top of page

የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት

መንፈስ ቅዱስ "ጰራቅሊጦስ" ናዛዚ መጽንዒ መስተፍሥሒ  (አረጋጊ አጽናኝ አስደሳች) ማለት ነው። መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከወልድ ጋር የነበረ ያለ የሚኖርም ነው፤ እርሱ መንፈስ ቅዱስም አምላክ ነው።

የቀደሙት አበው መጽሐፍ ቅዱስን ጠቅሰው ይመሰክራሉ። በጌታ በአዳኝ ከአብ በሠረጸ ከአብና ከወልድ ጋር በነቢያት በተናገረ በመንፈስ ቅዱስ እናምናለን፤ እንስግድለት፤ እናመስግነው። አንቀጸ ሃይማኖት"

 

"በመንፈሱ ሰማያት ውበትን አገኙ.....። (ኢዮብ 26:13) የእግዚአብሔር መንፈሱ ተብሎ የሚጠራው መንፈስ ቅዱስ ነው። በመንፈስ ቅዱስ ሰማያት ውበትን እንዳገኙ እንደተፈጠሩ ኢዮብ መሰከረ:።

 

የጌታ የኢየሱስ ክርስቶስ ጸጋ የእግዚአብሔርም ፍቅር የመንፈስ ቅዱስም ኅብረት ከሁላችሁ ጋር ይሁን፤ አሜን። (2ኛቆሮ 13:14) መንፈስ ቅዱስ በመለኮት በህልውና ከአብና ከወልድ ጋር አንድ ስለሆነ ቅዱስ ጳውሎስ ኅብረት እንዲሰጠን በኃይሉ እንዲያበረታን ጸለየልን። ስሙ የሚባርክ የሚቀደስ መሆኑን አስረዳን።

 

"እንግዲህ ሂዱና አሕዛብን ሁሉ በአብ በወልድና በመንፈስ ቅዱስ ስም እያጠመቃችኋቸው፥ ያዘዝኋችሁንም ሁሉ እንዲጠብቁ እያስተማራችኋቸው ደቀመዛሙርት አድርጓቸው፤ እነሆም እኔ እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ ሁልጊዜ ከእናንተ ጋር ነኝ።" (ማቴ 28:19) በመንፈስ ቅዱስም ስም መጠመቅ እንዳለብን ጌታ ራሱ አስረዳን፤  የባህርይ አምላክ ባይሆን ኖሮ በስሙ ለመጠመቅ ባልታዘዝን ነበር።

 

"መንፈስም የእግዚአብሔርን ጥልቅ ነገር እንኳ ሳይቀር ሁሉን ይመረምራልና ለእኛ እግዚአብሔር በመንፈሱ በኩል ገለጠው።" (1ኛቆሮ 2:10) ጳውሎስ መንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክ እንደሆነ ሲያስረዳን

"ባንድ ሰው ልብ ያለውን የሚያውቅ ማነው? ተዋሕዳው ያለች ነፍስ ብታውቅ እንጂ ሌላውማ ሰው እንዴት ሊያውቅ ይችላል።

እንዲሁም ሁሉ በእግዚአብሔር ህልውና ካለመንፈስ ቅዱስ በቀር የእግዚአብሔርን ምስጢር የሚያውቅ ማንም የለም ብሎ መንፈስ ቅዱስ የባህርይ አምላክ እንደሆነ አረጋግጦልናል።

የአበውንም ምስክርነ ብንሻ "ዳግመኛም መንፈስ ቅዱስ ከአብ ከወልድ ጋር እኩል ትክክል እንደሆነ ከአብ ከወልድ መለኮታዊ ባህርይ ልዩ እንዳይደለ እናምናለን፤ ልዩ ነው ማለት አይገባም" "መንፈስ ቅዱስም እግዚአብሔር ነው አስቀድመን እንደተናገርን መገኘቱ ከአብ ነው እንጂ ከሌላ አይደለም"

የመንፈስ ቅዱስ የባሕርይ አምላክነት

መንፈስቅዱስ አካላዊ እስትንፋስ ነው

መንፈስ ቅዱስ ዝርው ኃይል አይደለም:: እንደ አብና እንደ ወልድ ፍጹም አካል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክዕ ያለው ነው:: እኔ ማለት የሚችል ነው:: መንፈስ ተብሎ በመጽሐፍ ቅዱስ ስለተጠራ አካል የለውም የሚለው አባባል ከደካማ አስተሳሰብ የመነጨ ነው::መጽሓፍ ቅዱስ "እግዚአብሔር መንፈስ ነው" ዮሃ 4:24:: ማለቱ አካል የለውም ማለቱ እንዳልሆነ ሁሉ መንፈስ ቅዱስንም መንፈስ ብሎ መጥራቱ አካል የሌለው ለማለት አይደለም:: እግዚአብሄር አካል ያለው ሲሆን ነገር ግን እንደ ፍጡራን ውሱን አይደለም:: እግዚአብሔር በዓለምና ከዓለም ውጭ ያለ የሌለበት ቦታ የሌለ ምሉዕ ስፍህ ነው::ለዚህም የልበ አምላክ የዳዊትን አባባል ብቻ መጥቀሱ በቂ ነው:: "ሰማየ ሰማያት ብወጣ አንተ በዚያ አለህ ወደ ባህር ብጠልቅ አንተ በዚያ አለህ የሌለህበት ቦታ የለም"እግዚአብሔር የሚከፋፈልና የሚበታተን አካል ያለው አይደለም ነገር ግን በፍጹም መለኮት እሱው ራሱ በኁሉም ቦታ ይገኛል::

በተጨማሪም "ከአብ በሠረጸ ከአብ ከወልድ ጋር አንድ በሚሆን እንደ አብ እንደ ወልድ ፍጹም አካል ባለው በመንፈስ ቅዱስም እናምናለን::እንዲሁም በአካሉ በገጹ ጸንቶ ያለ ነው"14 በማለት ቅዱሳን አበው መጽሐፍ ቅዱስን ዋቢ አድርገው ያስረዳሉ:: መንፈስ ቅዱስ አካላዊ እስትንፋስ መሆኑን መጽሐፍ ቅዱስ እንደሚከተለው ያስረዳናል::ኦሪት ዘፍ18:1 :-በሰው አምሳል ከተገለጡት ከሦስቱ አካላት አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው ማቴ 3:16 :-...የእግዚአብሔር መንፈስ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ሲቀመጥ አየ" የእግዚአብሔር መንፈስ የተባለው መንፈስ ቅዱስ ለመሆኑ የሚያጠራጥር ነገር አይኖርም:: እንግዲህ በርግብ አምሳል መውረዱ ዝርው ኃይል ሳይሆን አካላዊ መሆኑን ሊያስገነዝበን ነው:: ብትን ሃይል ቢሆን ኖሮማ በርግብ አምሳል ወርዶ በራሱ ላይ ባልተቀመጠ ነበር::

ዮሃ 14:16 "እኔም አብን እለምነዋለሁ ጰራቅሊጦስንም ሌላውን አካል ይልክላችሁአል ለዘላለም ከእናንተ ጋር ይኖር ዘንድ" በአዳዲስ እትሞች ላይ ጰራቅሊጦስ የሚለው ሌላ አጽናኝ በሚለውተ ተክቶል ሌላውን አካል የሚለው እርሱም በሚለው ተተክቶል:: ይህም ቢሆን የመንፈስ ቅዱስን አካላዊነት የሚያስተባብል አይደለም::ሌላ አጽናኝ ሲል ፍጹም ገጽ ፍጹም መልክዕ ያለው ልዩ አካል መሆኑን የሚያስገነዝብ ሲሆን ሌላ ሲል ከአብና ከወልድ የተለየ ሦስተኛ አካል ማለቱ ነው::እርሱም የሚለው አባባልም ከአብና ከውልድ በተለየ አካል ያለ ልዩ በአካላት ሦስት ከሆኑት አንዱ እኔ ባይ አካል መኖሩን የሚገልጽ ነው::

"ነገር ግን አብ በስሜ የሚልክላችሁ የእውነት መንፈስ ጰራቅሊጦስ እርሱ ሁሉን ያስተምራችሁአል እኔ የነገርኩአችሁንም ሁሉ ያሳስባችሁአል" ከዚህ የምንረዳው መንፈስ ቅዱስ የእውነት አስተማሪና መሪ እንደሆነ ነው እንግዲህ ብትን ኃይል ሁሉን ማስተማር ይቻላል? ማሳሰብስ ይቻለዋል? መናገርስ ይቻለዋል? በእዚሁ በዮሃንስ ወንጌል 16:13 ".....ወደ እውነት ሁሉ ይመራችኃል" ተብሎ እንደተገለጸው መንገድ ማሳየት መምራት ይቻለዋል? እርሱ ተብሎስ ብትን ለሆነ ኃይል ይነገራል? በፍጹም:: አካል የሌለው እስትንፋስ ወይም መንፈስ እርሱ ተብሎ አይጠራም:: ወደ እውነትም አይመራም መናገርም አይቻልም መንፈስ ቅዱስ ግን አካላዊ እስትንፋስ ስለሆነ ከላይ የተጠቀሰው ሁሉ ሊነገርለት ተችሎዋል::ኢሳ 48:16 "...... አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።"

በዚህ ላይ እግዚአብሔር ብሎ አብን መንፈስ ብሎ መንፈስ ቅዱስን ማመልከቱ ነው: እንግዲህ መንፈስ ቅዱስ በአብ ውስጥ የተከማቸ ብትን ኃይል ነው ከተባለ ወልድን እንዴት ሊልክ ቻለ? መላክስ ይቻለዋል? ደግሞ የእግዚአብሔር መንፈስ ነው ያለው እንጂ መቼ መንፈስ ቅዱስ አለ እንዳይባል:: እግዚአብሔር ብሎ እና በሚለው ቃል በማያያዝ ሌላ አካል እንዳለም ገለጸ እንጂ የእግዚአብሔር መንፈስ ብሎ አንድ አካል ብቻ አድርጎ አላቀረበም:: ልከውኛል የሚለው ቃል የሚያመለክተው ሁለትነትን እንጂ አንድነትን አይደለም:: ተጨማሪ የመጽሐፍ ቅዱስ ማስረጃ ዘፍ 6:3 "እግዚአብሔርም፦መንፈሴ በሰው ላይ ለዘላለም አይኖርም፥እርሱ ሥጋ ነውና ዘመኖቹም መቶ ሀያ ዓመት ይሆናሉ አለ።" ዘፍ 18:1 "በቀትርም ጊዜ እርሱ በድንኳኑ ደጃፍ ተቀምጦ ሳለ እግዚአብሔር በመምሬ የአድባር ዛፍ ተገለጠለት።ዓይኑንም አነሣና እነሆ፥ሦስት ሰዎች በፊቱ ቆመው አየ ባያቸውም ጊዜ ሊቀበላቸው ከድንኳኑ ደጃፍ ተነሥቶ ሮጠ፥ወደ ምድርም ሰገደ፥እንዲህም አለ፦አቤቱ፥በፊትህስ ሞገስ አግኝቼ እንደሆነ ባሪያህን አትለፈኝ ብዬ እለምናለሁ

 

ኢሳ 48:16 "ወደ እኔ ቅረቡ ይህንም ስሙ እኔ ከጥንት ጀምሬ በስውር አልተናገርሁም ከሆነበት ዘመን ጀምሮ እኔ በዚያ ነበርሁ፥አሁንም ጌታ እግዚአብሔርና መንፈሱ ልከውኛል።"ዮሐ 15:26 "ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥እርሱስ ለእኔ ይመሰክራል፤ዮሐ 16:8 "እኔ ግን እውነት እነግራችኋለሁ፤እኔ እንድሄድ ይሻላችኋል።እኔ ባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣምና፤እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኋለሁ።እርሱም መጥቶ ስለ ኃጢአት ስለ ጽድቅም ስለ ፍርድም ዓለምን ይወቅሳል" ሐዋ 5:3-4 " ጴጥሮስም፦ሐናንያ ሆይ፥መንፈስ ቅዱስን ታታልልና ከመሬቱ ሽያጭ ታስቀር ዘንድ ሰይጣን በልብህ ስለ ምን ሞላ?ትሸጠው የአንተ አልነበረምን? ከሸጥኸውስ በኋላ በሥልጣንህ አልነበረምን? ይህን ነገር ስለምን በልብህ አሰብህ? እግዚአብሔርን እንጂ ሰውን አልዋሸህም አለው። 1ኛቆሮ 12:11 "ይህን ሁሉ ግን ያአንዱ መንፈስ እንደ ሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።" 2ኛጴጥ 1:21 "በክርስቶስም ከእናንተ ጋር የሚያጸናንና የቀባን እግዚአብሔር ነው፥ደግሞም ያተመን የመንፈሱንም መያዣ በልባችን የሰጠን እርሱ ነው።

መንፈስቅዱስ አካላዊ እስትንፋስ ነው

መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሠረጸ ነው

የመንፈስ ቅዱስ ግብሩ መሥረጽ ነው:: ከማን ነው የሠረጸ? ቢሉ ከአብ:: ከአብ ወጣ ሲባልም አብን አህሎ መስሎ ተገኘ ማለት ነው:: ያለ መቀዳደም ከአንድ የሻማ ብርሃን ሌላ ብርሃን እንደሚገኝ መንፈስ ቅዱስም እንደዚሁ አብን አህሎ አብን መስሎ ከአብ ወጣ (ተገኘ) (ምሳሌው በሻማው ብርሃን እንጂ በሻማው ላይ አለመመሰሉን ልብ ይበሉ)::

መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ ለመስረጹ ምን ማስረጃ አለህ? ቢሉ እንደሚከተለው ይጠቀሳል::

 

1.ዳሩ ግን እኔ ከአብ ዘንድ የምልክላችሁ አጽናኝ እርሱም ከአብ የሚወጣ የእውነት መንፈስ በመጣ ጊዜ፥እርሱ ስለ እኔ ይመሰክራል"

ጌታችን እንደ መሠከረው መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሚወጣ እንጂ ከወልድ የሚወጣ አይደለም:: ከወልድ የሚሠረጽማ ቢሆን ኖሮ ከእኔም የሚወጣው ብሎ በተናገረ ነበር:: ነገር ግን መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሚወጣ ስለሆነ ከአብ የሚወጣ ብሎ አረጋገጠልን:: እኛ ግን መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ እንደ ሠረፀ ቅዱሳት መጻህፍትን አብነት አድረገን እናምናለን።

ዩሐ.15:-26 ። "ከአብ የሚወጣ" አለ እንጂ "ከአብም ከወልድም የሚወጣ" አላለም።

 

2. "እኔ ግን በእውነት እነግራችኃለሁ።እኔ እንድሄድ ይሻላችኃል።እኔባልሄድ አጽናኙ ወደ እናንተ አይመጣም።እኔ ብሄድ ግን እርሱን እልክላችኃለሁ።

ዩሐ. 16:-7 ። እልክላችኃለሁ አለ እንጂ ከእኔ ይወጣል አላለም።

 

3. አብ በስሜ የሚልከው ግን መንፈስ ቅዱስ የሆነው አጽናኝ እርሱ ሁሉን ያስተምራችኃል ዩሐ. 14:-26 ።አብ በስሜ የሚልከው መንፈስ ቅዱስን ሰለ መላክ በተናገረባቸው አንቀጾች ሁሉ አብም ወልድም እንደሚልኩት ተናግሮአል። የመንፈስ ቅዱስን መሥረፅ በተመለከተ ግን ከአብ ብቻ የሚወጣ መሆኑን አስተምሮአል።

 

4. በጉባኤ ኒቂያ /325 ዓም/ እና በጉባኤ ቁስጥንጥያ /381 ዓም/ የተመሠከረለት ጸሎተ ሃይማኖት ስለመንፈስ ቅዱስ "ከአብ በሠረፀ: ህይወትን በሚያድል መንፈስ ቅዱስ እናምናለን" የሚል ምስክርነት ሰጥቶአል።

 

5. ይህ ጸሎተ ሃየማኖት ሊቀየር : ሊሻሻል : ወይም ሊጨመርለት እንደማይገባ ተደርጎ በጉባኤ ቁስጠንጥንያ የተዘጋ በወቅቱ የተሰበሰቡ የዓለምአብያተ ክረስቲያናት አበው የተስማሙበት እና ዓለምዓቀፋዊ ተቀባይነት ያለው ነው።ሊጨመርለት ይገባል ተብሎ ቢታሰብ እንካን ተመሳሳይ የሆነ አለም ዓቀፋዊ ጉባኤ ተጠርቶ ነገሩን ሊያየው በተገባ ነበር።

 

ታሪክ

ጉባኤ ቁስጥንጥንያ ካጸደቀው "ከአብ በሠረፀ በመነፍስ ቅዱስ እናምናለን" ከሚለው ዓንቀጽ ላይ "ከወልድም የሰረጸ ነው" የሚል የተጨመረበት ከ200 ዓመታት በኃላ ነው።ለመጀመርያ ይህ ኑፋቄ መዘራት የተጀመረው በወቅቱ "የክርስትናው ዓለም" ተብሎ ለሚጠራው አካናኒ እንደ ዳርቻ ይቆጠር በነበረው በዛሬዋ ስፔን ቶሌዶ በተባለች ከተማ በ589 ዓም በተደረገ ጉባኤ ላይ ነበር።በዚያች የዳርቻ ከተማ የተጀመረው ይህ ቤተክርስቲያን ከሌሎቹ ቀደማ በ633 ዓም እና በ653 ዓም በቶሌዶ ከተማ ባደረገችው ጉባኤ በይፋ ተቀበለችው።

በመጀመሪያዎቹ ጊዜያት የሮም ቤተክርስቲያን ስሕተቱን ተቃውማ ነብር።ሰለ ስቲያን: ታላቁ ልዩን: ሐርድያን: ቤኔዲክት 3ኛ የተባሉ የሮም ፖፖች ይህንን ሲቃወሙት ኖረዋል።ከ879-880 በሮም መንበር የነበረው ፖፓ ዩሐንስ የጉባኤ መግለጫ አውጥቶነበር።

 

በወቅቱ በኢየሩሳሌም በነበረ አንድም የሮም ገዳም በጸሎተ ሃይማኖት ላይ ተጨምሮ ሲነገር በመስማታቸው በዚያ የነበሩ የግሪክ መነኮሳት ለሮሙ ፖፓልዮን 3ኛ አመለከቱ።የሮሙ ፓፕልዮን 3ኛ ጭማሪው በነገረ ሃይማኖት ላይ ችግር የለበትም በሚል ተቃወመው:።ነገሩን የበለጠ ለማስረገጥም በቅዱስ ጴጥሮስ መቃብር በግሪክ እና በላቲን የተጻፉ የኒቂያ/ቁስጥንጥን ያጸሎተ ሃይማኖት ቅጅዎች ጭማሪው ሳይደረግባቸው በሰሌዳ እንዲሰቀሉ አድርጎ ነበር።

 

ይህ ሁሉ ቢሆንም የምዕራቡ አብያተ ክርስቲያናት ግን ተቀብለው ከጸሎተ ሃይማኖት ጨምረው መጠቀም ቀጠሉ።በ1014 ዓም አካባቢ የሮም ቤተክርስቲያንም ተቀብላ በቅዳሴዋ ላይ መጠቀም ጀመረች። 500 ዓመታት ስትቃወመው የነበረውን ይህንን ስሕተት የተቀበለችበት ዋናው ምክንያት በምዕራቡ ዓለም የነበራትን የበላይነት ሥልጣን ላለማጣት መሆኑን ሊቃውንት ይገምታሉ።በባዛንታይን ጉዳዮች ላይ ጥናት በማድረግ የታወቀው እንግሊዛዊ ሰርስ ቴቨንሩንሲማን:-

 

"ጸሎተ ሃይማኖት የጸደቀው ነገረ ሃይማኖትን የመግለጥ ሥልጣን ባለው /በምሥራቃዊያን ትምህርት መሠረት/ ዓለም ዓቀፋዊ ጉባኤ ነው።በዚያ ላይ መጨመር ጉባኤውን እና በዚያ የነበሩትን አበው ሥልጣን እና ክብር ጥያቄ ውስጥ መክተት ነው።በቀደሙት ጉባኤያት ላይ የማብራራት: የመጨመር: የማጉላት: የመቀየር ስልጣን ያለው ሌላ ተመሳሳይ ዓለም ዐቀፋዊ ጉባኤ ነው።

የምዕራብ አብያተክርስቲያናት በግላቸው ጸሎተ ሃይማኖትን የሚለውጡ ከሆነ ያለ ጥርጥር ኑፋቄ ውስጥ ይወድቃሉ።ፖፑ ለእነርሱ አግዞ ቢቀበላቸውም እንካን ከውግዘት አያመልጡም:"ብላል:

 

ይህ ትምህርት መንፈስ ቅዱስ ፍጹም መልክ ፍጹም ገጽ ያለው ሳይሆን በአብ እና በወልድ መካከል የሚገኝ ወዳጅነት ያስመስለዋል።ምሥጢረ ሥላሴንም በማፋለስ አብ መገኛነቱ:ሰሌዳነቱ እና ልብነቱ ለወልድ ብቻ ያደርገዋል።በሌላም በኩል ወልድን እንደ አብ መገኛ: ሰሌዳ እና ልብ ያደርገዋል።ይህ ዓይነቱ የስሕተት ትምህርት "ፊሊክ filioque" ተብሎ ይጠራል ትርጉሙም በላቲን ቋንቋ "እንዲሁም ከወልድ" ማለትነው።

 

ይህንን የስህተት ትምህርት መቀበል የመጽሐፍ ቅዱስን ትምሀርት : የጉባኤያትን ውሳኔዎች እና ሥልጣን : የቤተክርስቲያንን ትውፊትም መቃወም ብሎም ለሌሎች የስሕተት ጭማሬዎችም ዕድል መሰጠት ነው።

መንፈስ ቅዱስ ከአብ ብቻ የሠረጸ ነው

የመንፈስቅዱስ ጸጋ

መንፈስ ቅዱስ ከሦስቱ አካላት አንዱ ሲሆን ጸጋው ግን እጅግ ብዙ ነው።መንፈስ ቅዱስ በልዩ ጸጋ የተለያየ መንፈሳዊ ስጦታ ለተለያዩ አገልጋዮች እንደሚሰጥ የመንፈስ ቅዱስን ጸጋ ኢሳይያስ እንዲህ ሲል ይዘረዝረዋል ኢሳ.11:1 - 3 "የእግዚአብሔር መንፈስ፥የጥበብና የማስተዋልመንፈስ፥የምክርና የኃይል መንፈስ፥የእውቀትና እግዚአብሔርን የመፍራት መንፈስ ያርፍበታል።"

 

ብርሃነ ዓለም ጳውሎስ ደግሞ "የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው (አካሉ አንድ ሲሆን ስጦታው የበዛ ነው ማለቱ ነው) ለእያንዳንዱ በመንፈስ ቅዱስ የሚሰጠው ስጦታው ልዩ ልዩ ነውና ለሁሉም ጌታ እየረዳ እንደ ዕድሉ ይሰጠዋል ለእያንዳንዱ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው በግልጥ ይሰጠዋል የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለው በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃልን የሚሰጠው አለው በመንፈስ ቅዱስ ሃይማኖትን የሚሰጠው አለው ድውይን የመፈወስ ሥልጣንም የሚሰጠው አለው የእርዳታና የኃይል ሥራን የሚሰጠው አለው ትንቢት መናገርን የሚሰጠው አለው በመንፈስ ቅዱስ ትርጎሜ ማወቅን የሚሰጠው አለው የየአገሩን ቋንቋ እንዲያውቅ ትርጎሜውን የሚሰጠው አለው:: በዚህ ሁሉ ሁሉንም የሚረዳቸው መንፈስ ቅዱስ አንድ ነው ነገር ግን ለሁሉም እንደወደደ ያድላቸዋል"

 

1ኛቆሮ12:4-11 "ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር (ማወቅ) ይሰጠዋል፥ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን(ቋንቋ) መናገር፥ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደ ሚፈቅድለ እያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል።"

 

ቅዱሳን ሐዋርያትና አርደት መንፈስቅዱስ ስላደረባቸው ልዩ ልዩ ሕሙማንን የመፈወስ ኀይል : ርኩሳን መናፍስትን ከልዩ ልዩ በሽተኞች ላይ የማስወጣት ሥልጣን: ሙታንን ለማስነሣት የሚያስችል አሰደናቂ ኃይል ተሰጣቸው:: ቅዱሳን ሐዋርያትና ተከታዮቻቸው አርድእት የሰዎችን ኃጢአት ለማስተረይና ይቅር ለማለት የሚያስችል ሥልጣነ ክህነትያገኙት መንፈስ ቅዱሳን ስለተቀበሉ ነው(ዮሐ.20 : 21-23 ; የሐዋ.20:28)

 

መንፈስ ቅዱስ መከፈል ሳይኖርበት:በአብና በወልድ በራሱም ፈቅድ ልዩ ልዩ ጸጋውን ለተለያዩ ሰዎች ሲያድል: እርሱ ራሱ እንደማይከፈልና ሀብቱም እንደማያልቅበት ቅዱስ ባሳልዩስ ዘቂሳርያ ሲመሰክር እንዲህ ብሎአል:: "እንደ ሚሰጣቸው እንደ ሀብቱ መጠን ከእርሱ ይቀበሉ ዘንድ ከእነርሱም አንዱ (እያንዳንዱን) የበቁ ያደርጋቸዋል:ሀብቱም ሁሉ ከእርሱ ከራሱ ይሰጣል: ከእርሱም ስለ ተሰጠው ለእርሱ ምንም ምን አይጎድለውም: እርሱ መቼም መች (ምንጊዜም) ሕፀፅ (ጉድለት) የለበትምና።ፀሐይ በሰው ሁሉ ላይ ሰለተስጠው ሙቀት ብርሃን ምንም ምን እንዳይጎድለው መንፈ ስቅዱስም እንዲሁ በፍጥረት ሁሉ ላይ ሀብቱን ያሳድራል:ነገር ግን አይጎድልበትም:አይከፈልም"(ሃይማኖተአበውግጽ 114-115 ቁ. 47-48)።

 

በተጨማሪም ይህ ቅዱስ አባት ስለ መንፈስ ቅዱስ ሥራ ከጻፈው መልእክት እጅግ ጠቃሚ የሆነውን ክፍል ከዚህ ቀጥለን ጠቅሰነዋል። "ሕያው እግዚአብሔር በማሳወቅ ሁሉን አዋቂ ያደርጋል።በነቢያት ቃል ትንቢትን ይናገራል: በሕግ ጸንተው ላሉ ጥበብን ይገልጣል: ካህናትን ጻድቃን ያደርጋቸዋል: ለነገስታት ኃይልን ይሰጣል: መከራውንም ለሚታገሱ ትእግስትን ይሰጣል:እውነተኛ ሀብትን: ልጅነትን ( የጸጋልጅነትን) ያድላል: ሙታንን ያስነሳል:እስረኞችን ይፈታቸዋል: ከኃጢአት ከጣዖት የተለዩትን በጥምቀት ዳግመኛ እንሲወለዱ (የእግዚአብሔር ልጆች እንዲሆኑ) ያደርጋቸዋል: በእኒህና በሚመስላቸውም ላይ ይህን ያደርጋል"(ሃይማኖተ አበው ገጽ 115 ቁ. 49-50)።

 

መንፈስ ቅዱስ ያደረባቸ ሰዎች : ታጋሾች: ሃይማኖቶች : ፍቅርን መጽዋትን የሚወዱ : ጸሎተኞች ርኅሩሆች ናቸው።ምክነያቱም ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው። ገላ. 5:22-23 "የመንፈስ ቅዱስ ፍሬዎች ፍቅር ደስታ ሰላም ትዕግስት ቸርነት በጎነት እምነት የዋህነ ትራስን መግዛት ናቸውና።"

 

ቅዱሳን ነቢያት ትንቢት ሊናገሩ የቻሉት መንፈስ ቅዱስስላደረባቸው ነው።ቅዱሳት መጻሕፍት የተጻፉት የእግዚአብሔር መልእክተኞች በሆኑ መንፈስ ቅዱስ ባደረባቸው ሰዎች ነው(1ኛጴጥ.1 : 20 - 21)።ምስጢራተ ቤተክርስቲያንን የሚቀድስ መንፈስ ቅዱስ ነው።ማንኝያውም ሰው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ካልተወለደ በቀር ወደ እግዚአብሔር መንግስት ሊገባ አይችልም( ዩሐ. 3:5)።ዩሐንስ መጥምቁ ለንሰሐ በውኃ ያጠምቅ ነበር(ማቴ. 3:11)።ጌታችን ግን በመንፈስ ቅዱስና በእሳት ያጠምቃል(ማቴ. 3:11-12 : ዩሐ. 1: 32-34)።

የመንፈስቅዱስ ጸጋ
bottom of page