top of page
ገድለ ተክለሃይማኖት‘ሰይጣን ተጠመቀ’ ይላል

ገድለ ተክለሃይማኖት‘ሰይጣን ተጠመቀ’ ይላል?

 

አቡነ ተክለሃይማኖት ገድለ ተክለሃይማኖት ላይ ‘ሰይጣንን አጠመቁት’  ይላል እያሉ የተሐድሶ መናፍቃን ይተቻሉ፡፡እውን ግን ጻድቁ አባታችን አቡነ ተክለሃይማኖት በቁሙ ሰይጣንን አጥምቀዋልን?

በገድለ ተክለሃይማኖትና በልደተ አበው ላይ እንዲህ ይላል
“አቡነ ተክለሃይማኖት በእነዚህ አውራጃዎች ሲመላለስ አንድ ቀን በውኃ ዳር ዐረፍ አለ፡፡ጋኔንም ከውኃው ወጣና ደቀመዛሙሩን ያዘው፡፡አሳመመውም፡፡እርሱም ጋኔን መሆኑን ዐወቀ፡፡በረድኡ ላይም በመስቀል ምልክት አማተበበት፡፡ጋኔኑም ፈጥኖ ወጣ ሸሸ፡፡አቡነ ተክለሃይማኖትም በእጁ ያዘው፡፡ሥራዩንም አወጣበት፡፡ያን ጊዜም ለሁሉ ታየ፡፡እርሱም  “ማነው ስምህ?” አለው፡፡ጋኔኑም “ባሕር አልቀም” አለው፡፡አቡነ ተክለሃይማኖትም “ከኔጋር ትኖራለህን?” አለው፡፡እርሱም ገዘረውና ወደ ታላቁ የቤተክርስቲያን ምሥጢረ ጥምቀት አገባው፡፡ስሙንም ክርስቶስ ኀረዮ (ክርስቶስ መረጠው ማለት ነው) አለው፡፡ረድእም አደረገው፡፡ወደ በኣቱም አስገባው፡፡እርሷንም አስብናት፡፡እርሱም እግዚአብሔርን የሚወድና ወንድሞቹንም ሁሉ የሚያስደስት ሆነ፡፡” 

በጥንታውያን ሰዎች ዘንድ በአጋንንት አሠራር ተጠምደው የሚኖሩ ጣዖት አምላኪ ሰዎችን ባደሩባቸው አጋንንት ስም መጥራት የተለመደ ነው፡፡ሰው በውስጡ ባለው ነገር ይጠራልና፡፡ልክ ጌታ ጴጥሮስን 
“አንተ ሰይጣን ከኋላየ ሒድ” (ማቴ.16፡23)
እንዳለው ማለት ነው፡፡እንዲህ ዓይነት ታሪኮች በብዙ ጥንታውያን መጻሕፍት አሉ፡፡ሥጋ ለበስ አጋንንት የሚሏቸው እነርሱን ነው፡፡የተለያዩ የምትሐት ነገሮችን ይሠራሉ፡፡በባሕር ይኖራሉ፣በእሳት ውስጥም ገብተው በደኅና ይወጣሉ፡፡ዋሊስባጅ ባሳተመው የደብረሊባኖስ ገድለ ተክለሃይማኖት ላይ ጸሐፊው ከሌሎቹ የአካባቢው ቅጅዎች ለየት ብሎ አቡነ ተክለሃይማኖት ያጠመቁት ክፉ መንፈስ ያለበትን ሰው እንጂ መንፈስ የሆነውን ሰይጣን አለመሆኑን በቅዱሳት መጻሕፍት ማስረጃዎች ያብራራል፡፡

“የእናንተ ጌታና አምላክ ተክለሃይማኖት ነው”

“የእናንተ ጌታና አምላክ ተክለሃይማኖት ነው”

“የእናንተ ጌታና አምላ ክተክለሃይማኖት ነው፤” -የውስጥና የውጭ መናፍቃን “በጸጋ” የሚለውን ቃል ቆርጠው በማስቀረት እንደ ገደል ማሚቶ የሚቀባበሉት ቃል ነው።በመሠረቱ፡-ከእሾህ ወይን፥ከኵርንችት በለስ ስለማይለቀም ከመናፍቃን ጥሩ ነገር አይጠበቅም።ማቴ፡፯፥፲፮።ጥንታውያን አባቶቻችን ለመናፍቃኑ እግር በእግር እየተከታተሉ መልስ ይሰጡአቸው ስለነበረ ማኅበረ ምእመናን እምብዛም አይታወኩም ነበር።ሰርገው የገቡትንም በጉባኤ ክርክር ምላሽ በማሳጣት፥አውግዘው ይለዩ ስለነበረ የቤተክርስቲያን ሰላም ተጠብቆ ኖሮአል።ሃይማኖት አበው የሚባለው ትልቅ መጽሐፍ፥አባቶቻችን በየጊዜው ለተነሡ መናፍቃን የሰጡት መልስ ነው።ታላቁ ሊቅ አባጊዮርጊስም መጽሐፈ ምሥጢር በሚባለው መጽሐፉ ላይ ለመናፍቃን የማያፈናፍን መልስ ሰጥቶአል።ለምሳሌበ“ኖላዌ ምንባብ” ላይ አርዮስን፡- 
“እንግዲህ በዲቁናው ክህደትን ያበቀለ በቅስናውም የኃጢአትን እሾህ ያፈራ የአርዮስን ተግሣጽ እንናገር።አርዮስ የሰይጣን ሠረገላው የአጋንንትም ማኅበርተኛቸው ነው፤”እያለ ይገሥጸዋል።

በዓፄ ኃይለሥላሴ ዘመነ መንግሥትም ታላላቁ ሊቃውንት መላአከ ብርሃን አድማሱ ጀንበሬና አለቃ አያሌው ታምሩ በመጻሕፍቶቻቸው የማያዳግም መልስ ለካቶሊካውያን ሰጥተዋል።ሊቀመዘምራን ሞገስ ዕቁበጊዮርጊስም ፕርቴስታንቱ ለሚያነሡአቸው ጥያቄዎች ሁሉ በአፍም በመጽሐፍም መልስ ሰጥተዋል።በዚህ ዘመን ከተነሡ ሊቃውንትም የሚጠበቀው ልክ እንዳለፉት አባቶች ዘመን ተሻጋሪ የሆኑ መጻሕፍትን እያዘጋጁ መናፍቃንን ማሳፈር መንጋውን ደግሞ መጠበቅ ነው።ይኸንን በተመለከተ ማህበረቅዱሳን የአባቶቹ ልጅ ስለሆነ፥ጋን በጠጠር እንደሚደገፍ በተቻለው መጠን እንደ ተቋም ትልቅ ሥራ እየሠራ ነው።ለምሳሌ፡-“የገሃነም ደጆች እና ሁለቱ ኪዳናት” በሚባሉት መጻሕፍቱ የውስጥ መናፍቃንን የተሀድሶዎችን አከርካሪያቸውን ሰብሮአል።በሐመር መጽሔት እና በስምዐ ጽድቅ ጋዜጣም መናፍቃንን መድረሻ እያሳጣ ነው። 

መናፍቃኑ፡-“የእናንተ ጌታና አምላክ ተክለሃይማኖት ነው፤” እያሉ የተለመደ ጩኸታቸውን እንደ አዲስ ማላዘናቸው፥ምናልባት በቅዱሳን የምናፍር መስሎአቸው ከሆነ እንዲያው ድከሙ ቢላቸው ነው።ደግሞስ የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ወስኖ ሲጠራቸው፥ጠርቶም ሲያጸድቃቸውና ሲያከብራቸው፥እግዚአብሔር ያላፈረባቸውን እኛ የምናፍርባቸው ለምንድን ነው?ሮሜ፡፰፥፳፱።ደግሞስ ምን የሚያሳፍር ነገር አለባቸው።ቅዱስ ሉቃስ ወንጌላዊ ስለቅዱሳን ሲመሰክር፡-“በይሁዳ ንጉሥ በሄሮድስ ዘመን ከአብያ ክፍል የሆነ ዘካርያስ የሚባል አንድ ካህን ነበረ፤ሚስቱም ከአሮን ልጆች ነበረች፥ስምዋም ኤልሳቤጥ ነበረ።ሁለቱም በጌታ ትእዛዝና ሕግጋት ሁሉ ያለነቀፋ እየሄዱ በእግዚአብሔር ፊት ጻድቃን ነበሩ፤ ”ብሎአል።ሉቃ፡፩፥፭።ከሁሉም በላይ ከጥንት እስከ ዛሬ ለቅዱሳን የመሰከረ የሚያስመሰክርም እግዚአብሔር ነው።በመሆኑም እርሱ ያከበረቻውን እርሱን አብነት አድርገን እናከብራለን፥እርሱ ያላፈረባቸውንም አናፍርባቸውም።“ስለዚህ እግዚአብሔር አምላካቸው ተብሎ ሊጠራ በእነርሱ አያፍርም ከተማን አዘጋጅቶላቸዋልና፤” ይላል።ዕብ፡፲፩፥፲፮። 

-እኛ የምናምነው፡-“ኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌታ፥የባህርይ አምላክ ነው፤ቅዱሳን ደግሞ የጸጋ ጌቶችና የጸጋ አማልክት (ገዢዎች) ናቸው፤”ብለን ነው።እንዲህም ማለታችን በእግዚአብሔር ቃል ላይ ተመሥርተን እንጂ እንዲያው በልቦለድ አይደለም።ስለዚህ ጻድቁ አባታችን ተክለሃይማኖት፡-የጸጋ ጌታ እና የጸጋ አምላክ ነው።መናፍቃኑ ቅዱሳንን አማላጅ እንኳ ለማለት ሲቸገሩ፥እንዲህ ያለውን ጸጋ ለወዳጆቹ የሰጠ እግዚአብሔር ነው።መቼም መናፍቃን“ የሚሳናቸው” ነገር ስለሌለ፥“ለምን?” ብለው እርሱን ይከራከሩት።ደግሞ ስለቅዱሳን የተሰጠውን ጸጋ እየተቃወሙ እንዴት ነው?ከእግዚአብሔር ዘንድ የተሰጠን ጸጋ አለን፥የሚሉት። -ቅዱስ ዮሐንስ በራእይ መጽሐፉ ላይ፡-“የነገሥታት ንጉሥና የጌታዎች ጌታ የሚል ስም አለው።”በማለት፥ኢየሱስ ክርስቶስ ጌትነትና አምላክነት የባህር ይገንዘቡ መሆኑን መስክሮአል።በኢየሱስ ክርስቶስ የባህርይ ጌትነትና ንጉሥነት ስር ጌቶችና ነገሥታት የተባሉት በጸጋው የከበሩ ፥በገድል የተቀጠቀጡ ቅዱሳን ናቸው።ጌታ ደቀ መዛሙርቱን፡-“በአሥራ ሁለት ዙፋን ተቀምጣችሁ ትፈርዳላችሁ፤”ያላቸው ለዚህ ነው።ማቴ፡፲፱፥፳፭።ዙፋን የንጉሥ መቀመጫ ነው።

በተጨማሪም፡-“በፊተኛው ትንሣኤ ዕድል ያለው ብፁዕና ቅዱስ ነው፤ሁለተኛው ሞት በእነርሱ ላይ ሥልጣን የለውም፥ዳሩ ግን የእግዚአብሔርና የክርስቶስ ካህናት ይሆናሉ፥ከእርሱም ጋር ይህን ሺህ ዓመት(ለዘለዓለም) ይነግሣሉ።” የሚል አለ።ራእ፡፳፥፮። -የጸጋ ጌትነትን በተመለከተም፡-ሣራ አብርሃምን ጌታዬ ብለዋለች፤ዘፍ፡፲፰፥፲፪፣፩ኛ፡ጴጥ፡፫፥፭።ኤፍሮን እና የኬጢ ልጆችም ጌታ ብለው ጠርተውታል።ዘፍ፡፳፫፥፮፣፲፩።የያዕቆብ ልጆች ወንድማቸውን ዮሴፍን ጌታ ብለውታል።ዘፍ፡፵፬፥፲፰።ሊቀ ካህናቱ አሮንም ሙሴን ጌታዬ ብሎታል።ዘኁ፡፲፪፥፲፩።በአዲስ ኪዳን የወኅኒ ቤት ጠባቂው ቅዱስ ጳውሎስን እና ሲላስን ጌቶቼ ብሏቸዋል።የሐዋ፡፲፮፥፴። -የጸጋ አምላክነትን(ገዥነትን) በተመለከተ ደግሞ፡-“የአማልክት አምላክ እግዚአብሔር ተናገረ፤” የሚለው ኃይለ ቃል በቂ ማስረጃ ነው።መዝ፡፵፱፥፩።ምክንያቱም፡-ቅዱሳን የጸጋ አማልክት ባይሆኑ ኖሮ እርሱ የአማልክት አምላክ( የገዥዎች ገዥ) ተብሎ አይጠራም ነበር።ይኸውም ይታወቅ ዘንድ፥እግዚአብሔር ሙሴን፡-“እይ፥እኔ ለፈርዖን አምላክ አድርጌሃለሁ፤ወንድምህም አሮን ነቢይ ይሆንልሃል፤”ብሎታል።ዘጸ፡፯፥፩።በአዲስ ኪዳንም ጌታችን አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ፡-ቅዱሳን አማልክት እንደሚባሉ ከመዝሙረ ዳዊትጠቅሶአስተምሮአል።መዝ፡፹፩፥፮፣ዮሐ፡፲፥፴፩።ጌታችን አምላካችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደብረ ታቦር ክብሩን በገለጠ ጊዜ በአጠገቡ የነበሩት፡-የብሉይ ኪዳን ቅዱሳን ሙሴና ኤልያስ ፥እንዲሁም የአዲስ ኪዳን ቅዱሳን ጴጥሮስ ፣ዮሐንስና ያዕቆብ ናቸው።ማቴ፡፲፯፥፫።ባለፈው፡-መሬት፥ግንድ፥ቅርንጫፍና ፍሬ እንደማይለያዩ ምሳሌውን ፈትተን፥ንባቡን ተርጉመን እንደተማማርነው በምድርም በሰማይም ቅዱሳን ከጌታ የተለዩበት ጊዜ የለም።ስለዚህ ከጌታ የተለዩ ቅዱሳን እንደሌሉ ሁሉ ከቅዱሳንም የተለየ ጌታ የለም።

በውኑ የተክለሃይማኖት___ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል ነው’ ይላል?

በውኑ የተክለሃይማኖት___ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል ነው’ ይላል?

 

የተሐድሶ መናፍቃን ገድለ ተክለሃይማኖት ‘የተክለሃይማኖት ተቅማጥ ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል ነው’ ይላል ይላሉ፡፡በውኑ ይላልን?

መልስ፡- ሙሉ ገጸ ንባቡ
“ክቡር አባታችንም ጌታዬ ወደ ሰማዕትነት ዐደባባይ  ሄጄ በስምህ እንድሞት እዘዘኝ አለው፤ጌታም መጋደልስ ፈጸምክ ከሞት በቀር ምንም አልቀረህም፡፡” አለው ነው የሚለው፡፡ [ገድለ ተክለሃይማኖት፤ነሐሴ 1989 ዓ.ም፤ምዕራፍ፶፯፤ገጽ. 195]
ከዚህም በኋላ፡- “ወናሁ ትመውት በሕማመ ብድብድ በእኩይ ሞት ወእሬሲ ለከ ኪያሃ ከመስቅለትየ በከመ ደመ ሰማዕት እለ እም ቅድሜከ አኮ ለባሕቲትከ አላ ደቂቅከኒ እለ ይመውቱ በሕማመ ብድብድ በውስተ ዛቲ ገዳም እኌልቆሙ ምስለ ሰማዕታት ወአወፍዮሙ ለከ በመንግሥተ ሰማያት፡፡”[ዝኒ ከማሁ] ነው ያለው፡፡
የቃሉ የግእዝ ትርጒም
ሕማመ ብድብድ ማለት ቸነፈር ማለት ነው፡፡ጻድቁ ተክለሃይማኖት የሞቱት በቸነፈር በሽታ ነው፡፡ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም በዕለተ ዐርብ እንደ ተቀበልኩትመከራ መስቀል አደርግልሃለሁ ያለው፤ገድላቸውንና በደዌ የተቀበሉትን መከራ ነው፡፡
በመልክዐ ጊዮርጊስ ላይም እንዲህ የሚል አብነት ይገኛል፡፡ሰላም ለሰኳንዊከ ምስለ ክልኤሆን መከየድ፡፡ለአጻብዒከ ሰላም ወለ አጽፋረ እግርከ አምሳለ መረግድ፡፡ገባሬ መንክራት ጊዮርጊስ በአቊጽሎ ይቡስ ዐምድ፡፡አድኅነኒ በጸሎት ከእምነ መከራ ክቡድ፡፡እስመ እምኔሁ ይወጽእቀታሊ ብድብድ፡፡ (መልክዐ ጊዮርጊስ) ትርጓሜውም፡- ቅዱስ ጊዮርጊስ ሆይ በሁለቱ ተረከዞችህ ጋር ለጫሞችህ ሰላም እላለሁ፡፡እንደከበረ ዕንቊ ለሚያበሩት ለእግር ጽፍሮችህና ጣቶችህም ሰላም እላለሁ፡፡ተአምር አድራጊው ሰማዕት ሆይ! ደረቁን ምሰሶ ለምለም ተአምራትህን ገልጸሃልና ፡፡ከጽኑ መከራ በጸሎትህ አድነኝ፡፡ሰው ስለሥቃይ የሚዳርጉ ረኀብ ቸነፈር ከእሱ ይፈልቃሉና፡፡ማለት ነው፡፡ስለሆነም "ብድብድ" የሚለው ረኀብ፤ቸነፈር ተብሎ ይተረጎማል፡፡

የተሐድሶ መናፍቃኑ እንደሚሉት ‘ተቅማጥህ እንደ ስቅላቴደምነው’ የሚል ሐረግም ከገድሉ ላይ አይገኝም፡፡
“… እሷንም እንደስቅላቴና ካንተ በፊት እንደነበሩ ሰማዕታት ደም እቆጥርልሃለሁ፤” [ዝኒከማሁ(Ibid)] ነው ያለው፡፡
ይህም ማለት የተክለሃይማኖት ሕማም ከሰማዕታት ደም ጋር እኩል  እንደሆነ እንጂ ከክርስቶስ ደም ጋር እኩል እንደሆነ አያስረዳም፡፡ይህም የሆነበት ምክንያት ከገድሉ ላይ እንደምንረዳው መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ አባ ተክለሃይማኖት ብዙ ተጋድለሃል ከእንግዲህ ይበቃሃል ነፍስህ ከመከራ ተለይታ ወደ እረፍት መሄጃህ ጊዜ ደርሷል ባላቸው ጊዜ አባ ተክለሃይማኖት በሰማዕትነት እንድሞት አድርገኝ ብለው ስለለመኑት ነው፡፡

በሚሞቱበት ጊዜ የሚደርስባቸውን ሕማም እንደራሱ መከራና በጦር ተወግተው በስለት ተቆርጠው ደማቸው እንደፈሰሰው ሰማዕታት ደም ሲቆጠርላቸው ነው፡፡ሰማዕታት ለክርስቶስ ሲሉ በጦር ተወግተው በስለት ተቆርጠው ደማቸው እንደሚፈስ አባ ተክለሃይማኖትም ለክርስቶስ ሲሉ ሃገር ለሃገር ጫካ ለጫካ ሲንከራተቱ ሕማመ ብድብድን (ቸነፈርን) በጦር ተወግተው ደማቸው እንደፈሰሰው ሰማዕታት ቆጠረላቸው፡፡ስለዚህ የአባ ተክለሃይማኖት ሕማመ ብድብድ (ቸነፈር) እንደ ሰማዕታት ደም ሆኖ ቢቆጠር ሃይማኖት ላለውና ለሚያስተውል ሰው አያደንቅም፡፡
 

ገድለ ተክለሃይማኖት "ወደ መቃብርህ የሄደውን ወደ መቃብሬ"

ገድለ ተክለሃይማኖት "ወደ መቃብርህ የሄደውን ወደ መቃብሬ"

“ከሩቅም ከቅርብም ቢመጣ ወደ መቃብርህ የሄደውን እኔ ወደ መቃብሬኢየሩሳሌም እንደሄደ አደርገዋለሁ፤በመታሰቢያህ ቀን ሥጋውን ደሙን የተቀበለውንም ስማቸው ከተጠራው ገድላቸው ከተነገረው ልጆችህ ጋራ እኔ እቈጥረዋለሁ፡፡” [ገድለ ተክለሃይማኖት፤ነሐሴ 1989 ዓ.ም፤ምዕራፍ፶፯፤ገጽ. 193] ማለት ምን ማለት ነው?

መልስ፡- ወደ መቃብርህ የመጣውን ወደ መቃብሬ እንደመጣ አደርገዋለሁ ማለት በአንተ አማላጅነት በእኔ በርነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባል ማለት ነው፡፡ይህም እናንተን የተቀበለ እኔን ተቀበለ ያለው የወንጌል ቃል በተግባር ሲተረጎም ነው፡፡
በተክለሃይማኖት በመቃብር ላይ በተክለሃይማኖት ስም በተሠራው የእግዚአብሔር ቤተመቅደስ ወደ ሚገኝበት በመምጣት በመጸለይ ወደ መንግሥተ ሰማያት መግባት ነው፡፡የእግዚአብሔር በረከት ወደሚገኝበት ቦታ በመሄድ ጸጋ እንደሚገኝም መጽሐፍ ቅዱስ ያስተምረናል፡፡ 2ኛ.ነገ.5፡1፤ዕብ. 11፡23፤ሩት. 1፡16-18፡፡

“በመታሰቢያህ ቀን ሥጋውን ደሙን የተቀበለውንም ስማቸው ከተጠራው ገድላቸው ከተጻፈው ልጆችህ ጋር እኔ አኖራቸዋለሁ፡፡” 
የሚለውም ቃል የኢየሱስ ክርስቶስን መግቢያ በርነት የበለጠ ያስተምራል እንጂ አያስቀርም፡፡በአንተ መታሰቢያ ዕለት የእኔን ሥጋና ደም ተቀብሎ በአንተ አስተማሪነት በእኔ በርነት ወደ መንግሥተ ሰማያት ይገባልማለትነው፡፡

ገድለ ተክለሐይማኖት "እባብን የገደለ ይጽድቃል"

የመናፍቃን ጥያቄ ከገድለ ተክለሐይማኖት ውስጥ: "እባብን የገደለ ይጽድቃል" ይላል፡፡ 
ስለዚህ ሰዎች ሁሉ እባብን እየፈለጉ ለመጽደቅ እባብን መግደል አለባቸው ወይ የሚል ነው።አይ ይህቺ የመናፍቃን ጭንቅላት ትንሽ ብትሰፋ! ወገኖቼ መጸሐፍ ቅዱስ እውርን እውር ቢመራው ተያይዞ ገደል መግባት ነው ይላል:: አንዱ ብርሃን መሆን አለበት:: ዛሬ ብዙ ሰዎች በመጽሐፍ ቅዱስ ቃል ታውረዋል፡፡አባታችን ተክለሐይማኖት ይፈውሱዋቸው አሜን ::

ወገኖቼ እባብን የገደለ ይጸድቃል ማለት እባብ የተባለ ዲያቢሎስ ነው:: ለምሳሌ ያህል በመዝሙር ምህራፍ 73 ቁጥር 14 እንዲህ ይላል 
“አንተም የዘንዶውን እራስ ቀጠቀጥክ ለኢትዮጵያ ሰዎችም ምግባቸውን ሰጠሃቸው፤” ይላል ::
ታዲያ  አንተ የዘንዶውን እራስ ቀጠቀጥክ ሲል ታዲያ እግዚአብሔር ዘንዶ ያለበትን እየሔደ እራስ እራሱን ቀጠቀጠው ማለት ነውን? አይደለም :: ዘንዶ የተባለው ሰይጣን ነው :: ሰይጣንን ደግሞ እግዚአብሔር በመስቀሉ ቀጥቅጦታል :: 

እንዲሁም ገድለ ተክለሐይማኖት ላይም እባብን የገደለ ይጽድቃል ሲል ሰይጣንን የገደለ ይጸድቃል ማለቱ ነው :: ሰይጣንን የምንገለው ደግሞ በጾም በጸሎት እና በስግደት ነው:: በነዚህ እባብ (ዲያቢሎስን ) መግደል እንችላለን:: በተጨማሪም ደግሞ ራእይ ዮሐንስ ምእራፍ 12 ቁጥር 7 እንዲህ ይላል፡-“በሰማይም ሰልፍ ሆነ ሚካኤልና ሰራዊቱ ዘንዶውን ተዋጉት :: ዘንዶውም ከመላእክቱ ጋር ተዋጋ አልቻላቸውም፤ከዚያም ወዲያ በሰማይ ስፍራ አልተገኘላቸውም:: ዓለሙን ሁሉ የሚያስት ዲያቢሎስና ሰይጣን የሚባለው ታላቁ ዘንዶ እርሱም የቀደመው እባብ ተጣለ፡፡ወደ ምድርም ተጣለ፤መላእክቱም ከእርሱ ጋር ተጣሉ፤” ይላል::
ታዲያ ሚካኤልና ቅዱሳን መላእክቱ ከዘንዶው ጋር ተዋጉ ሲል ከእንስሳ ጋር ተዋጉ ማለት ነውን? አይደለም፡፡ዘንዶ የተባለው የቀደመው ሰይጣን እርሱ ዲያቢሎስ ነው ይለናል:፡

ገድለ ተክለሐይማኖት "እባብን የገደለ ይጽድቃል"

አቡነ ተክለሃይማኖት የሰማዕታትን ዋጋ የሚያገኙበት ሕመም...

 

አባታችን ጻድቁ አቡነ ተክለሃይማኖት በሰማዕትነት ሞተው ቅዱስ ጳውሎስ 
“እርሱንና የትንሣኤውን ኃይል እንዳውቅ በመከራውም እንድካፈል ወደ ሙታንም ትንሣኤ ልደርስ ቢሆንልኝ በሞቱ እንድ መስለው እመኛለሁ” ያለውን ለመፈጸም ይመኙ ነበር /ፊሊ.3፡11/፡፡ 
ነገር ግን ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደዌ ዘእሴት  (ዋጋን በሚያሰጥ የሆድ ሕመም) እንዲሞቱ ነው የፈቀደላቸው፡፡በዚህ አሟሟታቸውም ከጌታችን መከራ መስቀል እንደሚያሳትፋቸው እንደ ሰማዕትነትም እንደሚቆጠርላቸው ነው የተነገራቸው፡፡ይህ ደግሞ ፍጹም መጽሐፍ ቅዱሳዊ እውነት እንጂ መጽሐፍ ቅዱስን የሚቃረን አይደለም፡፡ኢዮብን ስንመለከተው በደዌ ተልቶ ሸቶ ነበር፡፡እንዲህ መሆኑ ግን ለጥቅሙ ነበር፡፡

ጳውሎስን ስናይ የጐድን ውጋት ነበረው /2ቆሮ.12፡7-10/፡፡ነገር ግን ለጥቅሙ የተሰጠው ነበረ፡፡ጢሞቲዎስን ስንመለከት የሆድ ሕመም ነበረው /1ጢሞ.3፡25/፡፡ነገር ግን ለጥቅሙ ነበረ፡፡ 

ታድያ አቡነ ተክለሃይማኖት ዐስበ ሰማዕትነት (የሰማዕታትን ዋጋ) የሚያገኙበትሕመም ያዛቸው ቢባል ምንድ ነው ብርቁ? አቡነ ተክለሃይማኖትም በዐረፍተ ዘመናቸው መጨረሻ የያዛቸው ደዌ ዘዕሴት ነበረ ቢባል ምንድ ነው ድንቁ? የክርስቶስን መከራ  የሚያሳትፍ እንጂ የክርስቶስን መከራ የሚተካ አልተባለም፡፡እንግዲያውስ ወንድሞችና እኅቶች! ያልተባለውን ተባለ፣ያልተፈጠረውን ተፈጠረ፣ያልተጣፈውን ተጣፈ እያልን ውሸት ከመናገር ብንቆጠብስ?

 

አቡነ ተክለሃይማኖት የሰማዕታትን ዋጋ የሚያገኙበት ሕመም...
bottom of page