top of page

የቤተክርስቲያን ትርጉም

ቤተ ክርስቲያን ሲባል የተለያዩ ትርጉሞች አሉት። በዚህም መሠረት ቤተ ክርስቲያን ሲባል ክርስቲያን ምእመናን፣ የቤተክርስቲያን መሪዎች፣ የቤተክርስቲያን አስተዳደርና የቤተክርስቲያን ሕንጻ ሊሆን ይችላል።
1-የመጀመሪያው ፍቺ የተወሰነ ቦታን ያመለክታል ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን እንለዋለን::
ሕንጻ ቤተ ክርስትያኑ የእግዚአብሔር መመለኪያ ቤት ስለሆነ ክርስቲያኖች ተሰባስበው የሚጸልዩበት የሚባረኩበት ሥርዐተ እግዚአብሔርን የሚፈጽሙበት ሕገ እግዚአብሔርን የሚፈጽሙበት ሕገ እግዚአብሔር የሚማሩበት ንስሐ የሚገቡበት ስለሆነ ቤተክርስቲያን ብለን እንጠራዋለን:: በመጽሐፈ ዲድስቅልያ አንቀጽ ዐሥርና አንቀጽ ሠላሳ አምስት በሕንጻ ቤተክርስቲያን አሠራር ሥርዓቶች ላይ ለሕንጻው ቤተ ክርስቲያንም የሚል እናገኛለን። ቤተክርስቲያን መባሉ ክርስቲያኖች ለጸሎት የሚሰበሰቡበትና የምስጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ሥርዓቶች የሚያከናውኑበት ቦታ ስለሆነ ነው። በብዙዎቻችን ዘንድ ቤተ ክርስቲያን በሚባልበት ጊዜ ይኸው የሚሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ሥርዓት የሚካሄድበትና ለጸሎትም የምንሰበሰብበት ቦታ እንጂ ሌላ አይደለም። እንደዚህ ላለው ቦታ ደግሞ እግዚአብሔር የተለየ ግምት የሚሰጠው መሆኑን ለመረዳት ወደ መጀመሪያው መጽሐፈ ነገሥት ምዕራፍ ስምንትና ዘጠኝ የተመለከትን እንደሆነ የሚከተለውን ሁናቴ እናገኛለን። ንጉሥ ሰሎሞን ቤተ  መቅደስን አሰርቶ በጨረሰ ጊዜ ለእግዚአብሔር ባቀረበው ጸሎት በቤተ መቅደስ ተገኝቶ የሚደረገው ጸሎት ሁሉ ተሰሚነትን እንዲያገኝ ብሎ ለለመነው ልመና እግዚአብሔር መልስ ሊሰጠው “በፊቴ የጸለይከውን ጸሎትህንና ልመናህን ሰምቼአለሁ፣ ለዘላለም ስሜ በዚህ ያድር ዘንድ ይህን የሰራኽውን ቤት ቀድሼአለሁ፡ ዐይኖቼና ልቤም በዘመኑ ሁሉ በዚያ ይሆናሉ  (፩ነገም፱፡ቊ፫)። እኛ እግዚአብሔር በሕንጻው ብቻ ይወሰናል አላልንም ነገር ግን የአምልኮቱ ቤት ነው አልን እንጂ:: ለዚህም እንዲሰራ ከእግዚአብሔር ትዕዛዝ ተሰጠ እንጂ አንዳችም በራሱ ፈቃድ የሠራ የለም::

ዘጸ 25:8 "በመካከላቸውም አድር ዘንድ መቅደስ ይሥሩልኝ። እኔ እንደ ማሳይህ ሁሉ፥ እንደ ማደሪያው ምሳሌ እንደ ዕቃውም ሁሉ ምሳሌ፥ እንዲሁ ሥሩት።

ዘፍ 28:16 "በእውነት እግዚአብሔር በዚህ ስፍራ ነው እኔ አላወቅሁም ነበር አለ። ፈራ፥ እንዲህም አለ፦ ይህ ስፍራ እንዴት ያስፈራ ይህስፍራ የእግዚአብሔር ቤት ነው እንጂ ሌላ አይደለም ይህም የሰማይ ደጅ ነው።"

1ኛነገ 6:1 "የእስራኤል ልጆች ከግብጽ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ።

1ኛዜና 22:1 "ዳዊትም፦ ይህ የእግዚአብሔር ቤት ነው፥ አለ"

ዘካ 1፥16 "ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ወደ ኢየሩሳሌም በምሕረት ተመልሻለሁ ቤቴ ይሠራባታል በኢየሩሳሌምም ላይ ገመድ ይዘረጋበታል፥ ይላል የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር፦"

ማር 11፥17 "ኢየሱስም ቤቴ ለአሕዛብ ሁሉ የጸሎት ቤት ትባላለች ተብሎ የተጻፈ አይደለምን? እናንተ ግን የወንበዶች ዋሻ አደረጋችኋት አላቸው።

ዮሐ 2:13 "በመቅደስም በሬዎችንና በጎችን ርግቦችንም የሚሸጡትን ገንዘብ ለዋጮችንም ተቀምጠው አገኘ፤ የገመድም ጅራፍ አበጅቶ ሁሉን በጎችንም በሬዎችንም ከመቅደስ አወጣቸው፥ የለዋጮችንም ገንዘብ አፈሰሰ ገበታዎቻቸውንም ገለበጠ፥ ርግብ ሻጪዎችንም። ይህን ከዚህ ውሰዱ፤ የአባቴን ቤት የንግድ ቤት አታድርጉት አላቸው። ደቀመዛሙርቱም። የቤትህ ቅናት ይበላኛል ተብሎ እንደተጻፈ አሰቡ።

1ኛጢሞ 3:15 "በእግዚአብሔር ማደሪያ ቤት መኖር እንዴት እንደሚገባ ታውቅ ዘንድ እጽፍልሃለሁ፤ ቤቱም የእውነት ዓምድና መሠረት፥ የሕያው እግዚአብሔር ቤተክርስቲያን ነው።

ሐዋ 20፥28 "በገዛ ደሙ የዋጃትን የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ትጠብቁአት ዘንድ መንፈስ ቅዱስ እናንተን ጳጳሳት አድርጎ ለሾመባት ለመንጋው ሁሉና ለራሳችሁ ተጠንቀቁ።"
2-ሁለተኛው የክርስትያኖች ሕብረት ወይም አንድነት ቤተ ክርስትያን ይባላል::
ማቴ 18:7 "ወንድምህም ቢበድልህ፥....ለቤተ ክርስቲያን ንገራት፤ ደግሞም ቤተክርስቲያንን ባይሰማት፥ እንደ አረመኔና እንደ ቀራጭ ይሁንልህ።

ሐዋ 8፥1 "በዚያን ቀንም በኢየሩሳሌም ባለች ቤተክርስቲያን ላይ ታላቅ ስደት ሆነ፤ ሁሉም ከሐዋርያትም በቀር ወደ ይሁዳና ወደ ሰማርያ አገሮች ተበተኑ።"
3-ሶስተኛው እያንዳንዱ ግለሰብ ቤተ ክርስትያን ይባላል::
በአብ፣ በወልድ፣ በመንፈስ ቅዱስ ስም የተጠመቁና በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አዳኝነት ያመኑ የክርስቲያን ሃይማኖት ምእመናን ቤተክርስቲያን ይባላሉ። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ወደ ሮም ሰዎች በላከው መልእክቱ ምዕራፍ ፲፮፣፬- ፭ ላይ "ለጵርስቅላና ለአቂላ ሰላምታ አቅርቡልኝ ካለ በኋላ፣ እነርሱን የአሕዛብም አብያተ ክርስቲያን ሁሉ የሚያመሰግኑአቸው ናቸው እንጂ እኔ ብቻ አይደለሁም " ብሏል። እንዲሁም በቤታቸው ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ ብሏል። እዚህ ላይ የአሕዛብ አብያተ ክርስቲያን የተባሉትና በቤታቸው ያለችው ቤተ ክርስቲያን የተባሉት ምዕመናን ናቸው እንጂ ሌላ አይደለም። በተመሳሳይ አባባል ለቆሮንቶስ ሰዎች በላከው የመጀመሪያ መልእክቱ ምዕራፍ፲፮፣፲፱ ላይ የእሲያ አብያተ ክርስቲያን ሰላምታ እንደሚያቀርቡ ገልጾአል። እንዲሁም በሐዋርያት ሥራ ምዕራፍ ፳፣፳፰ ላይ ለኤፌሶን ካህናት ባደረገው የመሰናበቻ ንግግር “ጌታ በገዛ ደሙ የዋጃትን ቤተክርስቲያን ጠብቁ ብሏቸዋል።” እዚህም ላይ እንዳለፉት አባባሎች ሁሉ ቤተ ክርስቲያን የተባለው ምእመናን ለማለት ነው። የክርስቲያኖች ሰውነት በመንፈስ ቅዱስ የተቀደሰ በሥጋ ወደሙ የታተመ የክርስቶስ ቤት ነው። ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ :-


1ቆሮ6:19 "ሥጋችሁ ከእግዚአብሔር የተቀበላችሁት በእናንተ የሚኖር የመንፈስ ቅዱስ ቤተ መቅደስ እንደሆነ አታውቁምን በዋጋ ተገዝታችኋልና ለራሳችሁ አይደላችሁም" በማለት አስተምሯል

1ኛቆሮ 3:17 "ማንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ቢያፈርስ እግዚአብሔር እርሱን ያፈርሰዋል፤ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ቅዱስ ነውና፥ ያውም እናንተ ናችሁ።"

ሐዋ 8፥3 "ሳውል ግን ቤተ ክርስቲያንን ያፈርስ ነበር፤ ወደ ሁሉም ቤት እየገባ ወንዶችንም ሴቶችንም እየጐተተ ወደ ወኅኒ አሳልፎ ይሰጥ  ነበር።"  

ሮሜ 16፥5 "በቤታቸውም ላለች ቤተ ክርስቲያን ሰላምታ አቅርቡልኝ። ከእስያ ለክርስቶስ በኵራት ለሆነው ለምወደው ለአጤኔጦን ሰላምታ አቅርቡልኝ።"

bottom of page