳቱ አደራ እንላለን።

ዶግማ እና ቀኖና

ቅዱስ ትውፊት (Holy Tradition)

 

ትወፊት ማለት ስጦታ፣ልማድ፣ትምህርት፣ወግ፣ታሪክ፣ሃይማኖት፣ሥርዓት፣ከጥንት ከአበው ሲያያዝ ሲወርድ፥ቃል በቃል ሲነገር የመጣ ማለት ነው ጽርዓውያንም “ፓራዶሲስ” ይሉታል፤አንድን ነገር እጅ በእጅ ለሌላ ሰው ማስረከብን ወይም ማቀበልንም ያመለክታል፡፡ዕብራውያን ደግሞ “ማሳር - ማቀበል” እና “ቂብል - መቀበል” የሚሉ ቃላትን ይጠቀማሉ፡፡
በቤተ ክርስቲያናዊ ትርጓሜው ስንመለከተው፥ትውፊት ማለት እግዚአብሔር ለሰው ልጆች በጠቅላላ በአበው፣በነቢያት፣በሐዋርያት፣በጳጳሳት፣በሊቃውንት፣በካህናት በኵል የሚያስተላልፈው ሕያው (ሕይወትን የሚሰጥ) ቃል ማለት ነው፡፡ይኽ ሕያው ቃል ቀደምት አበው ከእግዚአብሔር የተቀበሉትና ለቀጣዩ ትውልድ የሚያስተላልፉት፥ቤተ ክርስቲያንም በየጊዜው እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ የምትጠቀምበት ሕያው ትምህርት ነው፡፡

ክርስቲያናዊ ትውፊት (Christian Tradition) በብሉይ ኪዳን ከአበው ወደ መሳፍንት፣ከመሳፍንት ወደ ነገሥት፣ከነገሥት ወደ ነቢያት ሲተላለፍ ቆይቶ ኋላም በሐዲስ ኪዳን በጌታችን በኢየሲስ ክርስቶስ ትምህርት የተገለጠ፤ከክርስቶስ ወደ ሐዋርያት፣ከሐዋርያት ወደ ሐዋርያውያን አባቶች እና ወደ ተከታዮቻቸው ሰማእታት ከዚያም ለሊቃውንት በአፍ (Oral) እና በመጽሐፍ (Writen) እየተሸጋገረ ሲወርድ ሲዋረድ እስከዘመናችንም የደረሰ የክርስትና ትምህርት ነው።

በቅዳሴያችን ጊዜ ቄሱ “ነዋ ወንጌለ መንግሥት - መንግሥተ ሰማያትን የምትሰብክ አንድም ወደ መንግሥተ ሰማያት የምታገባ ወንጌል ይኽቺ ናት” ብሎ ለንፍቅ ካህኑ መስጠቱ፥ንፍቅ ካህኑም “መንግሥቶ ወጽድቆ ዘአወፈየኒ አወፈይኩከ - ጌትነቱንና ቸርነቱን የምትናገር የሰጠኝን ወንጌልን ሰጠኹኽ” ብሎ ለዲያቆኑ መስጠቱ ሐዋርያት ከሊቀ ካህናችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ወንጌልን ተቀብለው ለማስተማራቸው አምሳል ነውና ትውፊት ቅብብል፣ውርርስ መኾኑን በግልጽ ያሳያል /ሥርዓተ ቅደሴ 10፡53፣አንድምታው/፡፡ 

ትውፊት ሲባል ስላለፈ ነገር ብቻ የሚናገር፥ነገር ግን በአኹኑ ሰዓት ምንም ሕይወት እንደሌለው ተደርጐ የሚታሰብ አይደለም፡፡አኹንም ሕይወት ያለው ብቻሳ ይኾን ሕይወትንም የሚሰጥ ነው፡፡ለምሳሌ ትንሽ ቆይተን በስፋት እንደምንመለከተው፥መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ትውፊት አንድ አካል ነው፡፡ነገር ግን ስላለፈው ነገር ብቻ የሚናገር አይደለም፡፡አኹንም ሕይወትን የሚሰጥ ነው፡፡ስለዚኽ ትውፊትን መቀበል ያለፈውን ነገር የመጠበቅ ጕዳይ አይደለም ማለት ነው፤የሕይወት ጕዳይ እንጂ፡፡በሌላ አነጋገር የምንጠብቀው የሕይወት ጕዳይ እንደኾነ ስለሚገባን ነው ማለት ነው፡፡ 

እግዚአብሔር በዚኹ ቅዱስ ትውፊት ሲናገር ስላለፈው ነገር ብቻ ሳይኾን ሰለ አኹኑም ስለሚመጣውም ዘለዓለማዊ ሕይወት ነው፡፡ትውፊትን ቅዱስ ብለን መጥራታችንም የመንፈስ ቅዱስ ጥበቃ ስለማይለየው፥አንድም ከክርስቶስና ክርስቶስ አድሮባቸው ከሚኖር ከቅዱሳን ስለተገኘ ነው /Georges Florovsky; Bible, Church, Tradition: An Eastern Orthodox View; Vol.I; pp 46/፡፡ 

እንደ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን አስተምህሮ፥እግዚአብሔር ከፍጥረት መዠመሪያ አንሥቶ በጽሑፍም ያለ ጽሑፍም የገለጠውን እውነት የምናገኘው በቅዱስ ትውፊት ውስጥ ነው፡፡በመኾኑም የተጻፈውና ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ለድኅነታችን የሚኾን የእግዚአብሔርን መገለጥ የያዘ ስለኾነ እኵል አስፈላጊ ነው፡፡ 

መጽሐፍ ቅዱስ የቅዱስ ትውፊት አንዱ አካል ነው!!!
ምንም እንኳን መጽሐፍ ቅዱስ የመዠመሪያውን ስፍራ የሚይዝ  (የመዠመሪያ ስፍራ ይይዛል ስንልም ካልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት ይልቅ በቀላሉ ለስሕተት የማይጋለጥ በመኾኑ ነው፡፡ምክንያቱም በቀኖና አንዴ ተወስኖ የቀረበ ነውና፡፡በዚኽም ያልተጻፈው ቅዱስ ትውፊት የሚመዘንበት ሚዛን ነው፡፡) ቢኾንም፥ከሌላው የትውፊት አካል ግን ተነጥሎ የሚታይ አይደለም፡፡መጽሐፍ ቅዱስ እንዲኹ ጽሑፍ አይደለም፡፡ሊብራራና በሕይወት ሊተረጐም የሚገባው ነው፡፡ይኽም የሚኾነው የእውነት ዓምድና መሠረት በምትኾን በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ነው /1ኛጢሞ.3፡15/፡፡የሊቃውንተ ቤተክርስቲያን መጻሕፍት ይኽን መጽሐፍ በስፋትና በጥልቀት የሚተረጕሙ እንጂ እንደ ተጨማሪ የሚታዩ አይደሉም፡፡የቅዱሳኑ ገድላት በመጽሐፍ ቅዱስ የታዘዘውን እውነት በተግባር እንዴት እንደኖሩት የሚያሳይ ነው፡፡ሌላ ወንጌል አይደለም ማለት ነው፡፡ቅዱሳት ሥዕላቱ በኅብረ ቀለማትና በጥበባዊ መንገድ ነገረ እግዚአብሔርን ማንበብ ለማይችል ሰው የሚያብራሩ ናቸው፡፡ቅዳሴው፣ሥርዓተ ጸሎቱ፣የምሥጢራተ ቤተክርስቲያን አፈጻጸሙ፣ማዕጠንቱ፣እና የመሳሰለው ኹሉ ሥርዓተ አምልኮው የሚፈጸምበት መንገድ ነው፡፡ስለዚኽ መጽሐፍ ቅዱስ እና ሌላው ቅዱስ ትውፊት ርስበ ርሳቸው የሚደጋገፉ ናቸው፡፡አንዳቸው አንዳቸውን የሚተረጕሙ እንጂ የሚጣረሱ አይደሉም፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ ያልተጻፈው ሌላው ቅዱስ ትውፊት ነው የሚሞላው፡፡በመጽሐፍ ቅዱስ የተጻፈው እውነት ትክክለኛ ትርጕሙን የምናገኘው በሌላው ቅዱሱ ትውፊት ውስጥ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ከሰፊው የቤተክርስቲያን ትውፊት ዋና ዋናውን የያዘ እንጂ ብቻውን የቆመ አይደለም፡፡ወንጌል ከመጻፉ በፊት የነበረውንም ኹሉን በጽሑፍ የያዘ አይደለም /ዮሐ.20፡30-31/፡፡ስለዚ ኽመጽሐፍ ቅዱስ ያለ ትውፊት ብቻውን ፍጻሜ የለውም፤ሌላው ቅዱስ ትውፊትም ያለ መጽሐፍ ቅዱስ መሠረት የለውም፡፡በኦርቶዶክሳዊ አስተምህሮ ሌላውን ቅዱስ ትውፊት ከቅዱስ መጽሐፍ ጋር እኵል ሊቀበሉት የሚገባ የመለኮታዊ መገለጥ ምንጭ ነው ማለታችንም ከዚኹ የተነሣ ነው፡፡

ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ብሉይ
ትውፊት የምእመናን የዘወትር ሕይወት ነው፡፡በመኾኑም ትውፊት ሰው ከመፈጠሩ አንሥቶ የነበረ ነው፡፡እግዚአብሔር አዳምን፡- “መልካምንና ክፉን ከሚያስታውቀው ዛፍ አትብላ፤ከርሱ በበላህ ቀን ሞትን ትሞታለኽና” ብሎ ሲነግረው በጽሑፍ አልነበረም /ዘፍ.2፡17/፡፡አዳምና ሔዋን በገነት ለሰባት ዓመታት ሲኖሩ ይኽን ቅዱስ ትውፊት ጠብቀው ነው፡፡እግዚአብሔር ስይቅርና፥ሰይጣን እንኳን አዳምንና ሔዋንን ያታለላቸው በጽሑፍ አልነበረም፤ቅዱስ ባልኾነውና ከራሱ ካመነጨው ሐሰት እንጂ /ዘፍ.3/፡፡
ቅዱሱ ትውፊት በአቤል በኵል ሲቀጥል፥ዲያብሎስ ያስተዋወቀው ቅዱስ ያልኾነው ትውፊትም በቃየን በኵል ቀጥሏል፡፡የአቤልና የቃየን ትውፊት ግን በቃል እንዲኹም በግብር እንጂ በጽሑፍ የወረሱት አልነበረም /ዘፍ.4/፡፡
ኄኖክ አካሔዱን ከእግዚአብሔር ጋር አድርጐ ሞትን ሳይቀምስ የሔደው በቅዱሱ ትውፊት ሥርዓት መሠረት ስለኖረ ነው፡፡ኖኅ በዚያ ኀጢአት በነገሠበት ዘመን ጻድቅ ኾኖ የተገኘው፥ባልተጻፈው በቅዱሱ ትውፊት እንጂ ከእግዚአብሔር በጽሑፍ ያገኘው ነገር ስለነበረ አይደለም፡፡ኖኅ ንጹሐንና ንጹሐን ያልኾኑትን እንስሳት ለይቶ ያወቀው በጽሑፍ አልነበረም፡፡አብርሃም እግዚአብሔርን አምኖ ከቤተሰቡ ተለይቶ ሲወጣም በጽሑፍ አይደለም፡፡ኖኅ፣አብርሃም፣ይስሐቅና ያዕቆብ ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ይሠዉ ነበር፡፡ነገር ግን በጽሑፍ የተሰጣቸው መመሪያ ስለ ነበረ አይደለም፡፡ዮሴፍ በእግዚአብሔር ፊት ኀጢአት ማድረግ እንደማይገባ የተማረው ከቅዱስ ትውፊት በቃል እንጂ በጽሑፍ አይደለም፡፡በአጠቃላይ፥ሊቀ ነቢያት ሙሴ በ1500 ከክርስቶስ ልደት በፊት ተነሥቶ መጽሐፍ እስኪጽፍ ድረስ፥የእግዚአብሔር ሰዎች ከ4000 ዓመታት በላይ ሲመሩ የነበረው በጽሑፍ ሳይኾን በቃልና በተግባር በሚገለጠው ቅዱስ ትውፊት ነበር፡፡

ቅዱስ ትውፊት በዘመነ ሐዋርያት
በዘመነ ሐዲስ ያለውን ስንመለከትም፥ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከሦስት ዓመት በላይ ሕዝቡን ደቀ መዛሙርቱን ያስተምር የነበረው በጽሑፍ አልነበረም፡፡ቅዱሳን ሐዋርያትም ከጌታችንና ከመድኃኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ የተቀበሉት በወረቀት የተጻፈ ነገር አልነበረም፡፡ወንጌላውያን ከጌታ በቃል ተምረው በተግባር አይተው ኋላ የሚጽፉትን እየዞሩ አስተማሩ እንጂ አስቀድመው ጽፈው ጠቅሰው አላስተማሩም፡፡መጻሕፍት መጻፍ የተዠመሩት፥ቤተ ክርስቲያን በይፋ ከተመሠረተች ከ8 ዓመታት በኋላ ነው (ከሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት መዠመሪያ የተጻፈው መጽሐፍ የማቴዎስ ወንጌል ሲኾን ይኸውም በ41 ዓ.ም. ላይ ነው)፡፡እስከዚኽ ጊዜ ድረስ ቤተክርስቲያን ስትመራ የነበረው በቃልና በተግባራዊ ምልልስ ሲተላለፍ በነበረው ቅዱስ ትውፊት ነው፡፡በሌላ አገላለጽ ወንጌል ከመጻፉ በፊት፥ቤተ ክርስቲያን ወንጌልን በቅዱስ ትውፊት ታውቋለች፡፡ወንጌልን ስትኖረው ነበረች፡፡ 

ከጌታችን ጋር ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከዋለበት እየዋሉ፣ካደረበት እያደሩ ሲያስተምር፣ሲጸልይ፣ሰዎችን ሲያጽናና፣ድውያነ ሥጋን በተአምራት ድውያነ ነፍስንም በትምህርት ሲፈውስ፣ሙታነ ሥጋንና ሙታነ ነፍስን ሕይወት ሲሰጣቸውዐ ይተዋል፤ሰምተዋል፡፡ሥርዓተ ብሉይን አሳልፎ ሥርዓተ ሐዲስን ሲሠራ ተመልክተዋል፡፡ነገር ግን ይኽን ኹሉ በትውፊት ለተላውያነ ሐዋርያት (Apostolic Fathers - ተላውያነ ሐዋርያት የሚባሉት ከሐዋርያት በቀጥታ የተማሩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡) አስረከቡት እንጂ፥እነርሱ ራሳቸው እንደነገሩን ኹሉንም አልጻፉልንም፡፡የጻፉልን እጅግ ጥቂቱን ብቻ ነው /ዮሐ.21፡25፣ 1ኛዮሐ.1፡1/፡፡ “እንድጽፍላችኁ የምፈልገው ብዙ ነገር ሳለኝ በወረቀትና በቀለም ልጽፈው አልወድም፡፡ዳሩ ግን ደስታችኁ ፍጹም እንደኾነ ወደ እናንተ ልመጣ አፍለ አፍም ልነግራችኁ ተስፋ አደርጋለኹ” እንዲል /2ኛዮሐ.12፣ 3ኛዮሐ.13-14/፥እንኳንስ የጌታችን ይቅርና እነርሱ ራሳቸው ያስተማሩትን ትምህርት ያደረጉትንም ተአምራት በሙሉ አልጻፉልንም፡፡በጽሑፍ የጻፉትም ቢኾን በቃል ያስተማርዋቸውን ምእመናን እንዲጸኑበትና አንዳንድ ቢጽሐሳውያን (ሐሰተኛ ወንድሞች) እውነቱን አዛብተው መጻፍ ስለዠመሩ እንዳይታለሉ ለመጠበቅ ጥቂቱን ነው /ሉቃ.1፡2/፡፡ዋናው መሠረታቸው ግን ከላይ እንደገለጽነው በቃልና በተግባራዊ ሕይወት የተማሩት ትምህርት ነው፡፡

ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት እያልነው ያለ ነው፥እንዲኽ ዓይነቱን በገቢርና በቃል ዕለት ዕለት በቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት የሚገለጠውና አንድ ጊዜ ለቅዱሳን የተሰጠውን ሃይማኖት ነው /ይሁዳ ቁ.3/፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ይኽን በማስመልከት ሲናገር እንዲኽ ይላል፡- “ለእናንተ ደግሞ አሳልፌ የሰጠኁትን እኔ ከጌታ ተቀብያለኹና” /1ኛቆሮ.11፡23/፡፡ከዚኽ የሐዋርያው ቃል እንደምንረዳው፥ቅዱስ ትውፊት ማለት አንዳንድ የተሳሳቱ ሰዎች እንደሚሉት የአሮጊቶች ተረትተረት ወይም ከሰው የተገኘው ርስ ሳይኾን መለኮታዊ ስጦታ እንደኾነ ነው፡፡ “ትጸኑ ዘንድ መንፈሳዊ ስጦታ እንዳካፍላችኁ ላያችኁ እናፍቃለኹና” /ሮሜ.1፡11/፡፡

የቅዱስ ትውፊት ዋና ማዕከሉ ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡በሌላ አገላለጽ ቅዱስ ትውፊት ወንጌል ነው፡፡በዘመነ ብሉይ ቢነገር ይወርዳል ይወለዳል ብሎ ነው፤በዘመነ ሐዲስ ቢነገር ደግሞ ወረደ ተወለደ ብሎ የምሥራችን ለትውልድ ኹሉ በቃልም፣በገቢርም፣በጽሑፍም የሚያውጅ ነው፤ቅዱስ ትውፊት፡፡ “ወንድሞች ሆይ! የሰበክኁላችኁን ደግሞም የተቀበላችኁትን በርሱም ደግሞ የቆማችኁበትን በርሱም ደግሞ የምትድኑበትን ወንጌል አሳስባችኋለኹ፡፡በከንቱ ካላመናችኁ በቀር ብታስቡት በምን ቃል እንደሰበክኁላችኁ አሳስባችኋለኹ፡፡እኔ ደግሞ የተቀበልኹትን ከኹሉ በፊት ሰጠኋችኁ” እንዲል /1ኛቆሮ.15፡1/፡፡

ቅዱስ ትውፊት በሊቃውንት አስተምህሮ
ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ምስለ ቅዱስ ትውፊት ምንነት እጅግ ሰፊ የኾነ ትምህርትን አስተምረዋል፡፡ጥቂቶቹን ብቻ ለመጠቈም ያኽልም፡-
“በትወፊት አርባዕቱ ወንጌልን አወቅኁ፤እነርሱም እውነቶች ናቸው፡፡” / Origen, (cc Fr. Tadros Y. Malaty) Tradition and Orthodoxy, pp 18/
“ሐዋርያት ‘በቃል በመናገርም እንጂ በጽሑፍ ብቻ እንዳላስተማሩ በቃላችንም ቢኾን ወይም በመልዕክታችን የተማራችኁትን ወግ (ትውፊት) ያዙ’ በማለት ቅዱስ ጳውሎስ የተናገረው ቃል ያመለክታል፡፡ኹለቱም ማለት የተጻፈውና ያልተጻፈው ለትምህርተ ሃይማኖትና ለድኅነት አስፈላጊዎች ናቸው፡፡ስለዚኽ የቤተክርስቲያን ትውፊት መታመን የሚገባው መኾኑ እውነት ነው፡፡” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፥ 2ኛተሰ. 2፡15ን ሲተረጕም/
“በቅድስት ቤተክርስቲያን ተጠብቀው ካሉት ትምህርተ ሃይማኖትና ስብከቶች አንዳንዶች በጽሑፍ፥ሌሎች ግን በሐዋርያት ትውፊት የተሰጡን ናቸው፡፡ኹለቱም ተመሳሳይ ሥልጣን አላቸው፡፡ስለ ቤተክርስቲያን መቋቋም በጥቂቱም ቢኾን የሚያውቅ ሰው ይኽን ሊቃወም አይችልም፡፡ያልተጻፉትን ልማዶች ኹሉ ተገቢ እንዳይደሉ በቁጥር ብንጥላቸው በጣም አስፈላጊ የኾኑ የወንጌል ክፍሎችን እናጣለን፡፡ትምህርታችንም ባዶ ይኾናል፡፡” /አውሳብዮስ ዘቂሳርያ፣በእንተ መንፈስ ቅዱስ 27፡66/
“በኢየሱስ ክርስቶስ የሚያምኑ ኹሉ በትእምርተ መስቀል እንዲያማትቡ የትተጻፈ? በምንጸልይበት ጊዜፊታችንን ወደምሥራቅ ማዞር እንዳለብን የትተጻፈ? ወይኑንና ኅብስተ ቁርባኑን እንዲለውጥልን መንፈስ ቅዱስን ስለመጠየቅ (ስለቅዳሴ) ማንጻፈ? በዚኽ መሠረት ወንጌል ወይም የሐዋርያት መጽሐፍ በጠቀሱት ብቻ አንወሰንም፡፡በመስማትም የተማርነው ብዙ ነገር አለና፡፡” /ዝኒከማኁ/
“ለጥምቀት አገልግሎት ውኃን እንባርካለን፡፡ተጠማቂውን ለመቀባት ዘይት እንባርካለን፡፡ይኽ ኹሉ የትተጻፈ? ይኽን የተማርነው በምስጢራዊው ትውፊት አይደለምን? በሜሮን እንድንቀባ የት ተጻፈ? ተጠማቂው 3 ጊዜ ብቅ ጥልቅ ማድረግ የት ተጻፈ? ከጥምቀት ጋር ግኑኝነት ያላቸው ሌሎች ነገሮች፥ሰይጣንንና መላእክቱን መካድ የት ተጻፈ?” /ዝኒ ከማኁ/
እንደዚኹም መሠረተ ሐሳቡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ቢኖርም ስለ ሕፃናት ጥምቀት የሐዋርያት ትውፊት ነው፡፡ስለ እመቤታችን ስለ ቅድስት ድንግል ማርያም ዕረፍትና ትንሣኤ እንዲኹም ፍልሰት የምናስተምረው ትምህርት ኹሉ ከሐዋርያት ትውፊት የተገኘ ነው፡፡
መጽሐፍ ቅዱስን ስንተረጕም እንኳን የቅዱሳን አበውን አስተምህሮ የምንጠቅሰው የመጽሐፍ ቅዱስን ትክክለኛ ትርጕም የምናገኘው በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ስለኾነ ነው፡፡በዚኹ ዙርያ “ኦርቶዶክሳዊ ቅዱሳት መጻሕፍት አተረጓጐም ስልት” በሚል ርእስ በቀጣይ የምንመለስበት ይኾናል፡፡ 

ቅዱስ ትውፊት፥ቅዱስ ካልኾነው ትውፊት እንዴት ይታወቃል?
በቤተ ክርስቲያን ያለው ኹሉም በትውፊት የተገኘ ላይኾን ይችላል፡፡እያንዳንዱ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የሚገኘው ነገርም የቤተ ክርስቲያኒቱ መሪ መንፈስ ቅዱስ የሰጣት ነው ማለት አይደለም፡፡አንዳንድ ሰዋዊ ነገሮች ንልናገኝ እንችላለን፡፡ነገር ግን እነዚኽ ከሰው የኾኑ ነገሮች በራሳቸው ኀጢአት ወይም ስሕተት ላይ ኾኑይ ችላሉ፡፡ይልቁንም ለዋናው የቤተክርስቲያኒቱ ቅዱስ ትውፊት ማቀላጠፊያ ወይም ማስተላለፊያ መንገዶች ሊኾኑ ይችላሉ፡፡ለምሳሌ ድምጽ ማጉያ፣መቅረጸ ድምጽ፣ሲዲ፣ዲቪዲ፣እና የመሳሰሉት መጥቀስ ይቻላል፡፡ስለዚኽ ዋናውን የቤተክርስቲያኒቱ ትውፊትና ጊዜአዊው ማቀላጠፊያውን ለይተን ልናውቅ ይገባናል፡፡ 

ቤተ ክርስቲያን ማለት የክርስቲያኖች ጉባኤ እንደ መኾኗ መጠን፥እነዚኽ ክርስቲያኖችም በተለያ የግብረ ዓለም ሊያዙ ስለሚችሉ ይኽን የዓለም ሥራ ይዘው ቢመጡና ግብራቸውን በቤተክርስቲያን ውስጥ ቢያሠርፁ፥ይኽ ክፉ ግብር እንደ ቤተክርስቲያን ትውፊት ሊቈጠር አይገባውም፡፡
በመኾኑም ለቅዱስ ትውፊት ቀኖናዊ መመዘኛ እንዳለው ተረድተን ቅዱሱን ትውፊትና ቅዱስ ያልኾነውን ትውፊት ለይተን ልናውቅ ይገባናል /2ኛተሰ.2፡15/፡፡ትውፊት ኹሉ ከሐዋርያት ተያይዞ የመጣና ሐዋርያዊና ቤተክርስቲያናዊ ይዘት ያለው መኾን አለበት፤ከጥንት ዠምሮ በየትም ቦታ፥ኹልጊዜ በዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን የታመነ የተጠበቀና በተግባር ላይ የዋለ መኾን አለበት፤በዓለም አቀፋዊት ቤተክርስቲያን ዘንድ መለወጥና መቋረጥያልተደረገበትመኾንአለበት፡፡ 

እንደ ኦርቶዶክሳዊት ቤተክርስቲያን አስተምህሮ ሃይማኖት የሚቀበሉት ተቀብለውም የሚኖሩት ለቀጣዩ ትውልድም ሳያፋልሱ የሚያስተላልፉት እንጂ በየጊዜው የሚጨመርበት ወይም የሚቀነስበት አይደለም፡፡በፕሮቴስታንቱ ዓለም ደግሞ ከካቶሊካውያኑ ፍጹም ተቃራኒ በመኾን ቅዱስ ትውፊትን አንቀበልም ይላሉ፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ብቻውን በቂ እንደኾነ ያስተምራሉ፡፡ነገር ግን ይኽም ቢኾን ፍጹም የተሳሳተ ትምህርትነው፡፡አንድ ቀላል ምሳሌ እናንሣና ትምህርታቸው ምን ያኽል ስሕተት እንደኾነ እናሳይ፡፡እሑድን እንደ ጌታ ቀን አድርገው ያከብራሉ፡፡በብሉይ ኪዳን እንዲከበር የታዘዘው ግን ቅዳሜ ነው /ዘጸ.20፡8/፡፡ቅዳሜን ትተው እሑድን ማክበር ከየት አገኙት? ዳግመኛም የጌታችንን ልደት፣ጥምቀት፣ትንሣኤ እንዲኹም በዓለ ኃምሳ አብረዉን ያከብራሉ፡፡ነገር ግን ይኽን በተመለከተ መጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም አናገኝም፡፡ሌላ ጥያቄ እንጨምር፡፡ወደ ዓለም ኹሉ የተሰማሩት ሐዋርያት 12 መኾናቸውን ወንጌል ይነግረናል፡፡ነገር ግን ኹሉም ጽሑፍ አልጻፉም፡፡አላስተማሩም ማለት ግን አይደለም፡፡ታድያ ትምህርታቸው የት አለ? ትምህርታቸውን የምናገኘው በአንዲቱ ቤተ ክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ውስጥ ብቻ ነው፡፡

ስለዚኽ ቅዱስ ትውፊት መቀበል ግድ ነው፡፡ለምን? የትናንቱን የቤተክርስቲያን ኹለንተናዊ ሕይወት ወደ ዛሬ የሚያመጣ፥ዛሬ ላይ ያለውንም ወደ ነገ የሚያሻግር ቅዱስ ትውፊት ነውና፡፡ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ “የርሱን ግርማ ዐይተን እንጂ በብልሐት የተፈጠረውን ተረት ሳንከተል የጌታችንን የኢየሱስ ክርስቶስን ኃይልና መምጣት አስታወቅናችኁ” እንዳለ /2ኛጴጥ.1፡16/ ቅዱስ ትውፊት ሲባል እንዲኹ ከሰው የተገኘ ተረት ተረት እንዳልኾነ ልንረዳ ያስፈልጋል፡፡አለበለዚያ በትውፊት ያገኘነው መጽሐፍ ቅዱስም ተረት ተረት ማለታችን ነውና፡፡

ዳግመኛም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ “ወንድሞች ሆይ! በኹሉ ስለምታስቡኝና አሳልፌ እንደሰጠኋችኁ ወግን ፈጽማችኁ ስለያዛችኁ አመሰግናችኋለኹ” እንዳለን /1ኛቆሮ.11፡2/ የመጽሐፍ ቅዱስ አባት ራሱ ቅዱስ ትውፊት እንደኾነ ልናውቅ ይገባናል፡፡ “Sola Scriptura - መጽሐፍ ቅዱስ ብቻ” በሚለው የአንዳንዶች ስሕተትም ራሳችንንና ወንድማችንን ልንጠብቅ ይገባናል፡፡

ቅዱስ ትውፊት

ሀልዎተ እግዚብሔር(የእግዚአብሔርን መኖር)

ሀልዎተ ማለት ሀለወ ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ሲሆን ትርጉሙም መኖር ማለት ነው፡፡ስለዚህ ሀልዎተ እግዚአብሔር ማለት የእግዚአብሔር መኖር አኗኗር የምንረዳበት ትምህርትነው፡፡

እግዚአብሔር የማይመረመር ረቂቅ፣በዚህ ጊዜ ተገኘ የማይሉት ቀዳማዊ፣በዚህ ጊዜ ያልፋል የማይሉት ድኃራዊ፣ዓለምን ካለመኖር ወደ መኖር አምጥቶ የፈጠረ፣ዳግመኛም ዓለምን ከመኖር ወደ አለመኖር አሳልፎ የሚኖር ኃያል፣ፈጥሮ የሚገዛ ጌታ ነው፡፡ሰውን ጻድቅ ቢሉት ሐሰት፣ሀብታም ቢሉት ድኅነት፣ኃያል ቢሉት ድካም ይሰማዋል፡፡እሱ ግን ሐሰት የሌለበት ጻድቅ፣ድኅነት የሌለበት ባለጠጋ፣ድካም የሌለበት ኃያል ነው፡፡
“መጠኑ ይኽን ያክላል፤መልኩ ይኽን ይመስላል” ብሎ ልክና መልክ ሊሰጠው አይችልም፡፡ከነቢያት እስከ ሐዋርያት፣ከሐዋርያት እስከ ሊቃውንተ ቤተክርስቲያንም ይኽን እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ እንደ አንድ ልብ መካሪ ኾነው ተናግረዉታል፡፡

ለምሳሌ፡-
1.“የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር ልትመረምርት ችላለኽን? ወይስ ኹሉን የሚችል አምላክ ፈጽመኽ ልትመረምር ትችላለኽን? ከሰማይ ይልቅ ከፍ ይላል፤ምን ልታደርግት ችላለኅ? ከሲኦልም ይልቅ ይጠልቃል፤ምን  ልታውቅ ትችላለኅ? ርዝመቱ ከምድር ይልቅ ይረዝማል፥ከባሕርም ይልቅ ይሰፋል፤” /ኢዮብ.11፡7-11/፡፡

2. “የእስራኤል አምላክ መድኃኒት ሆይ! በእውነት አንተ ራስኽን የምትሰውር አምላክ ነኅ” /ኢሳ.45፡15/፡፡

3.“የእግዚአብሔር ባለጠግነትና ጥበብ ዕውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው፤ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው፥ለመንገዱም ፍለጋ የለውም።የጌታን ልብ ያወቀው ማን ነው? ወይስ አማካሪው ማን ነበር? ወይስ ብድራቱን ይመልስ ዘንድ ለርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው? ኹሉ ከርሱና በርሱ ለርሱም ነውና፤ለርሱ ለዘለዓለም ክብር ይኹን፤አሜን፤” /ሮሜ.11፡33-36/፡፡

4. “ብቻውን አምላክ ለሚኾን ለማይጠፋው ለማይታየውም ለዘመናት ንጉሥ ምስጋናና ክብር እስከ ዘላለም ድረስ ይሁን፤አሜን፤” /1ኛጢሞ.1፡17/፡፡

5. “ርሱ ብቻ የማይሞት ነው፤ማንም ሊቀርበው በማይችል ብርሃን ይኖራል፤አንድ ሰው እንኳ አላየውም ሊያይም አይቻለውም፤ለእርሱ ክብርና የዘላለም ኃይል ይኹን፤አሜን፤” /1ኛጢሞ.6፡16/፡፡

6. “ሕሊና የማይመረምሩትና (የሚረቅና) ያልተፈጠረ የፈጣሪን ምሥጢር እንደ ምን ማወቅ ይቻለናል?” /ጐርጐርዮስ ገባሬ መንክራት፣ሃይ.አበ.13፡16/፡፡ 

7. “መላዕክትና የመላዕክት አለቆች ኹሉ በየወገናቸው በየሥርዓታቸው ፍጡራን ከኾኑት ኹሉ ጋር አንድ ላይ በአንድነት ቢሰበሰቡ የእግዚአብሔርን ህላዌ በጥቂቱ ስንኳ ሊያገኙትአይችሉም” /ባስልዮስዘቂሣርያ፣ሃይ.አበ.33፡14/፡፡

8. “እግዚአብሔር በሰው ልጅ ሕሊና አይመረመርም፡፡የሰው አስተሳሰብ መለኮትንና ህላዌ መለኮትን መርምሮ ማወቅ አይችልም፡፡የመለኮት ህላዌ ከሰው ልጅ አስተሳሰብ የራቀ ነውና፡፡ከሐሳቦች ኹሉ ይልቅ በጣም ከፍ ከፍ ያለ ነውና፤” /ቴዎዶጦስ ዘዕንቆራ፣ሃይ.አበ.53፡2/፡፡

9.“አንደበት የርሱን ነገር እንደሚገባ አድርጐ መናገር አይቻለውም፡፡አፈሕሊና (የሕሊና አንደበት) ሊጠራው እዝነል ቡናም (የልቡ ናዦሮ) ሊሰማው አይቻለውም፡፡አንደበትስ ተወውና ከርሱ የሚበልጥ ሕሊና ልብ እንኳ ከጌታ ነገር ማናቸውንም ማወቅ መረዳት አይቻለውም፤” /ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ፣የዕብራውያን መልዕክት ትርጓሜ፣ድርሳን 2፡6-9/፡፡

10.“ሰውሆይ!ፍጥረታት ለማይመስሉት በምን ታመሳስለዋለኽ? የማይታሰበውንስ እንዴት አድርገኽ ልታስበው ትቃጣለኽ? በፍጡራን ሊያስተካክሉት የሚገባ አይደለም፡፡በምንም በማናቸውም ስለ ግርማው በመብረቅ፣ከፍተኛ ስለኾነው ብርሃኑ በፀሐይ፣ስለልዕልናው በሰማይ፣ስለስፋቱ በምድር፣ስለ ጥልቀቱ በባሕር፣እሳትስ ለማቃጠሉ በእሳት፣ስለርቀቱና (ረቂቅነቱና) ስለፍጥነቱ በነፋስ፣ወይም በማናቸውም ቢኾን የእውነት አምላክን መለኮትነት ሊያስረዳ ይችላል ተብሎ አይታሰብም፡፡ይኽ ለፍጥረት ያልተሰጠውና፣በምንም በማናቸውም ኹኔታውን ለመረዳት አይቻልም፡፡ስለዚኽም ኹኔታውን ለመመርመር አይቻልም፤” /ርቱዐሃይማኖት /፡፡

11.“በመመርመር ያገኘው የለም፤መርምሮ የሚያገኝኽ የለም፡፡በባሕርይኽ መርምሮ የሚያውቅኽ የለም፡፡በርቀት (በረቂቅነትኽ) አንተንማ የት የሚቻለው የለም፤ባሕርይኽን አንተ ታውቀዋለኽ እንጂ፤” /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡4-5/፡፡

12. “በሕሊና ተመርምሮ የማይገኝ ረቂቅ ነው፤በልቡና ተመርምሮ የማይገኝ ምጡቅ ነው፡፡ በተልዕኮ የሚኖሩ መላዕክት የማይመረምሩት በተሰጥሞ (በተመስጦ) የሚኖሩ ጻድቃን የማይመረምሩት ረቂቅ ነው፤” /ቅዳሴ ኤጲፋንዮስ፣ 1፡6/፡፡

“ፍጡር አስቦ ሊደርስበት አይችልም፤መርምሮም ሊያውቀ ውአይችልም፤” ማለት ግን እግዚአብሔር የለም ማለት አይደለም፡፡ወይም ደግሞ እግዚአብሔር ለሰዎች መገለጥን የማይወድ ዐይነ አፋር ነው ማለት አይደለም፡፡ይልቁንም እግዚአብሔር ህላዌውን (መኖሩን) እንዲኽ የሰወረው ስለ ብዙምክንያት ነው፡፡ጥቂቶቹን ለመግለጥ ያኽል፡-

1.ሰዎች ወድደውና ፈቅደው እንዲፈልጉት ፈቃዱ ስለኾነ፤


ለዚኽም ኹላችንም ርሱን እንድንፈልግ የምንገደድበት አዕምሮ በልቡናችን ውስጥ አሳድሯል /ሮሜ.2፡14-16/፡፡የሥነ ፍጥረት ውበትና ሥርዓት እንዲኹም አቀማመጥ እየተመለከትን ይኽን ያደረገ ማን እንደኾነ እንድንመራመር የአዕምሮ ሕግ ሰጥቶናል፡፡ለምሳሌ አንድ ሰው “አካላዊ አቋሜን ካለመኖር ወደ መኖር ያመጣኹት እኔ ነኝ፤እኔው ራሴ ራሴን ፈጠርኩ፤ከሌላ ቦታ ይልቅ አኹን ባለኹበት ቦታ ለመኖር ራሴ መረጥኩ” ለማለት እስካልደፈረ ድረስ ፈጣሪውን ለመፈለግ ይገደዳል፡፡እያንዳንዳችን ለአካላዊአ ቋማችን አየር፣ምግብ፣ልብስ፣ብርሃን፣ጤና ማግኘት አለብን፡፡ነገር ግን “እነዚኽን አስፈላጊ ነገሮች ካለ መኖር ወደ መኖር ያመጣኋቸው እኔ ነኝ” ለማለት እስካልደፈርን ድረስ ፈጣሪያችንን ለመመርመር እንገደዳለን፡፡ዳግመኛም በሥጋችን የጤና ጕድለት፣ረሃብ፣ጥም፣እርዛት፣የተፈጥሮ መዛባት (ለምሳሌ ድርቅ፣ውርጭ፣በረዶ…)፣እኛን የሚያጠቁ አውሬዎች ሲያስፈራሩንና ሲያሰቃዩን እናያለን፡፡በደመ ነፍሳችንም ኀዘን፣ጭንቀት፣መከራ፣ሥቃይ፣ፍርሐት፣ኃፍረት፣ውርደት፣ጥቃት ይደርስብናል፡፡በመንፈሳችንም የኃጢአተኝነት፣የበደለኝነት፣ለኃጢአታችን የሚከፈል ዕዳ እንዳለብን እናስባለን፡፡ “ከዚኽ ኹሉ ማን ያስመልጠኛል? ማን ይታደገኛል?” ስንል ፈጣሪያችንን እንድንፈልግ እንገደዳለን፡፡እነዚኽ ከላይ የጠቀስናቸው ምሳሌዎች በጭራሽ የማንክዳቸው እውነቶች ናቸው፡፡ለዚኽም ነው ሐዋርያው ጳውሎስ፡- “ምናልባትም እየመረመሩ ያገኙት እንደኾነ፥እግዚአብሔርን ይፈልጉ ዘንድ በምድር ኹሉ ላይ እንዲኖሩ የሰውን ወገኖች ኹሉ ከአንድ ፈጠረ፥የተወሰኑትንም ዘመኖችና ለሚኖሩበት ስፍራ ዳርቻ መደበላቸው።ቢኾንም ከእያንዳንዳችን የራቀ አይደለም” ያለው /ሐዋ.17፡26-27/፡፡ነገር ግን ኹሉም ሰው ፈጣሪውን አግኝቶታል ማለት አንችልም፡፡ለዚኽ ዋና ምክንያቱ ደግሞ ብዙዎች አስተሳሰባቸውን ከትክክለኛው መንገድ ይልቅ በአሳሳችና ቅያስ ጐዳና ስለለወጡ ነው፡፡አንዳንዶች ምንም ማድረግ በማይችሉ ፍጥረታት ይደገፋሉ፡፡አንዳንዶች በአዕምሮአቸው በፈጠሩት ሌላ ፈጣሪ (ያውም ኅሊናቸው ውስጥ ካልኾነ በቀር ህልውናና አቋም የሌለው) ይደገፋሉ፡፡ “እግዚአብሔር ስለገለጠላቸው፥ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና።የማይታየው ባሕርይ ርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ዠምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ኾኖይታያልና፤ስለዚኽም እግዚአብሔርን እያወቁ እንደእግዚአብሔርነቱ መጠን ስላላከበሩትና ስላላመሰገኑት የሚያመካኙት አጡ፤ነገር ግን በአሳባቸው ከንቱ ኾኑ የማያስተውለውም ልባቸው ጨለመ” /ሮሜ.1፡19-20/።

2.እግዚአብሔር በእግዚአብሔርነቱ የማይወሰን፥የፍጡራን የተፈጥሮ አቋም፣ዐቅምና ችሎታ ግን የተወሰነ ወይም የተመጠነ ስለኾነ፤


በግዘፍ ያለና በችሎታው ውሱን የኾነው የሰው አቋም የማይታየውንና የማይወሰነውን መለኮታዊ ባሕርይን መጨበጥና መወሰን አይችልም፡፡ይኸውም ሊቁ አባ ሕርያቆስ፡- “ይኽን ባሰብኍ ጊዜ ሕሊናዬ ወደ ላይ ሊወጣና ተሠውሮም ወጥቶ ሕያው የኾነ ጌታ የሚሠወርበት መጋረጃን ሊገልጥ ይፈቅዳል፡፡ወዲያውም ከሚነድ እሳት ይፈራና የአየራት ግማሽ እንኳ ሳያጋምስ (ሳይደርስ) ይቀራል፡፡ይኽን ባሰብኍ ጊዜም ሕሊናዬ በነፋስ ትከሻ ሊጫንና ወደ ምሥራቅና ወደምዕራብ፣ወደ ሰሜንና ወደ ደቡብ፣ወደ ዳርቻዎችም ኹሉ ሊበር ይፈልጋል፡፡በኹሉም አከባቢና በኹሉም ዘንድ ሊጋልብ ይፈቅዳል፡፡ዳሩ ግን መቀጠል ይሳነውና መዠመሪያ ወደ ነበረበት አቋም ይመለሳል” በማለት እንደ መሰከረው ከዐቅምና ከችሎታ ማነስ የሚመጣ መሳን (አለመቻል) ነው /ቅዳሴ ማርያም፣ቁ.85-88/፡፡ካለ መቻላችን የተነሣ እግዚአብሔርን ስላላወቅነው ግን፥አስቀድመን እንደ ተናገርን የለም አንለውም፡፡ይኸውም አንድ ማየት የተሳነው ሰው ፀሐይን ስላላያት የለችም እንደማይላት ማለት ነው፡፡የእግዚአብሔርስ ይቅርና የፍጡራንን ህላዌ ጨርሶ ሊመርምር የቻለ የለም፤ደግሞም አይችልም፡፡ስለ ፀሐይ ማን ያውቃል? ስለ ከዋክብት ማን ያውቃል? ሰውስ  ማወቅ ካልተቻለውማ ስለ ፈጣሪያቸው እንደ ምን ማወቅ ይችላል? ስለነዚኽስ ይቅርና ስለ ገዛ ሕሊናው ምን ያውቃል? ስለ ገዛ ሕሊናው ማወቅ ካልቻ ለሕሊናን ስለፈጠረማ እንደምን ይችላል?

3.ሰው ኹሉ በአዳም በደል ምክንያት ትክክለኛ የማሰብ ችሎታው ስለተበላሸበትና ስለወደቀበት፥ራሱም ከሰይጣን ገዢነት ሙሉለሙሉ ስላልተላቀቀ በተጣራ አዕምሮ እግዚአብሔርን ሊፈልግና ሊመረምር ዐቅም የለውም፡ታድያ የእግዚአብሔርን መኖር የምናውቀው እንዴት ነው?


ምንም እንኳን ነባቤ መለኮት ቅዱስ ዮሐንስ “ጌትነትኅ በአንተ ዘንድ የተሠወረ ነው፤አንተ በአንተ አለኽ፤ራስኽን ለራስኽ መጋረጃ አድርገኽ ትኖራለኽ፡፡ራስኽን በራስኽ ትሠውራለኽ” እንዳለው እግዚአብሔር ከሕሊናት (ከምናስበው) በላይ ቢኾንም፥ጭራሽ ልናገኘው አንችልም ማለት ግን አይደለም /ቅዳሴ ዮሐንስ ወልደ ነጐድጓድ፣ 1፡13/፡፡አስቀድመን እንደተናገርን ሰው ልቡናው ውስጥ በተቀመጠለት የመሻት አዕምሮው ተመርቶ ፈጣሪውን ቢፈልግ ያገኟል፡፡ሊቃውንቱ “እግዚአብሔር በመሔድ አይገኝም፤ቢፈልጉት ደግሞ አይታጣም” ያሉትም ስለዚኹ ነው /ቅዳሴ ሠለስቱ ምዕት፣ገጽ 291፣ቁ.11/፡፡በመሔድ አይገኝም ማለት በሳይንስ፣በመመራመር፣በፍልስፍና፣በሙከራ፣በዳሰሳ አይገኝም ሲሉ ነው፡፡ታድያ እንዴት ነው የሚገኘው?

-እግዚአብሔር ራሱ ለሰው ከሚሰጠው የራሱን መገለጥ፤


ይኸውም “ሥጋና ደም ይኽን አልገለጸልኽም፤ነገር ግን በሰማያት የሚኖር አባቴ ይኽን ገልፆልኻልና” እንዳለው ነው /ማቴ.16፡17/፡፡ፍጥረት ኹሉ ለርሱ የተፈጠረ ነውና፥ፍጥረት እንዲያውቀው ምራሱን ይገልጥለታል ማለት ነው (ኹሉ ከርሱ፣በርሱ፣ለርሱ የተባለውም ይኽንኑ ነው)፡፡አዳም /ዘፍ.3፡9-10/፣ኖኅ /ዘፍ.7፡1/፣አብርሃም /ዘፍ.18፡27/፣ሙሴ /ዘጸ.3፡6/፣ነቢያት /ኢሳ.6፡1-6፣ዕንባ.3፡2/፣ሐዋርያት የእግዚአብሔርን መኖር ያወቁት በዚኹ መንገድ ነው፤ራሱ ከሰጣቸው የራሱ መገለጥ፤ቃል በቃል አነጋግሯቸዋል፡፡ቅዱሳት መጻሕፍት እንኳን የተጻፉት በዚኹ መንገድ ነው፤በመገለጥ /2ኛጴጥ.1፡19-20/፡፡ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊት “የእስራኤል አምላክ ተናገረኝ” ይላል /2ኛሳሙ.23፡2-3/፤ነቢዩ ሳሙኤልም ይኽን መገለጥ ባገኘ ጊዜ “ባርያኽይ ሰማኻልና ተናገር” አለ /1ኛሳሙ.3፡10/፡፡ስለዚኽ እግዚአብሔር ስለራሱ ካልገለጠ ማንም ሊያውቀው አይችልም፡፡ “የክርስትና ሃይማኖት የመገለጥ ሃይማኖት እንጂ ሰዎች በስምምነት ቃለ ጕባኤ ይዘው በጠረጴዛ ዙርያ ያጸደቁት አይደለም” የምንለውም ከዚኹ አንጻር ነው፡፡

-ከእግዚአብሔር ቃል፤

 

ሌላው እግዚአብሔርን የምናውቅበት መንገድ የራሱ እስትንፋስ የኾኑና ፈቃዱን የገለጠባቸው ቅዱሳት መጻሕፍትን በማንበብ ነው፡፡መጽሐፍ ቅዱስ ገና ሲዠምር “በመዠመሪያ እግዚአብሔር ሰማይንና ምድርን ፈጠረ” በማለት የእግዚአብሔርን መኖር በመናገር ነው /ዘፍ.1፡1/፡፡ “በፍጡራን ኹሉ ዘንድ ፈጣሪን የሚመስለው የለም፡፡ከንግግርበላይነው፡፡ለመመርመርየማይደፈር (የማይቻል) ነው፡፡ይኽንታላቅምሥጢርናአስደናቂሥራውንያገኙዘንድከላይከታችምፍጥረታትኹሉማወቁንአይችሉም፡፡ነገር ግን እኛን በምሕረቱ ስለ ማረን፤ለእኛ ባለው ደግነት ለእኛ ባሳደረብን በእግዚአብሔር ጸጋ ብቻ ይኽን ዐወቅን፡፡እንዲኹም ንጹሐን ከኾኑት አበው፣ደጋግ ከኾኑ ነቢያት ልንረዳው ቻልን፡፡የቅድስትቤተክርስቲያንንእምነትባስተማሩበደጋግመምህራንትምህርትምተረዳነውእንጂ፤” /የእስክንድርያውሊቀጳጳስስኑትዩ፣ሃይ. አበ. 110፡13/፡፡ “ይኽእንደምንተደረገአንበል፡፡ቅዱሳት መጻሕፍት እንደ ተናገሩ ረቂቅ የኾነ የማይመረመር የመለኮትን ነገር ሳንጠራጠር እንመን እንጂ፡፡አብ የማይማረመር ነው፤ወልድም የማይመረመር ነው፤መንፈስ ቅዱስም የማይመረመር ነው፡፡ … እንደምን ኾነ በምን ሥራ ተደረገ ብለን አንመርምር፡፡የፈጠረ ርሱ ነውና፡፡ዕውቀትን ኹሉ ለእግዚአብሔር እንተው እንጂ የሚበልጠው ትእዛዝም በኦሪት በነቢያት በወንጌል በሐዋርያት ቃል እናምን ዘንድ ነው” /ቅዱስ አትናቴዎስ፣ሃይ.አበ.28፡39-41/፡፡ 

-በሃይማኖት (በእምነት)፤


ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ፡- “ያለ እምነትም ደስ ማሰኘት አይቻልም፤ወደ እግዚአብሔር የሚደርስ እግዚአብሔር እንዳለ ለሚፈልጉትም ዋጋ እንዲሰጥ ያምን ዘንድ ያስፈልጓልና” እንዳለው /ዕብ.11፡6/ እግዚአብሔር መንፈስ ስለኾነ፥በመንፈሳዊ እጅ እንጂ በሥጋዊና ደማዊ እጅ (በሳይንሳዊ ምርምር) ልናውቀውና ልንዳስሰው አንችልም፡፡እምነት ያስፈልጋል፡፡ከትዕቢት፣ከትምክሕት የነጻ ልቡና ያስፈልጋል፡፡ተመስጦ ያስፈልጋል፡፡ፆም ጸሎት ያስፈልጋል፡፡ይኽን ስናደርግ የእግዚአብሔርን መኖር በትክክል እናውቃለን፡፡ “አንተ ግን ታውቅ ዘንድ የምትፈልግ ከኾንኅ የምድር አኗኗርኽን ተው፤ከዋክብትንና የሥርዓታቸውን አቀማመጥ ተሻገር፡፡ከዚኽ ኹሉ በላይም ከፍ ከፍ ካልኅ በኋላ የማይጨፈለቀውን አንዱን ልዩ ሦስትን በልቡናኽ አስብ” /ቅዱስ ያሬድ፣ድጓ ስብከት መኃትው/፡፡ “እግዚአብሔርን ማወቅን ልንገልጽልኅ፣አንተም ለራስኽ ልትመረምር ከወደድክ ሥጋዊ ደማዊ ግብርን ከአንተ አርቅ፡፡ከምድራዊ ሥራ ራቅ፤ከዓለማዊ ግብርም ተለይ፡፡ሰማያዊ ነገርን አስብ፤በፍጥነት የሚለዋወጡትን ምሰዓቶችን ዕወቅ፡፡የከዋክብትን ጌጥ የሚያስደንቁትን ኹሉ ተው፡፡ከምድር ያሉትንም ፍጥረታትን ተው፡፡የሚመላለሱባቸውንም ሕግጋት ተው፡፡የፀሐይንና የጨረቃን አስደናቂዎችን ከዋክብትን ኹሉ የተዋበና የሚያምር አከባቢያቸውን ኹሉ ለመረዳት ተጣጣር፡፡የሚያስደንቅ ክበባቸውንና በየወገናቸው እንዴት እንደሚቀራረቡ ሲብለጨለጩ፣ሲያብረቀርቁ ሲመላለሱ፣በየጊዜው እርስበርሳቸው እንዴት እንደሚቀራረቡና እንዴት እንደሚራራቁ ይኽን ኹሉ ለማወቅ መርምር፡፡ይኽን ኹሉ መርምረኽ ከተረዳኽ በኋላ ከዚያው ወደሰማያት ከፍ ከፍ ብለኽ ውጣና በዚያን ጊዜ በሕሊናኽ ብቻ መንፈሳውያን ሠራዊት ወዳሉበት፣ሰማያውያን መላዕክትና የዙፋንቤቶች (ኪሩባውያን) ሥልጣናት አጋዕዝት ጌቶችና ኃይላት አለቆችና መኳንንት ወዳሉበት ደረጃና ቦታ መጥተኽ ተመልከት፡፡ከዚኽም በኋላ ይኽን ኹሉ ፍጥረታት ካለፍኅ ወዲያ ሕሊናኽም እነዚኽን ኹሉ አልፎ ወደ ላይ መውጣት ከቻልኽ ከፍጡራን ኹሉ በላይ ወደ ሚኾን ነባቢ ወደኾነው የማይፋለስ ዙፋን በሚገኝበት በአርያም ላይ የልብኽን ዐይኖች ከፍ ካደረግኽ የማይታመም የማይደክም ፈጽሞ መለወጥ የሌለበትን የመለኮት ባሕርይ በዐዋቂ በንጹሕ ልቡና አስተውል” /ባስልዮስ ዘቂሣርያ፣ሃይ.አበ.33፡15-20/፡፡ 

-በራዕይ፤

 

ይኸውም ለሐዋርያት በደብረ ታቦር፣ለዮሐንስ ወንጌላዊ በፍጥሞ ደሴት፣ለቅዱስ ጳውሎስ በደማስቆ መንገድ እንደታያቸው ማለት ነው፡፡እግዚአብሔር በራዕይ ሲገለጥም፥ሰዎች ሊረዱት በሚችሉት መጠን መናገር እንጂ “እግዚአብሔር መልኩና ቁመቱ  እንደዚያ ነው” ማለት አይደለም፡፡ለምሳሌ እግዚአብሔር “ብርሃን ነኝ” ሲል ስለ አዕምሮአችን ደካማነት በብርሃን እንድንመስለው ስለ ፈቀደ እንጂ ከብርሃንም  የሚያልፍ ነው፡፡ “ከነገር ኹሉ በፊት አስቀድሜ ለእግዚአብሔር ምንም ምሳሌ የለውም፤በምንም በማናቸውም ሊመስሉት አይቻልም ብዬ በመናገር እዠምራለኍ፡፡ልቡናዎቻችን ግን ደካማዎች ስለኾኑ በምሳሌ እንድንጠቀም ከፍለንም እንድንረዳ በነርሱ ልንመስለው ያስገድዱናል” /ሳዊሮስ ዘእስሙናይን፣ገጽ 142/፡፡ 

-በሥነፍጥረት፤

 

ከትንኟ ዠምሮ እስከ ዝሆኑ፥አዕምሮ ከሌለው ዠምሮ ከፍተኛ አዕምሮ እስካለው ፍጥረት ድረስ ኹሉም የእግዚአብሔርን መኖር ይመሰክራሉ፡፡ “እንስሶችን ጠይቅ ያስተምሩህማል፡፡የሰማይ ወፎችን ጠይቅ ይነግሩህማል፡፡ወይም ለምድር ተናገር ርሷም ታስተምርሃለች፡፡የባሕር ዓሣዎችም ይነግሩሃል፡፡የእግዚአብሔር እጅ ይኽን እንዳደረገ ከእነዚኽ ኹሉ የማያውቅ ማን ነው?” /ኢዮብ.12፡7-9/፡፡ “ሊቀ ነቢያት ሙሴ በመጽሐፉ ስለ ሥነ ፍጥረት ይናገራል፤ይኸውም ሥነ ፍጥረትና መጽሐፍ ቅዱስ የእግዚአብሔር ምስክሮች ስለኾኑ ነው፡፡ሥነ ፍጥረት ስለምንጠቀምበት መጽሐፍ ቅዱስ ደግሞስ ለምናነበው ስለእግዚአብሔር መኖር ይመሰክሩልናል፡፡እነዚኽ ኹለቱም ዘወትር በኹሉም ስፍራ የሚገኙና የእግዚአብሔርን መኖር ለሚጠራጠሩ ሰዎች የሚገስጹ ናቸው” /St. Ephrem the Syrian, Hymns on Paradise 5:2/፡፡ “እግዚአብሔርስ ለገለጠላቸው፥ስለ እግዚአብሔር ሊታወቅ የሚቻለው በነርሱ ዘንድ ግልጥ ነውና።የማይታየው ባሕርይ ርሱም የዘለዓለም ኃይሉ ደግሞም አምላክነቱ ከዓለም ፍጥረት ዠምሮ ከተሠሩት ታውቆ ግልጥ ኾኖ ይታያልና፤” /ሮሜ.1፡19/፡፡ልበ አምላክ ቅዱስ ዳዊትም፡- “ሰማያት የእግዚአብሔርን ክብር ይናገራሉ፤የሰማይም ጠፈር የእጁን ሥራ ያወራል፤” ብሏል /መዝ.19፡1/፡፡

-በታሪክአስረጂነት፤

 

የሰው ልጅ ወደዚኽች ምድር ከመጣበት ዘመን አንሥቶ በፈጣሪ የማያምን እንደሌለ የተረጋገጠ ነው፡፡ምናልባት ፈጣሪውን በትክክል ላያውቀው ይችል እንደኾነ እንጂ፤ከርሱ ውጪ ሌላ ኃይል እንዳለ ግን ያምናል፡፡ፍልስፍናው፣የፖለቲካው ርዕዮቱ፣አላህ፣ድንጋዩ፣ሰይጣን፣ወንዙ አምላክ ነው ብሎ ሊያምነው ይችላል፡፡ይኽን አስቀድመን እንደ ተናገርነው፥ (እግዚአብሔር) ርሱን እንዲፈልጉ የሚገደዱበት አዕምሮ በልቡናቸው ውስጥ ስላሳደረነው፡፡በየትኛውም ዓይነት ኹኔታ ውስጥ ይኹን ሰው አደጋ ሲደርስበት ፍርሐት ይይዟል፤ረዳት ይፈልጋል፡፡ይኽ ርዳታ እንዲያደርግለት የሚፈልገው ኃይልም እግዚአብሔር ነው፡፡

ሀልዎተእግዚአብሔር

የእግዚአብሔር ባሕርይ

እግዚአብሔር በመለከኮታዊ ክብሩ ለዘለዓለም የሚኖር ረቂቅ አምላክ ነው፡፡ሰውም እግዚአብሔርን ለማወቅ ያለው ችሎታ እጅግ ውሱን ነው፡፡በመሆኑም የእግዚአብሔርን ባሕርይ ለመመርመር አይችልም፡፡ 1ኛቆሮ 13÷12 ነገር ግን የአምላክን ባሕርይ በሚረዳን መልኩ እንመለከታለን፡፡

 

የእግዚአብሔርን ባሕርያት የሚገልጡ አሥር ነገሮች

 

·እግዚአብሔር መንፈስ ነው

እግዚአብሔር መንፈስ መሆኑ በሕዋሳታችና አማካይነት ዳሰን ልናውቀው የማነችል ረቂቅ ነው፡፡እግዚአብሔር መንፈስ ነው ስንል ዝርው ብትን ነው ማለት አይደለም፡፡ረቂቅ መንፈሳዊ አካል ያለው ነው፡፡ለግዙፍ አካል መሥፈርት የሚሆኑት እንደመጠን፣ትልቅነት፣ክብደት የመሳሰሉት ለእግዚአብሔር አይሆኑም፡፡ረቂቅ አምላክ ነው፡፡ዮሐ 4÷24፣ 2ኛቆሮ 3÷17፣ት.ኢሳ 40÷18

 

·እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ ነው

እግዚአብሔር ዓለም ከመፈጠሩ በፊት ያለ ከመፈጠርም በኋላና ዓለምን ካሳለፈም በኋላ የሚኖር አምላክ ነው፡፡ስለዚህ እግዚአብሔር በዘመናት የማይቆጠር መጀመሪያና መጨረሻ የሌለው ዘለዓለማዊ ነው፡፡የጊዜና የዘመናት ፈጣሪ እርሱ ነው፡፡በጊዜ የሚወሰን ለመገኘቱ ምክንያት ያለው ፍጡር ብቻ ነው፡፡መዝ 11 ÷24 መዝ 89÷2 ፣መዝ 144÷13 ፣ት.ኢሳ 44÷6፣ራዕይ 1÷8

 

እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ /ከሃሌኩሉ/ ነው

እግዚአብሔር ሁሉን ቻይ ክፍዎችን የሚታገስ ባሕርይ ያለው አምላክ ነው፡፡ስለሆነም የሚሳነው ነገር የለም፡፡ዘፍ 18÷14 ፣መዝ 134÷6 ፣ት.ኤር 32÷17 ፣ማቴ 19÷26 ፣ሉቃስ 1÷37 ፣ሉቃስ 18÷27

 

እግዚአብሔር አይለወጥም

እግዚአብሔር በውሳኔው የሚጸና፣ያለውን የሚያደረግ፣የተናገረውን የሚፈጽም፣በውሳኔውም እንደ ሰው የማይጸጸት አምላክነው፡፡ቃል ኪዳኑን የሚጠብ ቅጻድቅ የባሕርይ አምላክ ነው፡፡ዘኁ 23÷19 ፣ሚል 3÷6 ፣ማቴ 24÷35፣ሮሜ11 ÷29

 

እግዚአብሔር በሁሉ ሙሉ /ምሉዕ በኩለሄ/ ነው፡፡

እግዚአብሔር በዓለም ሁሉ ሙሉ ነው፡፡ከዚህ አለ ከዚያ የለም፤ወይም ከዚያ አለ ከዚህ የለም አይባልም፡፡በሰማይ ይኖራል በመባሉም ስለ ክብሩና ስለ ልዕልናው ነው፡፡ኤር 23÷23 ፣መዝ 2÷4 ፣ማቴ 5÷34 ፣የሐ 3÷13፡፡እርሱ በቦታ አይወሰንም፡፡መዝ 138÷5 ፣መዝ 77÷18

 

በመለኮታዊ ጥበቃው

በእርሱ ፈቃድ፣ከእርሱ ትእዛዝ ወይም በእርሱ ጥበቃ ካልሆነ በቀር የሚሆን የሚደረግ የሚደርስ ነገር የለም፡፡ሁሉ በእርሱ ጥበብ ይሆናል፤ይደረጋል፡፡በአጋጣሚ፣በእድል፣በስምምነት፣ወይም በግምት የሚሆን ነገር የለም፡፡ማቴ 10 ÷30

 

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነው

እግዚአብሔር ሁሉን አዋቂ ነውና ከእርሱ የተሰወረ ነገር የለም፡፡ያለፈውንና ያሁኑን የሚመጣውን ያልተነገሩ ሀሳቦችንና ቃላትን ተግባራትን ከመሆናቸው አስቀድሞ ያውቃል፡፡መዝ 93÷8 ፣መዝ 138÷1 ፣ማቴ 15÷13 ፣የሐዋ.ሥራ 2÷3 ፣ሮሜ 11÷33 ፣ዕብ 4÷13

 

·እግዚአብሔር ቅዱስ ነው

እግዚአብሔር ቅዱስ ነውና በሥራው ሁሉ ክፋትና ርኩሰት የለበትም፡፡ንጹህና ፍጹም ደግ ነው፡፡እውነተኛ ፈራጅ ነው፡፡ምህረቱ የበዛ ታጋሽ ለቁጣም የዘገየ እንዱሁም ፍጥረቱን የሚወድና ጸጋውን ያጎናጸፈ ነው፡፡እርሱ ቅዱስ እንደሆነ ፍጥረቱም ቅዱስ እንዲሆን ይፈልጋል፡፡ዘሌ 11÷44 ፣1ኛሳሙ 2÷2 ፣ዘሌ 19÷2 ፣ 1ኛጴጥ1÷16

 

እግዚአብሔር ፍጹም ነው

እግዚአብሔር ደግነቱ፣ቅዱስነቱ፣ፍቅሩ፣ርኅራኄው፣ትክክለኛ ፍርዱ፣ጸጋውና እንዲሁም ለፍጥረቱ የሚያደርገው ጥበቃ ነው፡፡

 

·የማንም እርዳታ አያስፈልገውም

 

ፍጥረታት የተፈጠሩት በእግዚአብሔር ቃል ሲሆን እርሱ የማንም እርዳታና ድጋፍ አያስፈልገውም፡፡በመለኮታዊ ክብሩ ቅድመ ዓለም የነበረ በማዕከለ ዓለም ያለ፤ድኅረ ዓለምን አሳልፎ የሚኖር ነው፡፡ዘፍ 1÷3 ፣ሮሜ 11÷34 ፣ት.ኢሳ 40÷13 ፣የሐዋ.ሥራ 17÷24

የእግዚአብሔር ባሕርይ
bottom of page